ለመልእክታችን እነማን ጆሮ ይሰጣሉ?
1 በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ሰዎች ከንቱና አሳሳች የሆኑ ወሬዎች ይሰማሉ። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ተሰላችተዋል። በመሆኑም ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት እንዲያዳምጡ ማድረግ ፈታኝ ሆኖብናል። ሰዎች የአምላክን ቃል ቢያዳምጡ ምን ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ አይገነዘቡም።— ሉቃስ 11:28
2 በዓለም ዙሪያ በተለያዩ የምድር ክፍሎች የሚኖሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚህ መልእክት ጆሯቸውን ሲሰጡና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያደርጉ የምናቀርብላቸውን ግብዣ ሲቀበሉ በጣም ያስደስተናል። በሌሎች የአገልግሎት ክልሎች የሚገኘው ውጤት ግን አነስተኛ ነው። በአገልግሎት እቤታቸው ሄደን የምናገኛቸው ሰዎች ጥሩ ምላሽ ሳይሰጡ ሲቀሩ ለመልእክታችን ጆሯቸውን የሚሰጡት እነማን ይሆኑ ብለን እናስብ ይሆናል።
3 ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እንዳያድርብን መጠንቀቅ ይገባናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? . . . ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ።” (ሮሜ 10:13-15) የመንግሥቱን ዘር ሳንታክት የምንዘራ ከሆነ አምላክ ይህን ዘር ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች ውስጥ ያሳድገዋል።— 1 ቆሮ. 3:6
4 ቁልፉ አዘውትሮ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ነው፦ ለመልእክታችን ጆሯቸውን የሚሰጡ ጥቂት ሰዎች ባሉባቸው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ጽሑፍ ብናበረክትም ባናበረከትም የምናገኘውን ማንኛውንም ፍላጎት ለማሳደግ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል። ምንም ውጤት አይገኝም ብለን ለመደምደም ለምን እንቸኩላለን? ዘር በምንዘራበት ጊዜ ዘሩ የት ቦታ እንደሚጸድቅ አናውቅም። (መክ. 11:6) ከቅዱሳን ጽሑፎች አንድ ነገር ለማካፈል ተዘጋጅተን ተመልሰን ከሄድን አጭር ውይይት የምናደርግ ቢሆንም እንኳ የሰውየውን ልብ መንካት እንችል ይሆናል። ትራክት ወይም በቅርብ ጊዜ የወጡ መጽሔቶችን ልናበረክት እንችላለን። ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚደረግ ማሳየት እንችል ይሆናል። ይሖዋ ጥረታችንን ምን ያህል እንደባረከልን ስናይ ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል።— መዝ. 126:5, 6
5 ፍላጎት ላሳየች አንዲት ሴት ትራክት ተበረከተላት። ሁለት ወር ሙሉ እቤቷ ካለመገኘቷም በላይ ከዚያም በኋላ ቢሆን በሥራ ብዛት ምክንያት ውይይት ማድረግ አልተቻለም። አሁንም የቀድሞ ዓይነት ትራክት ተበረከተላት። ምንም እንኳ አስፋፊዋ እቤቷ ድረስ እየሄደች እርሷን ለማግኘት ያልተቆጠበ ጥረት ብታደርግም ሌላ ሦስት ወር ሳታገኛት ቀረች። ከዚያም ታማ አገኘቻት። እህት በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሳ ሄደች፤ ትራክቱን በሚመለከት አጠር ያለ ውይይት አደረጉ። እህት በቀጣዩ ሳምንት ተመልሳ በሄደች ጊዜ ሴትየዋ ለመንግሥቱ መልእክት ልባዊ ፍላጎት እንዳላት አሳየች። በሕይወቷ ውስጥ የገጠማት የሁኔታዎች መለወጥ ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቿ ንቁ እንድትሆን አደረጋት። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየሳምንቱ በጋለ ስሜት ታጠናለች።
6 ማንኛውም ነገር ለምሳሌ ያህል አበባ፣ የጓሮ አትክልት ወይም ለመንግሥቱ መልእክት የታየ ፍላጎት እንዲያድግ ከተፈለገ እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህም ደግሞ ጊዜን፣ ድካምን፣ እንክብካቤ ማድረግንና ሳይታክቱ ለመሥራት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግን ይጠይቃል። ባለፈው ዓመት የመንግሥቱ ዘር በልባቸው ውስጥ ሥር እንዲሰድ የፈቀዱ ከሩብ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀዋል! በስብከቱ ሥራችን ከቀጠልን መልእክታችንን የሚሰሙ ብዙ ተጨማሪ ሰዎች እንደምናገኝ እርግጠኞች እንሆናለን።— ከገላትያ 6:9 ጋር አወዳድር።