ተስፋ የሌላቸው ሰዎች በሚያዝኑበት መንገድ አለማዘን
1 በራእይ 21:4 ላይ ያለው አስደናቂ ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ ሞት ሐዘን የሚያስከትል እውነታ መሆኑን ይቀጥላል። ብዙ ባሕሎች ከሞትና ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር የተያየዙ ስለሆነ በእነዚህ ጊዜያት አንድ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መከተል ስለሚገባው አካሄድ ብዙ ጥያቄዎች ይነሣሉ። በአካባቢያችን የሚገኙት በርካታ ጎሣዎች ለሚያከናውኗቸው የተለያዩ ልማዶች የሚሠሩ ደንቦችን ማውጣት ባንችልም ሕሊናችንን ለማሠልጠንና ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዱንን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች መለስ ብለን ከአምላክ ቃል ለመቃኘት እንፈልጋለን።
2 ብዙ ሰዎች የሚያስቡት ስለ ሞት ብቻ ቢሆንም እኛ ግን ወደፊት የምናገኘውን የዘላለም ሕይወትና ትንሣኤ በጉጉት እንጠባበቃለን። (ዮሐ. 11:25፤ 17:3) እንዲያውም ከታላቁ መከራ በሕይወት ለማለፍ ተስፋ እናደርጋለን። (ራእይ 7:9, 14) አምላካችን ይሖዋ “የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።” (ማቴ. 22:32) አዲስ ቡድን ወይም ጉባኤ ሲቋቋም በመጀመሪያ የሚያሳስበን የመቃብር ቦታ ማግኘት ሳይሆን የመንግሥት አዳራሽ የማግኘት ጉዳይ የሆነው ለዚህ ነው። በዚሁ ምክንያት እድር አንገባም። በሞት ላጣናቸው ወዳጆቻችን የሚያስፈልጉትን የቀብር ሥነ ሥርዓቶች በሙሉ በይሖዋ እርዳታ ማከናወን ችለናል።
3 ዓለም ምንም ተስፋ የለውም እንዲሁም ትንሣኤን የሚጠቅሰው እምብዛም ነው፤ እኛ ግን በዮሐንስ 5:28, 29 እንዲሁም በሥራ 17:31 ላይ ከምናነበው ሐሳብ ብርታት እናገኛለን። የምንወደው ሰው መሞቱ ሐዘን ቢያስከትልብንም ‘ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች . . . አናዝንም።’ (1 ተሰ. 4:13) ከልክ በላይ ማዘንና ዓለም ያወጣውን የሐዘን ሥርዓት መከተል እንዳለብን ሊሰማን አይገባም። (ሮሜ 12:2) ሰዎች የሚወዱት ሰው ሲሞትባቸው የተለያየ ዓይነት ሁኔታ ያሳያሉ፤ ስለዚህ ልንፈርድባቸው ወይም ልንተቻቸው አይገባም። አንዳንድ ጊዜ እህቶች አላግባብ ሌሎችን ላለማስቀየም ሲሉ በቀብር ወቅት ነጠላ አዘቅዝቀው ለመልበስ ሊወስኑ ይችላሉ። ቢሆንም በኢዩኤል 2:12, 13 ላይ ካሉት ቃላት ጋር በመስማማት ሐዘናችንን በልብሳችን ሳይሆን በልባችን ልንገልጽ እንችላለን። ብዙውን ጊዜ ምንም ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፣ ለረዥም ጊዜም ከሰው ይገለላሉ፤ በተቃራኒው እኛ ግን ተስፋችንን ለመግለጽ የምናገኘውን እያንዳንዱን አጋጣሚ ለመጠቀም እንፈልጋለን።— 1 ጴጥ. 3:15
4 እውነተኛ ክርስቲያኖች የጊዜውን አጣዳፊነት ይገነዘባሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 5:15, 16 ላይ በተናገራቸው ቃላት መሠረት ‘ዘመኑን በመዋጀት’ እንደ ጥበበኞች መመላለስ እንፈልጋለን። ለቅሶ ተቀምጠን ስለምናሳልፋቸው ቀናት ደንቦችን ማውጣት አያስፈልገንም። በአጠቃላይ ሲታይ ግን ለቅሶ ደራሾችን እየጠበቁ ብዙ ቀናት መቀመጥ ጥበብ አይደለም። በሐዘን ጊዜም ቢሆን ቲኦክራሲያዊ ልማዳችንን ማከናወን ጠቃሚ ነው። በሐዘን መቆራመድ ያዳክማል። በጸሎት፣ በግል ጥናት፣ ስብስባ ላይ በመገኘትና ምሥራቹን ለሌሎች በማካፈል ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር የተሻለ ነው።— ከሉቃስ 22:45 ጋር አወዳድር።
ቀላል ዓይን
5 ክርስቲያኖች ከሃይማኖታዊ ወጎች ነፃ የሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ይሻሉ። ነገሮችን ቀላል በማድረግ ወጪያችሁንና ጉልበታችሁን ልትቆጥቡ አልፎ ተርፎም ከጭንቀት ልትድኑ ትችላላችሁ። ለምሳሌ ምግብ በብዛት ማዘጋጀት አያስፈልግም። ኢየሱስ በሉቃስ 10:42 ላይ “የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው” ብሏል። ሌላው ቀርቶ ብዙውን ጊዜ ስለሚባክንና በዘመናችን በንጽሕና ጉድለት ምክንያት የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች ሊያስከትል ስለሚችል ንፍሮ በብዛት መቀቀል አያስፈልግም። ስለዚህ አንዳንዶች ምግብ ብቻ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ምግብ ብቻ የሚያዘጋጁትን መተቸት አይገባም። አላፊ አግዳሚውን፣ ለማኞችን ወይም የምናውቀውን ሰው ሁሉ የማብላት ግዴታ የለብንም። በተመሳሳይም ወደ ቀብር ለሚሄዱ መጓጓዣ ማቅረብ አያስፈልግም፤ ወደ ቀብር የሚሄዱ አብዛኞቹ ሰዎች የራሳቸውን ዝግጅቶች ማድረግ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ በዘልማድ ለቅሶ ሊደርሱ ለሚመጡ ሰዎች ተብሎ የሚተከለው ድንኳን እንኳ የግድ አያስፈልግም። ድንኳን መትከሉ በአብዛኛው በወቅቱና በአካባቢው ሁኔታ ይወሰናል። ጃንጥላና ሸራ መዘርጋት በበረንዳ ወይም በዛፎች አካባቢ ጥቂት አግዳሚ ወንበሮችን ማድረግ አስፈላጊውን ግልጋሎት ያበረክታል። ነገሮችን ቀላል ማድረግ የሚወዱት ሰው የሞተባቸው የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ወይም ጥናቶችን መርዳት የሚያስከትለውን ችግር ያቃልላል።
6 ከመካከላችን ትልቅ ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያላቸውም ቢሆኑ ልታይ ባይነትን የሚያወግዘውን የ1 ዮሐንስ 2:16, 17 ምክር ቢያስታውሱ ጥሩ ነው። በእነዚህ የኢኮኖሚ ችግር ባየለባቸው ጊዜያት ከፍተኛ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ከማዘጋጀት ይበልጥ ዋጋ ያላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ‘ባለን ሀብት እግዚአብሔርን እናክብር።’ (ምሳሌ 3:9) እርግጥ በግል ንብረታችን መጠቀሙ ሌሎች የማይወስኑበት የግል ጉዳይ ነው። (ሮሜ 14:4) ባለቤቱ ራሱን በማቴዎስ 6:33 ላይ በሚገኙ ቃላት መሠረት ሊመራ ይችላል።
ማጽናኛ
7 ቀላል የማጽናኛ መንገዶች ያሏቸው ባሕሎች ተገቢና የሚመረጡ ናቸው። ጳውሎስ በ1 ተሰሎንቄ 5:11 (አዓት ) ላይ “እርስ በርስ እንጽናና እንተናነጽ” በማለት ከተናገረ በኋላ በቁጥር 14 ላይ “የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ተናገሯቸው፤ ደካሞችን እርዱ” ሲል አክሏል። በለቅሶው ቦታ መገኘታችን ራሱ ጠቃሚ ነው፤ ሆኖም ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ከሚቀመጡት የተሻለ ማድረግ እንችላለንን? የሚያጽናኑ ቃላትን አስቡ፣ ፖስት ካርድ ስጧቸው ወይም ደብዳቤ ጻፉላቸው፣ (ይህም ብዙ ጊዜ ሊነበብ ይችላል) ስልክ ደውሉላቸው፣ በቤት አካባቢ የሚሠሩ ሥራዎችን በመሥራት ወይም አንዳንድ ሕግ ነክ ጉዳዮችን በማስፈጸም እርዷቸው። በራሳችሁ ተነሳስታችሁ አንድ ነገር አድርጉላቸው፣ በሐዘን ላይ ያሉትን ቅረቧቸው፣ አበረታቷቸው፣ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ልታካፍሏቸው እንድትችሉ አብራችኋቸው አጭር የእግር ጉዞ አድርጉ። እርግጥ በመክብብ 3:4 ላይ ያሉትን ቃላት በአእምሮአችን በመያዝ ከልክ በላይ መሳቅ የለብንም። ሌሎችን ማጽናናት ብንፈልግም የምናጽናናቸው ለወቅቱ በሚስማማ መንገድ ነው።— ሮሜ 12:15
8 የምናደርገውን ፍቅራዊ እርዳታ ሐዘኑ በተከሰተባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ መወሰን የለብንም፤ ከዚህ ይልቅ በቀጣዮቹ ወራትም በተደጋጋሚ ብናጽናናቸው ጥሩ ነው። “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ መጽናናት የሚያስፈልጋቸውን ለማጽናናት የሚረዳውን ቃሉንና ብዙ ጽሑፎችን ሰጥቶናል።— 2 ቆሮ. 1:3–7
9 ተስፋ የሌላቸው ሰዎች በሚያዝኑበት መንገድ ስለማናዝን ሩቅ ቦታ የሚኖር ዘመዳችን ሞቶ መርዶ ሲደርሰን ለቅሶ ደራሾችን እየጠበቅን ቤታችን ለመቀመጥ ምክንያት አለንን? በተጨማሪም በእነዚህ ጊዜያት ወዳጆቻችን ለቅሶ አልደረሱም ብለን ቅር እንሰኛለንን? ሌላ ቦታ ቀብረው መጥተው ለቅሶ መቀመጥን ባሕላቸው ያደረጉት የዚህ ዓለም ሰዎች እንደ እኛ ዓይነት ተስፋ የላቸውም። በመክብብ 7:8, 9 ላይ ያሉትን ቃላት ማስታወስና ሸክማችንን የመጽናናት አምላክ በሆነው በይሖዋ ላይ ጥሎ በአገልግሎቱ መቀጠል የተሻለ አይደለምን? እንደዚህ ካደረግን ወንድሞቻችንም ጊዜያቸውን ገዝተው የመንግሥቱን ጥቅሞች ሊከታተሉ ይችላሉ።
10 እንደዚህ ያሉት የሐዘን ወቅቶች ተስፋ ቢስ የሆነው የሰይጣን ዓለም ክፍል እንዳልሆንን በማሰብ በቃልም ሆነ በድርጊት ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይፈጥራሉ። አጠያያቂ በሆኑ ልማዶች አለመሳተፋችን ጎረቤቶቻችንና ዘመዶቻችን በእውነትና በሐሰት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። የዝግጅቶቹ ቀላል መሆን ራሱ ጥሩ ምሥክርነት ይሆናል። የቀብሩ ንግግር ስለ ትንሣኤ ተስፋ፣ ሰው ለምን እንደሚሞትና ሞት ድል እንደሚደረግ በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ ያተኩራል። ሆኖም ስለ ሟቹ የሚገልጹ አንዳንድ የደግነት አስተያየቶችንም ሊጨምር ይችላል። እርግጥ በግላችን የደግነት ተግባሮችን በመፈጸምና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች፣ በትራክቶች ወይም በሌሎች ጽሑፎች ተጠቅመን ለቅሶ ደራሾችን በማነጽ ብርሃናችን እንዲበራ ልናደርግ እንችላለን። (ማቴ. 5:14–16) እነዚህ ጥረቶች ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ከመቀመጥ ምንኛ የተሻሉ ናቸው!
ሐዘን
11 ስለዚህ አስደሳች ተስፋ ስላለን ሐዘናችን በልኩና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መገለጽ አለበት። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ “ለቅሶ” በሚለው ርዕስ ሥር እንዲህ ይላል:- “በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ለቅሶ ይደረግ የነበረው ብዙ ውጪያዊ የሐዘን መግለጫዎችን በማሳየት፣ በመጮኽና መላ ቅጡ በጠፋ ሁኔታ ነበር። ምንም እንኳ ኢየሱስ ‘በውስጡ ቢታወከም’ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ቢያለቅስም ከላይ የተገለጹትን የታይታ ድርጊቶች እንደፈጸመ የሚጠቁም መረጃ የለም።” (ጥራዝ 2 ገጽ 447) አርአያነቱ ሊኮረጅ ይገባዋል። እርግጥ ኢየሱስ እንዳደረገው ሐዘናችን እንድናለቅስ ሊያደረገን ይችላል፤ ሆኖም አንዳንዴ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ሲጮኹና ከልክ በላይ ሲያለቅሱ ይታያሉ። እንዲያውም አንዳንዶች ሬሳውን ይስማሉ። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ከልብ ላይሆን ይችላል፤ ተመልካቾችን ለመሳብ የሚደረግ የታይታ ድርጊት ሊሆን ይችላል። የዓለም ክፍል ስላልሆንን እንዲህ በማድረግ የተሳሳተ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ለመመሳሰል እንፈልጋለንን?— ዮሐ. 17:14
12 ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ አገሮች የተለያዩ ጎሣዎች የሙታን መናፍስት አሉ፤ በሚታዩ ትዕይንቶች ጸጥ ሊሉ ይችላሉ በሚል እምነት ላይ የተመሠረቱ ልማዶች አሏቸው። እነዚህ ልማዶች ሌሊቱን ሙሉ ሳይተኙ መዝፈን፣ ማልቀስ ወይም የአልኮል መጠጦችን መጠጣትን ይጨምራሉ። ሴቶች የቆሸሹ ልብሶችን ይለብሳሉ፣ መሬት ላይ ይቀመጣሉ፣ ፀጉራቸውን ይነጫሉ፣ በከፊል ራቁታቸውን ይሆናሉ፣ መናፍስት እንዲሰሟቸው ይጮኻሉ፣ እጅ ለእጅ ይተቃቀፋሉ ወይም በቡድን ሆነው ያለቅሳሉ። ሌሎች ደግሞ ብዙ ከብቶችን አርደው በዓል ያደርጉና ይጨፍራሉ። በተጨማሪም ቀን ተወስኖ የሙት ዓመት ሊወጣና የሐውልት ምርቃት ሊደረግ ይችላል። ይህ ሁሉ ሙታን አሁንም በሕይወት አሉ ከሚለው ከሰይጣን ውሸት ጋር የተያያዘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን አንዳች እንደማያውቁ በግልጽ ይናገራል።— ከዘዳግም 14:1, 2 ጋር አወዳድር።
13 እርግጥ እንደ እኛ ዓይነት ተስፋ የሌላቸው በዓለም የሚኖሩ ሰዎች የተለየ አኗኗራችንን ያስተውላሉ። አንዳንዶች ሊተቹን ይችላሉ። ይሁን እንጂ ዓለምን በሁሉም መንገድ ማስደሰት እንደማንችል እናውቃለን። “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።” (2 ጢሞ. 1:7) ሳያስፈልግ እንቅፋት ባንሆንም የዓለም ሰዎች ስለ እኛ ምን ይሉናል ብለን በመፍራት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት አንጥስም። እንዲያውም ለአምላክ ቃል አክብሮት ያላቸው ቅን ሰዎች በአቋማችን ምክንያት ስለ ሁኔታው የማወቅ ፍላጎታቸው ሊቀሰቀስና እውነት ሊማርካቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ዓለማዊ ሰዎች ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ልማዶች በቤታችን እንዲደረጉ ሊጠይቁ ይችላሉ። አንድ ክርስቲያን እነዚህን ሰዎች ከፈለጉ ሌላ ቦታ ያድርጉ እንጂ ቤቱ ውስጥ እንዲህ ማድረግ እንደማይችሉ በደግነት ግን በጥብቅ ሊያሳውቃቸው ይችላል። የቤተሰቡ ራስ የማያምኑ ዘመዶቹን መቆጣጠር ካልቻለ በቤተሰቡ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ይሖዋ ያወገዛቸውን ልማዶች እንደማይፈልጉ በማሳየት ራሳቸውን ከጉዳዩ ነፃ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ወጪዎች
14 ለቀብር የሚደረጉ ወጪዎችን መሸፈንን በተመለከተም ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ቀለል ያሉ ዝግጅቶችን ማድረግ ወጪዎችን ይቀንሳል። ጉባኤዎቻችን ለቀብር የሚውል ገንዘብ ስለሌላቸውና ለዚህ ብለን መዋጮዎች ስለማናሰባስብ የሟች ቤተሰቦች የራሳቸውን ገንዘብ መመደብ አለባቸው። አንዳንዶች ብድር ይጠይቃሉ። እርግጥ በመዋጮም ሆነ በብድር መልክ ለተቸገረው ቤተሰብ በግል የገንዘብ እርዳታ ማድረግ መጥፎ አይደለም። ይሁን እንጂ ወንድሞች በሕብረት ሆነው ለቀብር የሚውል ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ቢጀምሩ እንደ ዓለም ስለ ሞት ብቻ የምናስብ መሆናችን አይደለምን? በመዝሙር 37:25 እና በዕብራውያን 13:5, 6 ላይ ያሉት ቃላት እውነት መሆናቸው ተረጋግጧል፤ ወደፊትም እንደዚሁ መሆናቸውን ይቀጥላሉ።
15 መጽሐፍ ቅዱስ ደግነትንና ልግስናን ስለሚያበረታታ አንዳንድ ግለሰቦች እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመርዳት ይገፋፉ ይሆናል። (ዕብ. 13:16፤ ያዕ. 1:27፤ 2:15–17) በእርግጥም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ አንዳንዶች የሌሎችን ሸክም ለመሸከም በመርዳት ፍቅራቸውን ለመግለጽ ይችላሉ። (ገላ. 6:5) ይህም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ላዘኑ ወንድሞቻቸውና ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ፍቅራዊ አሳቢነት በማሳየት ራሳቸውን ማቅረባቸውን ይጨምራል። (ዮሐ. 13:35) ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ በግል የሚሰጥ እርዳታ በቂ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እርዳታ የሚገባቸው ሰዎች ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ በ1 ጢሞቴዎስ 5:3, 8–10, 16 ላይ ያለው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ምክር ጉባኤው በሆነ መንገድ ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚችል ያሳያል። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው የቤተሰብ አባሎች እንደሆኑ ይገልጻል፤ ይሁን እንጂ እንደ ቀላል የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ለማከናወን የሚያስችሉ እርዳታዎችን ጉባኤው ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ወቅት ሽማግሌዎች ይወያያሉ፤ አስፈላጊ ከሆነም ውሳኔውን ለጉባኤው ያቀርባሉ።
16 ሞት የሚቀርበትንና የምንወዳቸው ሰዎች በትንሣኤ የሚነሡበትን ጊዜ በጉጉት ስንጠባበቅ የሚያጽናናውን ምሥራች በግ መሰል ለሆኑ ሰዎች ለማዳረስ ጊዜያችንን እንገዛለን። ይህን ስናደርግ ተስፋ ቢስ ከሆነው ዓለም የተለየን መሆናችንን እናሳያለን፤ መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅም እንጥራለን።