የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች፣ ሐምሌ-መስከረም 2021
ከሐምሌ 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 11–12
“ይሖዋ በምን መንገድ እንዲመለክ ይፈልጋል?”
it-2 1007 አን. 4
ነፍስ
በሙሉ ነፍስ ማገልገል። ቀደም ሲል እንዳየነው፣ “ነፍስ” የአንድን ሰው ሁለንተና ያመለክታል። አንዳንድ ጥቅሶች ግን ይሖዋን ‘በሙሉ ልባችን እና በሙሉ ነፍሳችን’ እንድንፈልገው፣ እንድንወደውና እንድናገለግለው ይመክሩናል (ዘዳ 4:29፤ 11:13, 18)፤ ዘዳግም 6:5 ደግሞ “አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” ይላል። ኢየሱስም በሙሉ ነፍሳችንና በሙሉ ኃይላችን ብቻ ሳይሆን ‘በሙሉ አእምሯችንም’ ይሖዋን ማገልገላችን አስፈላጊ እንደሆነ ነግሮናል። (ማር 12:30፤ ሉቃስ 10:27) ይህ አንድ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል፤ ነፍስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሚያካትት ከሆነ ከነፍስ ጋር አብረው የተጠቀሱት ለምንድን ነው? ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ለማስረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ሰው ራሱን (ነፍሱን) ለሌላ ሰው በባርነት ሊሸጥ ይችላል፤ እንዲህ ሲያደርግ የዚያ ሰው ንብረት ይሆናል። ያም ቢሆን ጌታውን በሙሉ ልቡ ማለትም እሱን ለማስደሰት ባለው ልባዊ ፍላጎት ተነሳስቶ ላያገለግለው ይችላል፤ ይህ ደግሞ ሙሉ ጉልበቱን ወይም የማሰብ ችሎታውን ተጠቅሞ ጌታውን እንዳያገለግል ያደርገዋል። (ከኤፌ 6:5፤ ቆላ 3:22 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም እነዚህ ነገሮች ከነፍስ ጋር አብረው የተጠቀሱት ለይሖዋና ለልጁ በምናቀርበው አገልግሎት ትኩረት እንድንሰጣቸው ለማድረግ ታስቦ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም እኛ የይሖዋ ንብረት ነን፤ የተገዛነውም በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። ለአምላክ የምናቀርበው ‘የሙሉ ነፍስ’ አገልግሎት ሁለንተናችንን ይነካል፤ የምናስቀረው የሰውነት ክፍል፣ ችሎታ ወይም ፍላጎት አይኖርም ማለት ነው።—ከማቴ 5:28-30፤ ሉቃስ 21:34-36፤ ኤፌ 6:6-9፤ ፊልጵ 3:19፤ ቆላ 3:23, 24 ጋር አወዳድር።
it-1 84 አን. 3
መሠዊያ
እስራኤላውያን አረማዊ አምልኮ የሚቀርብባቸውን መሠዊያዎች በሙሉ እንዲያፈርሱ ተነግሯቸው ነበር፤ ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ መሠዊያዎች አጠገብ ይቆሙ የነበሩ ማምለኪያ አምዶችና ግንዶችንም ማስወገድ ነበረባቸው። (ዘፀ 34:13፤ ዘዳ 7:5, 6፤ 12:1-3) እነዚህን መሠዊያዎች ለራሳቸው አስመስለው መሥራትም ሆነ ከነአናውያን ያደርጉት እንደነበረው ልጆቻቸውን በእሳት መሠዋት የለባቸውም። (ዘዳ 12:30, 31፤ 16:21) መሠዊያዎች ከማብዛት ይልቅ ለእውነተኛው አምላክ አምልኮ የሚያቀርቡበት አንድ መሠዊያ ብቻ እንዲኖራቸው ተነግሯቸዋል፤ ይህ መሠዊያ የሚቆመውም ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ነው። (ዘዳ 12:2-6, 13, 14, 27፤ ይህን ሁኔታ በባቢሎን ከነበረው ጋር አነጻጽር፤ ኢሽታር ለተባለችው አምላክ ብቻ 180 መሠዊያዎች ተሠርተው ነበር።) እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ ካልተጠረቡ ድንጋዮች መሠዊያ እንዲሠሩ ታዘዋል (ዘዳ 27:4-8)፤ በዚህም መሠረት ኢያሱ በኤባል ተራራ ላይ መሠዊያ ሠራ። (ኢያሱ 8:30-32) ምድሪቱ ከተከፋፈለች በኋላ የሮቤል እና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ዮርዳኖስ አጠገብ አጠያያቂ መሠዊያ ሠርተው ነበር፤ ይህ መሠዊያ በሌሎቹ ነገዶች ዘንድ ለጊዜው ውዝግብ አስነስቶ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን መሠዊያው ክህደት እንደፈጸሙ የሚያሳይ ሳይሆን ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ስለ መሆኑ ምሥክር የሚሆን መታሰቢያ እንደሆነ ታወቀ።—ኢያሱ 22:10-34
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 925-926
ገሪዛን ተራራ
ሙሴ በሰጠው መመሪያ መሠረት ሁሉም የእስራኤል ነገዶች በኢያሱ አመራር ሥር በገሪዛን እና በኤባል ተራሮች ፊት ለፊት ተሰበሰቡ፤ ይህ የሆነው ጋይን ድል ካደረጉ ብዙም ሳይቆይ ነበር። ሕዝቡ እዚያ ተሰብስበው፣ ይሖዋን ከታዘዙ የሚያገኙት በረከት፣ በሱ ላይ ካመፁ ደግሞ የሚደርስባቸው ርግማን ተነበበላቸው። የስምዖን፣ የሌዊ፣ የይሁዳ፣ የይሳኮር፣ የዮሴፍና የቢንያም ነገዶች በገሪዛን ተራራ ፊት ለፊት ቆሙ። ሌዋውያኑ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው ሸለቆው መሃል ቆሙ፤ የቀሩት ስድስት ነገዶች ደግሞ በኤባል ተራራ ፊት ለፊት ቆሙ። (ዘዳ 11:29, 30፤ 27:11-13፤ ኢያሱ 8:28-35) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ በረከቶቹ ወደ ገሪዛን ተራራ አቅጣጫ ሲነበቡ በዚያ የቆሙት ነገዶች ምላሽ ሰጡ፤ ርግማኖቹ ወደ ኤባል ተራራ አቅጣጫ ሲነበቡ ደግሞ የቀሩት ነገዶች ምላሽ ሰጡ። በረከቶቹ ወደ ገሪዛን ተራራ አቅጣጫ የተነበቡት ደረቅና በአብዛኛው ጠፍ ከሆነው ከኤባል ተራራ ጋር ሲነጻጸር ገሪዛን ተራራ ይበልጥ ውብና ለምለም ስለሆነ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። “ሴቶችንና ልጆችን እንዲሁም በመካከላቸው የሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎችን ጨምሮ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት” ሕጉ ጮክ ተብሎ ተነበበ። (ኢያሱ 8:35) በዚያ የተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ የተነበበውን ነገር መስማት ችሎ ነበር። ሰው ሁሉ እንዲሰማ በተወሰነ መጠንም ቢሆን አስተዋጽኦ ያደረገው፣ የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ድምፅ ለማስተጋባት ስለሚያመች ሊሆን ይችላል።
ከሐምሌ 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 13–15
“ሕጉ፣ ይሖዋ ለድሆች ያለውን አሳቢነት የሚያሳየው እንዴት ነው?”
it-2 1110 አን. 3
አሥራት
እስራኤላውያን ተጨማሪ አሥራት ማለትም ሁለተኛ አሥራት ያወጡ ነበር፤ በየዓመቱ ይህን አሥራት የሚያወጡት የክህነት ሥርዓቱን ለመደገፍ ሳይሆን ለሌላ ዓላማ እንዲውል የነበረ ይመስላል፤ በእርግጥ ሌዋውያንም ከዚህ አሥራት ተካፋዮች ነበሩ። በአብዛኛው ይህ አሥራት የሚውለው እስራኤላውያን ቤተሰቦች ዓመታዊ በዓላትን ለማክበር በሚሰበሰቡበት ወቅት ነበር፤ በእነዚህ ወቅቶች ከዚህ አሥራት ይጠቀሙ ወይም ይመገቡ ነበር። አንዳንድ ቤተሰቦች የሚኖሩት ከኢየሩሳሌም በጣም ርቀው ሊሆን ይችላል፤ አሥራታቸውን ወደዚያ ማጓጓዝ ስለሚከብድ ምርቱን ወደ ገንዘብ መቀየር ይፈቀድላቸዋል፤ ከዚያም ገንዘቡ፣ ቤተሰቡ ለቅዱስ ስብሰባ ኢየሩሳሌም በሚገኝበት ወቅት ወጪውን ለመሸፈን ያገለግላል። (ዘዳ 12:4-7, 11, 17, 18፤ 14:22-27) በሦስተኛውና በስድስተኛው ዓመት (ከአንድ የሰንበት ዓመት እስከ ሌላ የሰንበት ዓመት ባለው ሰባት ዓመት ውስጥ ማለት ነው) ይህ አሥራት የሚውለው በዓመታዊ በዓላት ወቅት ወጪ ለመሸፈን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በከተማው ውስጥ ያሉ ሌዋውያን፣ የባዕድ አገር ሰዎች፣ መበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች እንዲጠቀሙበት ይደረጋል።—ዘዳ 14:28, 29፤ 26:12
it-2 833
የሰንበት ዓመት
የሰንበት ዓመት “ዕዳ የሚሰረዝበት” ወይም የሚተውበት ዓመት ተብሎ ተጠርቷል። (ዘዳ 15:9፤ 31:10) በዚህ ዓመት ምድራቸው ሙሉ በሙሉ ያርፋል፤ ሳይታረስ እንዲሁ ይተዋል። (ዘፀ 23:11) በተጨማሪም ዕዳ የሚተውበት ወይም የሚሰረዝበት ዓመት ነው። ዕዳው የሚሰረዘው “ለይሖዋ ሲባል” ነው። ሁሉም ተንታኞች የሚስማሙበት ሐሳብ ባይሆንም አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ዕዳው እስከ ወዲያኛው እንደማይሰረዝ ይናገራሉ፤ ከዚህ ይልቅ በዚህ ዓመት ገበሬው ምንም ዓይነት ገቢ ስለማይኖረው አበዳሪው ዕዳዬን ክፈለኝ ብሎ አያስገድደውም ይላሉ፤ በእርግጥ እስራኤላውያን አበዳሪዎች የባዕድ አገር ሰው ዕዳውን እንዲከፍል ማስገደድ ይችላሉ። (ዘዳ 15:1-3) አንዳንድ ረቢዎች፣ አንድ ሰው የተቸገረ ወንድሙን ለመርዳት ብሎ የገባው ዕዳ ቢሰረዝለትም ለንግድ ሥራ ብሎ የወሰደው ብድር አይሰረዝለትም የሚል አመለካከት አላቸው። እነዚህ ረቢዎች እንደሚሉት ከሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓመተ ምሕረት፣ ሂሌል አበዳሪው ፍርድ ቤት ቀርቦ ዕዳው እንዳይሰረዝ ወይም እንዲጸና ማድረግ የሚችልበት ሕጋዊ አሠራር ቀርጾ ነበር።
it-2 978 አን. 6
ባሪያ
በባሪያና በጌታ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከቱ ሕጎች። በእስራኤላውያን መካከል አንድ ዕብራዊ ባሪያ ያለው ቦታ የባዕድ አገር ሰው ወይም ሰፋሪ የሆነ ባሪያ ከሚኖረው ቦታ የተለየ ነው። ዕብራዊ ያልሆነ አንድ ባሪያ ለዘለቄታው የጌታው ንብረት ሆኖ ይቀጥላል፤ አልፎ ተርፎም ከአባት ወደ ልጅ ሊተላለፍ ይችላል (ዘሌ 25:44-46)፤ ዕብራዊ የሆነ ባሪያ ግን ለባርነት ከተሸጠ በሰባተኛው ዓመት ወይም በኢዮቤልዩ ዓመት (ማለትም ከሁለቱ ቀድሞ በመጣው ዓመት) ነፃ ይለቀቃል። አንድ ዕብራዊ ባሪያ ጌታውን በሚያገለግልባቸው ዓመታት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ሊያዝ ይገባል። (ዘፀ 21:2፤ ዘሌ 25:10፤ ዘዳ 15:12) አንድ ዕብራዊ ራሱን ለባዕድ አገር ሰው ወይም ሰፋሪ ለባርነት ቢሸጥ ራሱን በራሱ ሊዋጅ ይችላል፤ ወይም የመዋጀት መብት ያለው ሌላ ሰው ሊዋጀው ይችላል። የሚዋጅበት ዋጋ የሚወሰነው እስከ ኢዮቤልዩ ወይም እስከ ሰባተኛ ዓመቱ (ለባርነት ከተሸጠበት ጊዜ አንስቶ ሲቆጠር ማለት ነው) የሚቀሩትን ዓመታት በማስላት ነው። (ዘሌ 25:47-52፤ ዘዳ 15:12) ጌታው ዕብራዊ ባሪያውን ነፃ ሲለቀው ለመቋቋሚያ የሚሆነው ስጦታ እንዲሰጠው ይጠበቅበታል። (ዘዳ 15:13-15) ሰውየው ለባርነት ሲሸጥ ከሚስቱ ጋር መጥቶ ከነበረ እስከነሚስቱ ነፃ ይለቀቃል። ባሪያ በነበረበት ወቅት ጌታው ሚስት አጋብቶት ከነበረ ግን እሷም ሆነች ልጆቿ የጌታው ንብረት ሆነው ይቀጥላሉ፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ይህ የሚሆነው ጌታው የባዕድ አገር ሴት ካጋባው ነው፤ ምክንያቱም ዕብራዊት ሴት ብትሆን ኖሮ በሰባተኛ ዓመቷ ነፃ ትለቀቅ ነበር። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥምበት ወቅት፣ ዕብራዊው ባሪያ ጌታውን እያገለገለ ለመቀጠል ሊመርጥ ይችላል። ምርጫው ይህ ከሆነ ጆሮውን በወስፌ ይበሳል፤ ይህም ዕድሜ ልኩን ባሪያ ሆኖ ለማገልገል እንደመረጠ ምልክት ይሆናል።—ዘፀ 21:2-6፤ ዘዳ 15:16, 17
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በዘፀአት 23:19 ላይ ከሚገኘው “ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል” ከሚለው ሕግ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጽፎ የሚገኘውና የሙሴ ሕግ ክፍል የሆነው ይህ ትእዛዝ ይሖዋ ትክክለኛ ለሆነው ነገር ያለውን አመለካከት፣ አዛኝነቱንና ርኅራኄውን እንድናስተውል ይረዳናል። እንዲሁም ለሐሰት ሃይማኖት ያለውን ጥላቻ ጎላ አድርጎ ያሳያል።—ዘፀአት 34:26፤ ዘዳግም 14:21
ጠቦት ፍየልን ወይም ሌላ እንስሳን በእናቱ ወተት መቀቀል ይሖዋ በተፈጥሮ ካደረገው ዝግጅት ጋር የሚጋጭ ነው። አምላክ የእናት ጡት ወተትን ያዘጋጀው ግልገሉ እየተመገበው እንዲያድግበት ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደተናገሩት ግልገልን በእናቱ ወተት መቀቀል “አምላክ በወላጆችና በልጆች መካከል ለፈጠረውና ለቀደሰው ዝምድና ንቀት” ማሳየት ነው።
በተጨማሪም ጠቦትን በእናቱ ወተት መቀቀል፣ ዝናብ እንዲዘንብ ለመለማመን የሚከናወን አረማዊ የአምልኮ ሥርዓት ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች ይገምታሉ። ይህ እውነት ከሆነ፣ እገዳው እስራኤላውያንን በዙሪያቸው የነበሩ አሕዛብ ከሚፈጽሟቸው ፍሬ ቢስና ጭካኔ የሞላባቸው ሃይማኖታዊ ልማዶች ጠብቋቸዋል። እስራኤላውያን የእነዚህን ብሔራት ልማድ እንዳይከተሉ የሙሴ ሕግ በግልጽ ያዝዛል።—ዘሌዋውያን 20:23
በመጨረሻም፣ ይህ ሕግ ስለ ይሖዋ ርኅራኄ ትምህርት ይሰጠናል። ሕጉ በእንስሳት ላይ ጭካኔ መፈጸምንና ተፈጥሮን የሚጻረሩ ነገሮች ማድረግን የሚከለክሉ በዘፀአት 23:19 ላይ ካለው ጋር የሚመሳሰሉ በርካታ ደንቦች ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ እንስሳ ከእናቱ ጋር ቢያንስ ለሰባት ቀን ካልቆየ መሥዋዕት መሆን እንደሌለበት፣ አንዲት እንሰሳንና ልጅዋን በአንድ ቀን መሠዋት እንደማይገባ እንዲሁም ወፍንና እንቁላሎቿን ወይም ልጆቿን ከጎጆዋቸው አብሮ መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ ሕጉ ያዝዛል።—ዘሌዋውያን 22:27, 28፤ ዘዳግም 22:6, 7
ሕጉ የያዘው ውስብስብ የሆኑ ትእዛዞችና እገዳዎች ብቻ እንዳልሆነ ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል። የሙሴ ሕግ በርካታ ጥቅሞች ያስገኝልናል፤ ከእነዚህም አንዱ ሕጉ የያዛቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የይሖዋን ግሩም ባሕርያት በሚገባ የሚያንጸባርቅ ላቅ ያለ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖረን ማስቻሉ ነው።—መዝሙር 19:7-11
ከሐምሌ 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 16–18
“በጽድቅ ለመፍረድ የሚረዱ መመሪያዎች”
it-1 343 አን. 5
ዓይነ ስውርነት
በጥቅም ወይም በሌላ ነገር ተታልሎ ፍትሕ ማዛባት በዓይነ ስውርነት ተመስሏል፤ እንዲሁም ዳኞች በጉቦ፣ በስጦታ ወይም ሰውን ከውጭ አይቶ በመፍረድ ፍትሕ እንዳያዛቡ ሕጉ ብዙ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ነገሮች ዳኛውን ሊያሳውሩትና ትክክለኛ ፍርድ እንዳይፈርድ ሊያደርጉት ይችላሉ። “ጉቦ አጥርተው የሚያዩ ሰዎችን ዓይን ያሳውራል።” (ዘፀ 23:8) “ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራል።” (ዘዳ 16:19) አንድ ዳኛ የቱንም ያህል ቀናና አስተዋይ ቢሆን ጉዳያቸውን ከሚያይላቸው ሰዎች ስጦታ ከተቀበለ አውቆትም ይሁን ሳያውቀው ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል። የአምላክ ሕግ፣ ጉቦ ብቻ ሳይሆን የግል ስሜትም አንድን ዳኛ ሊያሳውረው እንደሚችል ይናገራል፤ “ለድሃው አታዳላ ወይም ባለጸጋውን ከሌሎች አስበልጠህ አትመልከት” የሚለው ለዚህ ነው። (ዘሌ 19:15) ስለዚህ አንድ ዳኛ ስሜቱ ጋርዶት ወይም ብዙኃኑን ለማስደሰት ሲል አንድ ሰው ሀብታም ስለሆነ ብቻ ሊፈርድበት አይገባም።—ዘፀ 23:2, 3
it-2 511 አን. 7
ቁጥር
ሁለት። ሁለት ቁጥር ብዙ ጊዜ ከሕግ ነክ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ይጠቀሳል። ሁለት ምሥክሮች የሚሰጡት ቃል ከተስማማ ምሥክርነታቸው ይበልጥ ተቀባይነት ያገኛል። ዳኞች ፊት አንድ ክስ እውነት መሆኑ የሚረጋገጠው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በሚሰጡት ምሥክርነት ነው። ይህ ደንብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ይሠራበታል። (ዘዳ 17:6፤ 19:15፤ ማቴ 18:16፤ 2ቆሮ 13:1፤ 1ጢሞ 5:19፤ ዕብ 10:28) አምላክ ልጁን የሰው ዘር አዳኝ አድርጎ ሲልክ ይህን ደንብ ተከትሏል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በሕጋችሁም ላይ ‘የሁለት ሰዎች ምሥክርነት እውነት ነው’ ተብሎ ተጽፏል። ስለ ራሴ የምመሠክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ደግሞም የላከኝ አብ ስለ እኔ ይመሠክራል።”—ዮሐ 8:17, 18
it-2 685 አን. 6
ካህን
የአምላክን ሕግ የማብራራት መብት በዋነኝነት የተሰጠው ለካህናት ነበር፤ በእስራኤል የፍትሕ ሥርዓት ውስጥም ወሳኝ ሚና ነበራቸው። ዳኞች ከፈለጉ በከተሞቻቸው ያሉ ካህናትን እገዛ ሊጠይቁ ይችላሉ፤ በተጨማሪም ከዳኞቹ አቅም በላይ የሆኑ ከባድ ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ካህናቱ ከዳኞቹ ጋር ሆነው ይዳኛሉ። (ዘዳ 17:8, 9) ነፍስ ግድያ ተፈጽሞ ገዳዩ ካልታወቀ ካህናቱ ከከተማዋ ሽማግሌዎች ጋር ሆነው ጉዳዩን ያጣራሉ፤ በከተማዋ ላይ የደም ዕዳ እንዳይመጣ ተገቢው እርምጃ መወሰዱን ይከታተላሉ። (ዘዳ 21:1, 2, 5) አንድ ባል በሚስቱ ቢቀናና በምንዝር ቢጠረጥራት ወደ መቅደሱ ይዟት ይመጣል፤ በዚያም ካህኑ፣ እንዲህ ያለ ጉዳይ በሚፈጠርበት ጊዜ ይሖዋ እንዲደረግ ያዘዘውን ሥርዓት ይፈጽማል፤ ይህ ሥርዓት፣ ሴትየዋ ንጹሕ መሆን አለመሆኗን ይሖዋ ራሱ እንዲፈርድ የሚያደርግ ነው። (ዘኁ 5:11-31) ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን፣ ካህናት ወይም የተሾሙ ዳኞች የሚያስተላልፉት ፍርድ ሊከበር ይገባል፤ ሆን ብሎ ይህን ፍርድ መተላለፍ ወይም መጣስ የሞት ቅጣት ያስከትላል።—ዘኁ 15:30፤ ዘዳ 17:10-13
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 787
ውገዳ
በሕጉ መሠረት፣ አንድ ሰው ከማኅበረሰቡ ተለይቶ እንዲጠፋ የሚወሰንበት ቢያንስ በሁለት ምሥክሮች ክሱ ከተረጋገጠ ነው። (ዘዳ 19:15) በጥፋተኛው ሰው ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ እንዲወረውሩ የሚጠበቅባቸው እነዚህ ምሥክሮች ናቸው። (ዘዳ 17:7) ይህም ለአምላክ ሕግና ለመላው የእስራኤል ጉባኤ ንጽሕና እንደሚቀኑ ያሳያል፤ እንዲሁም ይህ ሥርዓት አንድ ሰው በሐሰት፣ በግድ የለሽነት ወይም በችኮላ ምሥክርነት እንዳይሰጥ ይከላከላል።
ከሐምሌ 26–ነሐሴ 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 19–21
“የሰው ሕይወት በይሖዋ ፊት ውድ ነው”
ፍትሕና ምሕረት በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ
4 ስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ወደነበሩበት ቦታ መድረስ አስቸጋሪ አልነበረም። ይሖዋ ሦስቱን የመማጸኛ ከተሞች ከዮርዳኖስ ወዲህ፣ ሦስቱን ከተሞች ደግሞ ከዮርዳኖስ ወዲያ እንዲያደርጓቸው እስራኤላውያንን አዟቸው ነበር። ይህን ያላቸው ለምንድን ነው? ሳያስበው ነፍስ ያጠፋ ማንኛውም ሰው ብዙም ሳይቸገር በፍጥነት ወደ መማጸኛ ከተማ መድረስ እንዲችል ነው። (ዘኁ. 35:11-14) ወደ መማጸኛ ከተሞች የሚወስዱት መንገዶች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ይደረግ ነበር። (ዘዳ. 19:3) በተጨማሪም የአይሁዳውያን የማመሣከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት ወደ መማጸኛ ከተሞች የሚሸሹ ሰዎችን ለመርዳት ሲባል በመንገዶቹ ላይ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች ይቆሙ ነበር። በእስራኤል ውስጥ የመማጸኛ ከተሞች ስለተዘጋጁ፣ ሳያውቅ ሰው የገደለ ግለሰብ ወደ ሌላ አገር ለመሸሽ የሚገደድበት ምክንያት አይኖርም፤ ግለሰቡ ወደ ባዕድ አገር መሸሽ ቢኖርበት ግን የሐሰት አምልኮን ለመከተል ሊፈተን ይችላል።
ፍትሕና ምሕረት በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ
9 የመማጸኛ ከተሞች የተዘጋጁበት ዋነኛ ዓላማ እስራኤላውያን በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ሲባል ነው። (ዘዳ. 19:10) ይሖዋ ለሕይወት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሲሆን “ንጹሕ ደም የሚያፈሱ [እጆችን]” ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) ይሖዋ ፍትሐዊና ቅዱስ አምላክ ስለሆነ፣ ሳያውቅ የሰው ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ እንኳ በቸልታ እንዲታለፍ አይፈቅድም። እርግጥ፣ ሳያስበው ነፍስ ያጠፋው ሰው ምሕረት የሚያገኝበት ዝግጅት ተደርጓል። ያም ቢሆን ጉዳዩን ለሽማግሌዎች መናገር ነበረበት፤ ሽማግሌዎቹ፣ ነፍስ ያጠፋው ሳያውቅ እንደሆነ ከፈረዱለት ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማ ውስጥ መቆየት አለበት። ምናልባትም ቀሪ ሕይወቱን በመማጸኛ ከተማ ውስጥ ማሳለፍ ሊኖርበት ይችላል። እንዲህ ያለ ከባድ እርምጃ መወሰዱ፣ ሁሉም እስራኤላውያን የሰው ሕይወት ቅዱስ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ሕይወት ሰጪያቸው ለሆነው አምላክ አክብሮት ለማሳየት ሲሉ፣ የሌላ ሰውን ሕይወት አደጋ ላይ ላለመጣል የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ነበረባቸው።
it-1 344
ደም
ለማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት የሰጠው አምላክ ነው፤ ስለዚህ የሰውን ሕይወት ያጠፋ ሰው በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ ይሆናል። አምላክ ነፍሰ ገዳይ ለሆነው ለቃየን የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ይህን ያሳያል፤ ቃየንን “የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው” ብሎት ነበር። (ዘፍ 4:10) ነፍስ ማጥፋት ይቅርና ወንድሙን ከመጥላቱ የተነሳ እንዲሞት የሚመኝ ወይም ስሙን በማጥፋትና የሐሰት ምሥክርነት በመስጠት ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሰው እንኳ ከወንድሙ ደም ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ይሆናል።—ዘሌ 19:16፤ ዘዳ 19:18-21፤ 1ዮሐ 3:15
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 518 አን. 1
ፍርድ ቤት
የፍርድ ጉዳዮች የሚታዩት በከተሞቹ በር ላይ ነበር። (ዘዳ 16:18፤ 21:19፤ 22:15, 24፤ 25:7፤ ሩት 4:1) እዚህ ላይ “በር” ሲል ከተማዋ ውስጥ በሩ አቅራቢያ ያለውን ሰፊ ክፍት ቦታ ያመለክታል። በተሰበሰበ ሕዝብ ፊት ሕጉ የሚነበበው እንዲሁም ደንቦችና ሥርዓቶች የሚታወጁት በከተማዋ በር ላይ ነበር። (ነህ 8:1-3) የንብረት ሽያጭና የመሳሰሉት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በር ላይ ሲታዩ ምሥክሮች ማግኘት ቀላል ይሆናል፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰዎች በቀኑ ውስጥ ለተለያዩ ጉዳዮች መግባታቸውና መውጣታቸው አይቀርም። በተጨማሪም በሩ ላይ ብዙ አላፊ አግዳሚ ስለሚኖር ችሎቱ እዚያ መሰየሙ ዳኞቹ አንድን ጉዳይ በሚያዩበት ወቅትም ሆነ ፍርድ ሲያስተላልፉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። በበሩ አቅራቢያ ዳኞቹ ተቀምጠው የፍርድ ጉዳዮችን የሚያዩበት ምቹ ቦታ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (ኢዮብ 29:7) ሳሙኤል በቤቴል፣ በጊልጋል እና በምጽጳ እየተዘዋወረ ‘ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ ያገለግል ነበር’፤ በተጨማሪም ቤቱ በሚገኝበት በራማ ይፈርድ ነበር።—1ሳሙ 7:16, 17
ከነሐሴ 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 22–23
“ሕጉ፣ ይሖዋ ለእንስሳት ያለውን አሳቢነት የሚያሳየው እንዴት ነው?”
it-1 375-376
ሸክም
በጥንት ዘመን እንስሳትን ለጭነት መጠቀም የተለመደ ነበር፤ አንድ እስራኤላዊ፣ የሚጠላው ሰው አህያ ጭነቱ ከብዶት ወድቆ ቢያይ ትቶት ከመሄድ ይልቅ ‘ጭነቱን ከእንስሳው ላይ እንዲያወርድለት’ ታዝዟል። (ዘፀ 23:5) አንድ እንስሳ መሸከም የሚችለው መጠን ጭነት ተብሎ ተጠርቷል፤ ለምሳሌ “የሁለት በቅሎ ጭነት” የሚል አገላለጽ እናገኛለን።—2ነገ 5:17
it-1 621 አን. 1
ዘዳግም
ዘዳግም መጽሐፍ ላይ ለእንስሳትም አሳቢነት ስለ ማሳየት የሚገልጽ ሐሳብ እናገኛለን። እስራኤላውያን፣ ጫጩቶቿን ወይም እንቁላሎቿን የታቀፈችን ወፍ እንዳይወስዱ ተከልክለዋል፤ ምክንያቱም ወፏ በቀላሉ የምትያዘው እነሱን ከጥቃት ለመከላከል ስትል ነው። እስራኤላውያን ወፏን መልቀቅ አለባቸው፤ ከፈለጉ ግን ጫጩቶቿንና እንቁላሎቿን መውሰድ ይችላሉ። ወፏ መለቀቋ ሌሎች ጫጩቶች እንድትፈለፍል ያስችላታል። (ዘዳ 22:6, 7) አንድ ገበሬ አህያና በሬ አንድ ላይ እንዳይጠምድ ተከልክሏል፤ ይህ ሕግ የተሰጠው ደከም ያለው እንስሳ እንዳይጎዳ ነው። (22:10) እህል የሚያበራይን በሬ አፉን ማሰር ክልክል ነበር፤ ምክንያቱም እህሉ እዚያው ፊቱ እያለ በረሃብ እንዲሠቃይ ማድረግ ይሆናል፤ በዚያ ላይ እህሉን ለማበራየት እየለፋ ነው።—25:4
“በማይመች አካሄድ አትጠመዱ”
ከሥዕሉ ማየት እንደምትችለው በማረስ ላይ ያሉት ግመልና በሬ በጣም የተጎሳቆሉ ይመስላል። ተመሳሳይ መጠንና ጉልበት ያላቸውን እንስሳት አንድ ላይ ለማጥመድ ታስቦ የተሠራው ቀንበር ሁለቱንም እንስሳት ለሥቃይ ዳርጓቸዋል። አምላክ እነዚህን የመሳሰሉ የቤት እንስሳትን ደህንነት በሚመለከት ለእስራኤላውያን “በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 22:10) ይህ መመሪያ ለበሬና ለግመልም ይሠራል።
አንድ ገበሬ ብዙውን ጊዜ ከብቶቹን እንዲህ ላለ ሥቃይ ሊዳርጋቸው አይፈልግም። ሆኖም ሁለት በሬዎች ከሌሉት ያሉትን ሁለት እንስሳት በአንድነት ይጠምዳቸው ይሆናል። በሥዕሉ ላይ የሚታየው የ19ኛው መቶ ዘመን ገበሬ እንዲህ ለማድረግ የተገደደው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ሁለቱ እንስሳት መጠናቸውና ክብደታቸው ስለሚለያይ ደካማው እኩል ለመጎተት መጣጣር ሲያስፈልገው ብርቱው ደግሞ ጫናው ይበዛበታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 600
ዕዳ፣ ባለዕዳ
ዕዳ፣ አንድ ሰው ለሌላ ሰው ለመክፈል ወይም ሌላ ነገር ለመስጠት የሚገባው ግዴታ ነው። በጥንቷ እስራኤል፣ አንድን ሰው ዕዳ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ዋነኛው ነገር የገንዘብ ችግር ነው። ለአንድ እስራኤላዊ ዕዳ ውስጥ መግባት በጣም ከባድ ነገር ነበር፤ ተበዳሪው የአበዳሪው ባሪያ የሆነ ያህል ነበር። (ምሳሌ 22:7) በመሆኑም የአምላክ ሕዝቦች ለተቸገሩ ወገኖቻቸው በልግስና እንዲያበድሩ ታዝዘዋል፤ ወለድ በመጠየቅ በሌሎች ችግር ለመበልጸግ እንዳይሞክሩም ተነግሯቸዋል። (ዘፀ 22:25፤ ዘዳ 15:7, 8፤ መዝ 37:26፤ 112:5) ሆኖም እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሰዎችን ወለድ ማስከፈል ይችሉ ነበር። (ዘዳ 23:20) አይሁዳውያን ተንታኞች፣ ይህ ዝግጅት የሚሠራው ለንግድ ተብሎ ለተወሰደ ብድር እንጂ ተቸግሮ ለተበደረ ሰው እንዳልሆነ ይናገራሉ። በአብዛኛው የባዕድ አገር ሰዎች እስራኤል ውስጥ የሚቆዩት ለጊዜው ነው፤ ብዙውን ጊዜ የሚመጡት ለንግድ ስለነበር ወለድ እንዲከፍሉ መጠየቅ ምክንያታዊ ነው፤ በዚያ ላይ ደግሞ እነሱም ራሳቸው ቢያበድሩ ወለድ መጠየቃቸው አይቀርም።
ከነሐሴ 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 24–26
“ሕጉ፣ ይሖዋ ለሴቶች ያለውን አሳቢነት የሚያሳየው እንዴት ነው?”
it-2 1196 አን. 4
ሴት
ወታደራዊ ሕጎችም እንኳ የባልን ብቻ ሳይሆን የሚስትንም መብት የሚያስከብሩ ነበሩ፤ ለምሳሌ አንድ አዲስ ሙሽራ ለአንድ ዓመት ያህል ከውትድርና አገልግሎት ነፃ ይሆናል። ይህም ለአዲሶቹ ባለትዳሮች ልጅ የሚያፈሩበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል፤ በኋላ ላይ ባልየው ለጦርነት ሲሄድ አልፎ ተርፎም ጦር ሜዳ ላይ ቢሞት ሚስትየው የምትጽናናበት ነገር ይኖራታል።—ዘዳ 20:7፤ 24:5
it-1 963 አን. 2
ቃርሚያ
በምድሪቱ ላሉ ድሆች የተደረገው ይህ ግሩም ዝግጅት ልግስናን፣ አለመሰሰትንና በይሖዋ በረከት መታመንን ያበረታታል፤ ይሁንና ስንፍናን ፈጽሞ አያበረታታም። ይህ ዝግጅት፣ ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ የተናገረው ለምን እንደሆነ ፍንጭ ይሰጠናል፤ ዳዊት “ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም” ብሎ ነበር። (መዝ 37:25) በሕጉ ውስጥ በሚገኘው በዚህ ዝግጅት እስከተጠቀሙና ጠንክረው እስከሠሩ ድረስ ድሆችም እንኳ አይራቡም፤ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ምግብ አይለምኑም።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
በጥንቷ እስራኤል አንድ ሰው ወንድ ልጅ ሳይወልድ ከሞተ የትውልድ መስመሩ እንዲቀጥል ሲባል ወንድሙ የሟቹን ሚስት እንዲያገባ ይጠበቅበት ነበር። (ዘፍጥረት 38:8) ከጊዜ በኋላ ይህ ዝግጅት በሙሴ ሕግ ውስጥ የተካተተ ሲሆን የዋርሳነት ግዴታ በመባል ይታወቃል። በሩት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውና ቦዔዝ ስላደረገው ነገር የሚተርከው ዘገባ ሟቹ ወንድሞች ከሌሉት ይህ ግዴታ ወደ ሌሎች ዘመዶቹ ሊተላለፍ እንደሚችል ያሳያል።—ሩት 1:3, 4፤ 2:19, 20፤ 4:1-6
በማርቆስ 12:20-22 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሰዱቃውያን የተናገሩት ሐሳብ የዋርሳነት ግዴታ በኢየሱስ ዘመን የተለመደ እንደነበር ይጠቁማል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ፍላቭየስ ጆሴፈስ የተባለው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ ይህ ሕግ የቤተሰቡ የዘር ሐረግ እንዲጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሟቹ ንብረት ከቤተሰቡ እጅ እንዳይወጣና ባሏን በሞት ያጣችው ሴት በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ችግር እንዳያጋጥማት ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግሯል። በዚያን ወቅት አንዲት ሚስት የባሏን ንብረት መውረስ አትችልም ነበር። ይሁንና ከዋርሳ የሚወለደው ልጅ የሞተውን ግለሰብ ንብረት የመውረስ መብት ነበረው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 640 አን. 5
ፍቺ
የፍቺ የምሥክር ወረቀት። ስለ ፍቺ የሚገልጸው የሙሴ ሕግ ምንም እንኳ በኋላ ላይ አላግባብ ቢሠራበትም አንድ እስራኤላዊ ሚስቱን መፍታት ቀላል እንዲሆንለት የሚያደርግ አልነበረም። አንድ እስራኤላዊ ባል ፍቺ ከመፈጸሙ በፊት ሊከተለው የሚገባ ሕጋዊ አሠራር ነበር። ሰነድ ማዘጋጀት ይኸውም “የፍቺ የምሥክር ወረቀት” መጻፍ ነበረበት። ከዚያም የምሥክር ወረቀቱን ‘በመስጠት ከቤቱ ያሰናብታታል።’ (ዘዳ 24:1) ቅዱሳን መጻሕፍት ስለዚህ አሠራር ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም ይህ ሕጋዊ ሂደት፣ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንዶችን ማማከር የሚጠይቅ ሳይሆን አይቀርም፤ እነሱ ደግሞ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር እርቅ እንዲፈጠር ለማድረግ መሞከር ሊሆን ይችላል። ሰነድ ማዘጋጀትና ፍቺው በሕጋዊ መንገድ እንዲፈጸም ማድረግ የሚጠይቀው ጊዜ ፍቺ መፈጸም የፈለገው ባል ጉዳዩን እንዲያስብበት ዕድል ይሰጠዋል። ያለበቂ ምክንያት ፍቺ መፈጸም አይፈቀድም ነበር፤ ሕጉ በአግባቡ ከተሠራበት ደግሞ ግለሰቦች ፍቺ ለመፈጸም እንዳይቸኩሉ ያደርጋል። ሕጉ የሚስቶች መብትና ፍላጎት እንዲጠበቅም ያደርጋል። ‘የፍቺ የምሥክር ወረቀቱ’ ይዘት ምን እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት አይናገሩም።
ከነሐሴ 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 27–28
“‘እነዚህ ሁሉ በረከቶች ተከታትለው ይደርሱብሃል’”
በአምላክ መንፈስ በሚመራው ንጉሥ አማካኝነት የሚገኘውን በረከት እጨዱ!
18 አምላክን መስማት፣ ቃሉ ውስጥ በሰፈሩት ነገሮች ላይ በጥሞና ማሰብንና እሱ ያዘጋጃቸውን መንፈሳዊ ምግቦች በሚገባ መመገብን እንደሚያካትት ግልጽ ነው። (ማቴ. 24:45) እንዲሁም አምላክንና ልጁን መታዘዝን ይጨምራል። ኢየሱስ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ነው” ብሏል። (ማቴ. 7:21) በተጨማሪም አምላክን መስማት ሲባል እሱ ላደረገው ዝግጅት ይኸውም ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በተባሉት ሽማግሌዎች አማካኝነት ላቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ በፈቃደኝነት መገዛት ማለት ነው።—ኤፌ. 4:8
የይሖዋ በረከት ያገኝህ ይሆን?
2 በዘዳግም 28:2 ላይ የሚገኘው “ብትሰማ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት የሚያመለክት ቃል ነው። የይሖዋ ሕዝቦች እሱን የሚሰሙት አልፎ አልፎ መሆን የለበትም፤ ምንጊዜም እሱን መስማት አለባቸው። የአምላክን በረከቶች ማግኘት የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። “ያገኙህማል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ግስ ብዙውን ጊዜ “አንድን ነገር አሳድዶ መያዝ” ወይም “መድረስ” የሚል ትርጉም ያለው ከአደን ጋር የተያያዘ ቃል ነው።
የይሖዋን በረከት ከልብ ፈልጉ
4 እስራኤላውያን ታዛዥ መሆን ያለባቸው በምን ዓይነት መንፈስ ነበር? ሕዝቡ “በደስታና በሐሤት” የማያገለግሉት ከሆነ ይሖዋ እንደሚያዝንባቸው የአምላክ ሕግ ይገልጻል። (ዘዳግም 28:45-47ን አንብብ።) ሕዝቡ ግድ ስለሆነበት ብቻ አንዳንድ መመሪያዎችን እንዲታዘዝ ይሖዋ አይፈልግም፤ እንስሳትና አጋንንትም እንኳ እንዲህ ያደርጋሉ። (ማር. 1:27፤ ያዕ. 3:3) አምላክን ከልብ መታዘዝ የፍቅር መግለጫ ነው። እንዲህ ዓይነት መንፈስ ያለው ሰው የሚታዘዘው በደስታ ነው፤ ይህም ደስታ የይሖዋ ትእዛዛት ከባዶች አለመሆናቸውን እንዲሁም “ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን” አምኖ ከመቀበል የሚመነጭ ነው።—ዕብ. 11:6፤ 1ዮሐ. 5:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 360
የወሰን ምልክት
የይሖዋ ሕግ፣ የወሰን ምልክት መግፋትን ይከለክል ነበር። (ዘዳ 19:14፤ በተጨማሪም ምሳሌ 22:28ን ተመልከት) እንዲያውም “የጎረቤቱን የወሰን ምልክት የሚገፋ የተረገመ ይሁን” ይላል። (ዘዳ 27:17) ባለርስቶች በአብዛኛው መተዳደሪያ የሚያገኙት መሬታቸው ከሚሰጣቸው ምርት ነው፤ ስለዚህ የአንድን ሰው የወሰን ምልክት መግፋት ግለሰቡ የሚተዳደርበት ገቢ እንዲቀንስ ያደርጋል። ይህ ከስርቆት የማይተናነስ ድርጊት ነው፤ በጥንት ዘመን ሰዎች ለዚህ ድርጊት የነበራቸው አመለካከትም ይህ ነው። (ኢዮብ 24:2) ሆኖም እንዲህ ዓይነት ወንጀል የሚፈጽሙ አጭበርባሪ ሰዎች ነበሩ፤ በተጨማሪም በሆሴዕ ዘመን የነበሩ የይሁዳ መኳንንት ወሰን ከሚገፉ ሰዎች ጋር ተመሳስለዋል።—ሆሴዕ 5:10
ከነሐሴ 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 29–30
“ይሖዋን ማገልገል ያን ያህል ከባድ አይደለም”
ይሖዋ የራሳችንን ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል
አምላክ የሚፈልግብንን ነገር ማወቅና ያወቅነውን በተግባር ማዋል ከባድ ነው? ሙሴ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ዕለት የምሰጥህ ትእዛዝ ይህን ያህል አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀች አይደለችም።” (ቁጥር 11) ይሖዋ ልናደርገው የማንችለውን ነገር እንድንፈጽም አይጠይቀንም። መሥፈርቶቹ ምክንያታዊና ልናሟላቸው የምንችላቸው ናቸው። በተጨማሪም እነዚህን መሥፈርቶች ማወቅ ከባድ አይደለም። አምላክ ከእኛ የሚፈልገውን ለማወቅ ‘ወደ ሰማይ መውጣት’ ወይም ‘ባሕር መሻገር’ አያስፈልገንም። (ቁጥር 12, 13) መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን በግልጽ ይነግረናል።—ሚክያስ 6:8
ይሖዋ የራሳችንን ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል
“ለይሖዋ ታማኝ ሳልሆን እቀር ይሆን የሚል መሠረት የሌለው ፍርሃት ብዙ ጊዜ ያድርብኛል።” ይህን የተናገረችው አንዲት ክርስቲያን ስትሆን በልጅነቷ ያሳለፈቻቸው መጥፎ ገጠመኞች ‘ነገሮች አይሳኩልኝም’ የሚል ድምዳሜ ላይ እንድትደርስ አድርገዋታል። ታዲያ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ትክክል ነው? ሁኔታዎችን ለማስተካከል ምንም ዓይነት ምርጫ የለንም ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ አምላክ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ሕይወታችንን እንዴት እንደምንመራ የራሳችንን ምርጫ ማድረግ እንችላለን። ይሖዋ ትክክለኛ ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል፤ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይነግረናል። እስቲ በዘዳግም ምዕራፍ 30 ላይ የሚገኘውን ሙሴ የተናገረውን ሐሳብ እንመርምር።
ይሖዋ የራሳችንን ምርጫ እንድናደርግ ይፈልጋል
ይሖዋ የፈለግነውን የሕይወት ጎዳና ብንመርጥ ግድ እንደማይሰጠው ሊሰማን ይገባል? በፍጹም! ሙሴ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ “ሕይወትን ምረጥ” ብሏል። (ቁጥር 19) ታዲያ ሕይወትን መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው? ‘አምላክን በመውደድ፣ ቃሉን በማዳመጥና ከእርሱ ጋር በመጣበቅ’ እንደሆነ ሙሴ ገልጿል። (ቁጥር 20) ይሖዋን የምንወድ ከሆነ ታዛዦች በመሆን እሱን ለማዳመጥ ፈቃደኞች እንሆናለን፤ እንዲሁም የመጣው ቢመጣ ከእሱ ጋር በታማኝነት እንጣበቃለን። እንዲህ ያለውን ጎዳና በመከተል ሕይወትን መምረጥ እንችላለን። ይህን ጎዳና ከተከተልን በዛሬው ጊዜ ሕይወታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መምራት እንችላለን፤ እንዲሁም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖረናል።—2 ጴጥሮስ 3:11-13፤ 1 ዮሐንስ 5:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 665 አን. 3
ጆሮ
ይሖዋ ግትሮቹና ዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ‘ያልተገረዙ ጆሮዎች’ እንዳሏቸው በአገልጋዮቹ አማካኝነት ተናግሯል። (ኤር 6:10፤ ሥራ 7:51) የሆነ ነገር ጆሯቸውን የደፈነው ያህል ነበር። ይሖዋ የሚሰማ ጆሮ አልሰጣቸውም፤ ምክንያቱም እሱን ለሚፈልጉት ሰዎች የሚሰማና የሚታዘዝ ጆሮ የሚሰጠው ይሖዋ ነው፤ የማይታዘዙት ሰዎች ግን በመንፈሳዊ የመስማት ችሎታቸው እንዲደነዝዝ ይፈቅዳል። (ዘዳ 29:4፤ ሮም 11:8) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንዶች ከእውነተኛው እምነት ወጥተው ከሃዲ እንደሚሆኑና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለመስማት ፈቃደኛ እንደማይሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል፤ ጆሯቸውን ‘የሚኮረኩርላቸውን’ ነገር መስማት ስለሚፈልጉ የሐሰት አስተማሪዎችን ማዳመጥን ይመርጣሉ። (2ጢሞ 4:3, 4፤ 1ጢሞ 4:1) በተጨማሪም አስደንጋጭ ዜና በተለይ ስለ ጥፋት የሚናገር ወሬ ጆሮ ‘ሊሰቀጥጥ’ እንደሚችል ተገልጿል።—1ሳሙ 3:11፤ 2ነገ 21:12፤ ኤር 19:3
ከነሐሴ 30–መስከረም 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 31–32
“በመንፈስ መሪነት በተቀናበረ መዝሙር ላይ ካሉ ምሳሌያዊ አገላለጾች የምናገኘው ትምህርት”
“ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ”
8 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ ይሖዋ ለሙሴ አንድ መዝሙር አስተምሮት ነበር። (ዘዳ. 31:19) ሙሴ ደግሞ መዝሙሩን ለሕዝቡ እንዲያስተምር ታዟል። (ዘዳግም 32:2, 3ን አንብብ።) በቁጥር 2 እና 3 ላይ ስናሰላስል ይሖዋ ስሙ እንዲሰወር እንደማይፈልግ በግልጽ እንረዳለን፤ በሌላ አባባል ‘ስሙ በጣም ቅዱስ ስለሆነ መጠራት የለበትም’ የሚለውን አመለካከት አይደግፍም። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ በሙሉ ስሙን እንዲያውቁት ይፈልጋል! እስራኤላውያን ስለ ይሖዋ እንዲሁም ስለ ክብራማ ስሙ የመማር አጋጣሚ በማግኘታቸው ምንኛ ታድለዋል! ካፊያ ተክልን እንደሚያረሰርሰው ሁሉ ሙሴ ያስተማራቸው ነገርም እስራኤላውያንን እምነታቸው እንዲጠናከርና መንፈሳቸው እንዲታደስ አድርጓቸው መሆን አለበት። እኛስ ትምህርታችን እንዲህ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
9 ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ወይም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ስንካፈል መጽሐፍ ቅዱሳችንን ተጠቅመን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ለሰዎች ልናሳያቸው እንችላለን። ይሖዋን የሚያስከብሩ ግሩም ጽሑፎች ልንሰጣቸው እንዲሁም ቪዲዮዎች ወይም ድረ ገጻችን ላይ የሚገኙ ነገሮችን ልናሳያቸው እንችላለን። በተጨማሪም በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት አሊያም በጉዞ ላይ ስንሆን፣ ስለምንወደው አምላካችንና ስለ ማንነቱ የመናገር አጋጣሚ እናገኝ ይሆናል። ይሖዋ ለሰው ዘሮችና ለምድር ስላለው ፍቅር የተንጸባረቀበት ዓላማ ለምናገኛቸው ሰዎች ስንነግራቸው ከዚህ በፊት ስለ ይሖዋ ፈጽሞ ሰምተው የማያውቁትን ነገር እንዲያውቁ እየረዳናቸው ሊሆን ይችላል። አፍቃሪ ስለሆነው አባታችን እውነቱን ለሌሎች ስንናገር ስሙ እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው። ሰዎች ስለ ይሖዋ የተማሯቸውን ውሸቶች በዚህ መንገድ እናጋልጣለን። በእርግጥም ለሰዎች የምናስተምረው ትምህርት ከምንም በላይ መንፈስን የሚያድስ ነው።—ኢሳ. 65:13, 14
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ትረዳቸዋለህ?
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ከግዑዛን ነገሮች ጋር ያነጻጽረዋል። ይሖዋ ‘የእስራኤል ዐለት፣’ “መጠጊያ” እንዲሁም “ዐምባ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። (2 ሳሙኤል 23:3፤ መዝሙር 18:2፤ ዘዳግም 32:4) ይሖዋን ከእነዚህ ግዑዛን ነገሮች ጋር የሚያመሳስለው ነጥብ ምንድን ነው? አንድ ትልቅ ዐለት ከቦታው ንቅንቅ እንደማይል ሁሉ ይሖዋ አምላክም አስተማማኝ ከለላ እንደሚሆንልህ ያሳያል።
ልጆቻችሁን ስታሠለጥኑ ይሖዋን ምሰሉ
7 ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየውን ፍቅር ተመልከት። ሙሴ ልብ የሚነካ ምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም ይሖዋ ጨቅላ ለነበረው ለእስራኤል ብሔር ያሳየውን ፍቅር ገልጿል። እንዲህ እናነባለን፦ “ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፣ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፣ በክንፎቹም አዘላቸው። እግዚአብሔር ብቻውን [ያዕቆብን] መራው።” (ዘዳግም 32:9, 11, 12) አንዲት እናት ንስር ጫጩቶቿ እንዲበርሩ ለማስተማር ክንፎቿን እያማታችና እያርገፈገፈች እንዲሁም ጎጆዋን እየነቀነቀች ‘እንዲወጡ’ ታነሳሳቸዋለች። በመጨረሻም አንዱ ጫጩት ብዙውን ጊዜ ገደል ላይ ከሚገኘው ጎጆው ውስጥ ዘሎ ሲወጣ እናትየው ‘ከላዩ እየተንሳፈፈች’ ትከተለዋለች። ጫጩቱ መሬት ደርሶ የሚፈጠፈጥ ከመሰላት በፍጥነት ተወርውራ ከሥሩ በመግባት በክንፎቿ ‘ታዝለዋለች።’ ይሖዋም አዲስ ለተወለደው የእስራኤል ብሔር በተመሳሳይ መንገድ ፍቅራዊ እንክብካቤ አድርጎለታል። የሙሴን ሕግ ለሕዝቡ ሰጥቷል። (መዝሙር 78:5-7) ከዚያም ብሔሩን በጥንቃቄ እየተንከባከበ በሕዝቡ ላይ ሊደርስ ከሚችል አደጋ ታድጎታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የዘዳግም መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
31:12፦ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ልጆች ከትልልቆች ጋር አንድ ላይ ተቀምጠው ለማዳመጥና ለመማር ጥረት ማድረግ አለባቸው።