የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • od ምዕ. 11 ገጽ 116-122
  • አምልኳችንን የምናከናውንባቸው ቦታዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምልኳችንን የምናከናውንባቸው ቦታዎች
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ
  • የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ
  • የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች
  • ይህ የአምልኮ ቦታችን ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ለመንግሥት አዳራሻችሁ አክብሮት ታሳያላችሁ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
  • የአምልኮ ቦታችንን በሚገባ እንያዝ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
  • ለአምልኮ ቦታህ አክብሮት ታሳያለህን?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
od ምዕ. 11 ገጽ 116-122

ምዕራፍ 11

አምልኳችንን የምናከናውንባቸው ቦታዎች

እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ለመማርና እርስ በርስ ለመበረታታት አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ታዘዋል። (ዕብ. 10:23-25) የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች የነበሩት እስራኤላውያን ለአምልኮ ይጠቀሙበት የነበረው የመጀመሪያው ቦታ “የማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑ” ነበር። (ዘፀ. 39:32, 40) ከጊዜ በኋላ፣ የዳዊት ልጅ ሰለሞን ለአምላክ ክብር የሚውል ቤት ወይም ቤተ መቅደስ ሠርቷል። (1 ነገ. 9:3) ይህ ቤተ መቅደስ በ607 ዓ.ዓ. ከወደመ በኋላ አይሁዳውያን ምኩራብ ተብለው በሚጠሩ ሕንፃዎች ውስጥ ለአምልኮ ይሰበሰቡ ነበር። ውሎ አድሮ ቤተ መቅደሱ ዳግመኛ የተገነባ ሲሆን በድጋሚ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ኢየሱስ በምኩራቦችም ሆነ በቤተ መቅደሱ አስተምሯል። (ሉቃስ 4:16፤ ዮሐ. 18:20) ሌላው ቀርቶ በተራራ ላይ ስብሰባ ያደረገበት ጊዜም ነበር።—ማቴ. 5:1 እስከ 7:29

2 ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ክርስቲያኖች ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማስተማርና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አንድ ላይ ለመሰብሰብ ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ቦታዎችና በግል መኖሪያ ቤቶች ይጠቀሙ ነበር። (ሥራ 19:8, 9፤ ሮም 16:3, 5፤ ቆላ. 4:15፤ ፊልሞና 2) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከአሳዳጆቻቸው እይታ ለመሰወር ሲሉ ራቅ ባሉ ቦታዎች ለመሰብሰብ የተገደዱበት ጊዜም ነበር። በእርግጥም ቀደም ባሉት ዘመናት የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በአምልኮ ቦታዎች ተገኝተው ‘ከይሖዋ የመማር’ ልባዊ ፍላጎት ነበራቸው።—ኢሳ. 54:13

3 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ቦታዎችና በግል መኖሪያ ቤቶች ይሰበሰባሉ። ብዙውን ጊዜ የግል መኖሪያ ቤቶች የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ለማድረግ ያገለግላሉ። ቤታቸውን እንዲህ ላሉ ስብሰባዎች ክፍት የሚያደርጉ ወንድሞች ይህን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። ብዙዎች እንዲህ በማድረጋቸው በመንፈሳዊ እንደተጠቀሙ ይሰማቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ

4 የይሖዋ ምሥክሮች በዋነኝነት የሚሰበሰቡት በስብሰባ አዳራሾቻቸው ውስጥ ነው። አብዛኛውን ጊዜ መሬት ተገዝቶ አዲስ የስብሰባ አዳራሽ ይገነባል፤ አሊያም ቀድሞ የነበረን ሕንፃ አሻሽሎ በመሥራት ለዚህ ዓላማ እንዲውል ማድረግ ይቻላል። ወጪ ለመቀነስና ሕንፃውን በሚገባ ለመጠቀም ሲባል አመቺ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ የተወሰኑ ጉባኤዎች በአንድ የስብሰባ አዳራሽ እንዲጠቀሙ ይደረጋል። በአንዳንድ አካባቢዎች አዳራሽ መከራየት ሊያስፈልግ ይችላል። አዳዲስ የስብሰባ አዳራሾች ሲገነቡ ወይም በነባሮቹ አዳራሾች ላይ ሥር ነቀል የሆነ እድሳት ሲደረግ የውሰና ፕሮግራም ማዘጋጀት ተገቢ ይሆናል። ይሁን እንጂ በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ላይ መጠነኛ እድሳት ብቻ በሚደረግበት ጊዜ የውሰና ፕሮግራም ማዘጋጀቱ አስፈላጊ አይሆንም።

5 የስብሰባ አዳራሹ ሌሎችን የሚያስደምም የተንቆጠቆጠ ሕንፃ መሆን አያስፈልገውም። የሕንፃው ንድፍ ከቦታ ቦታ ሊለያይ ቢችልም ትልቅ ትኩረት የሚደረገው አዳራሹ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ነው። (ሥራ 17:24) አዳራሹ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የሚስማማና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ አመቺ መሆን ይኖርበታል።

6 ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች፣ ለሚጠቀሙበት የስብሰባ አዳራሽ ጥገናም ሆነ የተለያዩ ወጪዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ። ይሁንና ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም፤ ተሰብሳቢዎቹም ገንዘብ እንዲሰጡ ጫና አይደረግባቸውም። ተሰብሳቢዎች ከአዳራሹ ጋር በተያያዘ ለሚወጡት አስፈላጊ ወጪዎች መዋጮ ማድረግ ከፈለጉ በአዳራሹ ውስጥ በሚገኘው የመዋጮ ሣጥን ውስጥ መክተት ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉት በፈቃደኝነትና ከልባቸው ተነሳስተው ነው።—2 ቆሮ. 9:7

7 በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ የስብሰባ አዳራሹን በገንዘብ መደገፍም ሆነ አዳራሹ ንጹሕና በአግባቡ የተያዘ እንዲሆን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላቸው ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ብዙውን ጊዜ፣ ለጽዳትና ለጥገና ሥራው ፕሮግራም የሚያወጣ እንዲሁም ይህን የሚከታተል አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ይመደባል። በአብዛኛው ጽዳቱ የሚከናወነው በመስክ አገልግሎት ቡድኖች ሲሆን የቡድን የበላይ ተመልካቹ ወይም ረዳቱ ግንባር ቀደም ሆነው ይሠራሉ። የስብሰባ አዳራሹ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ይሖዋንና ድርጅቱን በሚገባ የሚወክል መሆን አለበት።

በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ የስብሰባ አዳራሹን በገንዘብ መደገፍ እንዲሁም አዳራሹ ንጹሕና በአግባቡ የተያዘ እንዲሆን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላቸው ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማቸዋል

8 በአንድ አዳራሽ ውስጥ ከአንድ በላይ ጉባኤዎች የሚሰበሰቡ ከሆነ የጉባኤዎቹ ሽማግሌዎች ከሕንፃውና ከንብረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚከታተል የስብሰባ አዳራሽ ኮሚቴ ያቋቁማሉ። የሽማግሌዎቹ አካላት አንድ ወንድም የኮሚቴው አስተባባሪ ሆኖ እንዲያገለግል ይመርጣሉ። ይህ ኮሚቴ በሽማግሌዎቹ አካላት አመራር ሥር ሆኖ አዳራሹ በንጽሕናና በጥሩ ሁኔታ መያዙን እንዲሁም አላቂ ዕቃዎች በበቂ መጠን መኖራቸውን ይከታተላል። ይህ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን አዳራሹን በሚጠቀሙት ጉባኤዎች መካከል የትብብር መንፈስ ሊኖር ይገባል።

9 በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ከአንድ በላይ ጉባኤዎች የሚጠቀሙ ከሆነ የስብሰባ ሰዓታቸውን በዙር መቀየር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ሽማግሌዎቹ ይህን ፕሮግራም ሲወስኑ የመተሳሰብ መንፈስ ሊያሳዩና የወንድማማች መዋደድ ሊኖራቸው ይገባል። (ፊልጵ. 2:2-4፤ 1 ጴጥ. 3:8) የትኛውም ጉባኤ ሌሎቹን ጉባኤዎች በመወከል ብቻውን ውሳኔ ማድረግ አይችልም። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በስብሰባ አዳራሹ ከሚጠቀሙ ጉባኤዎች መካከል አንዱን ሲጎበኝ ሌሎቹ ጉባኤዎች በዚያ ሳምንት ስብሰባ የሚያደርጉበትን ፕሮግራም እንደ አስፈላጊነቱ ሊያስተካክሉ ይችላሉ።

10 የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ በሚሰጠው ፈቃድ መሠረት የስብሰባ አዳራሹን ለጋብቻ ወይም ለቀብር ንግግር መጠቀም ይቻላል። ሽማግሌዎቹ እያንዳንዱን ማመልከቻ በጥንቃቄ የሚመረምሩ ሲሆን ከቅርንጫፍ ቢሮው ባገኙት መመሪያ ላይ ተመርኩዘው ውሳኔ ይሰጣሉ።

11 የስብሰባ አዳራሹን ለዚህ ዓላማ እንዲጠቀሙ የተፈቀደላቸው ሰዎች ከእውነተኛ ክርስቲያኖች የሚጠበቅ ምግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል። በአዳራሹ ውስጥ ጉባኤውን ቅር የሚያሰኝ ወይም በይሖዋና በጉባኤው ጥሩ ስም ላይ ነቀፋ የሚያመጣ ምንም ነገር መደረግ የለበትም። (ፊልጵ. 2:14, 15) ቅርንጫፍ ቢሮው በሚሰጠው መመሪያ መሠረት የስብሰባ አዳራሹ ለሌሎች መንፈሳዊ ጉዳዮች ለምሳሌ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤትና የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ለማካሄድ ሊያገለግል ይችላል።

12 ጉባኤው መሰብሰቢያ ቦታውን ምንጊዜም በአክብሮት መያዝ አለበት። አለባበሳችን፣ አጋጌጣችንም ሆነ ጠባያችን ክብር ለተላበሰው የይሖዋ አምልኮ የተገባ መሆን ይኖርበታል። (መክ. 5:1፤ 1 ጢሞ. 2:9, 10) በዚህ ረገድ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን አድናቆት እንዳለን ያሳያል።

13 በስብሰባ ወቅት የሚረብሽ ነገር እንዳይኖር ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ሲባል ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ቢቀመጡ የተሻለ ነው። በተጨማሪም ትናንሽ ልጆች ያሏቸው ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ለመቅጣት ወይም ሌሎች ነገሮችን ለማድረግ በሚወጡበት ጊዜ ተሰብሳቢዎቹን እንዳይረብሹ ለመውጣት አመቺ የሆነ ቦታ ላይ መቀመጣቸው ጥሩ ነው።

14 በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅት፣ ብቃት ያላቸው ወንድሞች አስተናጋጅ ሆነው እንዲያገለግሉ ይመደባሉ። እነዚህ ወንድሞች ንቁ፣ ተግባቢና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ከተጣሉባቸው ኃላፊነቶች መካከል አዲሶች ሲመጡ ሰላምታ መስጠትና ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ማድረግ፣ ዘግይተው የሚመጡ ሰዎች የሚቀመጡበት ወንበር እንዲያገኙ መርዳት፣ የተሰብሳቢዎችን ቁጥር መመዝገብ እንዲሁም አዳራሹ ጥሩ አየር እንዲያገኝ እንደ አስፈላጊነቱ መስኮቶችን መክፈት ወይም መዝጋት ይገኙበታል። በተጨማሪም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ወላጆች ልጆቻቸው መድረክ ላይ ወጥተው እንዳይጫወቱና ከስብሰባ በፊትም ሆነ በኋላ እንዳይሯሯጡ እንዲቆጣጠሯቸው ማሳሰቢያ ይሰጣሉ። አንድ ልጅ የሚረብሽ ከሆነ የአድማጮች ትኩረት ስለሚከፋፈል ወላጁ ልጁን ወደ ውጭ ይዞት እንዲወጣ አንድ አስተናጋጅ በደግነትና በዘዴ ሊጠይቀው ይችላል። አስተናጋጆች የሚያከናውኑት ሥራ ሁሉም ሰው ስብሰባውን በጥሩ ሁኔታ እንዲከታተል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። አስተናጋጅ ሆነው የሚመደቡ ወንድሞች የጉባኤ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች ቢሆኑ ይመረጣል።—1 ጢሞ. 3:12

የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ

15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንዳንድ ክርስቲያኖች ኑሯቸው ከሌሎች የተሻለ ነበር፤ በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የእናንተ ትርፍ የእነሱን ጉድለት እንዲሸፍን ነው፤ የእነሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት ይሸፍናል፤ ይህም ሸክሙን እኩል እንድትጋሩ ያስችላል።” (2 ቆሮ. 8:14) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ወጪዎችን በመሸፈን ረገድ “ሸክሙን እኩል እንዲጋሩ” ይደረጋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች የሚያዋጡት ገንዘብ አንድ ላይ ተጠራቅሞ ለስብሰባ አዳራሾች ግንባታና ጥገና የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ይውላል። ድርጅቱም ሆነ ከመዋጮው የሚጠቀሙት ጉባኤዎች፣ ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በልግስና ለሚሰጠው ድጋፍ አመስጋኞች ናቸው።

16 ቅርንጫፍ ቢሮው የተለያዩ ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ጉባኤዎችን በየስብሰባ አዳራሾቹ ይደለድላል። ከዚህም በተጨማሪ ቅርንጫፍ ቢሮው በሥሩ ባለው ክልል ውስጥ መቼና የት አዲስ የስብሰባ አዳራሽ መገንባት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ነባሮቹ አዳራሾች እድሳት ያስፈልጋቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ይወስናል። የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ጉዳት የደረሰባቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የወንድሞች መኖሪያ ቤቶች አስፈላጊው ጥገና እንዲደረግላቸው ዝግጅት ይደረጋል።

17 ቅርንጫፍ ቢሮው መሬት ከመግዛት፣ የስብሰባ አዳራሹን ንድፍ ከማዘጋጀት፣ የግንባታ ፈቃድ ከማውጣት እንዲሁም የግንባታና የጥገና ሥራውን ከማከናወን ጋር በተያያዘ እገዛ የሚያበረክቱ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያስተባብራል። በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጨማሪ የስብሰባ አዳራሾች ስለሚያስፈልጉ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። ብቃቱን የሚያሟሉና እርዳታ የማበርከት ፍላጎት ያላቸው የተጠመቁ አስፋፊዎች ለዚህ የተዘጋጀውን ቅጽ ሞልተው ለጉባኤያቸው የአገልግሎት ኮሚቴ መስጠት ይችላሉ። ያልተጠመቁ አስፋፊዎችም እንኳ የራሳቸው የስብሰባ አዳራሽ ሲገነባ ወይም ሲታደስ እገዛ ማበርከት ይችላሉ።

የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች

18 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በአብዛኛው የሚሰበሰቡት አነስ ባሉ ቡድኖች ነበር። አንዳንድ ጊዜ ግን “ብዙ ሕዝብ” አንድ ላይ ይሰበሰብ ነበር። (ሥራ 11:26) በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ብዙ ሆነው ይሰበሰባሉ። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን ስብሰባዎች የሚያደርጉት የመሰብሰቢያ ቦታ ተከራይተው ነው፤ እንዲህ ያሉ ቦታዎችን ማግኘት በማይቻልበት አሊያም በእነዚህ ቦታዎች መሰብሰብ አመቺ በማይሆንበት ጊዜ ግን ለአምልኮ የሚጠቀሙባቸውን የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ሊገነቡ ወይም ሊገዙ ይችላሉ።

19 አንዳንድ ጊዜ አንድ ሕንፃ ከተገዛ በኋላ እድሳት ተደርጎለት ትላልቅ ስብሰባዎች የሚደረጉበት አዳራሽ ሆኖ እንዲያገለግል ይደረጋል። አብዛኛውን ጊዜ ግን መሬት ይገዛና አዲስ አዳራሽ ይገነባል። የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ስፋት እንደ አካባቢው ሁኔታ ከቦታ ቦታ ሊለያይ ይችላል። ቅርንጫፍ ቢሮው ለዚህ አገልግሎት የሚውል ሕንፃ ለመግዛት ወይም ለመገንባት የሚወስነው ወጪውን በሚገባ ካጤነና ሕንፃው ምን ያህል አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል ከመረመረ በኋላ ነው።

20 ቅርንጫፍ ቢሮው ለትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ጥገናና ክትትል የሚያደርጉ ወንድሞችን ይሾማል። በአዳራሹ የሚጠቀሙት ወረዳዎች በስብሰባ ወቅትም ሆነ በስድስት ወር አንዴ የሚካሄደውን ጽዳት እንዲያከናውኑ እንዲሁም እድሳትና ክትትል እንዲያደርጉ ዝግጅት ይደረጋል። ወንድሞች ይህን ሥራ ለማከናወን ራሳቸውን በፈቃደኝነት ማቅረባቸው ጠቃሚ ነው። በመሆኑም ጉባኤዎች ለእነዚህ ዝግጅቶች የተሟላ ድጋፍ እንዲሰጡ ይበረታታሉ።—መዝ. 110:3፤ ሚል. 1:10

21 የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን ለማስተናገድ የሚውሉበት ጊዜ አለ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችንና ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚዘጋጁ ልዩ ስብሰባዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ፣ ልክ እንደ ስብሰባ አዳራሽ ለአምላክ አገልግሎት የተወሰነ የአምልኮ ቦታ ነው። በስብሰባ አዳራሽ ለአምልኮ በምንሰበሰብበት ጊዜ እንደምናደርገው ሁሉ በትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ በምንሰበሰብበት ወቅትም ምግባራችን፣ አለባበሳችንና አጋጌጣችን ሥርዓታማ ሊሆን ይገባል።

22 እነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ሊጠናቀቁ በተቃረቡበት በዛሬው ጊዜ አዳዲስ ሰዎች ወደ አምላክ ድርጅት በመጉረፍ ላይ ይገኛሉ። ይህም ይሖዋ ሥራውን እየባረከ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ኢሳ. 60:8, 10, 11, 22) በመሆኑም የአምልኮ ቦታዎቻችንን ንጹሕና ምቹ ለማድረግ እንዲሁም በአግባቡ ለመያዝ የሚደረጉትን ዝግጅቶች መደገፍ እንፈልጋለን። እንዲህ ማድረጋችን የይሖዋ ቀን እየቀረበ ባለበት በዛሬው ጊዜ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ መበረታታት የምንችልበት አጋጣሚ ለሚሰጡን ለእነዚህ የአምልኮ ቦታዎች አድናቆት እንዳለን ያሳያል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ