የጥያቄ ሣጥን
▪ ጉባኤው የቀብር ሥነ ሥርዓት ዝግጅት እንዲያደርግ ሲጠየቅ የሚከተሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ:-
የቀብር ንግግሩን መስጠት የሚኖርበት ማን ነው? ይህንን የሚወስኑት የቤተሰቡ አባላት ናቸው። ጥሩ አቋም ያለው አንድ የተጠመቀ ወንድም ንግግሩን እንዲሰጥላቸው ሊመርጡ ይችላሉ። ተናጋሪ እንዲያዘጋጅ የተጠየቀው የሽማግሌዎች አካል ከሆነ በማኅበሩ አስተዋጽኦ ላይ የተመሠረተ ንግግር እንዲያቀርብ አንድ ብቃት ያለው ሽማግሌ እንደሚመርጥ የታወቀ ነው። ስለሟቹ እያጋነንን ባንናገርም እርሱ ወይም እርሷ የነበሯቸውን ምሳሌ የሚሆኑ ባሕርያት መጥቀሱ ተገቢ ሊሆን ይችላል።
የመንግሥት አዳራሹን መጠቀም ይቻል ይሆን? የሽማግሌዎች አካል ከፈቀደና ቋሚ የሆነውን የስብሰባ ጊዜ የማይጋፋ ከሆነ መጠቀም ይቻላል። ሟቹ ጥሩ ስም ያተረፈ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከነበረ ወይም የአንድ የጉባኤው አባል ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ልጅ ከሆነ የመንግሥት አዳራሹን መጠቀም ይቻላል። ግለሰቡ ክርስቲያናዊ ባልሆነ አኗኗሩ በሰፊው የሚታወቅ ከነበረ ወይም በጉባኤው ላይ መጥፎ ነቀፋ የሚያሰነዝር ሌላ ዓይነት ሁኔታ ካለ ሽማግሌዎች የመንግሥት አዳራሹን ላለመፍቀድ ሊወስኑ ይችላሉ።— አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 62-3 ተመልከት።
በመሠረቱ የመንግሥት አዳራሾች ለማያምኑ ሰዎች የቀብር ሥርዓት ግልጋሎት አይውሉም። በሕይወት ያሉት የቤተሰቡ አባላት በአስፋፊነት የሚያገለግሉ የጉባኤ አባላት ከሆኑና ግለሰቡ ለእውነት ጥሩ አመለካከት እንደነበረው እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚያስነቅፍ አኗኗር እንዳልነበረው የሚያውቁ መጠነኛ ቁጥር ያላቸው የጉባኤ አባላት ካሉና ፕሮግራሙ ምንም ዓይነት ዓለማዊ ልማድ የማይጨምር ከሆነ ሊፈቀድ ይችላል።
ሽማግሌዎች የመንግሥት አዳራሹን እንዲጠቀሙ ሲፈቅዱ በአካባቢው ልማድ መሠረት አስከሬኑ በቀብር ንግግሩ ወቅት መገኘቱ የሚጠበቅ ነገር መሆን አለመሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል። ከሆነ ወደ መንግሥት አዳራሹ እንዲያመጡት ሊፈቅዱ ይችሉ ይሆናል።
ለዓለማዊ ሰዎች ስለሚደረግ የቀብር ሥነ ሥርዓትስ ምን ማለት ይቻላል? ሟቹ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ ጥሩ ስም ከነበረው አንድ ወንድም በቤታቸው ወይም በቀብር ቦታው ተገኝቶ የሚያጽናና ንግግር ሊሰጥ ይችል ይሆናል። ግለሰቡ ሥነ ምግባር የጎደለውና ሕገ ወጥ በመሆኑ የሚታወቅ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በከፍተኛ ደረጃ የሚቃረን አኗኗር የነበረው ከሆነ ጉባኤው የቀብር ሥነ ሥርዓቱን እንዲያዘጋጅ የቀረበለትን ጥያቄ አይቀበልም። አንድ ወንድም ከአንድ ቄስ ጋር በጋራ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማከናወንም ሆነ በየትኛውም የታላቂቱ ባቢሎን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚከናወን የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደማይተባበር የታወቀ ነው።
ሟቹ የተወገደ ሰው ቢሆንስ? በጥቅሉ ጉባኤው በጉዳዩ እጁን አያስገባም። የመንግሥት አዳራሹንም አይፈቅድም። ግለሰቡ የንስሐ ፍሬ እያሳየና ለመመለስ እንደሚፈልግ የሚያሳዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ከነበረ አንድ ወንድም ለማያምኑት ሰዎች ምሥክርነት ለመስጠትና ዘመዶቹንም ለማጽናናት በማሰብ በሟቹ ቤት ወይም በቀብር ቦታ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ለመስጠት ሕሊናው ይፈቅድለት ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ወንድም ይህንን ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ከሽማግሌዎች አካል ጋር ቢነጋገርና የሚሰጡትንም ሐሳብ በጥሞና ቢያስብበት ጥበብ ይሆናል። አንድ ወንድም በዚህ ጉዳይ እጁን ማስገባቱ ጥበብ ሆኖ በማይገኝበት ጊዜ የሟቹ ዘመድ የሆነ አንድ ወንድም ዘመዶቹን ለማጽናናት ንግግር ሊሰጥ ይችላል።
በሚከተሉት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል:- 20-111 ገጽ 30-31፤ መስከረም 15, 1981 ገጽ 31፤ መጋቢት 15, 1980 ገጽ 5-7፤ ሰኔ 1, 1978 ገጽ 5-8፤ ሰኔ 1, 1977 ገጽ 347-8፤ መጋቢት 15, 1970 ገጽ 191-2፤ እንዲሁም የእንግሊዝኛ ንቁ! መስከረም 8, 1990 ገጽ 22-3 እና ንቁ! መጋቢት 22, 1977 ገጽ 12-15