ለሌሎች አሳቢነትን አሳዩ— ክፍል 2
1 የይሖዋ ምሥክሮች በመልካም ባሕርያቸው ይታወቃሉ። በጎረቤት አካባቢ፣ በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ እንዲሁም በትልልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ የምናሳያቸው ግሩም የአቋም ደረጃዎች የብዙ መልካም አስተያየቶች ርዕስ ሆነዋል።— መጠበቂያ ግንብ 12–110 ገጽ 20 ተመልከት።
2 እርግጥ መልካም ጠባይ እንደ ሐቀኝነት፣ ትጋትና ጥሩ ሥነ ምግባር ያሉ ብዙ ነገሮችን ያካትታል። በመንግሥት አዳራሻችን አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች አክብሮት ማሳየትንም ይጨምራል። ለጎረቤቶቻችን አሳቢነት ካላሳየን በሌላ በኩል የምናሳየው አምላካዊ ጠባይ ላይስተዋል ይችላል። ጳውሎስ “ለምሥራቹ የሚገባ ጠባይ አሳዩ” ሲል አጥብቆ መክሯል።— ፊልጵ. 1:27 አዓት
3 አልፎ አልፎ በስብሰባ ላይ የሚገኙት ወንድሞች አሳቢነት እንዳላሳዩአቸው ስለሚሰማቸው በአንዳንድ የመንግሥት አዳራሾች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ቅሬታ ያሰማሉ። ወንድሞችና እህቶች በመንግሥት አዳራሹ ፊት ለፊት ባሉ መተላለፊያ መንገዶች ከመሰባሰብና በአቅራቢያው ባሉ ቤቶች ያሉትን ሊረብሹ ከሚችሉ የደሩ ጭውውቶች መቆጠብ አለባቸው። ልጆች በመንግሥት አዳራሹ አካባቢ እንዲሯሯጡ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በግዴለሽነት የመኪና በሮችን በኃይል መዝጋት ወይም ክላክስ ማድረግ በአካባቢው ያሉትን ሰዎች ሊረብሽ ይችላል። በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች በሚያከናውኑት ንግድ ውስጥ ጣልቃ ከመግባት እንቆጠባለን። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በጉባኤው ላይ ነቀፋ ሊያመጣ ይችላል። በተጨማሪም በዚያ አካባቢ መኪና ስንነዳ የትራፊክ ሕጎችን በሙሉ ማክበራችን አስፈላጊ ነው።— ሮሜ 13:1, 2, 5
4 መኪናዎች በሰው ቦታ ላይ ወይም የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን ወይም የመኪና መንገዶችን በሚዘጉበት ቦታ መቆም የለባቸውም። በአቅራቢያው የሚገኙ የንግድ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ብለው የያዟቸው የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ካላስፈቀዱ በስተቀር መጠቀም አይገባም።
5 መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ሲል ይመክረናል፤ ይህም በውጭ ላሉት አሳቢነት ማሳየትን ይጨምራል። (1 ቆሮ. 10:31–33) ‘የሌሎችን ጥቅም የምናስብ’ ከሆነ ሳናስፈቅድ በግዴለሽነት ንብረታቸውን አንወስድም። (ፊልጵ. 2:4 1980 ትርጉም ) የምናደርገውና የምንናገረው ‘ባልንጀራችንን እንደ ነፍሳችን የምንወድ’ መሆኑን የሚያሳይ መሆን አለበት።— ማቴ. 7:12፤ 22:39