‘ይህ የመንግሥት ምሥራች ይሰበካል!’
1. የስብከቱን ሥራ ምንም ነገር ሊያስቆመው እንደማይችል እንዴት እናውቃለን?
1 ይሖዋ ፈቃዱን ከመፈጸም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም። (ኢሳ. 14:24) መስፍኑ ጌዴዎንና ከእሱ ጋር የነበሩት 300 ሰዎች 135,000 ምድያማውያንን ማሸነፋቸው የማይሆን ነገር ቢመስልም ይሖዋ ለጌዴዎን “እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን?” ብሎት ነበር። (መሳ. 6:14) በዛሬው ጊዜስ ይሖዋ የትኛውን ሥራ እየደገፈ ነው? ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 24:14) ማንም ቢሆን ይህ ሥራ እንዳይከናወን ማስቆም አይችልም!
2. ይሖዋ በስብከቱ ሥራ ስንካፈል በግለሰብ ደረጃ ይረዳናል ብለን መጠበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?
2 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ይረዳናል፦ ይሖዋ፣ ምሥክሮቹ በስብከቱ ሥራ እንዲሳካላቸው በቡድን ደረጃ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ሆኖም በግለሰብ ደረጃ ይረዳናል ብለን መጠበቅ እንችላለን? ሐዋርያው ጳውሎስ እርዳታ ባስፈለገው ጊዜ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ በኩል በግለሰብ ደረጃ እንደረዳው ተሰምቶት ነበር። (2 ጢሞ. 4:17) እኛም ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም በግለሰብ ደረጃ የምናደርገውን ጥረት በተመሳሳይ መንገድ እንደሚባርከው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ዮሐ. 5:14
3. ይሖዋ በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን ይረዳናል?
3 የዕለት ተዕለቱ የሕይወት ውጣ ውረድ ኃይልህን አሟጦ ማገልገል እንዳትችል አድርጎሃል? ይሖዋ “ለደከመው ብርታት ይሰጣል።” (ኢሳ. 40:29-31) ስደት ወይም ተቃውሞ እየደረሰብህ ነው? “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል።” (መዝ. 55:22) አንዳንድ ጊዜ በራስ የመተማመን ስሜት ታጣለህ? ይሖዋ “በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ” ብሏል። (ዘፀ. 4:11, 12) በአገልግሎት እንደምትፈልገው እንዳትካፈል የሚያግድህ የጤና ችግር አለብህ? ምንም ያህል ትንሽ ቢሆንም ይሖዋ በሙሉ ነፍስ ጥረት ስታደርግ ይጠቀምብሃል እንዲሁም ጥረትህን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—1 ቆሮ. 3:6, 9
4. በይሖዋ መተማመናችን በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
4 የይሖዋ እጅ “ተዘርግቶአል? ማንስ ይመልሰዋል?” (ኢሳ. 14:27) ይሖዋ አገልግሎታችንን እንደሚባርከው በመተማመን “በይሖዋ ሥልጣን በድፍረት” መስበካችንን እንቀጥል!—ሥራ 14:3