መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በሚገባ እንጠቀምባቸው
1, 2. ብዙ ሰዎች ጽሑፎቻችንን በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?
1 “ከ1965 ጀምሮ ጽሑፎቻችሁን ሳነብብ ቆይቻለሁ። የማነብበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅሶቹን እየተመለከትኩ ሲሆን ጽሑፎቻችሁ ውስጥ የሰፈረው በጠቅላላ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል። ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ እውነቱን ለማወቅ ዘወትር እመኝ ነበር፤ አሁን በጽሑፎቻችሁና በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ለጥያቄዎቼ ትክክለኛ መልስ እያገኘሁ ነው ለማለት እችላለሁ።” ይህ አንድ ሰው ለይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የጻፈው ደብዳቤ ነው። በዚህ ደብዳቤ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርለት ጠይቋል።
2 እንደዚህ አመስጋኝ ሰው ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች ያደንቃሉ። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች “እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” ለመርዳት በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ጽሑፍ ይዘጋጃል። (1 ጢሞ. 2:4) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በሚገባ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
3. ጽሑፎችን ላለማባከን ምን ሊረዳን ይችላል?
3 አታባክኑ:- ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከምንጠቀምበት በላይ ብዙ ጽሑፎችን ልናከማች እንችላለን። ጠቃሚ የሆኑትን ጽሑፎቻችንን እንዳናባክን ምን ማድረግ እንችላለን? ለአገልግሎት የምንጠቀምበትን ጽሑፍ ስንወስድ አስተዋዮች መሆን ይገባናል። በዛ ያሉ የአንድ ጽሑፍ ቅጂዎች ከመውሰድ ይልቅ አንድ ወይም ሁለት ወስደን ካበረከትነው በኋላ እንደገና ተመልሰን ተጨማሪ ጽሑፎችን ልንወስድ እንችላለን። ይህ ደግሞ በቤታችን ውስጥ በጣም ብዙ የጽሑፍ ክምችት እንዳይኖር ይረዳል። በተመሳሳይም ያላበረከትናቸው በዛ ያሉ መጽሔቶች ካሉን የምናዘውን የጽሑፍ ቁጥር መቀነስ ይኖርብናል።
4. አንድ ጉባኤ የተከማቹ ጽሑፎች ካሉት ምን ማድረግ አለበት?
4 የተከማቹ ጽሑፎች:- ጉባኤያችሁ የተከማቹ ጽሑፎች ካሉት የጽሑፍ አስተባባሪው ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ ጉባኤዎች ትርፍ የሆነውን ጽሑፍ ሊጠቀሙበት ይችሉ እንደሆነ ያጣራል። አስፋፊዎች የቆዩትን ጽሑፎች ለማያምኑ የቤተሰብ አባላት፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና ለሌሎችም ማበርከት ይችላሉ። በቅርቡ ወደ ጉባኤ መምጣት የጀመሩ አዳዲሶች ለግል ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍታቸው የሚሆኑ የቆዩ ጽሑፎችን ቢያገኙ ደስ ይላቸው ይሆናል።
5. ለጽሑፎቻችን አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁት የይሖዋን አስደናቂ ዓላማ ቅን የሆኑ ሰዎች እንዲያውቁ ለመርዳት በመሆኑ ይህን ግብ እንዲመቱ እንፈልጋለን። ኢየሱስ የተሰበሰቡትን ሰዎች በተአምራዊ ሁኔታ ከመገበ በኋላ የተረፈውን ምግብ እንዳላባከነ ሁሉ እኛም የሚቀርቡልንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በሚገባ ለመጠቀም ግብ እናውጣ። (ዮሐ. 6:11-13) በጽሑፎቻችን ውስጥ የሚገኘው ሕይወት አድን መልእክት በመጽሐፍ መደርደሪያችን ወይም በቦርሳችን ውስጥ ካስቀመጥነው የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ልብ ሊነካ አይችልም። ስለዚህ ለአገልግሎት ጽሑፍ በምንወስድበት ጊዜ ምክንያታዊ እንሁን፤ እንዲሁም ሰዎችን መጥቀም እንድንችል ጽሑፎቻችንን በሚገባ እንጠቀምባቸው።—ፊልጵ. 4:5 NW