“ቀኑን ሙሉ” ይሖዋን ባርኩ
1 ንጉሥ ዳዊት በመዝሙር 145:2 [አዓት] ላይ “ቀኑን ሙሉ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለም አወድሳለሁ” በማለት ለይሖዋ ቃል ገብቷል። እኛም ሰማያዊ አባታችንን የምንባርክበትና የምናወድስበት ምክንያት አለን! ይሁን እንጂ “ቀኑን ሙሉ” የይሖዋን ሉዓላዊነት ከፍ ከፍ በማድረግ ረገድ የዳዊትን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
2 ልባችንን ለይሖዋ ባለን አመስጋኝነት እንሙላ፦ አዘውትሮ የአምላክን ቃል ማጥናት ይሖዋ ቀደም ሲል ላደረገልን፣ በአሁኑ ወቅት እያደረገልን ላለውና ወደፊት ለሚያደርግልን ነገር ያለን አመስጋኝነት ከፍ እንዲል ያደርጋል። አስገራሚ ለሆኑት ሥራዎቹ ያለን አድናቆት እያደገ ሲሄድ ላገኘነው ሰው ሁሉ ስለ ጥሩነቱ ለመናገር እንገፋፋለን። (መዝ. 145:7 አዓት) ባገኘነው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ ይሖዋን በግለት እናወድሰዋለን።
3 በዕለት ተዕለት ንግግራችን ይሖዋን እናወድሰው፦ ከጎረቤቶቻችን፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችን፣ ከሥራ ባልደረቦቻችንና በየዕለቱ ከምናገኛቸው ሌሎች ሰዎች ጋር ስንነጋገር ተስፋችንን ለእነርሱ ለማካፈል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እናገኝ ይሆናል። ጎረቤታችን በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጸሙት ወንጀሎች እንዳሳሰቡት ይናገር ይሆናል፣ የትምህርት ቤት ጓደኛችን የሚያየው አላግባብ ዕፅ የመጠቀም ጉዳይ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና አስጨንቆት ሊሆን ይችላል፣ የሥራ ባልደረባችን ስለ አንድ ፖለቲካዊ ጉዳይ ያለውን አስተያየት ይሰነዝር ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ ዛሬ ልንከተለው የሚገባን ትክክለኛ ጎዳና ምን እንደሆነና ወደፊት ለእነዚህ ችግሮች ምን መፍትሔ እንደሚገኝ የሚገልጹትን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ተስፋዎች ልንጠቁማቸው እንችላለን። ‘በተገቢው ጊዜ’ የተነገሩ እንዲህ ያሉ ቃላት በረከት ሊያስገኙ ይችላሉ!— ምሳሌ 15:23
4 ሙሉ ጊዜያችሁን ስለ ይሖዋ ተናገሩ፦ ለይሖዋ ጥልቅ አድናቆት ያለው ሰው በተቻለው መጠን ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማካፈል ይጓጓል። (መዝ. 40:8-10) በዚህ ረገድ ‘ሁኔታዬ የሚፈቅድልኝን ሁሉ እያደረግሁ ነውን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል። ብዙዎች መጠነኛ ማስተካከያዎችን ብቻ በማድረግ አቅኚ መሆን ችለዋል። አሁን ያለንበት ሁኔታ ይህን ለማድረግ የማይፈቅድልን ከሆነ ረዳት አቅኚ መሆን እንችላለንን? መጪው የመታሰቢያው በዓል ወቅት ሰፊ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ጊዜ በመሆኑ የመጋቢትና የሚያዝያ ወራት ረዳት አቅኚዎች በመሆን አገልግሎታችንን ከፍ የምናደርግባቸው ጥሩ ጊዜያት ይሆኑልናል።
5 አዲሶች ይሖዋን ለመባረክ ከእኛ ጋር እንዲተባበሩ እንርዳቸው፦ የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ሲከበር ለይሖዋ አመስጋኞች የምንሆንበትንና ስሙን የምናወድስበትን ምክንያት እንድናስብ ያስችለናል። ይህ ጊዜ በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ከእኛ ጋር ሆነው ስለ ይሖዋ ንግሥና ለሕዝብ እንዲናገሩ ለማበረታታት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ነው። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 173-5 ላይ ከአንቀጽ 7-9 ላይ የሰፈሩትን ሐሳቦች በጸሎት እንዲያሰላስሉባቸው አሳስቧቸው። ብቃቱን የሚያሟሉ ከሆነ ተሞክሮ ስለሚጎድላቸው ብቻ ወደኋላ የሚሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም። የመንግሥቱ የስብከት ሥራ እንዴት እንደሚሠራ ሌሎች ብቃት ያላቸው አስፋፊዎች ሊያሳዩአቸው ይችላሉ። አዲሶች ምሥራቹን ለመናገር ቆርጠው ከተነሡ ይሖዋ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።— ሥራ 4:31፤ 1 ተሰ. 2:2
6 ይሖዋን ቀኑን ሙሉ ለማወደስ ስንጣጣር ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ዘላለማዊ ጥቅሞችን እናስገኛለን።