ተሻሽለው ከወጡት የሕዝብ ንግግሮች መጠቀም
1 የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ በምሳሌ 4:18 ላይ ባሉት “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” በሚሉት ቃላት በትክክል ተገልጿል።
2 ከዚህ ጋር በመስማማት የክርስቲያን ጉባኤ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የሚገልጹ ወቅታዊ ማብራሪያዎችንና ማስተካከያ የተደረገባቸው እውቀቶችን መቀበሉን ቀጥሏል። (ማቴ. 24:45–47) ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተገናኘህ በኋላ ያስተዋልካቸውን ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች መናገር ትችል ይሆናል። የጉባኤ ስብሰባዎች (የሕዝብ ንግግሮችን ጨምሮ) ከዚህ እየጨመረ ከመጣ የእውነት ብርሃን ጋር እኩል እንድንራመድ ይረዱናል።
3 የተሻሻሉ አስተዋፅኦዎች፦ በቅርቡ ማኅበሩ አብዛኞቹን የሕዝብ ንግግር አስተዋፅኦዎች ማስተካከያ አድርጎባቸዋል። ማስተካከያ የተደረገበት ትምህርት ታክሎባቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦች ተብራርተዋል። ጉባኤው ከዚህ ማስተካከያ ከተደረገበት ትምህርት ሙሉ ጥቅም እንዲያገኝ ከተፈለገ የሕዝብ ንግግሮችን የሚሰጡ ወንድሞች በቅርቡ በወጡት አስተዋጽኦዎች ብቻ መጠቀም አለ ባቸው።
4 ከሕዝብ ንግግሮች ይበልጥ ለመጠቀም የሚሰጡትን የሕዝብ ንግግር ርዕሶች ጥቂት አስብባቸው። በሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ከመገኘትህ በፊት በቅርቡ ከቲኦክራሲያዊ ምንጮች በዚህ ርዕስ ላይ ስላገኘኸው እውቀት ለማስታወስ ሞክር። ከዚያም በምታዳምጥበት ወቅት ትምህርቱን በምን ዓይነት መንገድ እንደቀረበ በጉጉት ለመከታተል ጣር። እነዚህን እውነቶች ለወደፊት መጠቀም የሚቻልባቸውን መንገዶች በተመለከተ ያገኘኸውን ማንኛውንም አዲስ እውቀት በማስታወሻ አስፍር። ይህም ተሻሽለው ከቀረቡት የሕዝብ ንግግሮች ከፍተኛ ጥቅም እንድታገኝ ያደርግሃል።
5 የሕዝብ ንግግሮች አዲስ እውቀት የሚገኝባቸውና አድማጮችን ለተግባር የሚያነሳሱ መሆን አለባቸው፦ ክርስቶስ ንግግር በሚሰጥበት ወቅት የአድማጮቹን ልብ ይነካ ነበር። ማቴዎስ 7:28 “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ” ሲል እስከ ዛሬ ድረስ ከተሰጡት ንግግሮች ሁሉ ይበልጥ ዝነኛ በሆነው የኢየሱስ የተራራ ስብከት መደምደሚያ ላይ ሕዝቡ የተሰማውን ስሜት ይተርካል።
6 የኢየሱስን ምሳሌ በአእምሯቸው በመያዝ የሽማግሌዎች አካል አዲስ የሕዝብ ተናጋሪዎችን ሲመርጡ የማስተማር ችሎታ ያላቸውን፣ የማኅበሩን አስተዋፅኦ በጥብቅ የሚከተሉትንና የአድማጮችን ትኩረት መሳብ የሚችሉትን ወንድሞች ብቻ ለመመደብ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። የሕዝብ ንግግር የመስጠት መብት ያገኙ ወንድሞችም ሽማግሌዎች የሚሰጧቸውን ምክሮች በሙሉ በመቀበል የንግግር ችሎታቸውን ለማሻሻል መጣር አለባቸው።
7 በኢሳይያስ 65:13, 14 ላይ አስቀድሞ እንደተተነበየው የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ብልጽግና ይበልጥ በግልጽ እየታየ ነው። የሕዝብ ንግግር ‘ከይሖዋ ከምንማርባቸው’ አያሌ መንገዶች መካከል አንዱ ነው።— ኢሳ. 54:13