በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ዩክሬን
በዩክሬን፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎች አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ ሕግ ከወጣ 30 ዓመት ገደማ ይሆነዋል፤ የይሖዋ ምሥክሮችም ከዚህ ሕግ ተጠቃሚ ነበሩ። እንዲህ ያለው አማራጭ አገልግሎት ከሕሊናቸው ጋር የሚጋጭ ነገር ሳያደርጉ በተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ለመካፈል አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።
ይሁንና የካቲት 24, 2022 በዩክሬን ጦርነት ሲነሳ፣ አገሪቱ ውጊያ ላይ በምትሆንበት ወቅት አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ ዝግጅት እንደሌለ ግልጽ ሆነ፤ ሕሊናቸው በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል የማይፈቅድላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ የተነሳ የወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው። ይህ እርምጃ፣ እነዚህ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የማያወላውል አቋም የያዙት በጥብቅ በሚከተሉት እምነታቸው የተነሳ መሆኑን ከግምት ያስገባ አይደለም፤ እንዲሁም በሕሊናቸው ላይ ተመሥርተው አቋም የመውሰድ መብታቸውን የሚጥስ ነው። እንዲህ ያለው አካሄድ ከሰብዓዊ መብት መርሆች እንዲሁም ከዩክሬን ሕገ መንግሥት ጋር ይጋጫል፤ ሕገ መንግሥቱ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ዜጋ ወታደራዊ አገልግሎት መስጠቱ ከሃይማኖታዊ እምነቱ ጋር የሚጋጭበት ከሆነ በምትኩ አማራጭ (ወታደራዊ ያልሆነ) አገልግሎት እንዲሰጥ ይፈቀድለታል።”
እስከ ሰኔ 17, 2025 ባለው ጊዜ አራት የይሖዋ ምሥክር ወንዶች፣ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የሦስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ወህኒ ወርደዋል። ሌሎች ሦስት የይሖዋ ምሥክር ወንዶች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ማረፊያ ቤት ሆነው ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ነው።
ዓለም አቀፍ ተቋማት ስጋታቸውን ገልጸዋል
ሦስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለልተኛ አጣሪዎች፣ በዩክሬን አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት አለመኖሩ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። ኅዳር 8, 2023 ለዩክሬን መንግሥት በላኩት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት የማይሰጡ ሰዎችን መብት ለማስከበር የሚታገሉ ግለሰቦችን ጨምሮ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ግለሰቦች ወታደራዊ ግዳጃቸውን ባለመፈጸማቸው የተነሳ ለፍርድ መቅረባቸው አሳስቦናል።”
የጊዜ ሰሌዳ
ሰኔ 17, 2025
በአጠቃላይ ሰባት የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል።
የካቲት 24, 2022
አገሪቱ በወታደራዊ ሕግ መተዳደር ጀመረች፤ በመላ አገሪቱ ለጦርነት ክተት ታወጀ።
ሰኔ 23, 2015
የዩክሬን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቪታሊ ሻላይኮን ጉዳይ ተመልክቶ ለጦርነት ክተት በሚታወጅበት ወቅት በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎችን መብት አስከበረ።
ታኅሣሥ 1991
አማራጭ (ወታደራዊ ያልሆነ) አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕግ ወጣ።
የካቲት 28, 1991
በዩክሬን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ተሰጣቸው።