የጥያቄ ሣጥን
◼ የይሖዋ ምሥክሮች የተቀዱ ንግግሮችን ወይም የንግግር ማስታወሻዎችን ለሌሎች ሰዎች ማሰራጨት ይኖርባቸዋል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የሚቀርቡ ንግግሮችን ስናዳምጥ እንበረታታለን እንዲሁም እንጠናከራለን። (ሥራ 15:32) በመሆኑም በስብሰባው ላይ ላልነበሩ ሰዎች ይህን አበረታች ትምህርት ለማካፈል መፈለጋችን ያለ ነገር ነው። በዛሬው ጊዜ የተለያዩ የመቅጃ መሣሪያዎች ስላሉ አንድን ንግግር ቀድቶ ለሌሎች ማሰራጨት በጣም ቀላል ነው። አንዳንዶች ከረጅም ዓመታት በፊት የተሰጡ ንግግሮችን ጨምሮ የተቀዱ ንግግሮችን ሲያጠራቅሙ ቆይተዋል፤ በጥሩ መንፈስ ተገፋፍተው እነዚህን ንግግሮች ለጓደኞቻቸው ያውሷቸዋል ወይም አባዝተው ይሰጣሉ። ሌሎች ደግሞ የሚፈልግ ሰው ሁሉ እነዚህን ንግግሮች ዳውንሎድ ማድረግ እንዲችል ድረ ገጾችን ከፍተዋል።
ራሳችን ልንጠቀምበት አስበንም ይሁን ለቤተሰባችን አባላት ንግግሮችን ብንቀዳ ምንም ችግር እንደሌለው የታወቀ ነው። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ወደ ስብሰባ መምጣት ለማይችሉ የአቅም ገደብ ላለባቸው የጉባኤው አባላት ንግግሮች እንዲቀዱ ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የተቀዱ ንግግሮችንም ሆነ የንግግር ማስታወሻዎችን ለሌሎች ሰዎች የማናሰራጭበት በቂ ምክንያት አለን።
ብዙውን ጊዜ ንግግሮች የሚሰጡት ንግግሩ ለሚሰጥበት አካባቢ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት በመሆኑ የተቀዱ ንግግሮችን ስናዳምጥ ንግግሩ የተሰጠበትን ዓላማ ስለማናውቅ በተሳሳተ መንገድ ልንረዳው እንችላለን። በተጨማሪም ንግግሩን የሰጠው ማን እንደሆነ እንዲሁም ንግግሩ መቼ እንደተሰጠ ማጣራት አስቸጋሪ ስለሚሆን በዚያ ውስጥ የተጠቀሱት መረጃዎች ወቅታዊና ትክክል ስለመሆናቸው እምነት መጣል ሊያስቸግረን ይችላል። (ሉቃስ 1:1-4) በተጨማሪም የተቀዱ ንግግሮችና የንግግር ማስታወሻዎች መሰራጨታቸው አንዳንዶች ለግለሰቦች ተገቢ ያልሆነ ትኩረትና ክብር ለመስጠት ሌሎች ደግሞ እንዲህ ያለ ክብር ለማግኘት እንዲፈተኑ ሊያደርጋቸው ይችላል።—1 ቆሮ. 3:5-7
ታማኝና ልባም ባሪያ “በተገቢው ጊዜ” “በቂ” መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ ተግቶ እየሠራ ነው። (ሉቃስ 12:42) ይህ ደግሞ በየጉባኤው ንግግሮች እንዲቀርቡ እንዲሁም በድምፅ የተቀዱ ነገሮች jw.org ከተባለው ደረ ገጻችን ላይ ዳውንሎድ እንዲደረጉ ለማስቻል የተደረገውን ዝግጅት ይጨምራል። ታማኝና ልባም ባሪያ እንዲሁም የበላይ አካሉ በእምነት እንድንጠነክር የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ነገር ሁሉ እንደሚያቀርቡልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሥራ 16:4, 5