ምሥራቹን ሁሉንም ዓይነት ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች አካፍሉ
“ታማኝና ልባም ባሪያ” የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ በኩል የይሖዋ አምላክን ልግስና አንጸባርቋል። ማኅበሩ እስከ አሁን ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ጽሑፎችን አዘጋጅቷል። ምሥራቹን ለሌሎች ስናካፍል ብዙ ጊዜ፣ ጥረትና ወጪ ጠይቀው የሚዘጋጁትን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚረዱ መሣሪያዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዳለብን ማስታወስ ይኖርብናል። የማኅበሩን ጽሑፎች በማንበብና በማጥናት በግላችን ምን ያህል እንደተጠቀምን ስለምናውቅ የተማርናቸውን ነገሮች ለሌሎች ማካፈል እንደምንፈልግ ምንም አያጠራጥርም። (ዕብ. 13:15, 16) ስለዚህ በአገልግሎት ክልላችን ልንጠቀምባቸው በምንችላቸው በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች በሚገባ የታጠቅን መሆን አለብን። ይህም ማለት ከአማርኛ ሌላ በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች የመያዝ ግብ ማውጣት አለብን ማለት ነው።
የተወሰኑ ጽሑፎችን በወላይትኛ፣ በኦሮምኛና በሲዳማ ቋንቋ በማግኘታችን ተደስተናል። ከእነዚህም መካከል በደስታ ኑር የተባለው ብሮሹርና የተወሰኑ ትራክቶች ይገኙበታል። በተጨማሪም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ብሮሹር በኦሮምኛ አለን። እነዚህ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው የአገልግሎት ክልሎች ስናገለግል የአምላክን ቃል ተርቦ የነበረ ሰው በራሱ ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ሲያገኝ እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም። ይህ ራሱ ይሖዋና ሕዝቦቹ ለሌሎች ደህንነት ፍቅራዊ አሳቢነት እንደሚያሳዩ የሚያረጋግጥ ጥሩ ማስረጃ ነው።
በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁትን የተለያዩ ጽሑፎች ሁልጊዜ በመያዝና ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም በስብከቱ ሥራችን የቻልነውን ያህል ጠቃሚ ነገር እናከናውን።—1 ቆሮ. 9:22, 23