የስብከቱ ሥራ ለይቶ ያሳውቀናል
1 ብዙ ሰዎች “የይሖዋ ምሥክሮችን ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?” በማለት ይጠይቃሉ። ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረቱት እምነቶቻችን አንዳንድ ነገሮች ማስረዳት ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ለሕዝብ የምንሰጠው አገልግሎት ከሌሎች ሃይማኖቶች ምን ያህል ለይቶ እንደሚያሳውቀን የመጥቀሱን ጉዳይ አስበህበት ታውቃለህ?—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
2 በዛሬው ጊዜ፣ የሚያምኑባቸውን ነገሮች ለሌሎች ለማካፈል የሚነሳሱት ሃይማኖታዊ ሰዎች ጥቂት ናቸው። የቄሣርን ሕጎች ማክበር፣ በስነ ምግባር የታነጸ ሕይወት መምራት ወይም ለሌሎች የደግነት ድርጊት መፈጸም በቂ እንደሆነ ያስቡ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ መዳን ስለማግኘት የሚናገረውን ነገር ሌሎች እንዲያውቁ የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው አይሰማቸውም። እኛ የተለየን የሆንነው እንዴት ነው?
3 በቅንዓት የምናከናውነው አገልግሎት ሌሎች ሃይማኖቶች ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ጋር ሲነጻጸር ፍጹም የተለየ ሆኖ ይታያል። በዚህ ዘመን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች የቀድሞዎቹን ክርስቲያኖች አርአያ በመከተል ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት ምሥራቹን እስከ ምድር ዳር ድረስ በትጋት ሰብከዋል። የምንሰብክበት ዓላማ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር እንዲያስማሙ ለመርዳት ነው።—1 ጢሞ. 2:3፤ 2 ጴጥ. 3:9
4 ምን ዓይነት ስም አትርፈሃል? በሰዎች ዘንድ የምትታወቀው የአምላክ ቃል ቀናተኛ ሰባኪ በመሆንህ ነውን? (ሥራ 17:2, 3፤ 18:25) በምታደርገው የስብከት እንቅስቃሴ የተነሳ ጎረቤቶችህ በእነርሱና በአንተ ሃይማኖት መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ይታያቸዋልን? በሌሎች ዘንድ የምትታወቀው ተስፋውን ለሌሎች ለማካፈል ጉጉት ያለው ሰው ነው በሚል ነውን? በአገልግሎት የምትሳተፍበት ቋሚ ፕሮግራም አለህን? ራሳችንን ለይተን የምናሳውቀው በስማችን ብቻ ሳይሆን ስሙ የቆመለትን ነገር በማድረግ ይኸውም ስለ ይሖዋ በመመሥከር መሆኑን አትዘንጋ።—ኢሳ. 43:10
5 ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር በስብከቱ ሥራ እንድንሳተፍ ያነሳሳናል። (ማቴ. 22:37-39) በዚህም ምክንያት እንደ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ሁሉ እኛም ማንኛውንም አጋጣሚ ተጠቅመን የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማካፈል እንፈልጋለን። ምሥራቹን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥል። እንዲህ ማድረጋችን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያዩ’ ይረዳቸዋል።—ሚል. 3:18