የጥያቄ ሣጥን
◼ አንድ ክርስቲያን የሚያውቁት ዓለማውያን ባቀረቡለት የሠርግ ግብዣ ላይ ከመገኘቱ በፊት ምን ነገሮችን ማጤን አለበት?
ጊዜው የኢትዮጵያውያን የሠርግ ወቅት በመሆኑ ጥቂት ያልሆኑ ምሥክሮች ከሚያውቋቸውም ሆነ ብዙም ከማያውቋቸው ዓለማዊ ሰዎች የሠርግ ጥሪ ሊደርሳቸው ይችላል። አንድ ክርስቲያን እነዚህን ግብዣዎች ከመቀበሉ በፊት በአንዳንድ ነገሮች ላይ ቢያሰላስል ጥሩ ነው።
በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ዋና መመሪያ ይሆናል። ከዓለማውያን ጋር መቀራረብ ያንጻልን? ብዙ መጠጣት፣ ትንባሆ ማጨስ፣ የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ውዝዋዜ፣ ከልክ በላይ መብላት ወይም ክርስቲያናዊ ያልሆነ ሌላ ባሕርይ ይታያልን? ብዙ ዝግጅቶች የሚደረጉት ከ1 ዮሐንስ 2:15–17 መንፈስ በሚጻረረው የድግሱ ታላቅነት፣ ሀብቴ ይታይልኝ በሚል በዓለም መንፈስ ነው። በዝግጅቱ ላይ መገኘታችን የክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲጥሱ የሚያደርግ መጥፎ ተጽዕኖ በሌሎች የጉባኤ አባላት ላይ ሊያሳድር ይችላል። ብዙውን ጊዜ ለእነዚህ ዝግጅቶች የሚወጣው ፕሮግራም ከስብሰባ ጊዜያት ወይም ሌሎች አስፈላጊ ክርስቲያናዊ ግዴታዎች ማከናወን በሚገባን ወቅት ነው። (ዕብ. 10:24, 25፤ ኤፌ. 5:15, 16) የቅርብ የቤተሰብ አባል በሚያቀርብልን ግብዣና እምብዛም የማናውቀው ሰው በሚያቀርብልን ግብዣ መካከል ልዩነት አለ። አንድ ክርስቲያን ከላይ የተገለጹትን ሁኔታዎች አገናዝቦ መወሰን አለበት፤ ውሳኔው ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት በጸሎት ጉዳዩን መመርመራችን ጎዳናችንን ለማቅናት ሊረዳን ይችላል።— ምሳሌ 3:5, 6
◼ ለመንግሥት አዳራሹ ጥበቃ ትኩረት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
ከእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት አንፃር ሲታይ የመንግሥት አዳራሾችን በመጠበቅ ረገድ ትክክለኛ የማመዛዘን ችሎታ እንድንጠቀም ይፈለግብናል። ቤታችን ከአደጋ የተጠበቀና በደንብ የተዘጋ መሆኑን ለማረጋገጥ ጥንቃቄ እንደምናደርግ ሁሉ ለመንግሥት አዳራሾቻችንም ተመሳሳይ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። እያንዳንዱ የመንግሥት አዳራሽ በቂ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ማረጋገጥ የሽማግሌዎች ኃላፊነት ነው። በተለያዩ ቦታዎች ባሉ የመንግሥት አዳራሾች ንብረት እንደጠፋና ስርቆት እንደተፈጸመ ስንሰማ የዚህን አስፈላጊነት እንገነዘባለን።
ጥሩ ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችለው አንዱ መሠረታዊ ነገር የመንግሥት አዳራሹን ከተጠቀምን በኋላ በሮቹን፣ መስኮቶቹንና የውጭ በሮቹን መዝጋትና መቆለፍ ነው። በኃላፊነት ላይ ያሉ እምነት የሚጣልባቸው ወንድሞች አዳራሹ ስብሰባ ከተደረገበት ከእያንዳንዱ ጊዜ በኋላ እንደዚህ ያለውን ጥበቃ ለማከናወን ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው። ይህ ጥበቃ አዳራሹ እንደ ሠርግ ወይም ጽዳት ላሉ ከመደበኛዎቹ የጉባኤ ስብሰባዎች ለተለዩ ዓላማዎች ሲውልም ጭምር ሊደረግ ይገባል። አንዳንድ ጉባኤዎች አስተናጋጆች ሆነው የሚሠሩ ወንድሞች በስብሰባው ወቅት ሰዎች የቆሙ መኪናዎችን እንዳይሰርቁ፣ እንዳያበላሹና መስታወታቸውን እንዳይሰብሩ ለመጠበቅ ተራ በተራ ብቅ እያሉ ማየታቸውን ጥሩ ሆኖ አግኝተውታል። በእያንዳንዱ ጉባኤ ያሉ ሽማግሌዎች በአካባቢው ያሉትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ንብረት እንዳይጠፋና በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሰዎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል።