ከ1996 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጥቅም ማግኘት— ክፍል 3
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ወንጌል በድፍረት መናገር እንዲችል ወንድሞቹ እንዲጸልዩለት ጠይቋል። (ኤፌ. 6:18-20) እኛም ይህን ዓይነት ችሎታ እንዲኖረን እንፈልጋለን። ብቃቱን የሚያሟሉ ተሰብሳቢዎች ሁሉ የሚሳተፉበት የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በዚህ ረገድ የሚኖረውን እገዛ እንገነዘባለን።
2 ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን የመናገርና የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል የሚረዳ እኛን በግል የሚመለከት ምክር ይሰጠናል። (ምሳሌ 9:9) በተጨማሪም ለሌሎች ተማሪዎች የሚሰጠውን ምክር ሰምተን የተማርነውን በሥራ ላይ በማዋል መጠቀም እንችላለን። ክፍላችንን በትክክል ለማብራራት እንድንችል ክፍሉ የተወሰደበትን ጽሑፍ በሚገባ ማጥናት ይኖርብናል። የምናጎላቸው ዋና ዋና ነጥቦችና የምንጠቀምባቸው ጥቅሶች ከምናዳብረው አጠቃላይ ጭብጥ ጋር መጣጣም ይኖርባቸዋል። ክፍሉን የምናቀርበው ከሌላ ሰው ጋር ከሆነ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከማቅረባችን በፊት በሚገባ መለማመድ ይኖርብናል። እድገት እያደረግን ስንሄድ የምንናገረውን ጽፈን ከማንበብ ይልቅ ማስታወሻ በመያዝ በራሳችን አገላለጽ ለመናገር ጥረት ማድረግ ይገባናል።
3 በትምህርት ቤቱ ውስጥ ክፍል ያላቸው ሁሉ ቀደም ብለው በመገኘት የንግግር ምክር መስጫ ወረቀታቸውን ለትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች መስጠትና በአዳራሹ ውስጥ ከፊት ለፊት ባለው ቦታ መቀመጥ ይኖርባቸዋል። እህቶች ምን ዓይነት መቼት እንደሚኖራቸውና ክፍላቸውን የሚያቀርቡት ተቀምጠው ወይም ቆመው መሆኑን ለትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በቅድሚያ ማሳወቅ ይገባቸዋል። በእነዚህ መንገዶች መተባበራችን ፕሮግራሙ በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ ከማስቻሉም በላይ በመድረክ ላይ የሚሠሩት ወንድሞች ሁሉንም ነገር አስቀድመው እንዲያዘጋጁ ይረዳቸዋል።
4 ክፍል ቁጥር 2ን መዘጋጀት፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል አንዱ ዓላማ ተማሪው የንባብ ችሎታውን እንዲያሻሽል መርዳት ነው። ይህንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ማከናወን የሚቻለው እንዴት ነው? ከጽሑፉ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ የሚያስችለን ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጮክ ብለን ደግመን ደጋግመን ማንበባችን ነው። ተማሪው ከአሁን ቀደም የማያውቃቸውን ቃላት ትርጉምና ትክክለኛ አነባበብ ለማወቅ መዝገበ ቃላትን ማገላበጥ ይኖርበታል። ይህም የቃላቱ አነባበብ ምን መሆን እንዳለበት ከሚጠቁሙት የመዝገበ ቃላቱ ምልክቶች ጋር መተዋወቅን ይጠይቃል።
5 ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍሎቻቸውን እንዲዘጋጁ ሊረዷቸው ይችላሉ። ይህም ልጁ ክፍሉን ሲለማመድ በማዳመጥ ሊያሻሽልባቸው የሚገቡትን ጠቃሚ ነጥቦች ማቅረብን ሊጨምር ይችላል። ለክፍሉ የሚመደበው ጊዜ ልከኛ መግቢያና ቁልፍ የሆኑትን ነጥቦች ተግባራዊነት የሚጠቁም ተስማሚ መደምደሚያ እንዲኖረው የሚያስችል ነው። በዚህ መንገድ ተማሪው በራሱ አገላለጽ ንግግር የመስጠት ችሎታውን ያዳብራል።
6 መዝሙራዊው “አቤቱ ከንፈሮቼን ክፈት፣ አፌም ምስጋናህን ያወራል” በማለት ጸሎት አቅርቧል። (መዝ. 51:15) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ የምናደርገው ተሳትፎ ይህን ምኞታችን እንድንፈጽም ይርዳን።