የጥያቄ ሣጥን
◼ ለአንድ ሰው ጽሑፍ ለመስጠት ወይም ላለመስጠት እንድንወስን የሚረዳን ምንድን ነው?
ይህን ለመወሰን የሚረዳን ዋነኛው ነገር የግለሰቡ ፍላጎት ነው። ግለሰቡ እውነተኛ ፍላጎት ካሳየ ሁለት መጽሔቶች፣ ብሮሹር፣ መጽሐፍ ወይም በዚያን ወቅት የምናበረክተውን ሌላ ጽሑፍ ልንሰጠው እንችላለን። ግለሰቡ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ለማድረግ በቂ ገንዘብ በማይኖረው ጊዜም እንኳ ይህን ማድረግ እንችላለን። (ኢዮብ 34:19፤ ራእይ 22:17) በሌላ በኩል ግን፣ ውድ የሆኑትን ጽሑፎቻችንን አድናቂ ላልሆኑ ሰዎች መስጠት አንፈልግም።—ማቴ. 7:6
የቤቱ ባለቤት ፍላጎት እንዳለው ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ከእኛ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑ አንድ ጥሩ ምልክት ነው። ስንናገር ልብ ብሎ የሚያዳምጥ፣ ለምንጠይቀው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ እንዲሁም የተሰማውን የሚገልጽ ከሆነ ከእኛ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑን ይጠቁማል። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተን ስናነብ የሚከታተል ከሆነ ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዳለው ያሳያል። የምንሰጠውን ጽሑፍ ያነበው እንደሆነ መጠየቃችን ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አስፋፊዎች የግለሰቡን ፍላጎት ለማወቅ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ መንገድ ላይ በምናገለግልበት ወቅት በአጠገባችን ለሚያልፍ ሰው ሁሉ መጽሔቶችን፣ ብሮሹሮችን ወይም መጽሐፎችን ማደል ተገቢ አይደለም። የግለሰቡን ፍላጎት ማወቅ አስቸጋሪ ከሆነብን የስብሰባ መጋበዣ ወረቀት ወይም ትራክት መስጠታችን የተሻለ ነው።
በተመሳሳይም አንድ አስፋፊ ከጽሑፍ ክፍል የሚወስደው የጽሑፍ ብዛት የተመካው የገንዘብ መዋጮ በማድረግ አቅሙ ላይ ሳይሆን አገልግሎቱን ለማከናወን በሚያስፈልገው የጽሑፍ ብዛት ነው። የገንዘብ መዋጮ የምናደርገው ለምንወስዳቸው ጽሑፎች ክፍያ ለመፈጸም ሳይሆን ከዓለም አቀፉ የስብከት ሥራችን ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ነገሮችን በገንዘብ ለመደገፍ ነው። የገንዘብ አቅማችን ምንም ይሁን ምን፣ ያለን አድናቆት የመንግሥቱን ሥራዎች ለመደገፍ ከትርፋችን ሳይሆን የአቅማችንን ያህል በልግስና እንድንሰጥ ይገፋፋናል። (ማር. 12:41-44፤ 2 ቆሮ. 9:7) በተጨማሪም አድናቆታችን ጽሑፎች ስንወስድ የሚያስፈልገንን ያህል ብቻ በመውሰድ የይሖዋን ድርጅት ንብረት ከብክነት እንድንጠብቅ ያነሳሳናል።
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አስፋፊዎች የግለሰቡን ፍላጎት ለማወቅ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ይኖርባቸዋል