በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ደቡብ ኮሪያ
ጥቅምት 26, 2020 ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው ለማይፈቅድላቸው ሰዎች ታሪካዊ ቀን ነው፤ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት አጋጣሚ የተከፈተላቸው በዚህ ዕለት ነው። ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደገለጹት የደቡብ ኮሪያ አማራጭ አገልግሎት በርዝመቱም ሆነ በክብደቱ ቀጪነትና መድልዎ የሚንጸባረቅበት ነው። ሦስት ዓመት የሚፈጀው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ወታደራዊ አገልግሎቱ ከሚፈጀው ጊዜ በእጥፍ ይበልጣል፤ ይህ ደግሞ ከዓለም አቀፍ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ ነው። ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች በሚደነግጉት መሠረት፣ አሳማኝና ከአድልዎ ነፃ የሆነ ምክንያት እስከሌለ ድረስ አማራጭ አገልግሎት ከወታደራዊው አገልግሎት የሚበልጥበት ጊዜ ወደ እጥፍ የሚጠጋ መሆን የለበትም። አንዳንድ የደቡብ ኮሪያ የይሖዋ ምሥክሮች በአማራጭ የሲቪል አገልግሎት ፕሮግራሙ ላለመካፈል ወስነዋል። አንዳንዶቹ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበዋል። ግንቦት 30, 2024 የደቡብ ኮሪያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት፣ ከአማራጭ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የቀረቡትን ቅሬታዎች በሙሉ 5 ለ4 በሆነ ድምፅ ውድቅ አድርጓቸዋል። ይሁንና ፍርድ ቤቱ በሰጠው የተቃርኖ አስተያየት ላይ የአገሪቱ አማራጭ አገልግሎት የቅጣት ባሕርይ ያለው መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለው አማራጭ አገልግሎት፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች ነፃነት የሚጋፋና ከቅጣት የማይተናነስ ነው።”
በደቡብ ኮሪያ በአማራጭ አገልግሎቱ ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የታሰረው የመጀመሪያው ሰው ብዮን ኡ ጂን ነው፤ የ29 ዓመቱ ኡ ጂን ባለትዳር ነው። ኡ ጂን በአማራጭ የሲቪል አገልግሎቱ ላለመካፈል የግሉን ውሳኔ አድርጓል። ኡ ጂን የቅጣት ባሕርይ የሌለው አማራጭ አገልግሎት ፕሮግራም ከተዘጋጀ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን በአክብሮት ቢገልጽም ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 24, 2024 የአንድ ዓመት ተኩል እስራት በይኖበታል።
ብዮን ኡ-ጂንን ጨምሮ እስከ ዛሬ ድረስ 14 የይሖዋ ምሥክሮች በአማራጭ አገልግሎት ዝግጅቱ ላለመካፈል ወስነዋል፤ እንዲሁም 11 የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው። ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሎ ሊቀጣቸውና እስራት ሊፈርድባቸው ይችላል። በሌላ በኩል ግን በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆኑት አብዛኞቹ፣ አማራጭ የሲቪል አገልግሎቱ የቅጣት ባሕርይ ያለው ቢሆንም ይህን አገልግሎት ለመስጠት ወስነዋል።
የጊዜ ሰሌዳ
ሐምሌ 24, 2024
ብዮን ኡ ጂን አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስራት ተፈረደበት።
ኅዳር 10, 2022
ብዮን ኡ ጂን ለምልመላ ሲጠራ ወታደራዊ አገልግሎትም ሆነ አማራጭ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት የሚገልጽ ደብዳቤ ለወታደራዊ የሰው ኃይል አስተዳደር ላከ።
ጥቅምት 26, 2020
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎች አማራጭ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ፕሮግራም አስጀመረ።
ኅዳር 1, 2018
የደቡብ ኮሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን እንደ ወንጀል እንደማይቆጠር 9 ለ4 በሆነ ድምፅ በየነ።
ሰኔ 28, 2018
የደቡብ ኮሪያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት፣ ወታደራዊ አገልግሎትን የሚደነግገው የአገሪቱ ሕግ በከፊል ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚጣረስ ገለጸ፤ ፍርድ ቤቱ ይህን ያለው ሕጉ፣ በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለማይካፈሉ ሰዎች አማራጭ አገልግሎት የማያቀርብ በመሆኑ ነው።
ጥቅምት 18, 2016
የግዋንግጁ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሦስት ሰዎች ያቀረቡትን ይግባኝ ተመልክቶ ጥፋተኛ አይደሉም የሚል ብይን አሳለፈ፤ እንዲህ ዓይነት ፍርድ ሲተላለፍ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ነሐሴ 30, 2011
የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ፣ በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች እንዲቀጡ የሚያዝዘውን ሕግ በድጋሚ አጸና።
ነሐሴ 26, 2004
የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ፣ በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች እንዲቀጡ የሚያዝዘው ደንብ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚስማማ መሆኑን ገለጸ።
1975
መንግሥት፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ጀመረ፤ ሁሉም ሰው በዚህ አገልግሎት የመካፈል ግዴታ ነበረበት።
1973
መንግሥት፣ የታሰሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ማሠቃየት ጀመረ፤ ይህ ሁኔታ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ቀጥሏል።
1953
በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር ታሰረ።