የእኩዮች ተጽዕኖ እና የስብከት መብትህ
1 የእኩዮች ተጽዕኖ በጎ ወይም መጥፎ ግፊት የማሳደር ኃይል አለው። እንደ እኛው ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች መልካም የሆኑ ክርስቲያናዊ ሥራዎችን እንድንሠራ በማነቃቃት በጎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። (ዕብ. 10:24) ይሁን እንጂ ምሥክር ያልሆኑ የቤተሰብ አባሎች፣ የሥራ ባልደረቦች፣ በትምህርት ቤት አብረውን የሚማሩ፣ ጎረቤቶች ወይም የምናውቃቸው ሌሎች ሰዎች ከክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን ጎዳና እንድንከተል ግፊት ሊያሳድሩብን ይችላሉ። ‘በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችንን ይሳደቡ’ ይሆናል። (1 ጴጥ. 3:16) አፍራሽ የእኩዮች ተጽዕኖ እያለብንም ስብከታችንን ለመቀጠል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
2 የቤተሰብ አባላት:- አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ባል እና አባት ሚስቱ እና ልጆቹ በሕዝባዊ አገልግሎት እንዲካፈሉ አይፈልግ ይሆናል። በሜክሲኮ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ተከስቶ ነበር። አንድ ሰው ሚስቱና ሰባት ልጆቹ እውነትን ተቀበሉ። ሰውዬው ቤተሰቡ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ እንዲሰብክና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲያሰራጭ ስላልፈለገ በጣም ተቃወመ። እንዲህ ማድረግ የቤተሰቡን ክብር እንደሚነካ ተሰማው። ይሁን እንጂ ባለቤቱና ልጆቹ ይሖዋን ለማገልገልና ዘወትር በአገልግሎት ለመካፈል ባደረጉት ውሳኔ ጸኑ። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው፣ አምላክ ለስብከቱ ሥራ ያወጣውን ዝግጅት መቀበል ጥቅም እንዳለው የተገነዘበ ሲሆን እሱም ራሱን ለይሖዋ ወስኗል። እውነትን ለመቀበል 15 ዓመት ፈጅቶበታል። ሆኖም ቤተሰቡ የመስበክ መብቱን አቋርጦ ቢሆን ኖሮ ይህ ሰው እውነትን ይቀበል ነበር?—ሉቃስ 1:74፤ 1 ቆሮ. 7:16
3 የሥራ ባልደረቦች:- ለሥራ ባልደረቦችህ ለመመስከር የምታደርገው ጥረት አንዳንዶችን አያስደስት ይሆናል። አንዲት እህት በቢሮ ውስጥ ስለ ዓለም ፍጻሜ ውይይት ሲነሳ ማቴዎስ ምዕራፍ 24ን እንዲያነቡ ስትነግራቸው አፊዘውባት እንደነበረ ተናግራለች። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሥራ ባልደረቦቿ አንዷ ምዕራፉን አንብባ በጣም መገረምዋን ነገረቻት። ለሴትዮዋ ጽሑፍ ተበረከተላትና ለእርሷና ለባለቤትዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ዝግጅት ተደረገ። የመጀመሪያው ቀን ጥናት እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ቆይቶ ነበር። ለሦስተኛ ጊዜ ካጠኑ በኋላ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ትንባሆ ማጨሳቸውን አቆሙና በመስክ አገልግሎት መካፈል ጀመሩ። እህታችን ተስፋዋን ለሌሎች ለማካፈል ጥረት ባታደርግ ኖሮ ይህ ውጤት ይገኝ ነበር?
4 ትምህርት ቤት አብረውን የሚማሩ:- የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወጣቶች በትምህርት ቤት የእኩዮች ተጽዕኖ የሚያጋጥማቸው መሆኑና በስብከቱ ሥራ ላይ ስንካፈል ሌሎች ወጣቶች ያሾፉብናል ብለው መፍራታቸው አዲስ ነገር አይደለም። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት ክርስቲያን “ማሾፊያ ያደርጉኛል ብዬ ስለምፈራ ለሌሎች ወጣቶች ለመመሥከር አፍራለሁ” ብላለች። ስለዚህ በትምህርት ቤትና በክልሏ ውስጥ ለሚገኙ እኩዮቿ ለመመስከር የሚያስችላትን አጋጣሚ አትጠቀምም ነበር። የእኩዮችህን ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት በመጣጣር በእሱ ታመን። (ምሳሌ 29:25) በአገልግሎትህ የአምላክን ቃል መጠቀም በመቻልህ ልትኮራ ይገባሃል። (2 ጢሞ. 2:15) እዚህ ላይ የተጠቀሰችው ወጣት አብረዋት ለሚማሩ ልጆች የመመስከር ፍላጎትዋን እንዲያሳድግላት ይሖዋን በጸሎት ትጠይቀው ጀመር። በትምህርት ቤቱ ውስጥ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት መስጠት ጀመረች፣ ጥሩ ውጤቶችንም አገኘች ብዙም ሳይቆይ የምታውቃቸውን ሰዎች በሙሉ ማነጋገር ቻለች። በመጨረሻም “እነዚያ ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ ማየት ይፈልጋሉ፤ ይሖዋ ደግሞ እነርሱን ለመርዳት በእኛ እየተጠቀመ ነው” ብላለች።
5 ጎረቤቶች:- በማንነታችንና በእምነታችን የሚናደዱ አንዳንድ ጎረቤቶቻችን ወይም ሌሎች የምናውቃቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። እነሱ ስለሚሰማቸው ነገር በማሰብ የምትፈራ ከሆነ ‘ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውነት ያውቃሉ? ልባቸውን ለመንካት ምን ማድረግ እችላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ለጎረቤቶች ዘወትር ትንሽ ትንሽ መመስከር ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ተገንዝቧል። ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችን ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ለመቀጠል የሚያስፈልግህን ጥንካሬና ጥበብ እንዲሰጥህ ይሖዋን ተማጸን።—ፊልጵ. 4:13
6 እኩዮች ለሚያሳድሩብን አሉታዊ ተጽዕኖ የምንሸነፍ ከሆነ ተቃዋሚዎቻችን ደስ ይላቸው ይሆናል፤ ሆኖም ይህ ለእኛም ሆነ ለእነሱ ይበጃልን? ኢየሱስ ከራሱ ወገኖች ተቃውሞ አጋጥሞት ነበር። ሌላው ቀርቶ የገዛ ወንድሞቹ ይሰነዝሩበት የነበረውን የሰላ ትችት ተቋቁሟል። እነሱን መርዳት የሚችለው አምላክ የሚፈልግበትን ለማሟላት ሲጸና ብቻ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ ‘ከኃጢአተኞች እንዲህ ያለ ተቃውሞ ቢደርስበትም ጸንቷል።’ (ዕብ. 12:2, 3) እኛም ብንሆን እንዲሁ ማድረግ ይገባናል። የመንግሥቱን መልእክት ለመስበክ ባገኘኸው መብት ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንደዚህ በማድረግ ‘ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ።’—1 ጢሞ. 4:16