የስብከቱ ሥራ ጽናት ይጠይቃል
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ወንጌላዊ ሆኖ ያከናወነው ሥራ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶለታል። አንድን ጠቃሚ ሥራ ለማከናወን የተለያዩ እንቅፋቶችን ማለፍ እንደሚጠይቅ ሁሉ ጳውሎስም የስብከቱን ሥራ ለመፈጸም አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎችን መወጣት አስፈልጎታል። (2 ቆሮ. 11:23-29) ሆኖም ጳውሎስ ተስፋ ቆርጦ የስብከቱን ሥራ አላቆመም። (2 ቆሮ. 4:1) አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጠው ተገንዝቦ ነበር። (ፊልጵ. 4:13) ጳውሎስ በታማኝነት በመጽናት ግሩም ምሳሌ የተወልን በመሆኑ “እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ” ለማለት ችሏል።—1 ቆሮ. 11:1
2 በአሁኑ ጊዜ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም፦ በርካታ ወንድሞቻችን በየዕለቱ ከቤተሰባቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ወይም አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች ፌዝና ተቃውሞ ይሰነዘርባቸዋል፤ አሊያም እነዚህ ሰዎች ለመልእክቱ አዎንታዊ ምላሽ አይሰጡም። (ማቴ. 10:35፤ ዮሐ. 15:20) ምናልባት አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ችግር ሊኖርብህ ይችላል፤ ወይም በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዳታደርግ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብህ ነገሮች እንዲሁም እምነትህንና የጸና አቋምህን ሊያዳክሙ ከሚችሉ ፈተናዎች ጋር በየዕለቱ መታገል ያስፈልግህ ይሆናል። በጥንት ዘመን የነበሩት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችም ሆኑ በዛሬው ጊዜ የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን የተቋቋሙ የእምነት ባልደረቦቻችን የተዉትን ምሳሌ በመመርመር ብርታት ማግኘት እንችላለን።—1 ጴጥ. 5:9
3 በጽናት አገልግሎታችንን ማከናወናችንን እንድንቀጥል “ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ [መልበስ]” ይኖርብናል። (ኤፌ. 6:10-13, 15) ከዚህም በተጨማሪ መጽናት እንድንችል ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው። ፈተናዎችን ተቋቁመን እንድንኖር አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 6:4-7) በመንፈሳዊ ውጊያችን ድል ማድረግ እንድንችል አምላክ መንፈሳችንን እንድናድስ የሚሰጠንን ማሳሳቢያዎች መከተል ይኖርብናል። (መዝ. 119:24, 85-88) አንድ ልጅ ከሚወደው አባቱ የተላከለትን ደብዳቤ ደጋግሞ እንደሚያነበው ሁሉ እኛም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የምናነብ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ይጠናከራል። አዘውትረን የግል ጥናት ማድረጋችን ፈታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ እንድናገኝ ይረዳናል። ይህ ደግሞ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ በአምላክ አስተሳሰብ እንድንመራ ያስችለናል፤ እንዲሁም ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።—ምሳሌ 2:10, 11
4 ጽናት በረከት ያስገኛል፦ የጳውሎስ ተሞክሮ እንደሚያሳየው አገልግሎታችንን በጽናት ማከናወናችን የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኝ ከመሆኑም ሌላ ለእኛም ሆነ ለሌሎች በረከት ያስገኛል። (ምሳሌ 27:11) አገልግሎታችንን በጽናት ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እምነታችን ጠንካራ እንደሆነ እንዲሁም “በእሳት የተፈተነ ቢሆንም እንኳ ሊጠፋ ከሚችለው ወርቅ እጅግ የላቀ ዋጋ” እንዳለው በተግባር ማሳየት እንችላለን።—1 ጴጥ. 1:6, 7