በአገልግሎታችሁ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ
1. በአገልግሎታችን እድገት ማድረግ እንዳለብን የሚጠቁመው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የተዉት የትኛው ምሳሌ ነው?
1 ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው እድገት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንጻር ኢየሱስ ተከታዮቹ በስብከቱ ሥራ እድገት እንዲያደርጉ የሚያስችል ሥልጠና ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 9:1-5፤ 10:1-11) አቂላና ጵርስቅላም አጵሎስን ወስደው “የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል [ያብራሩለት]” ለዚህ ነው። (ሥራ 18:24-26) ጳውሎስም ቢሆን ጢሞቴዎስ ተሞክሮ ያለው ወንጌላዊ ቢሆንም የማስተማር ችሎታውን ለማሳደግ የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ አበረታቶታል፤ ይህም እድገቱ “በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ” ያስችላል። (1 ጢሞ. 4:13-15) የምሥራቹ ሰባኪ በመሆን ጌታን ያገለገልንበት ጊዜ ምንም ያህል ረጅም ቢሆን በስብከቱ ሥራ ረገድ ችሎታችንን ማሳደግ ይኖርብናል።
2. ከሌሎች መማር የምንችለው እንዴት ነው?
2 ከሌሎች ተማሩ፦ ችሎታችንን ማሳደግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ከሌሎች መማር ነው። (ምሳሌ 27:17) በመሆኑም የእምነት ባልንጀሮቻችሁ የሚጠቀሙበትን መግቢያ ልብ ብላችሁ ተከታተሉ። ውጤታማ የሆኑ ሰባኪዎች እናንተን በቀጥታ የሚመለከት ምክር እንዲሰጧችሁ ጠይቁ፤ እንዲሁም የሚሰጧችሁን ሐሳብ በጥሞና አዳምጡ። (ምሳሌ 1:5) ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ፣ ጥናት ማስጀመር ወይም በአንድ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል ይከብዳችኋል? ከሆነ የቡድናችሁ የበላይ ተመልካች ወይም ተሞክሮ ያለው አንድ አስፋፊ እርዳታ እንዲሰጣችሁ ቅድሚያውን ወስዳችሁ ጠይቁ። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ችሎታችንን እንድናሻሽል ሊረዳን እንደሚችልም አስታውሱ፤ በመሆኑም መንፈሱን ለማግኘት ምንጊዜም ጸልዩ።—ሉቃስ 11:13
3. አንድ ሰው ማሻሻል ያለብንን ነገር ቢነግረን ምናልባትም ሳንጠይቀው ምክር ቢሰጠን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
3 አንድ ሰው ማሻሻል ያለብህን ነገር ቢነግርህ ሌላው ቀርቶ ሳትጠይቀው እንኳ እንዲህ ያለ ምክር ቢሰጥህ መናደድ የለብህም። (መክ. 7:9) እንደ አጵሎስ የተሰጠህን እርዳታ በትሕትናና በአመስጋኝነት ተቀበል። እንዲህ ማድረግ የጥብብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 12:15
4. ኢየሱስ በወንጌላዊነቱ ሥራ እድገት የማድረግን አስፈላጊነት የሚጠቁም ምን አሳማኝ ምክንያት ጠቅሷል?
4 እድገት ማድረግ አምላክን ያስከብራል፦ ኢየሱስ ተከታዮቹ በአገልግሎታቸው እድገት እንዲያደርጉ ለማስተማር በምሳሌ ተጠቅሟል። ራሱን ከወይን ተክል ጋር፣ ቅቡዓን ተከታዮቹን ደግሞ ከቅርንጫፍ ጋር አመሳስሏቸዋል። ኢየሱስ አባቱ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ “ይበልጥ እንዲያፈራ” እንደሚያጠራው ተናግሯል። (ዮሐ. 15:2) አንድ የወይን እርሻ ባለቤት የወይን ተክሎቹ ቅርንጫፎች ይበልጥ እንዲያፈሩ እንደሚፈልግ ሁሉ ይሖዋም “የከንፈር ፍሬ” በማፍራት ረገድ ያለንን ችሎታ ይበልጥ እንድናሳድግ ይፈልጋል። (ዕብ. 13:15) በወንጌላዊነቱ ሥራ እድገት ማድረጋችን ምን አስደሳች ውጤት ያስገኛል? ኢየሱስ “ብዙ ፍሬ ማፍራታችሁን ብትቀጥሉ . . . በዚህ አባቴ ይከበራል” በማለት መልስ ሰጥቷል።—ዮሐ. 15:8