ልጃችሁ ከባድ ውሳኔ የማድረግ ችሎታ አለው?
1. የደም አጠቃቀምን በተመለከተ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት አቋም ወስደዋል? ምሳሌ ስጥ።
1 ከባድ ውሳኔ፤ በምን ጉዳይ ላይ? ደም መውሰድን በተመለከተ። በሰኔ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ይሖዋ ባስተማራችሁ መንገድ ሂዱ” በሚለው ርዕስ ሥር እንደተገለጸው ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች፣ እነርሱም ልክ እንደ ወላጆቻቸው አምላክ ደምን አስመልክቶ ያወጣውን ሕግ ለመታዘዝ ፍላጎት እንዳላቸው ግልጽና የማያሻማ አቋም በመያዝ እንዲያረጋግጡ የሚያስገድድ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። የእናንተም ልጅ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያደርግ ይጠበቅበታል?
2. አንድ ፍርድ ቤት ደም አልወስድም ላለች አንዲት ወጣት የትኛውን ደንብ ተግባራዊ አድርጓል? ክርስቲያን ወላጆችና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቻቸው ከዚህ ምን ሊማሩ ይችላሉ?
2 ሕጉ ምን ይላል? በዩናይትድ ስቴትስ፣ አንድ ልጅ ዕድሜው ባይፈቅድለትም ከባድ ውሳኔ ማድረግ ይችላል በሚል ደም ያለመውሰድ መብትን በተመለከተ ውሳኔ የሰጠው ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የኢሊኖይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆነችን የአንዲት የ17 ዓመት ልጅ ጉዳይ ከመረመረ በኋላ ፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል ውሳኔ አስተላልፏል:- “የምትወስነው ውሳኔ ምን ነገር ሊያስከትልባት እንደሚችል በደንብ የተረዳች [እና] እንደ ትልቅ ሰው ውሳኔ ማድረግ የምትችል መሆኑን የሚያሳይ ግልጽና አሳማኝ ማስረጃ ካለ፣ ለአካለ መጠን ባይደርሱም ጥሩ የማስተዋል ችሎታ ላላቸው ልጆች የሚሠራውን ደንብ ተግባራዊ በማድረግ እንደ አንድ አዋቂ ሰው የምትመርጠው የሕክምና ዓይነት ሊፈቀድላት ይገባል።” በመሆኑም አንድ ልጅ ዕድሜው ለአካለ መጠን ባይደርስም በራሱ ውሳኔ ማድረግ ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ሐኪሞች ወይም ባለ ሥልጣናት ለምን ደም እንደማይወስድ ለማወቅ የተለያዩ ጥያቄዎች ሊያቀርቡለት ይችላሉ። ወጣቱ የሚደረግለት ሕክምና ምን ያህል ከባድ እንደሆነና የሚያደርጋቸው ምርጫዎች የሚያስከትሉትን መዘዝ በደንብ መረዳት ይኖርበታል፤ እንዲሁም ደምን በተመለከተ ስለአምላክ ሕግ ያለውን የራሱን ሃይማኖታዊ እምነቶች በግልጽና በድፍረት ማሳወቅ ይጠበቅበታል።
3. ወላጆች በቁም ነገር ሊያስቡባቸው የሚገቡት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ?
3 ልጃችሁ ምን ይላል? የእናንተ ልጆችስ በዚህ ረገድ አቋማቸውን በግልጽ ማስረዳት ይችላሉ? ‘ከደም መራቅ’ መለኮታዊ ትእዛዝ መሆኑን ከልባቸው ያምኑበታል? (ሥራ 15:29፤ 21:25) ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ እምነታቸው ማስረዳት ይችላሉ? ወላጆቻቸው በአቅራቢያቸው ባይኖሩና ሐኪም ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ቢነግራቸው ስለ ደም ያላቸውን ቁርጥ ውሳኔ በድፍረት ማስከበር ይችላሉ? ‘ጊዜና አጋጣሚ ሁላችንንም’ እንደሚገናኘን የታወቀ ነገር ነው፤ ስለዚህ ልጆቻችሁ ታማኝነታቸውን የሚፈታተን ነገር በሚገጥማቸው ወቅት መወጣት እንዲችሉ እንዴት ልታዘጋጅዋቸው ትችላላችሁ?—መክ. 9:11 NW፤ ኤፌ. 6:4
4, 5. (ሀ) ወላጆች ምን ኃላፊነት አለባቸው? እንዴትስ ማሟላት ይችላሉ? (ለ) ወላጆችን ለመርዳት የሚያስችሉ ምን ዝግጅቶች አሉ?
4 ወላጆች፣ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? አምላክ ለደም ያለውን አመለካከት ለልጆቻችሁ የማስተማር ኃላፊነት አለባችሁ። (2 ጢሞ. 3:14, 15) በማመራመር መጽሐፍ ከገጽ 69-72 ላይ የሰፈረውን ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ከቤተሰባችሁ ጋር በጥንቃቄ አጥኑት። ከገጽ 73-75 ላይ በሚገኘው “አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ” በሚለው ክፍል ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁ ምን እንደሚያምኑና ለምን እንደሚያምኑ ማስረዳት እንዲችሉ የልምምድ ፕሮግራም አድርጉ። (1 ጴጥ. 3:15) የደም ጉዳይን በተመለከተ እኛን ለመርዳት ከተደረጉት ሌሎች ዝግጅቶች መካከል ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? የሚለው ብሮሹር እንዲሁም የሰኔ 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14-24 ይገኙበታል። በተጨማሪም በደም ምትክ የሚሰጥ ሕክምና—የሕሙማንን መብትና ፍላጎት ማክበር እንዲሁም ደም አልወስድም—የሕክምናው መስክ መፍትሔ አስገኝቷል የተባሉት የቪዲዮ ፊልሞች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደም ምትክ የሚሰጡ ሕክምናዎች—ተከታታይ ጥናታዊ ፊልሞች በሚል ርዕስ በዲቪዲ መልክ የተዘጋጁ ሲሆን ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና ምክንያታዊና ውጤታማ ስለመሆኑ አሳማኝ የሆነ መረጃ ያቀርባሉ። ቤተሰባችሁ በቅርቡ ይህን ፊልም አይቶ ተወያይታችሁበታል?
5 ልጆቻችሁ ደምን አስመልክቶ ‘መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትነው እንዲያውቁ’ ልትረዷቸው ይገባል። እንዲህ ካደረጋችሁ ልጆቻችሁ ማስተዋል የታከለበትና የይሖዋን በረከት የሚያስገኝ ውሳኔ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ሮሜ 12:2