የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በየዕለቱ እውነትን ማወጅ
1 ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ አንድ የሚያከናውነው ሥራ ነበረው። ወደ ምድር የመጣው ‘ለእውነት ለመመስከር’ ነበር። (ዮሐ. 18:37) ስለ አባቱ አስደናቂ ባሕርያትና ዓላማዎች የሚገልጸውን እውነት አውጆአል። ይህ ሥራ ለእርሱ የምግብ ያህል ነበር። መላ ሕይወቱ ያተኮረው በዚህ ሥራ ላይ ነበር። (ዮሐ. 4:34) ኢየሱስ ‘በየዕለቱ በመቅደስ ያስተምር’ እንደነበር ሉቃስ ጽፏል። (ሉቃስ 19:47) ኢየሱስ የነበረውን ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞበታል። (ዮሐ. 9:4) ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” በማለት ለአባቱ መናገር ችሎ ነበር።— ዮሐ. 17:4
2 እኛም ልባችን ይሖዋ በሠራቸው ነገሮች አድናቆት ሲሞላ በየዕለቱ ስለ እርሱ ለመናገር እንገፋፋለን። “እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” በማለት በድፍረት እንደተናገሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንሆናለን። (ሥራ 4:20) ዘገባው ‘ያለማቋረጥ በየዕለቱ ’ በማለት ስለሚናገር ደቀ መዛሙርቱ ስለ ይሖዋ ዘወትር ይናገሩ ነበር። (ሥራ 5:42) ‘የአስተማሪዬን የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተልኩ ነውን?’ በማለት ራሳችንን መጠየቅ አለብን።
3 በጥድፊያ ስሜት መስበክ፦ ‘መጨረሻው የሚመጣው’ የመንግሥቱ መልእክት በመላው ምድር ከተሰበከ በኋላ እንደሆነ ኢየሱስ ተንብዮአል። (ማቴ. 24:14) ይህም የሥራችንን አስፈላጊነትና አጣዳፊት ሊያስገነዝበን ይገባል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ ስለሚገኝ ከዚህ የተሻለ አስፈላጊ ወይም ጠቃሚ ሥራ ማግኘት አንችልም። ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ስለሆነ ሥራው ለመጠናቀቅ የቀረው ጊዜ አነስተኛ ነው!
4 ይሖዋ በግ መሰል የሆኑትን ሰዎች የመሰብሰቡን ሥራ እያፋጠነው እንዳለ የተለያዩ ሪፖርቶች ያሳያሉ። (ኢሳ. 60:22) በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” ብለው በደስታ በመናገር ቃል በቃል ወደ እውነት እየጎረፉ ነው! (ዘካ. 8:23) “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ . . . የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት እውነተኝነት ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ጎላ ብሎ ታይቷል። (ማቴ. 9:37, 38) ይህ ‘ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ’ እንደኖሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቀናተኞች እንድንሆን አያነሳሳንምን?— ሉቃስ 24:53
5 በየዕለቱ እውነትን አስታውቁ፦ በየዕለቱ እውነትን ለሰዎች የምናካፍልበትን መንገድ መፈለግ አለብን። ምንጊዜም እንዲህ ማድረግ የምንችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ መልእክቱን ሊቀበል ይችላል ብለህ ለምታስበው ጓደኛህ ወይም ለአንድ ለምታውቀው ሰው ስልክ መደወል ትችላለህን? ወይም እቤቱ ሄደህ ላጣኸው አንድ ሰው ደብዳቤ ብትጽፍስ? ዕቃ ስትገዛ ለባለሱቁ ትራክት ለማበርከት አስበህ ታውቃለህን? በየዕለቱ ተስፋህን ለሌሎች ማካፈል የምትችልባቸውን ሌሎች ብዙ አጋጣሚዎች ማሰብ ትችላለህ። ጥረት ካደረክና ትንሽ ድፍረት ካሳየህ ይሖዋ ይረዳሃል።— 1 ተሰ. 2:2
6 ስለዚህ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን ከመጀመራችን በፊት ‘ዛሬ አጋጣሚ ካገኘሁ ተስፋዬን ለሌሎች ለማካፈል ጥረት አደርጋለሁን?’ በማለት ራሳችንን መጠየቅ አለብን። የኢየሱስን ዝንባሌ ኮርጅ። ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው ለምን እንደሆነ ሲናገር “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” ብሏል። (ሉቃስ 4:43) እንደ አስተማሪያችን ለመሆን ከፈለግን እርሱ ያደረገውን እናደርጋለን።— ሉቃስ 6:40