የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—የካቲት 2019
ከየካቲት 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሮም 1-3
“ሕሊናችሁን ሁልጊዜ አሠልጥኑ”
(ሮም 2:14, 15) ሕግ የሌላቸው አሕዛብ በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሲያደርጉ እነዚህ ሰዎች ሕግ ባይኖራቸውም እንኳ እነሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና። 15 የሕጉ መሠረታዊ ሐሳብ በልባቸው እንደተጻፈ የሚያሳዩት እነሱ ራሳቸው ናቸው፤ ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ በሚመሠክርበት ጊዜ ሐሳባቸው በውስጣቸው እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል።
በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ
6 ይሖዋን የማያውቁ ሰዎችም እንኳ ትክክል ወይም ስህተት የሆኑ ነገሮች እንዳሉ አብዛኛውን ጊዜ አይጠፋቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሐሳባቸው በውስጣቸው እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል” በማለት ይናገራል። (ሮም 2:14, 15) ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቹ ሰዎች መግደል ወይም መስረቅ ስህተት እንደሆነ ያውቃሉ። ይህን እንዲገነዘቡ ያደረጋቸው ሕሊናቸው ማለትም ይሖዋ በውስጣቸው ያስቀመጠው ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ባያስተውሉትም እንኳ ሕሊናቸውን እያዳመጡ ነው። በተጨማሪም የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተከተሉ ነው ማለት ይቻላል፤ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎች ማድረግ እንድንችል እኛን ለመርዳት ሲል ያስቀመጠልን መሠረታዊ እውነታዎች ናቸው።
(ሮም 2:15) የሕጉ መሠረታዊ ሐሳብ በልባቸው እንደተጻፈ የሚያሳዩት እነሱ ራሳቸው ናቸው፤ ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ በሚመሠክርበት ጊዜ ሐሳባቸው በውስጣቸው እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል።
በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ
8 አንዳንዶች ሕሊናቸውን መስማት ሲባል ስሜታቸውን ማዳመጥ ማለት እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነሱን እስካስደሰታቸው ድረስ የፈለጉትን ቢያደርጉ ምንም ችግር እንደሌለው ያስባሉ። ሆኖም ፍጹም ባለመሆናችን ስሜታችን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራን ይችላል። ስሜታችን በሕሊናችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም። ማንስ ሊያውቀው ይችላል?” (ኤርምያስ 17:9) በመሆኑም ስህተት የሆነውን ነገር እንኳ ትክክል እንደሆነ አድርገን ልናስብ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከባድ ስደት ያደርስ የነበረ ሲሆን ድርጊቱም ትክክል እንደሆነ ይሰማው ነበር። ጳውሎስ ጥሩ ሕሊና እንዳለው ያስብ ነበር። ይሁንና ጳውሎስ፣ ስለ ድርጊቱ ይሖዋ ምን አመለካከት እንዳለው ሲያውቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ንጹሕ ሕሊና መያዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም ተረድቷል። (1 ቆሮንቶስ 4:4፤ የሐዋርያት ሥራ 23:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:3) ከዚህ መማር እንደምንችለው፣ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ‘ይሖዋ የሚፈልገው ምን እንዳደርግ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው።
9 አንድን ሰው የምትወደው ከሆነ ግለሰቡን ላለማሳዘን እንደምትጠነቀቅ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ይሖዋን ስለምንወደው እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አንፈልግም። ይሖዋን እንዳናሳዝነው ልንፈራ ማለትም ፈሪሃ አምላክ ሊኖረን ይገባል። ነህምያ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። የሕዝቡ ገዢ ቢሆንም ሥልጣኑን ተጠቅሞ ለመበልጸግ አልሞከረም። ነህምያ እንዲህ ያላደረገው ለምንድን ነው? ‘አምላክን ስለሚፈራ’ መሆኑን ተናግሯል። (ነህምያ 5:15) ነህምያ ይሖዋን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አልፈለገም። እንደ ነህምያ ሁሉ እኛም፣ መጥፎ ነገር በመፈጸም ይሖዋን እንዳናሳዝን እንፈራለን። ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ማወቅ እንችላለን።—ተጨማሪ ሐሳብ 6ን ተመልከት።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሮም 3:4) በፍጹም! ከዚህ ይልቅ “በቃልህ ጻድቅ ሆነህ ትገኝ ዘንድ፣ በፍርድም ፊት ትረታ ዘንድ” ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ሆኖ ቢገኝ እንኳ የአምላክ እውነተኝነት የተረጋገጠ ነው።
የሮሜ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
3:4፦ የሰዎች ሐሳብ አምላክ በቃሉ ውስጥ ካሰፈረው ሐሳብ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው መልእክት ላይ እምነት በማሳደርና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ‘አምላክ እውነተኛ’ ሆኖ እንዲገኝ እናደርጋለን። ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈልም ሌሎች ሰዎች አምላክ እውነተኛ መሆኑን እንዲገነዘቡ እንረዳቸዋለን።
(ሮም 3:24, 25) ይሁንና ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት በጸጋው ጻድቃን ናችሁ መባላቸው እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው። 25 በኢየሱስ ደም የሚያምኑ ሁሉ ማስተሰረያ ያገኙ ዘንድ አምላክ እሱን መባ አድርጎ አቅርቦታል። አምላክ ይህን ያደረገው የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ቻይ በመሆን በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር ብሏል።
የሮሜ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
3:24, 25—‘በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው ቤዛነት’፣ ሳይከፈል በፊት “ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት” ሊሸፍን የቻለው እንዴት ነው? በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው የመጀመሪያው መሲሐዊ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በሞተበት ወቅት ነበር። (ገላ. 3:13, 16) ሆኖም አምላክ ዓላማውን እንዳይፈጽም የሚያግደው ምንም ነገር ስለሌለ ይህን ትንቢት በተናገረበት ወቅት የቤዛውን ዋጋ እንደተከፈለ አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል። በመሆኑም ይሖዋ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት የሚያቀርበውን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ በዚህ ተስፋ ላይ እምነት የሚያሳድሩ የአዳም ዘሮችን ኃጢአት ይቅር ማለት ችሏል። እንዲሁም ቤዛው ከክርስትና በፊት የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ከፍቷል።—ሥራ 24:15
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሮም 1:1-17) የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ከሆነው፣ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራውና የአምላክን ምሥራች እንዲያውጅ ከተሾመው ከጳውሎስ፤ 2 ይህ ምሥራች አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ሲሆን 3 በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደው ልጁ የሚገልጽ ነው፤ 4 ይሁንና እሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የአምላክ ልጅ መሆኑ እንዲታወቅ ተደርጓል። ይህም የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በተነሳ ጊዜ ነው። 5 ለስሙ ክብር በብሔራት ሁሉ መካከል በእምነት የሚታዘዙ ሰዎች እንዲገኙ ሲባል በእሱ አማካኝነት ጸጋና ሐዋርያነት ተቀብለናል፤ 6 የኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከአሕዛብ ከተጠሩት መካከል እናንተም ትገኙበታላችሁ። 7 ቅዱሳን እንድትሆኑ ለተጠራችሁና በአምላክ ለተወደዳችሁ በሮም ለምትኖሩ ሁሉ፦ አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 8 ከሁሉ አስቀድሜ፣ ስለ እምነታችሁ በመላው ዓለም ስለሚወራ ስለ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአምላኬ ምስጋና አቀርባለሁ። 9 ያለማቋረጥ ዘወትር በጸሎቴ እናንተን ሳልጠቅስ እንደማላልፍ፣ ስለ ልጁ የሚገልጸውን ምሥራች በማወጅ በሙሉ ልቤ ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለት አምላክ ምሥክሬ ነው፤ 10 ደግሞም በአምላክ ፈቃድ አሁን በመጨረሻ እንደ ምንም ተሳክቶልኝ ወደ እናንተ መምጣት እንድችል ልመና እያቀረብኩ ነው። 11 ለመጽናት የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እጓጓለሁና፤ 12 ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው። 13 ይሁንና ወንድሞች፣ በሌሎች አሕዛብ መካከል ፍሬ እንዳፈራሁ ሁሉ በእናንተም መካከል ፍሬ አፈራ ዘንድ ወደ እናንተ ለመምጣት ብዙ ጊዜ አቅጄ እንደነበር እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ሆኖም ለመምጣት ባሰብኩ ቁጥር የሆነ እንቅፋት ያጋጥመኛል። 14 ለግሪካውያንም ሆነ ግሪካውያን ላልሆኑ እንዲሁም ለጠቢባንም ሆነ ላልተማሩ ዕዳ አለብኝ፤ 15 በመሆኑም በሮም ላላችሁት ለእናንተም ምሥራቹን ለማወጅ እጓጓለሁ። 16 እኔ በምሥራቹ አላፍርምና፤ እንዲያውም ለሚያምን ሁሉ ይኸውም በመጀመሪያ ለአይሁዳዊ ከዚያም ለግሪካዊ ምሥራቹ መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው። 17 ምክንያቱም “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ እምነት ያላቸው ሰዎች፣ አምላክ በምሥራቹ አማካኝነት ጽድቁን እንደሚገልጥ ይረዳሉ፤ ይህ ደግሞ እምነታቸውን ያጠነክርላቸዋል።
ከየካቲት 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሮም 4-6
“አምላክ . . . ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል”
(ሮም 5:8) ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።
(ሮም 5:12) ስለሆነም በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።
አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳይቷል
5 ጳውሎስ ይህን ጉዳይ ማብራራት የጀመረው የሚከተለውን ነጥብ በመናገር ነው፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) አምላክ የሰውን ሕይወት አጀማመር አስመልክቶ ያስጻፈው ዘገባ ስላለ ጳውሎስ የጠቀሰውን ነጥብ መረዳት እንችላለን። በመጀመሪያ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን የተባሉ ሁለት ሰዎችን ፈጥሮ ነበር። ፈጣሪ ፍጹም ነው፤ ወላጆቻችን የሆኑት የመጀመሪያዎቹ ሰዎችም ፍጹማን ነበሩ። አምላክ፣ እነዚህን ሰዎች አንድ ነገር ብቻ የከለከላቸው ሲሆን ይህንን ሕግ አለመታዘዝም የሞት ቅጣት እንደሚያስከትልባቸው ነግሯቸው ነበር። (ዘፍ. 2:17) ይሁንና አዳምና ሔዋን፣ ምክንያታዊ የሆነውን የአምላክን ሕግ ሆን ብለው በመጣስ ክፋት ፈጸሙ፤ በዚህ መንገድ አምላክን እንደ ሕግ ሰጪያቸውና ሉዓላዊ ገዥያቸው አድርገው ለመቀበል አሻፈረን አሉ።—ዘዳ. 32:4, 5
(ሮም 5:13, 14) ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ላይ ነበርና፤ ሆኖም ሕግ በሌለበት ማንም በኃጢአት አይጠየቅም። 14 ይሁንና አዳም ትእዛዝ በመተላለፍ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ባልሠሩት ላይም እንኳ ሳይቀር ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት በሁሉ ላይ ነገሠ፤ አዳም በኋላ ለሚመጣው አምሳያ ነበር።
አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳይቷል
6 አዳም ልጆች የወለደው ኃጢአተኛ ከሆነ በኋላ በመሆኑ ኃጢአትንና ኃጢአት የሚያስከትላቸውን መዘዞች ለልጆቹ በሙሉ አስተላልፏል። እርግጥ ነው፣ ዘሮቹ አዳም እንዳደረገው መለኮታዊውን ሕግ ስላልጣሱ እሱ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ፈጽማችኋል ተብለው አልተከሰሱም፤ ደግሞም በወቅቱ ምንም ዓይነት ሕግ አልተሰጠም ነበር። (ዘፍ. 2:17) ያም ሆኖ የአዳም ዘሮች ኃጢአትን ወርሰዋል። በመሆኑም አምላክ ለእስራኤላውያን ሕግ እስከሰጠበት ጊዜ ድረስ ኃጢአትና ሞት ነግሦ ቆይቷል፤ ሕጉም ሕዝቡ ኃጢአተኞች መሆናቸውን በግልጽ አሳይቷል። (ሮም 5:13, 14ን አንብብ።) ከአዳም የወረስነውን ኃጢአት በዘር ከሚተላለፉት እንደ ሜድትራንያን አኒሚያ ወይም ሂሞፊሊያ ካሉት በሽታዎች ጋር ማመሳሰል ይቻላል። የሩሲያ ዛር የነበረው የዳግማዊ ኒኮላስ እና የአሊግዛንድረ ልጅ የሆነው አሌክሰስ፣ ሂሞፊሊያ የተባለውን ደም እንዳይረጋ የሚያደርግ እክል ከወላጆቹ እንደወረሰ አንብበህ ይሆናል። እውነት ነው፣ እንደዚህ ባለው ቤተሰብ ውስጥም እንኳ አንዳንድ ልጆች ይህን እክል የሚያስተላልፈው ጂን ቢኖራቸውም የሕመም ምልክት አይታይባቸው ይሆናል። ከኃጢአት ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው እንደዚህ አይደለም። አዳም ለዘሮቹ ያወረሳቸው ኃጢአት ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ የሚቻልበት መንገድ የለም። ሁሉም የዚህ ችግር ሰለባ ናቸው። በመሆኑም ሁሉም መሞታቸው አይቀርም። እንዲሁም በዘር ከሚተላለፉ አንዳንድ በሽታዎች በተቃራኒ የአዳም ልጆች በሙሉ ኃጢአትን ይወርሳሉ። ታዲያ ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ነፃ መውጣት የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን?
(ሮም 5:18) ስለዚህ አንድ በደል ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲኮነኑ እንዳደረገ ሁሉ አንድ የጽድቅ ድርጊትም ሁሉም ዓይነት ሰዎች ጻድቃን ናችሁ ተብለው ለሕይወት እንዲበቁ ያስችላል።
(ሮም 5:21) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኃጢአት ከሞት ጋር እንደነገሠ ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ አማካኝነት እንዲነግሥ ነው።
አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አሳይቷል
9 “ጻድቃን ተብለው እንዲጠሩ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ይህን አገላለጽ በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ተለዋጭ ዘይቤን በመጠቀም ሁኔታው ከሕግ አንጻር ተገልጿል ማለት ይቻላል። አንድ ሰው በአምላክ ፊት ያለው ሁኔታ እንደተለወጠ የሚጠቁም ሐሳብ ነው፤ ይሁን እንጂ ግለሰቡ ውስጣዊ ለውጥ ይኖረዋል ማለት አይደለም። . . . ይህ ዘይቤያዊ አነጋገር አምላክን እንደ ዳኛ አድርጎ ይገልጸዋል፤ ይህ ዳኛ፣ ጻድቅ ባለመሆኑ ምክንያት ተከስሶ በምሳሌያዊ አነጋገር በእሱ ችሎት ፊት ለቀረበው ሰው ፈርዶለታል። አምላክ፣ ተከሳሹ ነፃ እንደሆነ የሚገልጽ ብያኔ አስተላልፏል።”
10 ጻድቅ የሆነው “የምድር ሁሉ ዳኛ” ጻድቅ ያልሆነን ሰው ነፃ ለማውጣት መሠረት የሚሆነው ምንድን ነው? (ዘፍ. 18:25) አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ይህን ለማድረግ የሚያስችለውን መሠረት ጥሏል። ኢየሱስ ፈተናዎች ያጋጠሙት፣ የተፌዘበትና ከፍተኛ እንግልት የደረሰበት ቢሆንም የአባቱን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ፈጽሟል። በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታማኝ ሆኗል። (ዕብ. 2:10) ኢየሱስ፣ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት የአዳምን ዘሮች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ወይም ለመዋጀት የሚያስችል ቤዛ አቅርቧል።—ማቴ. 20:28፤ ሮም 5:6-8
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሮም 6:3-5) ወይስ ክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ የተጠመቅን ሁላችን እሱ ሞት ውስጥ እንደተጠመቅን አታውቁም? 4 ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደተነሳ ሁሉ እኛም አዲስ ሕይወት እንድንኖር እሱ ሞት ውስጥ በመጠመቅ ከእሱ ጋር ተቀብረናል። 5 ሞቱን በሚመስል ሞት ከእሱ ጋር አንድ ከሆንን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእሱ ጋር አንድ እንደምንሆን ጥርጥር የለውም።
የሮሜ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
6:3-5—ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ለመሆን መጠመቅና ከሞቱ ጋር አንድ ለመሆን መጠመቅ የሚሉት አገላለጾች ምን ትርጉም አላቸው? ይሖዋ የክርስቶስን ተከታዮች በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባቸው ከኢየሱስ ጋር አንድ ከመሆናቸውም ሌላ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ አባላት ይሆናሉ፤ ይህ ጉባኤ የክርስቶስ አካል ሲሆን የአካሉ ራስ ደግሞ ኢየሱስ ነው። (1 ቆሮ. 12:12, 13, 27፤ ቈላ. 1:18) ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ለመሆን መጠመቅ የሚለው አገላለጽ ትርጉም ይህ ነው። በተጨማሪም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የመሥዋዕትነት ሕይወት ስለሚመሩና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን ስለሚተዉ ‘[ከክርስቶስ] ሞት ጋር አንድ ለመሆን እንደሚጠመቁ’ ተገልጿል። በመሆኑም የቅቡዓኑ ሞት ቤዛዊ ጥቅም ባይኖረውም እንደ ኢየሱስ የመሥዋዕትነት ሞት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ከሞቱ በኋላ ወደ ሰማይ ለመሄድ ትንሣኤ ሲያገኙ ከክርስቶስ ሞት ጋር አንድ ለመሆን የሚጠመቁት ጥምቀት ይጠናቀቃል።
(ሮም 6:7) የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷልና።
በቀድሞ ዘመን የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
ዓመፀኞች ከሞት በሚነሱበት ጊዜ የሚፈረድባቸው ከመሞታቸው በፊት ያደረጉትን ነገር መሠረት በማድረግ ነው? አይደለም። ሮም 6:7 “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” በማለት ይናገራል። ዓመፀኞች ሲሞቱ የኃጢአታቸውን ዋጋ ከፍለዋል። በመሆኑም የሚፈረድባቸው ትንሣኤ ካገኙ በኋላ በሚሠሩት ነገር እንጂ ከመሞታቸው በፊት ባለማወቅ በሠሩት ነገር መሠረት አይደለም። ይህ ዓመፀኞችን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሮም 4:1-15) እንዲህ ከሆነ ታዲያ በሥጋ አባታችን የሆነው አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? 2 ለምሳሌ አብርሃም ጻድቅ የተባለው በሥራ ቢሆን ኖሮ የሚመካበት ነገር በኖረው ነበር፤ ሆኖም በአምላክ ፊት ሊመካ አይችልም። 3 የቅዱስ መጽሐፉስ ቃል ምን ይላል? “አብርሃም በይሖዋ አመነ፤ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።” 4 ይሁንና ለሚሠራ ሰው ደሞዙ እንደ ሥራው ዋጋ እንጂ እንደ ጸጋ ስጦታ ተደርጎ አይቆጠርለትም። 5 በሌላ በኩል ግን በራሱ ሥራ ከመመካት ይልቅ ኃጢአተኛውን ጻድቅ ነህ ብሎ በሚጠራው አምላክ የሚያምን እምነቱ እንደ ጽድቅ ይቆጠርለታል። 6 ይህም ዳዊት፣ አምላክ ያለሥራ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረው ሰው ስለሚያገኘው ደስታ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ 7 “የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው፤ 8 ይሖዋ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው።” 9 ታዲያ ይህን ደስታ የሚያገኙት የተገረዙ ሰዎች ብቻ ናቸው ወይስ ያልተገረዙትም ጭምር? ምክንያቱም “አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ብለናል። 10 ታዲያ እምነቱ እንደ ጽድቅ የተቆጠረው በምን ዓይነት ሁኔታ እያለ ነው? ተገርዞ እያለ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? ተገርዞ እያለ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው። 11 ገና ከመገረዙ በፊት በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ ምልክት ሆኖ የሚያገለግለውን ግርዘትን እንደ ማኅተም ተቀበለ፤ ስለዚህ ባይገረዙም እንኳ በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት ሆኗል፤ 12 ለተገረዙት ዘሮቹም አባት ነው፤ ይሁንና ግርዘትን አጥብቀው ለሚከተሉት ብቻ ሳይሆን አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት ተከትለው በሥርዓት ለሚመላለሱ ሰዎችም ሁሉ አባት ነው። 13 ምክንያቱም አብርሃም ወይም ዘሩ የዓለም ወራሽ እንደሚሆን ተስፋ የተሰጠው በሕግ አማካኝነት ሳይሆን በእምነት በሚገኘው ጽድቅ ነው። 14 ወራሾች የሚሆኑት ሕጉን በጥብቅ የሚከተሉ ቢሆኑ ኖሮ እምነት ከንቱ በሆነ ነበርና፤ የተስፋውም ቃል ባከተመ ነበር። 15 እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ ቁጣ ያስከትላል፤ ሆኖም ሕግ ከሌለ ሕግን መተላለፍ የሚባል ነገር አይኖርም።
ከየካቲት 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሮም 7-8
“‘በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቅክ’ ነው?”
(ሮም 8:19) ፍጥረት የአምላክን ልጆች መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው።
ይሖዋ ወደ እውነተኛው ነፃነት ይምራችሁ!
17 ጳውሎስ፣ ይሖዋ በምድር ላይ ለሚኖሩ አገልጋዮቹ ስላዘጋጀው ነፃነት ሲናገር “ፍጥረት የአምላክን ልጆች መገለጥ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው” በማለት ጽፏል። አክሎም “ፍጥረት ራሱ . . . ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት” እንደሚያገኝ ተናግሯል። (ሮም 8:19-21) “ፍጥረት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በመንፈስ የተቀቡት የአምላክ ልጆች ‘በመገለጣቸው’ ምክንያት ጥቅም የሚያገኙትን ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ነው። የአምላክ “ልጆች” የሚገለጡት ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ በሚሄዱበት ጊዜ ነው፤ በዚህ ወቅት ከክርስቶስ ጋር በመሆን ክፉዎችን ከምድረ ገጽ የሚያጠፉ ሲሆን ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦችን’ ደግሞ ወደ አዲሱ ሥርዓት ያስገባሉ።—ራእይ 7:9, 14
(ሮም 8:20) ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷልና፤ የተገዛው ግን በገዛ ፈቃዱ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእሱ አማካኝነት ነው፤
በተስፋችን ደስ ይበለን
11 ይሖዋ ተስፋ በተደረገበት ‘ዘር’ አማካኝነት ‘ከመጀመሪያው እባብ’ ማለትም ከሰይጣን ዲያብሎስ ነፃ እንደሚያደርጋቸው ቃል በመግባት ለሰው ልጆች “ተስፋ” ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 3:15፤ ራእይ 12:9) የዚህ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ገላ. 3:16) የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የሰው ዘርን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል መሠረት ጥሏል። የዚህ ተስፋ ፍጻሜ ‘ከአምላክ ልጆች መገለጥ’ ጋር የተያያዘ ነው። ‘የዘሩ’ ሁለተኛ ክፍል የሚሆኑት ክብር የተላበሱት ቅቡዓን ናቸው፤ እነዚህ ቅቡዓን ‘የሚገለጡት’ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በመሆን የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት በሚመጡበት ጊዜ ነው። (ራእይ 2:26, 27) ይህ ከታላቁ መከራ ለሚያልፉ ሌሎች በጎች መዳን ያስገኝላቸዋል።—ራእይ 7:9, 10, 14
(ሮም 8:21) ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥቶ የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት ማግኘት ነው።
በተስፋችን ደስ ይበለን
12 ሰብዓዊው “ፍጥረት” በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በቃላት ሊገለጽ የማይችል እፎይታ ያገኛል! ክብር የተላበሱት ‘የአምላክ ልጆች’ በዚህ ወቅትም በሌላ መንገድ ይገለጣሉ፤ ይህ የሚሆነው ከክርስቶስ ጋር ካህናት በመሆን የሰው ዘር ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች እንዲያገኝ ሲያደርጉ ነው። የሰማያዊው መንግሥት ተገዥ የሆነው ሰብዓዊ “ፍጥረት” ኃጢአትና ሞት ካስከተሏቸው መጥፎ ውጤቶች ነፃ መሆን ይጀምራል። በዚህ መንገድ ታዛዥ የሆኑት የሰው ልጆች ቀስ በቀስ “ከመበስበስ ባርነት ነፃ” ይሆናሉ። በተጨማሪም እስከ ሺው ዓመት ፍጻሜ ድረስ ለይሖዋ ታማኝ ከሆኑና መጨረሻ ላይ የሚቀርበውን ፈተና ካለፉ ስማቸው “የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል” ላይ ለዘላለም ይጻፋል። በዚህ ወቅት ‘የአምላክ ልጆች የመሆን ክብራማ ነፃነት’ ያገኛሉ። (ራእይ 20:7, 8, 11, 12) በእርግጥም ይህ፣ ክብራማ የሆነ ተስፋ ነው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሮም 8:6) በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል፤
ታስታውሳለህ?
‘በሥጋዊ ነገሮች ላይ በማተኮር’ እና ‘በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር’ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? (ሮም 8:6)
በሥጋዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩር ሰው ትኩረቱ ያረፈው ፍጽምና የጎደለው ሥጋው ባሉት ምኞቶችና ዝንባሌዎች ላይ ነው፤ አዘውትሮ የሚያወራው ስለ ሥጋዊ ነገር ነው። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሰው ግን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖር ከመሆኑም ሌላ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ወደ ሞት ይመራል፤ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል።—w16.12 ከገጽ 15-17
(ሮም 8:26, 27) በተመሳሳይም መንፈስ በድካማችን ይረዳናል። ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ግራ የምንጋባበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመንና ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ተስኖን ስንቃትት መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል። 27 ይሁንና ልብን የሚመረምረው አምላክ የመንፈስን ዓላማ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ ለቅዱሳን የሚማልደው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው።
የምታቀርበው ጸሎት ስለ አንተ ምን ይገልጻል?
20 በግላችን በምንጸልይበት ወቅት ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ሊጠፋን ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ችግሩ መጸለይ በሚያስፈልገን ጊዜ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን አለማወቃችን ነው፤ ሆኖም በቃላት መግለጽ ተስኖን በምንቃትትበት ጊዜ መንፈስ [ቅዱስ] ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል። ይሁንና ልብን የሚመረምረው አምላክ የመንፈስን ትርጉም ያውቃል።” (ሮም 8:26, 27) ይሖዋ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በርካታ ጸሎቶች እንዲካተቱ አድርጓል። በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን እነዚህን ልመናዎች እኛ እንዳቀረብነው ጸሎት አድርጎ በመቀበል ምላሽ ይሰጠናል። አምላክ ምን እንደምንፈልግ ያውቃል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመንፈሱ እየተመሩ የጻፉት ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው ያውቃል። መንፈሱ ስለ እኛ “በሚማልድበት” ወይም እኛን ወክሎ በሚለምንበት ጊዜ ይሖዋ ልመናችንን ይሰማል። ሆኖም የአምላክን ቃል ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ልንጸልይበት የሚገባው ጉዳይ በቀላሉ ወደ አእምሯችን ሊመጣ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሮም 7:13-25) ታዲያ ይህ ጥሩ የሆነው ነገር ሞት አመጣብኝ ማለት ነው? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ የገደለኝ ኃጢአት ነው። የኃጢአት ምንነት እንዲገለጥ ጥሩ በሆነው ነገር አማካኝነት ሞት ያመጣብኝ ኃጢአት ነው። ትእዛዙም ኃጢአት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ አሳይቷል። 14 ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ። 15 ለምን እንዲህ እንደማደርግ አላውቅም። ለማድረግ የምፈልገውን ነገር አላደርግምና፤ ከዚህ ይልቅ የማደርገው የምጠላውን ነገር ነው። 16 ይሁን እንጂ የማደርገው የማልፈልገውን ከሆነ ሕጉ መልካም ነው በሚለው እስማማለሁ። 17 ሆኖም አሁን ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 18 ምክንያቱም በውስጤ ማለትም በሥጋዬ ውስጥ የሚኖር ምንም ጥሩ ነገር የለም፤ መልካም የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም። 19 የምመኘውን መልካም ነገር አላደርግምና፤ የማልፈልገውን መጥፎ ነገር ግን አደርጋለሁ። 20 እንግዲህ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን በውስጤ የሚኖረው ኃጢአት ነው። 21 እንግዲያው ይህ ሕግ በራሴ ላይ ሲሠራ አያለሁ፦ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው። 22 በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ 23 በሰውነቴ ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። 24 እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል? 25 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! ስለዚህ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለአምላክ ሕግ ባሪያ ስሆን በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።
ከየካቲት 25–መጋቢት 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሮም 9-11
“የወይራ ዛፉ ምሳሌ”
(ሮም 11:16) በተጨማሪም በኩራት ተደርጎ የተወሰደው የሊጡ ክፍል ቅዱስ ከሆነ ሊጡ በሙሉ ቅዱስ ነው፤ እንዲሁም ሥሩ ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው።
‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
13 ሐዋርያው ጳውሎስ የአብርሃም ዘር ክፍል የሚሆኑትን ሰዎች ከምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ጋር አነጻጽሯቸዋል። (ሮም 11:21) በእርሻ ላይ የተተከለው ይህ የወይራ ዛፍ፣ አምላክ ከአብርሃም ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ አፈጻጸም ያመለክታል። የዚህ ዛፍ ሥር ቅዱስ ሲሆን ይህ ሥር ለመንፈሳዊ እስራኤላውያን ሕይወት የሰጣቸውን ይሖዋን የሚወክል ነው። (ኢሳ. 10:20፤ ሮም 11:16) ግንዱ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነውን ኢየሱስን ይወክላል። ቅርንጫፎቹ በአጠቃላይ ደግሞ በአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል ውስጥ የሚካተቱትን ሰዎች ‘ሙሉ ቁጥር’ ያመለክታሉ።
(ሮም 11:17) ይሁን እንጂ ከቅርንጫፎቹ መካከል አንዳንዶቹ ቢሰበሩና አንተ የዱር ወይራ ሆነህ ሳለህ በእነሱ መካከል ከተጣበቅክ እንዲሁም ከወይራው ዛፍ ሥር ከሚገኘው በረከት ተካፋይ ከሆንክ
(ሮም 11:20, 21) እውነት ነው! እነሱ ባለማመናቸው ተሰብረዋል፤ አንተ ግን በእምነት ቆመሃል። ቢሆንም መፍራት እንጂ መታበይ አይገባህም። 21 አምላክ በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራ ለአንተም አይራራምና።
‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
15 ታዲያ ይሖዋ ዓላማውን ለማሳካት ምን አደረገ? ጳውሎስ የተሰበሩትን ቅርንጫፎች ለመተካት ሲባል ከዱር የወይራ ዛፍ የተወሰዱ ቅርንጫፎች በእርሻ ላይ በተተከለው የወይራ ዛፍ ላይ እንደተጣበቁ ገልጿል። (ሮም 11:17, 18ን አንብብ።) በመሆኑም ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ቅቡዓን (ለምሳሌ በሮም በሚገኘው ጉባኤ የነበሩት አንዳንድ ክርስቲያኖች) በዚህ ምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ላይ ተጣበቁ። በዚህ መንገድ የአብርሃም ዘር ክፍል ሆኑ። እነዚህ ክርስቲያኖች መጀመሪያ ላይ እንደ ዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ስለነበሩ የዚህ ልዩ ቃል ኪዳን ክፍል የመሆን አጋጣሚ አልነበራቸውም። ይሁንና ይሖዋ መንፈሳዊ አይሁዳውያን መሆን የሚችሉበትን በር ከፈተላቸው።—ሮም 2:28, 29
(ሮም 11:25, 26) ወንድሞች፣ በራሳችሁ ዓይን ጥበበኞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ቅዱስ ሚስጥር እንድታውቁ እፈልጋለሁ፦ የአሕዛብ ቁጥር እስኪሞላ ድረስ የእስራኤል ሕዝብ በከፊል ስሜቱ ደንዝዟል፤ 26 በዚህም መንገድ እስራኤል ሁሉ ይድናል። ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው፦ “አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ የያዕቆብም ዘሮች የክፋት ድርጊታቸውን እንዲተዉ ያደርጋል።
‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
19 አዎን፣ ይሖዋ ‘ከአምላክ እስራኤል’ ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ አስገራሚ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። (ገላ. 6:16) ጳውሎስ እንደተናገረው “እስራኤል ሁሉ ይድናል።” (ሮም 11:26) ይሖዋ በወሰነው ጊዜ “እስራኤል ሁሉ” ይኸውም መንፈሳዊ እስራኤላውያን በሙሉ በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። ምንም ነገር የይሖዋ ዓላማ ዳር እንዳይደርስ ሊያደርግ አይችልም!
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሮም 9:21-23) ሸክላ ሠሪው ከዚያው ከአንዱ ጭቃ፣ አንዱን ዕቃ ክቡር ለሆነ አገልግሎት ሌላውን ዕቃ ደግሞ ክብር ለሌለው አገልግሎት ለመሥራት በጭቃው ላይ ሥልጣን እንዳለው አታውቅም? 22 አምላክ ቁጣውን ለማሳየትና ኃይሉ እንዲታወቅ ለማድረግ ቢፈልግም እንኳ ጥፋት የሚገባቸውን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏቸው እንደሆነስ ምን ታውቃለህ? 23 ይህን ያደረገው ታላቅ ክብሩን አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች ላይ ለመግለጥ
የይሖዋ ተግሣጽ እንዲቀርጻችሁ ፍቀዱ
5 የሰው ልጆች ልባቸውን ቢያደነድኑና በታላቁ ሸክላ ሠሪ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ባይሆኑስ? በዚህ ጊዜ ይሖዋ መለኮታዊ ሥልጣኑን የሚጠቀምበት እንዴት ነው? አንድ ሸክላ ሠሪ የያዘው ጭቃ ላሰበው ዓላማ ተስማሚ ባይሆን ምን ያደርጋል? በዚሁ ጭቃ ሌላ ዓይነት ዕቃ ይሠራበታል ካልሆነም ጭቃውን ይጥለዋል! ይሁንና ጭቃው ጥቅም ላይ ካልዋለ አብዛኛውን ጊዜ ጥፋቱ የሸክላ ሠሪው ነው። ከታላቁ ሸክላ ሠሪ ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው ፈጽሞ የተለየ ነው። (ዘዳ. 32:4) አንድ ሰው በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ካልሆነ ጥፋቱ ምንጊዜም የራሱ የግለሰቡ ነው። ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመቅረጽ ያለውን ሥልጣን የሚጠቀምበት ሊቀርጻቸው ሲሞክር የሚሰጡትን ምላሽ መሠረት በማድረግ ነው፤ የሚሰጡትን ምላሽ በመመልከት እነሱን የሚይዝበትን መንገድ ይቀያይራል። ይሖዋ ሲቀርጻቸው ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ በሚችሉበት መንገድ ይቀረጻሉ። ለምሳሌ ያህል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ክቡር ለሆነ አገልግሎት የሚሆኑ ዕቃዎች’ ሆነው የተቀረጹ “የምሕረት ዕቃዎች” ናቸው። በሌላ በኩል ግን ልበ ደንዳና በመሆን አምላክን የሚቃወሙ ሰዎች ‘ለጥፋት የተዘጋጁ የቁጣ ዕቃዎች’ ይሆናሉ።—ሮም 9:19-23
(ሮም 10:2) ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁና፤ ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም።
it-1-E 1260 አን. 2
ቀናተኛ፣ ቅንዓት
የተሳሳተ ቅንዓት። ለአንድ ነገር ልባዊ ቅንዓት ያለው ሰውም እንኳ ቅንዓቱ አምላክን የማያስደስት ወይም የተሳሳተ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ አይሁዳውያን እንዲህ ዓይነት ቅንዓት አሳይተዋል። እነዚህ አይሁዳውያን የሙሴን ሕግ በመታዘዝ በሚያከናውኗቸው ሥራዎች መጽደቅ ይፈልጉ ነበር። ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የተሳሳተ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጿል። በዚህ የተነሳ ከአምላክ የሚገኘውን እውነተኛ ጽድቅ አላገኙም። እነዚህ ሰዎች ለመጽደቅና ከሕግ ኩነኔ ነፃ ለመሆን ከፈለጉ፣ መሳሳታቸውን ተገንዝበው በክርስቶስ አማካኝነት ወደ አምላክ መቅረብ አለባቸው። (ሮም 10:1-10) የጠርሴሱ ሳኦል የተሳሳተ ቅንዓት ከነበራቸው አይሁዳውያን አንዱ ነው፤ ሳኦል ለአይሁድ ሃይማኖት እጅግ ከመቅናቱ የተነሳ ‘የአምላክን ጉባኤ ክፉኛ ያሳድድና ለማጥፋት ጥረት ያደርግ ነበር።’ ሕጉን በጥብቅ ይከተል ስለነበር “እንከን የማይገኝብኝ መሆኔን አስመሥክሬአለሁ” በማለት ተናግሯል። (ገላ 1:13, 14፤ ፊልጵ 3:6) ይሁንና ለአይሁድ ሃይማኖት የነበረው ቅንዓት የተሳሳተ ነው። ሳኦል ቅን ልብ ያለው ሰው በመሆኑ ይሖዋ ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲመለስ በመርዳት በክርስቶስ አማካኝነት ጸጋውን አሳይቶታል።—1ጢሞ 1:12, 13
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሮም 10:1-15) ወንድሞች፣ ለእስራኤላውያን ከልቤ የምመኘውና ስለ እነሱ ለአምላክ ምልጃ የማቀርበው እንዲድኑ ነው። 2 ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁና፤ ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም። 3 የአምላክን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለፈለጉ ራሳቸውን ለአምላክ ጽድቅ አላስገዙም። 4 የሚያምን ሁሉ መጽደቅ ይችል ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። 5 ሙሴ በሕጉ አማካኝነት ስለሚገኘው ጽድቅ ሲገልጽ “እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው በእነሱ አማካኝነት በሕይወት ይኖራል” ሲል ጽፏል። 6 ሆኖም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ በተመለከተ እንዲህ ተብሏል፦ “በልብህ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7 ወይም ‘ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሳት ነው።” 8 ይሁንና ቅዱስ መጽሐፉ ምን ይላል? “ቃሉ ለአንተ ቅርብ ነው፤ ደግሞም በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው”፤ ይህም እኛ የምንሰብከው የእምነት “ቃል” ነው። 9 ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ በይፋ ብትናገር እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህና። 10 ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና፤ በአፉ ደግሞ እምነቱን በይፋ ተናግሮ ይድናል። 11 ቅዱስ መጽሐፉ “በእሱ ላይ እምነት የሚጥል ሁሉ አያፍርም” ይላል። 12 በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ምንም ልዩነት የለምና። የሁሉም ጌታ አንድ ነው፤ እሱም የሚለምኑትን ሁሉ አብዝቶ ይባርካል። 13 “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።” 14 ይሁንና ካላመኑበት እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እሱ ሳይሰሙስ እንዴት ያምኑበታል? ደግሞስ የሚሰብክላቸው ሳይኖር እንዴት ይሰማሉ? 15 ካልተላኩስ እንዴት ይሰብካሉ? ይህም “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።