ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለግበታል
1 እውነትን በማወቃችን ምንኛ ታድለናል! ራሳችንን ለይሖዋ በመወሰናችን ‘ወንጌሉ በአደራ ተሰጥቶናል።’ (1 ተሰ. 2:4) ይህም ከፍተኛ ኃላፊነት ይጥልብናል። ኢየሱስ “ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል” ብሏል።— ሉቃስ 12:48
2 እነዚህ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! ሁላችንም በአምላክ ቃል እውቀት፣ ከወንድሞች ጋር ባለን ግሩም ቅርርብና በአስደናቂ ተስፋ ስለ ተባረክን በእርግጥም ብዙ ተሰጥቶናል ሊባል ይችላል። ስለዚህ በምላሹ ከእኛ ብዙ የሚጠበቅብን መሆኑ ተገቢ ነው።
3 ስለሚፈለጉብን ብቃቶች ተገቢ አመለካከት ያዙ፦ አንዳንዶች በጣም ብዙ ነገሮች ይፈለጉብናል ብለው ደምድመዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደመሆኑ መጠን ጉባኤው በአግባቡ እንዲሠራ “ምን እንደሚያስፈለግ” ይወስናል። (ኤፌ. 4:15, 16 አዓት ) ‘ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙም ቀሊል’ እንደሆነ አረጋግጦልናል። (ማቴ. 11:28–30) አቅማቸው ውስን የሆኑትን ሰዎች ሁኔታ በፍቅር ግምት ውስጥ ያስገባል። (ሉቃስ 21:1–4) መጠኑ የቱንም ያህል ቢሆን ምርጣችንን ከሰጠን እንባረካለን።— ቆላ. 3:23, 24
4 ‘በሕይወቴ ውስጥ የመንግሥቱን ጥቅሞች አንደኛ ቦታ እሰጣቸዋለሁን? ጊዜዬንና ያሉኝን ንብረቶች ለአምላክ ስም ክብር በሚያመጣና ለሌሎች ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ እየተጠቀምኩበት ነውን? በሥጋዊ ነገሮች በራስ ወዳድነት ከመርካት ይልቅ ይሖዋን በማገልገል እደሰታለሁን?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጣቸው ሐቀኛ መልሶች በልባችን ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ያሳያሉ።— ሉቃስ 6:45
5 መጥፎ ነገር እንድታደርጉ ከሚመጣባችሁ ፈታና ራቁ፦ የራስን ጥቅም በመፈለግ፣ በስግብግብነትና ስሜታዊ ደስታን በመውደድ ረገድ እንደዚህ ያሉ ፈተናዎችና ግፊቶች የተስፋፋበት ዘመን ኖሮ አያውቅም። በየዕለቱ አቋማችንን እንድናላላ የሚገፋፉ የሥነ ምግባር ፈተናዎች ይገጥሙናል። እነዚህን ፈተናዎች በተሳካ መንገድ ለመቋቋም ይሖዋ እንዲረዳን መጠየቅ አለብን። (ማቴ. 26:41) ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ሊያበረታን ይችላል። (ኢሳ. 40:29) በየዕለቱ የአምላክን ቃል ማንበብ ብዙ ጠቀሜታ አለው። (መዝ. 1:2, 3) በተጨማሪም ራስን መገሠጽና ራስን መግዛት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።— 1 ቆሮ. 9:27
6 መልካሙን መውደድ ብቻ አይበቃም፤ ክፉውንም መጥላት አለበን። (መዝ. 97:10) ይህም ማለት መጥፎ ለሆኑት ነገሮች ጉጉት ማሳደር የለብንም ማለት ነው። ምሳሌ 6:16–19 ይሖዋ የሚጠላቸውን ሰባት ነገሮች ይዘረዝራል። ይሖዋን ማስደሰት የፈለገ ሰው እነዚህን ነገሮች መጥላት እንዳለበት ግልጽ ነው። የእውነትን ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ስለ ተባረክን አእምሯችን በመልካም ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ሁልጊዜ ካገኘነው እወቀት ጋር ተስማምተን ለመኖር መፈለግ አለብን።
7 ሁልጊዜ ‘የጌታ ሥራ እንዲበዛልን’ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩልን መጸለያችን ተገቢ ነው። (1 ቆሮ. 15:58) ብዙዎች የማይረቡ ነገሮችን ከማሳደድ ስለሚጠብቅ በይሖዋ አገልግሎት መጠመድ ጥበቃ እንደሆነ ተገንዝበዋል።
8 ከእነዚህ ሐሳቦች መረዳት እንደምንችለው ይሖዋ ከእኛ የሚፈልግብን ሁሉ ምክንያታዊ ነው። (ሚክ. 6:8) ለእያንዳንዱ የአገልግሎት መብት አመስጋኝ እንድንሆን የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉን። (ኤፌ. 5:20) ስለዚህ ከእኛ የሚፈለግብን ማንኛውም ነገር ከምናገኘው ሽልማት ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ በመተማመን “ጠንክረን መሥራታችንና ጥረት ማድረጋችንን” እንቀጥል።— 1 ጢሞ. 4:10 አዓት