በስብሰባ ላይ አዘውትሮ መገኘት ጸንቶ ለመኖር የግድ አስፈላጊ ነው
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “በእምነት ጤናማዎች” ሆነን እንድንቀጥል አጥብቆ መክሮናል። (ቲቶ 1:9, 13 የ1980 ትርጉም ) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚያንጹ ነገሮችን ለማሰብ ከመቻላችንም በላይ ‘የሰይጣንን ሽንገላ መቃወም’ የሚያስችሉንን መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች እንደለበስን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ትምህርት እናገኛለን።— ኤፌ. 6:11፤ ፊልጵ. 4:8
2 ስብሰባዎች የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያቀርቡልናል፦ ጸንተን ለመኖር እንድንችል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት የግድ አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮ. 16:13) በስብሰባዎች ላይ አምላክን ለማመስገንና ለማወደስ እንዲሁም ስለ ጉባኤውና ጉባኤው የሚያስፈልገውን ነገሮች ለመጠየቅ ጸሎት ይቀርባል። (ፊልጵ. 4:6, 7) የመንግሥቱን መዝሙሮች ከሌሎች ጋር በአንድነት መዘመራችን ያነቃቃናል፤ እንዲሁም ይሖዋን በማምለካችን የሚሰማንን ስሜት ለመግለጽ ያስችለናል። (ኤፌ. 5:19, 20) ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ በመንግሥት አዳራሹ ተገናኝተን የምናደርገው ጭውውት ያበረታታናል፣ ያንጸናል እንዲሁም መንፈሳችንን ያድስልናል።— 1 ተሰ. 5:11
3 ባለፈው ሚያዝያ የተሰጠው “የሐሰት ሃይማኖት ፍጻሜ ቀርቧል” የተባለው ልዩ ንግግር እውነትን የሚያፈቅሩ ሰዎች ከታላቂቷ ባቢሎን ለመውጣት ፈጣን እርምጃ የመውሰዱን አጣዳፊነት እንዲገነዘቡ ኃይለኛ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። (ራእይ 18:4) የጻድቃን መንገድ እየበራ እንዲሄድ ያደረጉትን የእውቀት ብልጭታዎች በተመለከተ በሰኔና በሐምሌ ወር ሦስት የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች ማጥናታችን እንዴት የሚያነቃቃ ነበር! (ምሳሌ 4:18) በእነዚያ ስብሰባዎች ላይ ባንገኝ ኖሮ ምን ነገር ያመልጠን እንደነበር አስብ።
4 “ደስተኛ አወዳሾች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባችን ላይ አገልግሎታችንን ሊያሻሽልልን ስለሚችል ትምህርት አስፈላጊነት ጎላ ተደርጎ ተገልጾ ነበር። አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የተባለው መጽሐፍ በገጽ 73 ላይ እንደሚገልጸው የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ጉባኤው በጠቅላላ ትምህርት የሚያገኝበት አንዱ መንገድ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዚህ ፕሮግራም ከሚቀርቡት ክፍሎች አንዱ በአገልግሎታችን ላይ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ተጠቅመን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ መልእክታችንን ማቅረብ የምንችልባቸውን መንገዶች ጥሩ አድርገን እንድናውቅ እየረዳን ነው። ይህ ትምህርት እንዲያመልጠን መፍቀድ የለብንም።
5 የአገልግሎት ስብሰባችን በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ያስችለናል። ይህም የመንግሥት ዜና ቁ. 34ን በሰፊው በማሰራጨቱ ሥራ እንድንካፈል የሚያስችለንን ትምህርት ባገኘንበት ስብሰባ ላይ ታይቷል። በዓለም ዙሪያ ከተገኙት ከፍተኛ ውጤቶች ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ይህንን ሥራ አብዝቶ ባርኮታል። (ከ2 ቆሮንቶስ 9:6, 7 ጋር አወዳድር።) በስብሰባዎቹ ላይ አዘውትረው የተገኙ ሰዎች ማበረታቻ ከማግኘታቸውም በላይ ለዘመቻው የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለመስጠት አስችሏቸዋል።
6 በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ራእይ መደምደሚያ በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ከአምላክ ቃል የተማርናቸው ነገሮች ስለ ጊዜው አጣዳፊነት ያለንን ስሜት አጠናክረውልናል። በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች በፍጥነት እየተፈጸሙ ሲሄዱ ጥልቅ የሆኑትን የራእይ ትንቢቶች መረዳት ያስፈልገናል።
7 ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ ዘወትር በስብሰባ ላይ ለመገኘት ቅድሚያ ስጥ፦ ወንድሞቻችን መከራ እየደረሰባቸው ባሉባቸው አያሌ አገሮች በየሳምንቱ እርስ በርስ የመገናኘትን አስፈላጊነት አልዘነጉም። ለምሳሌ በብሩንዲ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤርያ፣ በቦስኒያና ሄርዞጎቪና ከአስፋፊዎቹ ሁለት እጥፍ አልፎ ተርፎም ሦስት እጥፍ የሚያክሉ በጣም ብዙ አዳዲስ ሰዎች በስብሰባ ላይ ይገኛሉ። ይሖዋ በዚህ መንገድ ወንድሞች በአንድ መንፈስ ጸንተው እንዲኖሩ እየረዳቸው ነው።— ፊልጵ. 1:27፤ ዕብ. 10:23–25
8 አዘውትሮ በስብሰባ ላይ የማይገኝ ሰው አሁኑኑ እርምጃ ወስዶ አቋሙን ማስተካከል አለበት። (መክ. 4:9–12) ጸንተን ለመኖር እንድንችል ከጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች ጋር እርስ በርስ መተናነጽ ያስፈልገናል፤ ይህ ደግሞ የሚገኘው አዘውትሮ በስብሰባ ላይ በመገኘት ነው።— ሮሜ 1:11