ጠንካራ እምነት እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ!
1. ኢየሱስ ምን አስጨናቂ የሆኑ ነገሮች እንደሚመጡ አስቀድሞ ተናግሯል?
1 ኢየሱስ፣ ስለመገኘቱና ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ሲናገር ሐዋርያቱ በትኩረት ያዳምጡት ነበር። ኢየሱስ ጦርነት፣ ረሃብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና ቸነፈር የመሳሰሉ አስጨናቂ ነገሮች በሰው ዘሮች ላይ እንደሚደርሱ ተናገረ። ቀጥሎም ተከታዮቹ እንደሚጠሉ፣ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው እንደሚሰጧቸውና እንደሚገደሉ ገለጸ። ከዚህም በተጨማሪ ሐሰተኛ ነቢያት እንደሚነሱና ብዙዎችን እንደሚያስቱ እንዲሁም የብዙ ሰዎች ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ተናገረ።
2. ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ በመሰበክ ላይ መሆኑን አስደናቂ የሚያደርገው ምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ከላይ የተዘረዘሩት አሳዛኝ ክስተቶች በሚፈጸሙበት ዘመን ውስጥ የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም ሁሉ እንደሚሰበክ መናገሩ ሐዋርያቱን አስገርሟቸው መሆን አለበት። (ማቴ. 24:3-14) በዛሬው ጊዜ ይህ አስገራሚ ትንቢት በከፍተኛ ሁኔታ ሲፈጸም እያየን ነው። የምንኖረው እጅግ አደገኛ በሆነ ጊዜ ውስጥ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በቅንዓት በማወጅ ላይ ይገኛሉ። በዓለም የሚገኙ ሰዎች ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲቀዘቅዝ የእኛ ፍቅር ግን ይበልጥ እየተቀጣጠለ ነው። “በሕዝብ ሁሉ ዘንድ” የተጠላን ብንሆንም እንኳ በሁሉም አገሮች ማለት ይቻላል ምሥራቹን እንሰብካለን።
3. በዓለም አቀፉ ሪፖርት ውስጥ ምን አበረታች አኃዛዊ መረጃዎችን አስተዋልክ?
3 የይሖዋ ምሥክሮች ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ያደረጉትን እንቅስቃሴ መመልከታችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ይህ እንቅስቃሴ ከገጽ 3 እስከ 6 ላይ ባለው ሠንጠረዥ ውስጥ ሰፍሯል። እንዳለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ሁሉ በዚህም ዓመት በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ከአንድ ቢሊዮን ሰዓት በላይ አሳልፈዋል። ይህ በእርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች ጠንካራ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ነው! የአቅኚዎች ቁጥር 5.8 በመቶ፣ የአስፋፊዎች ቁጥር 3.1 በመቶ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር 4.4 በመቶ ጭማሪ ነበረው። የተጠማቂዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት 20.1 በመቶ ከፍ ብሏል። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ሰባት ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በታማኝነት ይሖዋን እያገለገሉ እንዳለ ማየት የሚያስደስት ነው! ሠንጠረዡን በምትመረምርበት ጊዜ በተለይ አንተን የሚያበረታታ ምን ነገር አስተዋልክ?
4. ጊልየርሞ ለመጠመቅ ባደረገው ጥረት ምን ፈተናዎችን አሸንፏል?
4 አኃዛዊ መረጃዎቹ በራሳቸው አስደሳች ቢሆኑም ለዚህ ውጤት መገኘት ምክንያት የሆኑትንና እምነታቸውን በሥራ ያስመሠከሩትን ሰዎች ፈጽሞ መዘንጋት አይገባንም። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በ1935 የተወለደው ጊልየርሞ ያደገው በቦሊቪያ ሲሆን በኮካ እርሻ ውስጥ መሥራት የጀመረው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። ከባድ የጉልበት ሥራ መሥራቱ የሚያስከትልበትን ሥቃይ ለማስታገስ ሲል የኮካ ቅጠል ማኘክ የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር። ቆይቶም የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ ጀመረ። ጊልየርሞ፣ ይሖዋ ከእሱ ምን እንደሚፈልግ እየተማረ ሲመጣ ማጨሱንና የአልኮል መጠጥ ያላግባብ መጠጣቱን አቆመ። ትልቅ ፈተና የሆነበት የዕድሜ ልክ ሱስ የሆነውን የኮካ ቅጠል ማኘኩን ማቆም ነበር። ይሁን እንጂ ያለማቋረጥ በመጸለይ ይህን ልማድ ማሸነፍ ቻለ። በመጨረሻም መጥፎ ልማዶቹን ሁሉ እርግፍ አድርጎ በመተው ተጠመቀ። ጊልየርሞ፣ “አሁን ንጹሕና በጣም ደስተኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል” ብሏል።
5. ፍላጎትህ ምንድን ነው?
5 ይሖዋ በእርግጥ ለሰዎች ያስባል። ሁሉም ሰዎች ለንስሐ እንዲበቁ ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:9) ይህ የእኛም ፍላጎት ነው። እንግዲያው ከልብ በመነሳሳት ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች እንደ እኛው ይሖዋን እንዲያውቁትና እንዲወዱት መርዳታችንን ለመቀጠል የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።