በአውራጃ ስብሰባ ላይ በወጣው አዲሱ መጽሐፍ ሁሉም ሰው ተደስቷል አዲሱ መጽሐፍ አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ጎላ አድርጎ ይገልጻል
1 በቅርቡ ባደረግነው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የቀረቡት ፕሮግራሞች በጠቅላላ እንዴት የሚያስደስቱ ነበሩ! ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ መውጣቱንና ቀጥሎ የቀረበውን ከመጽሐፉ ጋር የተያያዘ መግለጫ ስንሰማ ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆኖ ነበር። በምድር ላይ የሚኖሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከአምላክ ብቻ ሊገኝ የሚችለው እውቀት ይኸውም ስለ አምላክና ስለ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።— ምሳሌ 2:1–6፤ ዮሐ. 17:3
2 ተናጋሪው የመጽሐፉን ክፍሎች ሕያው በሆነ መንገድ ገልጿቸዋል! ስሜትን የሚማርኩት ርዕሶቹ፣ በጥሩ ሁኔታ የቀረቡት ሥዕሎቹ፣ እውነትን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ማቅረቡ፣ ያልተወሳሰቡ ጥያቄዎቹና በእያንዳንዱ ምዕራፍ መደምደሚያ ላይ የቀረበው “እውቀትህን ፈትሽ” የሚለው ሣጥን ይህንን መጽሐፍ የሚያነቡትን ሰዎች ትኩረት ከሚስቡት የመጽሐፉ ገጽታዎች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ትምህርቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመማር የሚያስችላቸው በመሆኑ ይበልጥ ይጠቀማሉ።
3 ቅዳሜና እሑድ በቀረቡት የመደምደሚያ ንግግሮች ላይ ይህንን አዲስ መጽሐፍ ለቤተሰብ ጥናታችን እንድንጠቀምበት ማበረታቻ ተሰጥቶናል። አዲሱን መጽሐፍ እንዳገኘን ከይዘቱ ጋር መተዋወቅ አለብን። ይህንን አዲስ መጽሐፍ በመስክ አገልግሎት ስታበረክት የምትጠቀምባቸውን ነጥቦች ከወዲሁ ትኩረት እንደምትሰጥባቸው አያጠራጥርም።
4 አንዳንድ ነጥቦችን ለመከለስ ያህል፦ “የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠው እውቀት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?” የሚለው ንግግር ሲቀርብ ተናጋሪው የሚከተሉትን ጨምሮ ብዙ ነጥቦች ጎላ አድርጎ እንደገለጸ ታስታውስ ይሆናል:- (1) ይህን መጽሐፍ ጥናቶችን ለማስጠናት ስትጠቀምበት ዋና ዋና ነጥቦችን ሊያዳፍን የሚችል ሐሳብ ከሌላ ጽሑፍ መጨመሩ ጥበብ አይደለም፤ መጽሐፉ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ሊያስገነዝብ በፈለገው ነጥብ ላይ አትኩር። (2) የእያንዳንዱ ምዕራፍ ርዝመት ልከኛ ስለሆነ አብዛኛውን ጊዜ በአንድ የጥናት ወቅት አንድ ምዕራፍ መጨረስ ትችላለህ። (3) በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ ባለው “እውቀትህን ፈትሽ” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡት ጥያቄዎች እጥር ምጥን ያለ ክለሳ ለማድረግ ያስችላሉ።
5 መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ተጠቀምበት፦ ብዙ አስፋፊዎች የሚያስጠኑበትን መጽሐፍ በአዲሱ መጽሐፍ መተካቱ አስፈላጊ እንደሆነና እንዳልሆነ ጠይቀዋል። እያስጠናህበት ባለው መጽሐፍ ብዙ ገፍታችሁ ከሆነ መጽሐፉን መጨረሱ ጥሩ ነው። አለበለዚያ ግን እውቀት በተባለው መጽሐፍ ማጥናት ጀምሩ። በብሮሹር ወይም በትራክት ተጠቅመህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመርክ ተስማሚ በሆነ ጊዜ ላይ አዲሱን መጽሐፍ ለምታስጠናው ሰው አስተዋውቅና ለማስጠናት ተጠቀምበት። በመጪዎቹ ወራት በሚወጡ የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞች ላይ እውቀት በተባለው መጽሐፍ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩ ተጨማሪ ሐሳቦች ይወጣሉ።
6 ይሖዋ ሰዎችን ወደ ዘላለም ሕይወት ስለሚመራው እውቀት ለማስተማር የሚረዳንን ይህን አዲስ መጽሐፍ አዘጋጅቶልናል። በጥሩ ሁኔታ መዘጋጀትና በቀሪው ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ይፈለግብናል።