የአምልኮ ቦታችንን በሚገባ እንያዝ
1. የይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለምን አገልግሎት ይውላል?
1 በዓለም ዙሪያ ከ94, 000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አሉ። አብዛኞቹ ጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማርና ከወንድሞቻቸው ጋር ለመገናኘት የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ሆኖ በሚያገለግለው በአካባቢያቸው በሚገኝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይሰበሰባሉ።
2. የመሰብሰቢያ አዳራሹ በንጽሕናና ማራኪ በሆነ ሁኔታ መያዝ ያለበት ለምንድን ነው?
2 በቋሚነት መከናወን ያለበት ጽዳት:- የመሰብሰቢያ አዳራሹን ማጽዳት የቅዱስ አገልግሎታችን ዐቢይ ክፍል ነው። አገልግሎታችን የተባለው መጽሐፍ በገጽ 61-2 ላይ እንዲህ ይላል:- “ወንድሞች የመንግሥት አዳራሹን በገንዘብ መደገፉን ብቻ ሳይሆን አዳራሹን ንጹሕና ደስ የሚል አድርጎ ለመያዝና ለመጠገን ጉልበታቸውን በፈቃደኝነት መስጠቱን እንደ መብት ሊቆጥሩት ይገባቸዋል። የመንግሥት አዳራሹ በውጭውም ይሁን በውስጡ የይሖዋን ድርጅት በትክክል የሚወክል መሆን ይኖርበታል።” አዳራሹ በሳምንቱ ውስጥ ደጋግመን ስለምንሰበሰብበት ዘወትር መጸዳት ይኖርበታል። አብዛኛውን ጊዜ ይህን ሥራ የሚያከናውኑት በአዳራሹ የሚጠቀሙት ፈቃደኛ ወንድሞችና እህቶች ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮችም የአምልኮ ቦታቸውን ‘ለመጠገንና ለማደስ’ ትጉዎች መሆን ይገባቸዋል።—2 ዜና 34:10
3. የመሰብሰቢያ አዳራሹ ጽዳት በምን መልኩ ሊደራጅ ይችላል? በዚህ መብት እነማን መሳተፍ ይችላሉ?
3 የሳምንቱ የጽዳት ፕሮግራም ማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ መለጠፍ ይኖርበታል። ሁሉም የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች አዳራሹ እንዴት መጸዳት እንዳለበት የወጣውን ዝርዝር በመከተል በየሳምንቱ ተራ ገብተው ማጽዳት አለባቸው። ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ሁሉ አዳራሹን ንጹሕና ማራኪ ለማድረግ ባላቸው መብት መሳተፍ ይገባቸዋል። ልጆች፣ ወላጆቻቸው እየተከታተሏቸው በጽዳት ሥራው መካፈል ይችላሉ። በዚህ መንገድ ለዚህ መብት አድናቆት እንዲኖራቸው ትምህርት ያገኛሉ። በተለይ በአዳራሹ የሚጠቀሙት ከአንድ በላይ ጉባኤዎች በሚሆኑበት ጊዜ አዳራሹን በየጊዜው የማጽዳቱ ኃላፊነት በጥቂት ወንድሞች ላይ እንዳይወድቅ ጥሩ ቅንጅት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
4. ወንድሞች የአዳራሹ ጽዳት የሚያጠቃልላቸውን ነገሮች እንዲያውቁ ምን ማድረግ ይቻላል?
4 አዳራሹን ማጽዳት ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል የሚገልጽ ዝርዝር ለሥራው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በሚቀመጡበት ቦታ መለጠፍ ይቻላል። አቧራ ማንሳት፣ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫቶችን መድፋት፣ ወለሉን መወልወልና መጸዳጃ ቤቶችን ማጽዳትን ጨምሮ በየሳምንቱ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች በዝርዝሩ ላይ መካተት አለባቸው። መስተዋቶችን መወልወል፣ ከእንጨት የተሠሩ ዕቃዎችን ሰም መቀባት እንዲሁም ወንበሮችን፣ መጋረጃዎችን፣ ማብሪያና ማጥፊያዎችንና ሶኬቶችን በሚገባ እንደ ማጽዳት የመሳሰሉ ሥራዎችን አልፎ አልፎ ማድረግ ይቻላል። ለጽዳት የሚውሉ ኬሚካሎች በሙሉ ልጆች በማይደርሱበት ቦታ መቀመጥና ዓይነታቸው በግልጽ መጻፍ አለበት። እያንዳንዱ ኬሚካል ለምን ዓላማ እንደሚውል የሚያስረዳ አጭር መግለጫ ሊለጠፍበት ይገባል።
5. አደጋ የሚያስከትሉ ነገሮችን ለማስወገድ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል? በየጊዜው ክትትል የሚያስፈልጋቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (በገጽ 3 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
5 በአዳራሹና በግቢው ውስጥ አደጋ የሚያስከትል ነገር እንዳይኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። (ዘዳ. 22:8) በገጽ 3 ላይ የሚገኘው ሣጥን አደጋዎችን ማስወገድ እንዲቻል በየጊዜው ክትትል ሊደረግላቸው ስለሚገቡ ነገሮች አንዳንድ ነጥቦችን ይዟል።
6. አዳራሹን በጥሩ ሁኔታ ለመያዝ ሥራው የሚቀናጀው እንዴት ነው?
6 የመንግሥት አዳራሹን ማደስ:- አዳራሹን በሚገባ ለመያዝ ክትትል ማድረግ የሽማግሌዎች አካል ኃላፊነት ነው። በአብዛኛው አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ የሥራው አስተባባሪ ሆኖ ይሾማል። አዳራሹ ንጹሕና በሚገባ የተያዘ መሆኑን እንዲሁም ለሥራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን በመከታተል የአዳራሹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ያቀናጃል። በአዳራሹ ወይም በግቢው ውስጥ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች መኖር የለባቸውም። ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ጉባኤዎች በአንድ አዳራሽ የሚጠቀሙ ከሆነ የሽማግሌዎቹ አካላት አዳራሹንና ንብረቶቹን የሚከታተል ኮሚቴ ያቋቁማሉ። ይህ ኮሚቴ በሽማግሌዎቹ አካላት ሥር ሆኖ ይሠራል።
7. (ሀ) አዳራሹን ጥሩ አድርጎ ለመያዝ በየዓመቱ ምን መደረግ አለበት? (ለ) በዓመት አንድ ጊዜ ክትትል ሊደረግላቸው የሚገቡ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (በገጽ 4 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
7 አዳራሹ ጥገና ያስፈልገው እንደሆነ ለማወቅ በየዓመቱ እያንዳንዱ ነገር አንድ በአንድ ይታያል። ለሁሉም ጉባኤዎች የተላከው “ዓመታዊ የመንግሥት አዳራሽ ጥገና እና የሰነዶች መከታተያ ቅጽ” (N-14) ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል። ሽማግሌዎች ትኩረት የሚያሻቸው ሥራዎች በሚገባ እንዲከናወኑ አስፈላጊውን ዝግጅት የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ለአዳራሹ በሚደረገው የእደሳና የጥገና ሥራ እንዲካፈሉ አስፋፊዎችን መጠየቅ ይቻላል። በሥራው የሚሳተፉ ሁሉ መስተካከል ያለባቸውን ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ላለማለፍና ትኩረት የሚያሻቸውን ነገሮች ወዲያውኑ ለመጠገን ንቁ መሆን አለባቸው።
8. ሽማግሌዎች እድሳትን በተመለከተ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቢሮውን ማነጋገር የሚያስፈልጋቸው መቼ ነው?
8 ሽማግሌዎች የአዳራሹን እድሳት በተመለከተ ሐሳብ ወይም እርዳታ ማግኘት ከፈለጉ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቢሮውን ማነጋገር ይችላሉ። ይህም ግድግዳ ላይ ያሉ ስንጥቆችን፣ የሚያፈስስ ጣሪያንና እርጥበት ያዘሉ ቦታዎችን የመሳሰሉ ነገሮችን ሊጨምር ይችላል።
9. ሕንፃ ተቋራጭ መቅጠር ካስፈለገ ሽማግሌዎች የትኛውን አሠራር መከተል ይኖርባቸዋል?
9 የጉባኤውን ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም:- ከአዳራሹና ከግቢው ጥገና ጋር በተያያዘ አብዛኛው ሥራ የሚከናወነው በፈቃደኛ ሠራተኞች ነው። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሚያከናውኑት ሥራ የፍቅራቸው መግለጫ ከመሆኑም በላይ ወጪ ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንዳንዱን ሥራ በሕንፃ ተቋራጭ ማሠራት ካስፈለገ ሽማግሌዎቹ ሥራውን በአነስተኛ ዋጋ የሚያከናውን ሰው ለማግኘት ጨረታ ያወጣሉ። ይህን ለማድረግ ሥራው የሚያካትታቸውን ነገሮች እና ለሥራው የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች ዝርዝር በጽሑፍ ማዘጋጀት አለባቸው። ሁሉም ተወዳዳሪዎች የሚጠበቅባቸውን ነገር በሚገባ ተገንዝበው መጫረት እንዲችሉ የዚህ ዝርዝር ቅጂ ይሰጣቸዋል። ሽማግሌዎቹ የተጫራቾቹን ማመልከቻ ከተቀበሉ በኋላ የሚያዋጣቸውን ዋጋ ይመርጣሉ። በተወሰነ ዋጋ ሥራውን ለማከናወን ወይም የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ለማቅረብ የሚችል ወንድም ቢኖርም እንኳ ይህን አሠራር መከተል ያስፈልጋል።
10. የጉባኤው ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
10 ከዚህ በተጨማሪ ከቀረጥ ነፃ መሆን የሚቻልበት ዝግጅት ካለ በዚህ ተጠቃሚ ለመሆን ሽማግሌዎች አስፈላጊውን ነገር ያደርጋሉ። በአዳራሹ ከአንድ በላይ ጉባኤዎች የሚጠቀሙ ከሆነ የአዳራሹን ሁኔታ የሚከታተለው ኮሚቴ የራሱ የባንክ ሒሳብ ይኖረዋል። እንዲሁም ሽማግሌዎቹ የተደረጉትን ወጪዎች ማወቅ እንዲችሉ ለእያንዳንዱ ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል በየወሩ የሒሳብ ሪፖርት በጽሑፍ ያቀርባል። ሽማግሌዎቹ የጉባኤው ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው።
11. መጠነ ሰፊ እድሳት ወይም ጥገና በሚያስፈልግበት ጊዜ ምን መደረግ ይኖርበታል?
11 ከፍተኛ እደሳና ጥገና:- የአዳራሹን ሁኔታ የሚከታተለው ኮሚቴ አዳራሹ ከበድ ያለ እደሳ እንደሚያስፈልገው ከተስማማ ጉዳዩን ለሽማግሌዎቹ አካላት ያቀርባል። መጠነ ሰፊ እደሳ እንደሚያስፈልግ ከተወሰነ ወይም በአዳራሹ ከሚሰበሰቡት ጉባኤዎች በተጨማሪ የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልግ ከሆነ ሽማግሌዎች የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቢሮን ማነጋገር ይኖርባቸዋል። በዚህ መስክ ችሎታውና ልምዱ ያላቸው እነዚህ ወንድሞች ጠቃሚ ሐሳብ ያቀርባሉ እንዲሁም ሥራውን በበላይነት ይቆጣጠራሉ። እድሳቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ከሆነ ወጪውን በተመለከተ ትክክለኛ ግምት ማግኘት እንዲሁም ግምቱን የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቢሮው እንዲገመግመውና ጉባኤው በድምፀ ውሳኔ እንዲያጸድቀው ማድረግ ያስፈልጋል።—በየካቲት 1994 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን የጥያቄ ሣጥን ተመልከት።
12. በመንግሥት አዳራሹ የመሰብሰብ መብታችንን እንደምናደንቅ እንዴት ማሳየት እንችላለን?
12 በአዳራሹ አንድ ላይ የመሰብሰብ መብታችንን በጣም እናደንቃለን! ስብሰባዎቻችንን በቸልታ ወይም አቅልለን መመልከት አንፈልግም። የመንግሥት አዳራሻችንን በአግባቡ ለመያዝ ለሚደረገው ጥረት የተሟላ ድጋፍ በመስጠት ማበረታቻ ለምናገኝበት ለዚህ ዝግጅት መሳካት ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። እንደዚህ ማድረጋችን ንጹሑን አምልኮ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ስም ያስከብራል። የአምልኮ ቦታችንን በሚገባ ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
[ገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለቅድሚያ ጥንቃቄ የሚረዱ ሐሳቦች
◻ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎች በቀላሉ ለማግኘት አመቺ በሆነ ቦታ ላይ መቀመጥና በየዓመቱ መታደስ ይኖርባቸዋል።
◻ ዋናው በርም ሆነ የአደጋ ጊዜ መውጫዎችና ደረጃዎች በግልጽ የሚነበብ ምልክትና በቂ ብርሃን ሊኖራቸው እንዲሁም ለመክፈት የማያስቸግሩ (ይህም በስብሰባ ወቅት መቆለፍ የለባቸውም ማለት ነው) ሊሆኑ ይገባል። ደረጃው ላይ ያሉ የእጅ መደገፊያ ብረቶች ደግሞ ጥብቅ መሆን አለባቸው።
◻ የዕቃ ማስቀመጫ ክፍሉና መጸዳጃ ቤቱ ንጹሕና ያልተዝረከረከ ሊሆን ይገባል። በክፍሉ ውስጥ በቀላሉ በእሳት የሚያያዙ ነገሮች፣ የግለሰቦች ዕቃና ቆሻሻ መቀመጥ የለባቸውም።
◻ ጣሪያውንና አሸንዳዎቹን በየጊዜው ማየትና ማጽዳት ያስፈልጋል።
◻ የእግረኛ መተላለፊያዎችና የመኪና ማቆሚያው አካባቢ በቂ ብርሃን ሊኖረው የሚገባ ሲሆን የሚያዳልጥና የሚያደናቅፍ ነገር መወገድ አለበት።
◻ የኤሌክትሪክ፣ የማሞቂያና የአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያዎች ክትትልና ተገቢው ጥገና ሊደረግላቸው ይገባል።
◻ እርጥበት አዳራሹን እንዳያበላሸው ውኃ የሚያንጠባጥቡ ቦታዎች ወዲያውኑ መጠገን አለባቸው።
◻ አዳራሹ ውስጥ ሰው በማይኖርበት ጊዜ በሩ መቆለፍ አለበት።
[ገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለጉባኤው አዳራሽና ንብረት ክትትል ማድረግ
◻ ከውጭ በኩል:- ጣሪያው፣ የግድግዳው ቀለም፣ መስኮቶቹ እንዲሁም “የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ” የሚለው ምልክት በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው?
◻ ቅጥር ግቢው:- ግቢው በደንብ የተያዘ ነው? የእግረኛ መተላለፊያው፣ አጥሩና የመኪና ማቆሚያው ቦታ በሚገባ ተይዟል?
◻ የአዳራሹ ውስጥ:- ወንበሮቹ፣ ግድግዳው ላይ የተገጠሙት የኤሌትሪክ ዕቃዎችና የቧንቧ መስመሮች፣ የግድግዳው ቀለም እና የጽሑፍ መደርደሪያው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
◻ መሣሪያዎች:- የመብራትና የድምፅ መሣሪያዎቹ በሚገባ ይሠራሉ?
◻ መጸዳጃ ቤቶች:- ንጽሕናቸው የተጠበቀና ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው?
◻ የጉባኤው ሰነዶች:- የባለቤትነት ሰነዶች ወቅታዊና ትክክለኛ ናቸው? ሕጉ የሚጠይቅ ከሆነ ለቦታውና ለሕንፃው የሚጠየቀው ግብር በየዓመቱ ይከፈላል?