መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ የሚሆነው ማን ይሆን?
1 ነቢዩ አሞጽ በእስራኤል ምድር ላይ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠጣት ያልሆነ’ ረሃብ እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር። (አሞጽ 8:11) በመንፈሳዊ ሁኔታ ለተራቡና ለተጠሙ ሰዎች ጥቅም ሲባል የይሖዋ ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው ጽሑፍ እያሰራጨ ነው።
2 እስከዚህ ጊዜ ድረስ 70 ሚልዮን እውቀት መጽሐፍና 91 ሚልዮን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ብሮሹር ታትሟል። እነዚህ ጽሑፎች ቀላልና ውጤታማ በሆነ መንገድ እውነትን ለማስተማር የሚረዱ መሆናቸውን እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ ጽሑፎቻችን የደረሷቸው ቃል በቃል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት አልጀመሩም። በዚህ ረገድ ምን ማድረግ እንችላለን?
3 እያንዳንዱ ጽሑፍ የተበረከተለት ሰው ጥናት የመጀመር አጋጣሚው ሰፊ ነው! ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ለመጀመሪያ ጊዜ ላነጋገራት ሴት ጥናት እንድትጀምር ሐሳብ ያቀረበላትን የአንድ አስፋፊ ተሞክሮ ተመልከት። ሴትዬዋ ምንም ሳታቅማማ ጥናት ለመጀመር ተስማማች። ከጊዜ በኋላ እንዲህ አለችው:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድጀምር ሐሳብ ያቀረበልኝ የመጀመሪያው ሰው አንተ ነህ።” በአገልግሎት ክልላችሁ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር የሚናገሩ አስቀድሞም ጽሑፎቻችን ያሏቸው ምን ያህል ሰዎች ይገኙ ይሆን? ጽሑፍ ባበረከታችሁ ቁጥር ተመላልሶ መጠየቅ የማድረግና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር አጋጣሚ ይኖራችኋል።
4 አብዛኛውን ጊዜ አስቀድመው ጽሑፎቻችንን ያገኙ ሰዎች ስለሚያጋጥሙን ጽሑፉ ምን ቁም ነገር እንደያዘ የማወቅ ጉጉታቸውን እንዴት ማነሳሳት እንችላለን? አንዲት ምሥክር ለአንዲት የቤት ባለቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ይኖራት እንደሆነ በቀጥታ ጠየቀቻት። ያገኘችው መልስ ግን “የለኝም” የሚል ነበር። እህት ተስፋ ባለመቁረጥ “አንዳንድ ጥያቄዎች እንደሚኖሩሽ እርግጠኛ ነኝ” አለቻት። በእርግጥም ይህች ሴት ጥያቄዎች ነበሯት፤ ከዚያ ጥናት ጀመረች። የቤቱ ባለቤት ስለሚያሳስበው አንድ ጥያቄ ወይም ርዕሰ ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስን አመለካከት ማወቅ ይፈልግ እንደሆነ ለምን አትጠይቁትም? እርሱ ጥያቄ ከሌለው አንድ ጉጉት የሚያሳድር ጥያቄ ለማንሳት ዝግጁ ሁኑ። እንዲህ ዓይነቱ ውይይት መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በቋሚነት ለማጥናት መንገድ ሊከፍት ይችላል።
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የአገልግሎታችን ዓቢይ ክፍል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ማን ፈቃደኛ እንደሚሆን ስለማናውቅ በአገልግሎት ለምታገኙት ሰው ሁሉ ጥናት እንዲጀምር ሐሳብ ከማቅረብ ወደኋላ አትበሉ። ጉዳዩን ለይሖዋ በጸሎት ንገሩት። እንዲሁም ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ ነገር አድርጉ። ብዙም ሳይቆይ፣ ጥናት እንዲጀምር ባቀረባችሁለት ሐሳብ የሚስማማ አንድ ሰው ታገኙ ይሆናል!—1 ዮሐ. 5:14, 15