የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሰኔ 2019
ከሰኔ 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ገላትያ 4-6
“‘ምሳሌያዊ ትርጉም” ካላቸው ነገሮች የምናገኘው ትምህርት”
(ገላትያ 4:24, 25) እነዚህ ሴቶች ሁለት ቃል ኪዳኖችን ስለሚወክሉ እነዚህ ነገሮች ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው፤ አንደኛው ቃል ኪዳን የተገባው በሲና ተራራ ሲሆን በዚህ ቃል ኪዳን ሥር ያሉት ልጆች ሁሉ ባሪያዎች ናቸው፤ ይህ ቃል ኪዳን ደግሞ አጋርን ያመለክታል። 25 አጋር፣ በዓረብ አገር የሚገኘውን የሲና ተራራ የምትወክል ሲሆን ዛሬ ካለችው ኢየሩሳሌም ጋር ትመሳሰላለች፤ ኢየሩሳሌም ከልጆቿ ጋር በባርነት ሥር ናትና።
it-1 1018 አን. 2
አጋር
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው አጋር፣ በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት ከይሖዋ ጋር የታሰረውን የእስራኤልን ብሔር ታመለክታለች፤ ይህ ቃል ኪዳን ሥራ ላይ መዋል የጀመረው በሲና ተራራ ላይ ሲሆን በዚህ ቃል ኪዳን ሥር ያሉት ልጆች “ባሪያዎች ናቸው።” ሕዝቡ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ቃል ኪዳኑ የሚጠብቅባቸውን ነገሮች መፈጸም አልቻሉም። ቃል ኪዳኑ፣ እስራኤላውያን ነፃ እንዲወጡ ከመርዳት ይልቅ ሞት የሚገባቸው ኃጢአተኞች መሆናቸውን በማሳየት ኮንኗቸዋል፤ በመሆኑም ባሪያዎች ነበሩ። (ዮሐ 8:34፤ ሮም 8:1-3) በጳውሎስ ዘመን የነበረችው ኢየሩሳሌም ከአጋር ጋር ልትመሳሰል ትችላለች፤ ምክንያቱም የእስራኤል ብሔርን የምትወክለውና የብሔሩ ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም ከነልጆቿ በባርነት ሥር ነበረች። በሌላ በኩል ግን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች፣ የአምላክ ምሳሌያዊ ሴት የሆነችው ‘የላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም’ ልጆች ናቸው። እንደ ነፃዪቱ ሴት እንደ ሣራ ሁሉ ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌምም በባርነት ሥር ሆና አታውቅም። ይሁን እንጂ እስማኤል ይስሐቅን እንዳሳደደው ሁሉ የባሪያዪቱ ኢየሩሳሌም ልጆችም በወልድ አማካኝነት ነፃ በወጡት ‘የላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም’ ልጆች ላይ ስደት አድርሰዋል። ሆኖም አጋር ከነልጇ ተባርራለች፤ ይህም ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር እንደተወው ያመለክታል።—ገላ 4:21-31፤ በተጨማሪም ዮሐ 8:31-40ን ተመልከት።
(ገላትያ 4:26, 27) ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን ነፃ ናት፤ እሷም እናታችን ናት። 27 “አንቺ የማትወልጂ መሃን ሴት፣ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ምጥ የማታውቂ ሴት፣ እልል በይ፣ ጩኺም፤ ምክንያቱም ባል ካላት ሴት ይልቅ የተተወችው ሴት ልጆች እጅግ በዝተዋል” ተብሎ ተጽፏልና።
በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑራችሁ
11 የአብርሃም ዘሮች ተስፋይቱን ምድር ሲወርሱ የአብርሃም ቃል ኪዳን የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል፤ ያም ቢሆን ይህ ቃል ኪዳን በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍጻሜ እንዳለው ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቁማሉ። (ገላ. 4:22-25) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዳብራራው የአብርሃም ቃል ኪዳን ታላቅ ፍጻሜውን በሚያገኝበት ጊዜ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል የሚሆነው ክርስቶስ ሲሆን የዘሩ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ በመንፈስ የተቀቡ 144,000 ክርስቲያኖች ናቸው። (ገላ. 3:16, 29፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 4) ዘሩን የምታስገኘው ሴት “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ይኸውም ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን የምታቅፈው የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ናት። (ገላ. 4:26, 31) በአብርሃም ቃል ኪዳን ላይ በተሰጠው ተስፋ መሠረት የሴቲቱ ዘር ለሰው ልጆች በረከት ያመጣል።
(ገላትያ 4:28-31) እንግዲህ ወንድሞች፣ እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ። 29 ሆኖም ያን ጊዜ በሥጋዊ መንገድ የተወለደው በመንፈስ የተወለደውን ማሳደድ እንደጀመረ ሁሉ አሁንም እንደዚያው ነው። 30 ይሁንና ቅዱስ መጽሐፉ ምን ይላል? “የአገልጋዪቱ ልጅ ከነፃዪቱ ልጅ ጋር በምንም ዓይነት አብሮ ስለማይወርስ አገልጋዪቱን ከነልጅዋ አባር።” 31 ስለዚህ ወንድሞች፣ እኛ የነፃዪቱ ልጆች እንጂ የአገልጋዪቱ ልጆች አይደለንም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ገላትያ 4:6) አሁን እናንተ ልጆች ስለሆናችሁ አምላክ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ልኳል፤ ይህም መንፈስ “አባ፣ አባት!” እያለ ይጣራል።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ኢየሱስ ሲጸልይ ይሖዋን “አባ፣ አባት” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?
“አባ” የሚለው የአረማይክ ቃል “አባት” ወይም “አባት ሆይ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝባቸው በሦስቱም ቦታዎች ላይ የተሠራበት ከጸሎት ጋር በተያያዘ ሲሆን “አባ” የተባለውም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ ነው። ይህ ቃል ምን ትርጉም አለው?
ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው ይጠቀሙበት በነበረው ቋንቋ፣ ‘አባ’ የሚለው ቃል በዋነኝነት የሚያገለግለው ልጆች ከአባታቸው ጋር ያላቸውን ቅርርብ እንዲሁም ለአባታቸው ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ ነበር።” ቃሉ፣ አንድ ልጅ አባቱን በፍቅር የሚጠራበት መንገድ ከመሆኑም ሌላ ሕፃናት መጀመሪያ ከሚያውቋቸው ቃላት አንዱ ነው። ኢየሱስ ይህንን ቃል የተጠቀመው አባቱን በጸሎት በተማጸነበት ጊዜ ነበር። ከመሞቱ ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ሆኖ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “አባ፣ አባት” በማለት ጠርቶታል።—ማርቆስ 14:36
ከላይ የተጠቀሰው ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የግሪካውያንና የሮማውያን ባሕል ተዋሕዶ በነበረበት ዘመን፣ በአይሁዳውያን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ አምላክን ለመጥራት ‘አባ’ የሚለውን ቃል መጠቀም ፍጹም ያልተለመደ ነገር ነበር፤ ይህም የሆነው ቅርበትን በሚያመለክተው በዚህ ቃል አምላክን መጥራት አክብሮት አለማሳየት እንደሆነ ተደርጎ ስለሚቆጠር መሆን አለበት።” ይኸው መጽሐፍ እንደገለጸው “ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ . . . ይህንን ቃል መጠቀሙ ከአባቱ ጋር በጣም እንደሚቀራረቡ የተናገረውን ሐሳብ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደግፍ ነው።” ጳውሎስ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ የሚገኙት “አባ” የሚለው ቃል የገባባቸው ሌሎች ሁለት ጥቅሶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ክርስቲያኖችም ይህንን ቃል በጸሎታቸው ውስጥ ይጠቀሙበት እንደነበረ ይጠቁማሉ።—ሮም 8:15፤ ገላትያ 4:6
(ገላትያ 6:17) የኢየሱስ ባሪያ መሆኔን የሚያሳይ መለያ ምልክት በሰውነቴ ላይ ስላለ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
ሐዋርያው ጳውሎስ “የኢየሱስ ባሪያ [መሆኑን] የሚያሳይ መለያ ምልክት” በሰውነቱ ላይ እንዳለ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?—ገላትያ 6:17
▪ ጳውሎስ የተናገረውን ይህን ሐሳብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በተለያየ መንገድ ተረድተውት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ጊዜ የጦር እስረኞች፣ የቤተ መቅደስ ዘራፊዎች ወይም ከጌቶቻቸው የኮበለሉ ባሪያዎች በጋለ ብረት ምልክት ይደረግባቸው ነበር። እንዲህ ያለው ምልክት የሚያሳፍር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።
ይሁንና መለያ ምልክቶች አሳፋሪ እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩት ሁልጊዜ አልነበረም። በጥንት ጊዜ የነበሩ ብዙ ሕዝቦች የአንድ ጎሣ ወይም ሃይማኖት አባል መሆናቸውን ለማሳወቅ እንደዚህ ያለ መለያ ምልክት በሰውነታቸው ላይ ያደርጉ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “የሶርያ ሰዎች ሐዳድ እና አታርጋቲስ ለተባሉት አማልክት ራሳቸውን መቀደሳቸውን ለማሳየት የእጃቸውን አንጓ ወይም አንገታቸውን በመተኮስ ምልክት ይደረግባቸው ነበር፤ . . . ዳዮናይሰስ [የተባለው አምላክ] ተከታዮች ደግሞ [ሰውነታቸውን በመተኮስ] የሐረግ ቅጠል ምልክት ያደርጋሉ።”
በዘመናችን ያሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች፣ ጳውሎስ የጠቀሰው ምልክት የሚስዮናዊነት አገልግሎቱን ሲያከናውን በተለያዩ ጊዜያት በመደብደቡ በሰውነቱ ላይ የቀረውን ጠባሳ የሚጠቁም እንደሆነ ይናገራሉ። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27) ምናልባትም ጳውሎስ ከላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር ቃል በቃል በሰውነቱ ላይ ምልክት እንዳለ መናገሩ ሳይሆን የተከተለው የሕይወት ጎዳና ክርስቲያን መሆኑን ለይቶ እንደሚያሳውቅ መግለጹ ሊሆን ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ገላትያ 4:1-20) እንግዲህ ይህን እላለሁ፦ ወራሹ የሁሉም ነገር ጌታ ቢሆንም እንኳ ሕፃን እስከሆነ ድረስ ከባሪያ በምንም አይለይም፤ 2 ይልቁንም አባቱ አስቀድሞ የወሰነው ቀን እስኪደርስ ድረስ በሞግዚቶችና በመጋቢዎች ሥር ሆኖ ይቆያል። 3 በተመሳሳይ እኛም ልጆች በነበርንበት ጊዜ በዓለም ውስጥ ላሉ ተራ ነገሮች ባሪያ ሆነን ቆይተናል። 4 ሆኖም ዘመኑ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ ከሴት የተወለደውንና በሕግ ሥር የነበረውን ልጁን ላከ፤ 5 ይህን ያደረገው እኛን ልጆቹ አድርጎ መውሰድ ይችል ዘንድ በሕግ ሥር ያሉትን ዋጅቶ ነፃ ለማውጣት ነው። 6 አሁን እናንተ ልጆች ስለሆናችሁ አምላክ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ልኳል፤ ይህም መንፈስ “አባ፣ አባት!” እያለ ይጣራል። 7 በመሆኑም ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅ ከሆንክ ደግሞ አምላክ ወራሽም አድርጎሃል። 8 ይሁንና አምላክን ከማወቃችሁ በፊት በእርግጥ አማልክት ላልሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ትገዙ ነበር። 9 አሁን ግን አምላክን አውቃችኋል፤ እንዲያውም አምላክ እናንተን አውቋችኋል፤ ታዲያ ደካማና ከንቱ ወደሆኑ ተራ ነገሮች መመለስና እንደገና ለእነዚህ ነገሮች ባሪያ መሆን ትፈልጋላችሁ? 10 ቀናትን፣ ወራትን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን በጥንቃቄ እየጠበቃችሁ ታከብራላችሁ። 11 የእናንተ ሁኔታ ያሳስበኛል፤ ምክንያቱም ለእናንተ የደከምኩት በከንቱ እንዳይሆን እሰጋለሁ። 12 ወንድሞች፣ እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ፤ ምክንያቱም እኔም በአንድ ወቅት እንደ እናንተ ነበርኩ። እናንተ ምንም የበደላችሁኝ ነገር የለም። 13 በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእናንተ ምሥራቹን ለመስበክ አጋጣሚ ያገኘሁት በመታመሜ የተነሳ እንደነበር ታውቃላችሁ። 14 ሕመሜ ፈተና ሆኖባችሁ የነበረ ቢሆንም እንኳ አልናቃችሁኝም ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ አምላክ መልአክ ወይም እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። 15 ታዲያ ያ ሁሉ ደስታችሁ የት ጠፋ? የሚቻል ቢሆን ኖሮ ዓይናችሁን እንኳ አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደነበር እርግጠኛ ነኝ። 16 ታዲያ እውነቱን ስለምነግራችሁ ጠላት ሆንኩባችሁ ማለት ነው? 17 እነሱ ወደ ራሳቸው ሊስቧችሁ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን ለበጎ ሳይሆን እናንተን ከእኔ በማራቅ እነሱን አጥብቃችሁ እንድትከተሏቸው ለማድረግ ነው። 18 ይሁን እንጂ አንድ ሰው ምንጊዜም እናንተን አጥብቆ የሚፈልገው ለበጎ ዓላማ ከሆነ ጥሩ ነው፤ ይህም መሆን ያለበት እኔ ከእናንተ ጋር ስሆን ብቻ አይደለም፤ 19 የምወዳችሁ ልጆቼ፣ ክርስቶስ በውስጣችሁ እስኪቀረጽ ድረስ በእናንተ ምክንያት እንደገና ምጥ ይዞኛል። 20 በእናንተ ግራ ስለተጋባሁ አሁን በመካከላችሁ ተገኝቼ ለየት ባለ መንገድ ላነጋግራችሁ ብችል ደስ ባለኝ ነበር።
ከሰኔ 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኤፌሶን 1-3
“የይሖዋ አስተዳደር እና የሚያከናውነው ሥራ”
(ኤፌሶን 1:8, 9) ጸጋውንም ከጥበብና ከማስተዋል ሁሉ ጋር አትረፍርፎ ሰጥቶናል፤ 9 ይህን ያደረገው የፈቃዱን ቅዱስ ሚስጥር ለእኛ በማሳወቅ ነው። ይህ ሚስጥር ደግሞ እሱ ራሱ ካሰበው ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው፤
it-2 837 አን. 4
ቅዱስ ሚስጥር
መሲሐዊው መንግሥት። ጳውሎስ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ ስለ ክርስቶስ ቅዱስ ሚስጥር መገለጥ በሚገባ አብራርቷል። ጳውሎስ በኤፌሶን 1:9-11 ላይ አምላክ የፈቃዱን “ቅዱስ ሚስጥር” እንዳሳወቀ ከተናገረ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሚስጥር ደግሞ እሱ ራሱ ካሰበው ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው፤ ዓላማውም በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ አንድ አስተዳደር ለማቋቋም ይኸውም ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችንና በምድር የሚሆኑ ነገሮችን በክርስቶስ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ነው። አዎ፣ በእሱ አማካኝነት ሁሉም ነገሮች ይሰበሰባሉ፤ እኛም ከእሱ ጋር አንድነት ያለን ሲሆን ወራሾች እንድንሆንም ተመርጠናል፤ ምክንያቱም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሁሉንም ነገር በወሰነው መንገድ የሚያከናውነው እሱ ከዓላማው ጋር በሚስማማ ሁኔታ አስቀድሞ መርጦናል።” ይህ “ቅዱስ ሚስጥር” ከአንድ መንግሥት ይኸውም ከአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ጋር የተያያዘ ነው። ጳውሎስ “በሰማያት የሚሆኑ ነገሮች” ያላቸው፣ በሰማይ ያለውን መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የሚወርሱት ናቸው። “በምድር የሚሆኑ ነገሮች” የተባሉት ደግሞ በምድር ላይ የሚኖሩት የመንግሥቱ ተገዢዎች ናቸው። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥር የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል” ሲላቸው ቅዱሱ ሚስጥር ከመንግሥቱ ጋር ተያያዥነት ያለው ነገር መሆኑን ጠቁሟል።—ማር 4:11
(ኤፌሶን 1:10) ዓላማውም በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ አንድ አስተዳደር ለማቋቋም ይኸውም ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችንና በምድር የሚሆኑ ነገሮችን በክርስቶስ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ነው። አዎ፣ በእሱ አማካኝነት ሁሉም ነገሮች ይሰበሰባሉ፤
ይሖዋ ቤተሰቡን ይሰበስባል
3 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ከዓላማው ጋር በሚስማማ መልኩ ነው። በመሆኑም አምላክ “በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ . . . አስተዳደር” አቋቁሟል። ይህ አስተዳደር ይሖዋ፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡሮቹን በሙሉ አንድ ለማድረግ ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። (ኤፌሶን 1:8-10ን አንብብ።) አስተዳደሩ ዓላማውን ዳር ለማድረስ በሁለት ምዕራፎች የተከፈሉ ተግባሮችን ያከናውናል። የመጀመሪያው ምዕራፍ፣ ቅቡዓኑ በኢየሱስ ክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆነው ሥራቸውን ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ እነሱን በሰማይ ለሚኖራቸው ሕይወት ማዘጋጀት ነው። ይህ ምዕራፍ የጀመረው ይሖዋ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙትን መምረጥ በጀመረበት ማለትም በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት ነው። (ሥራ 2:1-4) አምላክ፣ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ቅቡዓኑን ጻድቃን ብሎ የጠራቸው ከመሆኑም በላይ ሕይወት እንደሚገባቸው አድርጎ ይመለከታቸዋል፤ በዚህም የተነሳ ቅቡዓኑ “የአምላክ ልጆች” ተደርገው እንደተቆጠሩ እርግጠኞች ናቸው።—ሮም 3:23, 24፤ 5:1፤ 8:15-17
4 ሁለተኛው ምዕራፍ፣ በክርስቶስ መሲሐዊ መንግሥት በምትተዳደረውና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን መሰብሰብ ነው። ለዚህ ቡድን መሠረት የሚሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ናቸው። (ራእይ 7:9, 13-17፤ 21:1-5) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ደግሞ፣ ከሞት የሚነሱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ቡድን ይቀላቀላሉ። (ራእይ 20:12, 13) ትንሣኤ የሚያገኙ ብዙ ሰዎች መኖራቸው በመካከላችን ምን ያህል አንድነት እንዳለ ለማሳየት ሰፊ አጋጣሚ ይፈጥርልናል! በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የመጨረሻ ፈተና ይጠብቃቸዋል። ታማኝነታቸውን የሚያስመሠክሩ ሁሉ አምላክ በምድር ላይ እንደሚኖሩ ‘ልጆቹ’ አድርጎ ይቆጥራቸዋል።—ሮም 8:21፤ ራእይ 20:7, 8
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ኤፌሶን 3:13) ስለዚህ ለእናንተ ስል እየደረሰብኝ ባለው መከራ የተነሳ ተስፋ እንዳትቆርጡ አደራ እላችኋለሁ፤ ይህ ለእናንተ ክብር ነውና።
የአምላክን ክብር እንዳታገኙ ምንም ነገር እንቅፋት አይሁንባችሁ
15 የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ስንል ፈተናዎችን በጽናት መቋቋማችን ሌሎች አምላክ የሚሰጠውን ክብር እንዲያገኙ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኘው ጉባኤ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ለእናንተ ስል እየደረሰብኝ ባለው መከራ የተነሳ ተስፋ እንዳትቆርጡ አደራ እላችኋለሁ፤ ምክንያቱም ይህ ለእናንተ ክብር ነው።” (ኤፌ. 3:13) ጳውሎስ የደረሰበት መከራ በኤፌሶን ለሚገኙ ክርስቲያኖች “ክብር” የሆነው በምን መንገድ ነው? ጳውሎስ መከራዎች ቢደርሱበትም እነሱን ለማገልገል ሲል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑ የኤፌሶን ወንድሞች፣ ክርስቲያን በመሆናቸው ያገኟቸው መብቶች ምን ያህል ውድና የላቁ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ጳውሎስ መከራ ሲደርስበት ወደኋላ ቢል ኖሮ በኤፌሶን የሚገኙት ክርስቲያኖች ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና፣ አገልግሎታቸው እንዲሁም ተስፋቸው ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችል ነበር። ጳውሎስ በጽናት ማገልገሉ ክርስትና እንዲከበር ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የትኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ነገር እንደሆነ አሳይቷል።
(ኤፌሶን 3:19) እንዲሁም አምላክ በሚሰጠው ሙላት ሁሉ ትሞሉ ዘንድ ከእውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስ ፍቅር እንድታውቁ ነው።
‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’
21 “ማወቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በተግባር፣ በተሞክሮ” ማወቅ የሚል ፍቺ አለው። ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንፈስ ሌሎችን በመርዳት፣ በርኅራኄ ተነሳስተን የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት በመጣርና ከልብ ይቅር በማለት ኢየሱስ ያሳየው ዓይነት ፍቅር የምናሳይ ከሆነ የእሱን ስሜት በትክክል መረዳት እንችላለን። በዚህ መንገድ “ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር” እንዲሁ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ማወቅ እንችላለን። ኢየሱስ የይሖዋ ፍጹም ነጸብራቅ በመሆኑ እሱን እየመሰልን በሄድን መጠን አፍቃሪ ወደሆነው አምላካችን ይበልጥ እየቀረብን እንደምንሄድ መዘንጋት የለብንም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ኤፌሶን 1:1-14) በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ በኤፌሶን ላሉ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ታማኝ የሆኑ ቅዱሳን፦ 2 አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 3 ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ ስለባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ 4 በእሱ ፊት ፍቅር እንድናሳይ እንዲሁም ቅዱሳንና እንከን የለሽ ሆነን እንድንገኝ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ከክርስቶስ ጋር አንድ እንድንሆን መርጦናልና። 5 ደግሞም እሱ እንደወደደና እንደ በጎ ፈቃዱ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የገዛ ራሱ ልጆች አድርጎ ሊወስደን አስቀድሞ ወስኗል፤ 6 ይኸውም በተወደደው ልጁ አማካኝነት በደግነት ለእኛ በሰጠው ክቡር በሆነው ጸጋው የተነሳ እንዲወደስ ነው። 7 በተትረፈረፈ ጸጋው መሠረት በልጁ ደም አማካኝነት ቤዛውን በመክፈሉ ነፃ ወጥተናል፤ አዎ፣ ለበደላችን ይቅርታ አግኝተናል። 8 ጸጋውንም ከጥበብና ከማስተዋል ሁሉ ጋር አትረፍርፎ ሰጥቶናል፤ 9 ይህን ያደረገው የፈቃዱን ቅዱስ ሚስጥር ለእኛ በማሳወቅ ነው። ይህ ሚስጥር ደግሞ እሱ ራሱ ካሰበው ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው፤ 10 ዓላማውም በተወሰኑት ዘመናት ማብቂያ ላይ አንድ አስተዳደር ለማቋቋም ይኸውም ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሰማያት የሚሆኑ ነገሮችንና በምድር የሚሆኑ ነገሮችን በክርስቶስ አንድ ላይ ለመሰብሰብ ነው። አዎ፣ በእሱ አማካኝነት ሁሉም ነገሮች ይሰበሰባሉ፤ 11 እኛም ከእሱ ጋር አንድነት ያለን ሲሆን ወራሾች እንድንሆንም ተመርጠናል፤ ምክንያቱም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሁሉንም ነገር በወሰነው መንገድ የሚያከናውነው እሱ ከዓላማው ጋር በሚስማማ ሁኔታ አስቀድሞ መርጦናል፤ 12 ይህም የሆነው በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ አምላክን ከፍ ከፍ እንድናደርግና እንድናወድስ ነው። 13 ይሁንና እናንተም የእውነትን ቃል ማለትም ስለ መዳናችሁ የሚገልጸውን ምሥራች ከሰማችሁ በኋላ በእሱ ተስፋ አድርጋችኋል። ካመናችሁ በኋላ በእሱ አማካኝነት፣ ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል፤ 14 ይህም ለአምላክ ታላቅ ምስጋና ያስገኝ ዘንድ የራሱ ንብረት የሆኑትን በቤዛ አማካኝነት ነፃ ለማውጣት ለውርሻችን አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ ነው።
ከሰኔ 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኤፌሶን 4-6
“ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ”
(ኤፌሶን 6:11-13) የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ፤ 12 ምክንያቱም የምንታገለው ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከመንግሥታት፣ ከሥልጣናት፣ ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዢዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው። 13 ስለሆነም ክፉው ቀን በሚመጣበት ጊዜ መቋቋም እንድትችሉና ሁሉንም ነገር ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ አንሱ።
ወጣቶች—ዲያብሎስን ተቋቋሙ
ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያኖችን ሕይወት በጨበጣ ውጊያ ላይ ካሉ ወታደሮች ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። እርግጥ ነው፣ ይህ ሲባል ቃል በቃል እንዋጋለን ማለት አይደለም፤ ውጊያው መንፈሳዊ ነው። ያም ቢሆን ጠላቶቻችን በእውን ያሉ አካላት ናቸው። ሰይጣንና አጋንንቱ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያካበቱ ተዋጊዎች ናቸው። በመሆኑም በውጊያው ለማሸነፍ ጨርሶ ተስፋ የሌለን ይመስል ይሆናል። በተለይ ደግሞ ወጣት ክርስቲያኖች በቀላሉ የሚሸነፉ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ታዲያ ወጣቶች ከሰው በላይ አቅም ካላቸው ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውጊያ አሸናፊ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ወጣቶች በውጊያው ማሸነፍ ይችላሉ፤ ደግሞም እያሸነፉ ነው! እንዲያሸንፉ የረዳቸው ምንድን ነው? ‘ከጌታ ኃይል’ ማግኘታቸው ነው። ከዚህም ሌላ ለጦርነት ታጥቀዋል። ጥሩ ሥልጠና እንዳገኙ ወታደሮች ሁሉ እነዚህ ወጣቶችም “ሙሉ የጦር ትጥቅ [ለብሰዋል]።”—ኤፌሶን 6:10-12ን አንብብ።
(ኤፌሶን 6:14, 15) እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁና የጽድቅን ጥሩር ለብሳችሁ ጸንታችሁ ቁሙ፤ 15 እንዲሁም የሰላምን ምሥራች ለማወጅ ዝግጁ በመሆን እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ።
ወጣቶች—ዲያብሎስን ተቋቋሙ
4 በተመሳሳይም ከአምላክ ቃል የምንማራቸው እውነቶች የሐሰት ትምህርቶች ከሚያስከትሉት መንፈሳዊ ጉዳት ይጠብቁናል። (ዮሐ. 8:31, 32፤ 1 ዮሐ. 4:1) በተጨማሪም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ይበልጥ ፍቅር ባዳበርን መጠን ‘ጥሩራችንን’ መሸከም ይኸውም በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች መመራት የበለጠ ቀላል ይሆንልናል። (መዝ. 111:7, 8፤ 1 ዮሐ. 5:3) ከዚህም ሌላ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶች ግልጽ ሲሆኑልን፣ ተቃዋሚዎች በእውነት ላይ ለሚሰነዝሩት ጥቃት በልበ ሙሉነት መከላከያ ማቅረብ እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:15
7 ወታደሮቹ የሚለብሱት ጥሩር፣ ምሳሌያዊውን ልባችንን ከጉዳት ከሚጠብቁት የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ምሳሌ 4:23) አንድ ወታደር ከብረት የተሠራ ጥሩሩን አውልቆ መናኛ በሆነ ንጥረ ነገር የተሠራ ጥሩር እንደማያደርግ የታወቀ ነው፤ በተመሳሳይ እኛም ትክክል የሆነውን ነገር በተመለከተ የይሖዋን መሥፈርቶች ትተን በራሳችን መሥፈርቶች ለመመራት ፈጽሞ አንፈልግም። የሰው ልጆች፣ ልባችንን ለመጠበቅ የሚያስችል የማመዛዘን ችሎታ ጨርሶ የለንም። (ምሳሌ 3:5, 6) በመሆኑም ይሖዋ የሰጠንን ‘የብረት ጥሩር’ ልባችንን በሚገባ በሚከልል መንገድ መታጠቃችንን አዘውትረን ማረጋገጥ ይኖርብናል።
10 የሮም ወታደሮች ይህን ጫማ የሚያደርጉት ለጦርነት ዝግጁ ለመሆን ነው፤ ክርስቲያኖች ግን ምሳሌያዊውን ጫማ ማድረጋቸው የሰላምን መልእክት ለማድረስ መዘጋጀታቸውን ያመለክታል። (ኢሳ. 52:7፤ ሮም 10:15) እርግጥ ነው፣ አጋጣሚውን በምናገኝበት ጊዜ ምሥራቹን መናገር ድፍረት ይጠይቃል። የ20 ዓመቱ ቦ እንዲህ ብሏል፦ “አብረውኝ ለሚማሩ ልጆች መስበክ ያስፈራኝ ነበር። የምፈራው ምሥራቹን መናገር ስለሚያሳፍረኝ ነበር። መለስ ብዬ ሳስበው ግን ምኑ እንዳሳፈረኝ አይገባኝም። አሁን ለእኩዮቼ መመሥከር ያስደስተኛል።”
(ኤፌሶን 6:16, 17) ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን የምትችሉበትን ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ። 17 በተጨማሪም የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤ እንዲሁም የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ያዙ፤
ወጣቶች—ዲያብሎስን ተቋቋሙ
13 ሰይጣን ከሚያስወነጭፋቸው ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ መካከል ስለ ይሖዋ የሚነገሩ ውሸቶች ይገኙበታል፤ ሰይጣን ይሖዋ እንደማይወዳችሁና ማንም ስለ እናንተ ግድ እንደሌለው ሊያሳምናችሁ ይፈልጋል። የአሥራ ዘጠኝ ዓመቷን ኢዳን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ኢዳ ዋጋ ቢስ እንደሆነች ይሰማታል። “ይሖዋ እንደማይቀርበኝና ወዳጄ መሆን እንደማይፈልግ ብዙ ጊዜ ይሰማኛል” ብላለች። ኢዳ፣ ሰይጣን የሚሰነዝረውን ይህን ጥቃት የምትቋቋመው እንዴት ነው? እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ስብሰባዎች እምነቴን በጣም ያጠናክሩልኛል። ማንም ሰው እኔ የምሰጠውን ሐሳብ መስማት እንደማይፈልግ ስለማስብ በስብሰባዎች ላይ ምንም መልስ አልመልስም ነበር። አሁን ግን ለስብሰባዎች እዘጋጃለሁ፤ እንዲሁም ሁለት ወይም ሦስት መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ። ይህን ማድረግ ከባድ ቢሆንም መልስ ስመልስ በጣም ደስ ይለኛል። ወንድሞችና እህቶችም በጣም ያበረታቱኛል። ሁልጊዜ ከስብሰባ ስመለስ፣ ይሖዋ እንደሚወደኝ ይሰማኛል።”
16 የራስ ቁር የወታደሩን አንጎል ከጉዳት እንደሚጠብቅለት ሁሉ ‘የመዳን ተስፋችንም’ አእምሯችንን ማለትም የማሰብ ችሎታችንን ከጉዳት ይጠብቅልናል። (1 ተሰ. 5:8፤ ምሳሌ 3:21) ተስፋ፣ አምላክ በገባልን ቃል ላይ እንድናተኩርና ለሚደርሱብን ችግሮች ተገቢውን አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። (መዝ. 27:1, 14፤ ሥራ 24:15) ይሁን እንጂ ‘የራስ ቁራችን’ ከአደጋ እንዲከላከልልን ከፈለግን አውልቀን በእጃችን ከመያዝ ይልቅ በጭንቅላታችን ላይ ልናጠልቀው ይገባል።
20 ጳውሎስ የአምላክን ቃል ከሰይፍ ጋር አመሳስሎታል፤ ይህን ሰይፍ ያገኘነው ከይሖዋ ነው። ይሁንና ለምናምንባቸው ነገሮች ጥብቅና ለመቆምም ሆነ አስተሳሰባችንን ለማስተካከል የአምላክን ቃል ጥሩ አድርገን የመጠቀም ችሎታ ልናዳብር ይገባል። (2 ቆሮ. 10:4, 5፤ 2 ጢሞ. 2:15) ታዲያ ችሎታችሁን ማሻሻል የምትችሉት እንዴት ነው? የ21 ዓመቱ ሴባስትያን እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ከእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ አንድ ቁጥር መርጬ የመጻፍ ልማድ አለኝ። በዚህ መንገድ፣ የምወዳቸውን ጥቅሶች አንድ ላይ አሰባስባለሁ። ይህን ማድረጌ የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ለመረዳት እንዳስቻለኝ ይሰማኛል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ፣ በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ለመርዳት የምጠቀምባቸውን ጥቅሶች ለማግኘት እሞክራለሁ። ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዳለንና እነሱን ለመርዳት ልባዊ ጥረት እያደረግን እንደሆነ ሲመለከቱ መልእክቱን እንደሚቀበሉ አስተውያለሁ።”
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ኤፌሶን 4:30) በተጨማሪም በቤዛው ነፃ ለምትወጡበት ቀን የታተማችሁበትን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ።
it-1 1128 አን. 3
ቅድስና
መንፈስ ቅዱስ። በሥራ ላይ ያለው የይሖዋ ኃይል ወይም መንፈስ በእሱ ቁጥጥር ሥር ሲሆን ምንጊዜም የሚያከናውነው የእሱን ዓላማ ነው። የአምላክ መንፈስ ንጹሕ፣ የጠራ፣ ቅዱስ እንዲሁም አምላክ ለሚያከናውናቸው መልካም ነገሮች የተለየ ኃይል ነው። በመሆኑም “ቅዱስ መንፈስ” እና “መንፈስ ቅዱስ” ተብሎ ተጠርቷል። (መዝ 51:11፤ ሉቃስ 11:13፤ ሮም 1:4፤ ኤፌ 1:13) ይህ መንፈስ በአንድ ሰው ላይ በሚሠራበት ጊዜ፣ ግለሰቡ ቅዱስ ወይም ንጹሕ እንዲሆን የሚገፋፋ ኃይል ነው። ማንኛውንም ርኩስ የሆነ ወይም የተሳሳተ ድርጊት የሚፈጽም ሰው ይህን መንፈስ ሊቃወም ወይም ‘ሊያሳዝን’ ይችላል። (ኤፌ 4:30) መንፈስ ቅዱስ የራሱ ማንነት ያለው አካል ባይሆንም ቅዱስ የሆነው አምላክ ማንነት መገለጫ ነው፤ ከዚህ አንጻር ‘ያዝናል’ ሊባል ይችላል። ማንኛውንም መጥፎ ድርጊት መፈጸም “የመንፈስን እሳት” ሊያጠፋ ይችላል። (1ተሰ 5:19) አንድ ሰው እንዲህ ያለውን ድርጊት መፈጸሙን ከቀጠለ ደግሞ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ‘እንዲያዝን’ ሊያደርግ ይችላል፤ በዚህም የተነሳ አምላክ በዓመፀኛው ሰው ላይ ጠላት ሊሆንበት ይችላል። (ኢሳ 63:10) መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝን ሰው፣ የአምላክን መንፈስ እስከ መሳደብ ሊደርስ ይችላል፤ እንዲህ ያለውን ኃጢአት የፈጸመ ግለሰብ ደግሞ በዚህም ሆነ በሚመጣው ሥርዓት ይቅርታ እንደማይደረግለት ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል።—ማቴ 12:31, 32፤ ማር 3:28-30
(ኤፌሶን 5:5) እንደምታውቁትና በሚገባ እንደምትገነዘቡት ሴሰኛ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ማለትም ጣዖት አምላኪ የሆነ ማንኛውም ሰው በክርስቶስና በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ የለውም።
‘ከስግብግብነት ሁሉ ራሳችሁን ጠብቁ’
8 አንድ መዝገበ ቃላት ስግብግብነት የሚለውን ቃል “ሀብት ወይም ንብረት አሊያም የሌላን ሰው ንብረት ለማግኘት ከመጠን በላይ መመኘት” በማለት ፈቶታል። ስግብግብነት የማይረካ ፍላጎትን፣ ስስታምነትንና ምናልባትም የሌሎችን ንብረት መመኘትን የሚያካትት ሲሆን እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያለው ሰው የሚመኘው ነገር አስፈልጎት ላይሆን ይችላል፤ እንዲህ ማድረጉ በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖም አያስብም። ስግብግብ የሆነ ሰው አንድ ነገር ለማግኘት ያለው ፍላጎት አስተሳሰቡንና ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረው ስለሚፈቅድ ይህ ነገር አምላኩ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስስታም የሆነ ሰው ከጣዖት አምላኪ ጋር እኩል መሆኑን እንደገለጸ ልብ በል፤ እንዲህ ያለው ሰው ደግሞ የአምላክን መንግሥት አይወርስም።—ኤፌሶን 5:5፤ ቈላስይስ 3:5
ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የምትችለው እንዴት ነው?
መሠረታዊው ችግር የገንዘብ ፍላጎታችንን መቆጣጠር አለመቻላችን ነው። ያከማቸነው ገንዘብም ሆነ ቁሳዊ ንብረት ፍላጎታችንን ያሟሉልናል ወይስ ፍላጎቶቻችን የገንዘብ ባሪያዎች ያደርጉናል? ጳውሎስ ‘ስግብግብ ሰው ጣዖትን የሚያመልክ ነው’ ብሎ የተናገረው ለዚህ ነው። (ኤፌሶን 5:5) እንደ እውነቱ ከሆነ ለአንድ ነገር መስገብገብ ማለት ፈቃዳችንን ለዛ ነገር ማስገዛት ወይም በሌላ አባባል ጌታችንና አምላካችን ማድረግ እንዲሁም ያንን ነገር ማገልገል ማለት ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን አምላክ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል።—ዘጸአት 20:3
በተጨማሪም ስግብግብ መሆናችን አምላክ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን በገባው ቃል ላይ ትምክህት እንደሌለን ያሳያል። (ማቴዎስ 6:33) ስለዚህ ስግብግብነት ከአምላክ እንድንርቅ ያደርገናል። በዚህ መሠረት ስግብግብነት “የጣዖት አምልኮ” ነው። ጳውሎስ ከዚህ እንድንርቅ ግልጽ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ያለ ምክንያት አይደለም!
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ኤፌሶን 4:17-32) ስለዚህ አሕዛብ በአእምሯቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ እናንተም ከእንግዲህ እንዳትመላለሱ በጌታ እናገራለሁ እንዲሁም እመሠክራለሁ። 18 እነሱ በውስጣቸው ካለው ድንቁርናና ከልባቸው መደንደን የተነሳ አእምሯቸው ጨልሟል፤ እንዲሁም ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት ርቀዋል። 19 የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ዓይን ላወጣ ምግባር አሳልፈው ሰጥተዋል። 20 እናንተ ግን ክርስቶስ እንዲህ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ 21 ይህ ሊሆን የሚችለው በእርግጥ ኢየሱስ ካስተማረው እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን ከሰማችሁና ከእሱ ከተማራችሁ ነው። 22 ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውንና አታላይ በሆነው ምኞቱ እየተበላሸ የሚሄደውን አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል። 23 ደግሞም አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ፤ 24 እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል። 25 ስለዚህ አሁን አታላይነትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ ምክንያቱም ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን። 26 ተቆጡ፤ ሆኖም ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ 27 ዲያብሎስ አጋጣሚ እንዲያገኝ አታድርጉ። 28 የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ ለተቸገረ ሰው የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ። 29 እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል ብቻ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ። 30 በተጨማሪም በቤዛው ነፃ ለምትወጡበት ቀን የታተማችሁበትን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ። 31 የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ። 32 ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።
ከሰኔ 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ፊልጵስዩስ 1-4
“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ”
(ፊልጵስዩስ 4:6) ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤
“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም”
10 ስለ ምንም ነገር እንዳንጨነቅ እንዲሁም “የአምላክ ሰላም” እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል? ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ የጭንቀት ማርከሻው ጸሎት እንደሆነ ያሳያል። በመሆኑም ምንም ነገር ሲያስጨንቀን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7ን አንብብ።) ይሖዋ እንደሚያስብልህ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ወደ እሱ ጸልይ። ከይሖዋ ያገኘኻቸውን በረከቶች በማስታወስ ጸሎትህን “ከምስጋና ጋር” አቅርብ። ይሖዋ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” እንደሚችል ማስታወሳችን በእሱ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር ያደርጋል።—ኤፌ. 3:20
(ፊልጵስዩስ 4:7) ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።
“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም”
7 በፊልጵስዩስ የነበሩት ወንድሞች ጳውሎስ የጻፈላቸውን ደብዳቤ ሲያነቡ ጳውሎስን ስላጋጠመው ሁኔታ እንዲሁም ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቁት መንገድ እንዴት እንደረዳው አስታውሰው መሆን አለበት። ጳውሎስ ሊያስተምራቸው የፈለገው ነጥብ ምን ነበር? በአጭር አነጋገር፣ ‘አትጨነቁ’ እያላቸው ነበር። ወደ ይሖዋ ከጸለዩ የአምላክን ሰላም እንደሚያገኙ ገልጾላቸዋል። ይሁንና የአምላክ ሰላም “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” እንደሆነ ልብ በል። ይህ ምን ማለት ነው? አንዳንድ ተርጓሚዎች ይህን አገላለጽ “ከምናልመው ሁሉ በላይ” አሊያም “ከሰዎች ግምት ሁሉ የላቀ” ብለው ተርጉመውታል። ጳውሎስ “የአምላክ ሰላም” በአእምሯችን ልናስበው ከምንችለው ሁሉ በላይ አስገራሚ እንደሆነ መናገሩ ነበር። በመሆኑም በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ ችግሮቻችንን መወጣት የምንችልበት ምንም መንገድ የሌለ ቢመስልም ይሖዋ ግን መውጫ መንገዱን የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ ፈጽሞ ያልጠበቅነውን ነገር ሊያደርግ ይችላል።—2 ጴጥሮስ 2:9ን አንብብ።
“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም”
16 ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክን ሰላም’ ማግኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:7) “ይጠብቃል” ተብሎ የተተረጎመው ቃል መጀመሪያ ላይ በተጻፈበት ቋንቋ፣ አንድን የታጠረ ከተማ እንዲጠብቁ የተመደቡ ወታደሮችን የሚያመለክት ከውትድርና ጋር በተያያዘ የሚሠራበት ቃል ነው። ፊልጵስዩስ እንዲህ ባለ መንገድ የምትጠበቅ ከተማ ነበረች። የፊልጵስዩስ ነዋሪዎች ወታደሮቹ የከተማዋን በሮች እንደሚጠብቁ ስለሚያውቁ ያለምንም ስጋት ተኝተው ያድራሉ። እኛም በተመሳሳይ “የአምላክ ሰላም” ሲኖረን ልባችንና አእምሯችን ከስጋት ነፃ ይሆናል። ይሖዋ እንደሚያስብልንና እንዲሳካልን እንደሚፈልግ እናውቃለን። (1 ጴጥ. 5:10) ይህን ማወቃችን ከልክ በላይ በጭንቀት አሊያም በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳንዋጥ ይጠብቀናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ፊልጵስዩስ 2:17) ይሁንና በእምነት ተነሳስታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና ቅዱስ አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ መባ ብፈስ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እንዲሁም ከሁላችሁም ጋር ሐሴት አደርጋለሁ።
it-2 528 አን. 5
መባዎች
የመጠጥ መባዎች። የመጠጥ መባዎች ከአብዛኞቹ ሌሎች መባዎች ጋር አብረው ይቀርቡ ነበር፤ በተለይም እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር መኖር ከጀመሩ በኋላ እንዲህ ያለ መባ ያቀርቡ ነበር። (ዘኁ 15:2, 5, 8-10) መባ ሆኖ የሚቀርበው የወይን ጠጅ (‘የሚያሰክር መጠጥ’) ሲሆን በመሠዊያው ላይ ይፈስ ነበር። (ዘኁ 28:7, 14፤ ከዘፀ 30:9 እና ከዘኁ 15:10 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ “በእምነት ተነሳስታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና ቅዱስ አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ መባ ብፈስ . . . ደስ ይለኛል” ብሏል። ጳውሎስ እዚህ ላይ የመጠጥ መባን በምሳሌያዊ መንገድ የተጠቀመው ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ጥቅም ሲል ራሱን ሳይቆጥብ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ለመግለጽ ነው። (ፊልጵ 2:17) ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ደግሞ “እኔ እንደ መጠጥ መባ እየፈሰስኩ ነውና፤ ደግሞም ነፃ የምለቀቅበት ጊዜ በጣም ቀርቧል” ሲል ለጢሞቴዎስ ጽፏል።—2ጢሞ 4:6
(ፊልጵስዩስ 3:11) ደግሞም በተቻለ መጠን መጀመሪያ ላይ ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል መሆን ነው።
‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ በመከናወን ላይ ነው!
5 ቀጥሎም፣ በመንፈስ የተቀቡት ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመተባበር ትንሣኤ አግኝተው ሰማያዊ ክብር መጎናጸፍ ይኖርባቸዋል፤ በዚያም ‘ለዘላለም ከጌታ ጋር ይሆናሉ።’ (ገላትያ 6:16፤ 1 ተሰሎንቄ 4:17) ይህ ክንውን ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ በመባል ይታወቃል። (ራእይ 20:6) ይህ ትንሣኤ ሲጠናቀቅ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት መነሳት የሚጀምሩበት ጊዜ ይከተላል። በዚህም የተነሳ፣ ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ‘የመጀመሪያውን ትንሣኤ’ ትኩረት ሰጥተን መመርመራችን ተገቢ ነው። የመጀመሪያው ትንሣኤ ምን ዓይነት ነው? የሚፈጸመውስ መቼ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ፊልጵስዩስ 4:10-23) አሁን ለእኔ እንደገና ማሰብ በመጀመራችሁ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል። ስለ እኔ ደህንነት ታስቡ የነበረ ቢሆንም ይህን በተግባር ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ አላገኛችሁም። 11 ይህን ስል እንደተቸገርኩ መናገሬ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ። 12 በትንሽ ነገር እንዴት መኖር እንደሚቻልም ሆነ ብዙ አግኝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻል አውቃለሁ። በማንኛውም ነገርና በሁሉም ሁኔታ ጠግቦም ሆነ ተርቦ፣ ብዙ አግኝቶም ሆነ አጥቶ መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬአለሁ። 13 ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ። 14 የሆነ ሆኖ የመከራዬ ተካፋዮች በመሆናችሁ መልካም አድርጋችኋል። 15 እንዲያውም እናንተ የፊልጵስዩስ ወንድሞች፣ ምሥራቹን መጀመሪያ ከሰማችሁ በኋላ ከመቄዶንያ ስወጣ በመስጠትም ሆነ በመቀበል ረገድ ከእናንተ በስተቀር ከእኔ ጋር የተባበረ አንድም ጉባኤ እንዳልነበረ ታውቃላችሁ፤ 16 በተሰሎንቄ በነበርኩበት ጊዜ የሚያስፈልገኝን ነገር ከአንዴም ሁለቴ ልካችሁልኛልና። 17 ይህን ስል ስጦታ ለማግኘት በመፈለግ ሳይሆን እናንተ የምታገኙት ጥቅም እንዲጨምር የሚያደርገውን ፍሬ ለማየት በመፈለግ ነው። 18 ይሁን እንጂ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ፣ እንዲያውም ከሚያስፈልገኝ በላይ አለኝ። የላካችሁልኝን ከአፍሮዲጡ ስለተቀበልኩ ሞልቶ ተትረፍርፎልኛል፤ ይህም ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ፣ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕትና አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው። 19 በአጸፋው ደግሞ አምላኬ እንደ ታላቅ ብልጽግናው መጠን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አሟልቶ ይሰጣችኋል። 20 እንግዲህ ለአምላካችንና ለአባታችን ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። 21 ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታዬን አድርሱልኝ። ከእኔ ጋር ያሉ ወንድሞች ሰላምታ ልከውላችኋል። 22 ቅዱሳን ሁሉ በተለይ ደግሞ ከቄሳር ቤተሰብ የሆኑት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 23 የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን።