ወጣቶች—የትምህርት ቤት ሕይወታችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት
1 የክረምቱን ዕረፍት ጨርሳችሁ ወደ ትምህርት ገበታ ስትመለሱ ምን ይሰማችኋል? ከመጪው የትምህርት ዓመት ለመጠቀም ትጓጓላችሁን? እውነትን ለክፍል ጓደኞቻችሁና ለአስተማሪዎቻችሁ ለማካፈል እንድትችሉ ትምህርት ቤት የሚሰጣችሁን አጋጣሚ በሚገባ ትጠቀሙበት ይሆን? በትምህርት ቤት የተቻላችሁን ሁሉ ለማድረግ እንደምትጥሩ እንተማመንባችኋለን።
2 ጎበዝ ተማሪዎች ሁኑ፦ ጥሩ አድርጋችሁ ተዘጋጅታችሁ ትምህርት ቤት የምትሄዱና በክፍል ውስጥ የሚሰጡትን ትምህርቶች በትኩረት የምትከታተሉ ከሆነ ለዘለቄታው የሚጠቅማችሁን እውቀት ትገበያላችሁ። የሚሰጣችሁን የቤት ሥራ በትጋት ሥሩ። ሆኖም የትምህርት ቤት ሥራችሁ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴያችሁን እንዲያስተጓጉልባችሁ አትፍቀዱለት።—ፊልጵ. 1:10
3 አዲሱን የትምህርት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት ቤት የተባለውን ብሮሹር በማንበብ ጀምሩ። ከዚያም እናንተ ወይም ወላጆቻችሁ ለአስተማሪዎቻችሁ በሙሉ አንዳንድ ቅጂ መስጠት ይኖርባችኋል። ጥያቄዎች ካሏቸው ጥያቄያቸው ሁሉ መልስ ማግኘት እንደሚችሉ ግለጹላቸው። የምትከተሏቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶችና የያዛችሁትን እምነት በተሻለ መንገድ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል፤ እንዲሁም የተማራችኋቸውን ነገሮች በተግባር ላይ ስታውሉ ይተባበሯችኋል። ከዚህም በተጨማሪ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንድታገኙ በሚረዷችሁ ጊዜ እናንተም ሆናችሁ ወላጆቻችሁ ከእነርሱ ጋር ለመተባበር ያላችሁን ፈቃደኝነት ለአስተማሪዎቻችሁ የሚያረጋግጥ ይሆናል።
4 ጎበዝ ምሥክሮች ሁኑ፦ ትምህርት ቤታችሁን መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት የምትሰጡበት የግል የአገልግሎት ክልላችሁ አድርጋችሁ ለምን አትመለከቱትም? በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ምሥክርነቱን ለመስጠት የሚያስችል ተወዳዳሪ የሌለው አጋጣሚ ታገኛላችሁ። ያካበታችሁትን ግሩም የሆነ መንፈሳዊ እውቀት ለሌሎች ካካፈላችሁ ‘ራሳችሁንም ሆነ የሚሰሟችሁን ለማዳን’ ትችላላችሁ። (1 ጢሞ. 4:16) ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያናዊ ጠባይ በማሳየትና ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ሁሉ ባለማለፍ ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን ትጠቅማላችሁ።
5 አንድ ወጣት ወንድም አብረውት ለሚማሩ ተማሪዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሠከረላቸው። ጥሩ ምላሽ ከሰጡት መካከል አንድ ካቶሊክ፣ በአምላክ በሚያምኑ ሰዎች ላይ ያፌዝ የነበረ አንድ አምላክ የለም ባይና ከባድ አጫሽና የመጠጥ ሱስ የነበረበት አንድ ወጣት ይገኙበታል። ይህ ወጣት ወንድም በጠቅላላው 15 እኩዮቹ ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ረድቷል!
6 ስለዚህ እናንት ወጣቶች፣ ትምህርት ለመቅሰምና ተወዳዳሪ በሌላው በዚህ የአገልግሎት ክልል ለመመሥከር የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። እንደዚህ ካደረጋችሁ ከትምህርት ቤት ከፍተኛ ጥቅም ታገኛላችሁ።