ጽሑፎቻችንን በአግባቡ ተጠቀሙባቸው
1 ጽሑፎችን በተደራጀ መልኩ መጠቀም የጀመርነው የሐምሌ 1, 1879 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እትም 6, 000 ቅጂዎች በተሠራጩ ጊዜ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ጽሑፎች ታትመው በብዛት ተሠራጭተዋል።
ሙሉ በሙሉ በመዋጮ የሚደገፍ ዝግጅት
2 ለአስፋፊዎችም ሆነ ፍላጎት ላሳዩ ሌሎች ሰዎች መጽሔቶችና ጽሑፎች የሚሠራጩት ሙሉ በሙሉ በመዋጮ በሚደገፍ ዝግጅት እንደሚሆን ባለፈው ኅዳር ወር ተገልጾ ነበር። ይህም ማለት ከጽሑፎቻችን አንዱን ማግኘት ከፈለጉ የተወሰነ ገንዘብ እንዲከፍሉ አንጠይቅም ወይም አንጠቁምም ማለት ነው። ጽሑፎችን ስናበረክት በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን ምሥራቹን የማወጅ ሥራ ለመደገፍ በፈቃደኝነት የሚሰጡ መዋጮዎችን እንቀበላለን። ይሖዋ ይህንን ዝግጅት እንደሚባርከው ሙሉ እምነት አለን።—ከማቴዎስ 6:33 ጋር አወዳድር።
በመስክ አገልግሎት ማድረግ ያለብን ነገር
3 የሰዎችን ፍላጎት ለመቀስቀስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመወያያ ርዕሶችን መጠቀማችንን እንቀጥላለን። ምንም ፍላጎት ላላሳየ ሰው ጽሑፍ መስጠት አስፈላጊ አይደለም። ፍላጎት ለሌላቸው ሰዎች በመስጠት የትኛውንም ጽሑፍ ቢሆን ማባከን አንፈልግም። በሌላ በኩል የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካሳየና ጽሑፉን እንደሚያነበው ከተስማማ መስጠት ይቻል ይሆናል። ጽሑፎቻችንን በአግባቡ መጠቀም እንፈልጋለን።
4 መጽሔቶችን ስታበረክት አንዱን ርዕስ በሚመለከት ጥያቄ ካነሣህ በኋላ እንዲህ በል:- “ዝርዝር ሁኔታውን ከዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሊያገኙ ይችላሉ። እነዚህን ሁለት መጽሔቶች ለማንበብ የሚፈልጉ ከሆነ ትቼልዎት ብሄድ ደስ ይለኛል።” ጽሑፎቹን ከወሰደ አክለህ እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “ይህን ሐሳብ ላካፍልዎ በመቻሌ ደስ ብሎኛል። ይህን ርዕሰ ጉዳይ ተጨማሪ እውቀት ያገኙበታል ብዬ አምናለሁ። እንዲያውም በሚቀጥለው ሳምንት መጥቼ አስተያየትዎን ብሰማ ደስ ይለኛል። ይህ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ በዓለም ዙሪያ ከ22, 000, 000 በላይ በሆኑ ቅጂዎች ይሰራጫል። ይህ ሥራ ሙሉ በሙሉ የሚታገዘው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነው። እርስዎም ለዚህ የማስተማር ሥራ መጠነኛ መዋጮ ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ በደስታ እንቀበላለን።”
የምናነጋግረው ሰው እውነተኛ ፍላጎት አለውን?
5 ዓላማችን ለምናገኘው ሰው ሁሉ ጽሑፍ ማደል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ጽሑፉ ለታለመለት ዓላማ ይኸውም ቅን ሰዎች ግሩም ስለሆነው የይሖዋ ዓላማ እንዲማሩ ለመርዳት እንዲውል እንፈልጋለን። ለመንፈሳዊ ነገሮች ምንም አድናቆት ለሌለው ሰው ሰጥቶ መሄድ ጽሑፎችን ማባከን ሊሆን ይችላል። (ዕብ. 12:16) ጽሑፎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማሰራጨት የምትችለው እውነተኛ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለይተህ ማወቅ ከቻልህ ብቻ ነው። ይህ ፍላጎት እንዳላቸው እንዴት ሊታወቅ ይችላል? በደግነት ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑ ጥሩ ምልክት ነው። ወይም አንተ በምትናገርበት ጊዜ በትኩረት ማዳመጡ፣ ለጥያቄዎች መልስ መስጠቱና የራሱን አመለካከት መግለጹ በውይይቱ እንደተመሰጠ ያመለክታል። በአክብሮትና በወዳጃዊ መንፈስ የሚያነጋግርህ ከሆነ ጥሩ ዝንባሌ እንዳለው የሚያሳይ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብለት የሚከታተልህ ከሆነ ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዳለው ያሳያል። ብዙውን ጊዜ የምንሰጣቸውን ጽሑፍ የሚያነቡት መሆኑን መጠየቅ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም የጀመራችሁትን ውይይት ለመቀጠል ተመልሰህ እንደምትመጣ ልትገልጽለት ትችል ይሆናል። አዎንታዊ መልስ ከሰጠ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው። እውነተኛ ፍላጎት እንዳለ የሚጠቁሙ እነዚህን የመሳሰሉ ማስረጃዎችን ካስተዋልክ ግለሰቡ የምትሰጠውን የትኛውንም ጽሑፍ በአግባቡ ይጠቀምበታል ብሎ ማመን ይቻላል።