የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 8:- 563 ከዘአበ ገደማ ጀምሮ—ነጻነት ያስገኛል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት የእውቀት ጮራ
“አንድ ሃይማኖት ወይም ፍልስፍና የሚፈተነው ሊያብራራቸው በሚችላቸው ነገሮች ብዛት ነው።”—ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን የ19ኛው መቶ ዘመን አሜሪካዊ ባለቅኔ
ስለ እርሱ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር ቢኖር በጣም ጥቂት ነው። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አፈ ታሪክ ስሙ ሲድሃርታ ጎታማ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት 600 መቶ የሚሆኑ ዓመታት አስቀድሞ በሰሜናዊው የህንድ መንግሥት በሳኪያ ውስጥ የተወለደ መስፍን ነው ይላል። ሳኪያሙኒ (የሳኪያ ጎሳ ጠቢብ) እየተባለና ትርጓሜው በማይታወቅ ታታጋታ በሚል ስያሜ ይጠራ ነበር። ይህን ሰው የምታውቁት ይበልጥ በሚታወቅበት ቡድሃ በሚል መጠሪያው ብቻ ሳይሆን አይቀርም።
ጎታማ ያደገው ቤተ መንግሥት በመሰለ ቤት ውስጥ ነው፤ ይሁን እንጂ 29 ዓመት ሲሞላው ድንገት በዙሪያው ያለውን መከራ ተገነዘበ። በዛሬው ጊዜ ክፋትና መከራ ሊኖሩ የቻሉት ለምንድን ነው እያሉ እንደሚያስቡት ሰዎች እርሱም ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ለማግኘት ፈለገ። ሚስቱንና ጨቅላ ወንድ ልጁን ትቶ ለስድስት ዓመታት የብህትውና ኑሮ ወዳሳለፈበት ወደ በረሃ ተሰደደ። የሚተኛው በእሾህ ላይ ነበር፤ የሚኖረውም በቀን አንድ የሩዝ ፍሬ እየበላ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አንዳችም ዓይነት የእውቀት ብርሃን ሊያስገኝለት አልቻለም።
35 ዓመት ገደማ ከሆነው በኋላ ጎታማ መካከለኛ መንገድ ወይም ጎዳና ብሎ የጠራውን ሻል ያለ ዘዴ ለመጠቀም ወሰነ። የእውቀት ጮራ እስኪፈነጥቅልኝ ድረስ ከበለስ ዛፍ ሥር እቀመጣለሁ ብሎ ተሳለ። በመጨረሻ በአንድ ሌሊት ራእዮችን ካየ በኋላ ፍለጋው እንደሰመረለት ተሰማው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቡድሃ በሚል መጠሪያ የታወቀ ሆነ። ትርጓሜውም “የእውቀት ጮራ የፈነጠቀለት” ማለት ነው። ይሁን እንጂ ጎታማ ይህ መጠሪያ ለእኔ ብቻ የተወሰነ ነው አላለም። ስለዚህ አንድን ቡድሃ ለማመልከት ኤ የተባለውን የእንግሊዝኛ አመልካች ቃል ከፊት በማስገባት መጠቀም ይገባል፤ ራሱን ጎታማን ለማመልከት ደግሞ ዘ የተባለውን የእንግሊዝኛ አመልካች ቃል ከፊት በማስገባት መጠቀም ይገባል።
ወደ ነፃነት የሚወስደው መንገድ
ኢንድራና ብራህማ የተባሉት የሂንዱ አማልክት ቡድሃ ያገኛቸውን አዳዲስ እውነቶች ለሌሎች እንዲናገር እንደ ተማጸኑት ይነገራል። እርሱም ይህን ለማድረግ ቆርጦ ተነሣ። ቡድሃ ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው የሚለውን የሂንዱይዝምን ችሎ የመኖር ዝንባሌ ቢደግፍም በኅብረተሰባዊ ክፍሎች ሥርዓቱና የእንስሳት መሥዋዕቶች መቅረብ አለባቸው በሚለው ነጥብ አልተስማማም። የሂንዱ ጽሑፎች የሆኑት ቬዳዎች መለኮታዊ ምንጭ ያላቸው ጽሑፎች ናቸው የሚለውን አባባል አልተቀበለውም። አምላክ ምናልባት ሊኖር ይችላል የሚለውን አባባል ባይቃወምም የአምላክን ፈጣሪነት ግን አልተቀበለውም። የክስተቶች ሂደት ሕግ መጀመሪያ የለውም ሲል ይከራከራል። በመጀመሪያው ስብከቱ ወቅት እንዲህ ብሎ በመናገር ከሂንዱይዝምም አልፎ ሄዷል:- “ይህ ምንኩስና ወደ ማስተዋል፣ ወደ ጥበብ የሚመራ፣ ወደ ሰላም፣ ወደ እውቀት፣ ወደ ፍጹም የእውቀት ጮራ፣ ወደ ኒርቫና ለመድረስ የሚረዳ . . . መካከለኛ የእውቀት መንገድ ነው።”
‘ኒርቫና ምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። “መምህሩ ነጥቡን ስለደበቀውና ተከታዮቹም ለቃሉ ከጸሐይ በታች ያለውን ትርጓሜ ሁሉ ስለሚሰጡት ለዚህ ጥያቄ የተሳሳተ መልስ ማግኘት አስቸጋሪ ነው” በማለት ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት ይናገራሉ። “አንድ ወጥ የሆነ የቡድሂስት አመለካከት የለም” በማለት ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ከዚህ ሐሳብ ጋር ይስማማል። ምክንያቱም “በባህል፣ በታሪካዊ ወቅቶች፣ በቋንቋ፣ በጽንሰ ሐሳብና አልፎ ተርፎም በግለሰብ ደረጃ ይለያያል።” አንድ ጸሐፊ “የፍላጎት አለመኖር፣ ፍጻሜና ገደብ የሌለው ባዶነት . . . ዳግም የማይወለዱበት ሰላም የሰፈነበት ዘላለማዊ ሞት” ሲሉ ገልጸውታል። ሌሎች ደግሞ “ማጥፋት” የሚለውን በሳንስክሪት ቋንቋ የሚገኘውን የቃሉን መሠረታዊ ትርጉም በመጥቀስ ነዳጁ ሲያልቅ እንደሚጠፋ የእሳት ነበልባል ነው ይላሉ። ያም ሆነ ይህ ኒርቫና ነጻነትን ያስገኛል።
ቡድሃ ነጻነት ያስፈለገበትን ምክንያት በአራት ዋና ዋና እውነታዎች ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል:- ሕይወት ሥቃይና መከራ ነው፤ ሁለቱም የሚከሰቱት ለመኖርና ፍላጎቶችን ለማሳካት በጣም ከመጓጓት የተነሣ ነው፤ የጥበብ መንገድ ይህን ከፍተኛ ጉጉት አምቆ መያዝ ነው፤ ይህን ማድረግ የሚቻለው ስምንት ነገሮችን አጣምሮ የያዘውን መንገድ በመከተል ነው። ይህ መንገድ ትክክለኛ እምነት፣ ትክክለኛ ዓላማ፣ ትክክለኛ አነጋገር፣ ትክክለኛ ድርጊት፣ ትክክለኛ አኗኗር፣ ትክክለኛ ጥረት፣ ትክክለኛ አስተሳሰብና በትክክል ማሰላሰልን ይጠይቃል።
በውጭ አገር ያገኛቸው ድሎችና በአገር ውስጥ የገጠመው ሽንፈት
ቡድሂዝም ገና ከጅምሩ ጥሩ ምላሽ አግኝቶ ነበር። በዘመኑ የነበረ አንድ ካራቫካስ ተብሎ የሚጠራ በቁስ አካል የሚያምኑ ሰዎች ያሉት ቡድን ጥርጊያ መንገድ አዘጋጅቶለት ነበር። ሰዎቹ የሂንዱን ቅዱሳን ጽሑፎች የማይቀበሉና በአምላክ በማመን ሐሳብ የሚሳለቁ ነበሩ። በጥቅሉ ሃይማኖትን የካዱ ነበሩ። ያሳደሩት ተጽዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው። ዱራንት “አዲስ ሃይማኖት እንዲያቆጠቁጥ ያደረገ ክፍተት” ብለው የጠሩት ነገር እንዲከሰት እገዛ አድርጓል። ይህ ክፍተት “ከምሁራኑ የቆየ ሃይማኖት መዳከም” ጋር ተዳምሮ በጊዜው ለነበሩት ሁለት ዋና ዋና የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ማለትም ለቡድሂዝምና ለጃኒዝም መነሣት አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ አብዛኛውን የህንድ አህጉራዊ ክፍል ያቀፈ ግዛት የነበረው ንጉሥ አሶካ ቡድሂዝም እውቅና እንዲያገኝ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ሚስዮናውያንን ወደ ሴይሎን (ስሪላንካ) እና ምናልባትም ወደ ሌሎች አገሮች ጭምር በመላክ ሚስዮናውያንን የመላኩን ሥራ አጠናክሮታል። በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ቡድሂዝም በመላዋ ቻይና ተሰራጨ። ከዚያ በመነሣት በኮሪያ አሳብሮ በጃፓን ውስጥ ተሰራጨ። በስድስተኛውና በሰባተኛው መቶ ዘመናት እዘአ በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ክፍሎች ሁሉ ይገኝ ነበር። በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ300 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ቡድሂስቶች ይገኛሉ።
ከንጉሥ አሶካ ዘመን በፊትም እንኳን ቡድሂዝም እየተስፋፋ ነበር። “በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ማብቂያ ላይ የቡድሂስት ሚስዮናውያን አቴንስ ውስጥ ይገኙ ነበር” በማለት ኢ ኤም ሌይማን ጽፈዋል። ክርስትና ካቆጠቆጠ በኋላ የጥንቶቹ ሚስዮናውያን በየሄዱበት ቦታ ሁሉ የቡድሂስት መሠረተ ትምህርት ከፊታቸው ይጋረጥ ነበር በማለት አክለዋል። እንዲያውም የካቶሊክ ሚስዮናውያን በመጀመሪያ ወደ ጃፓን በሄዱበት ጊዜ አዲስ የቡድሂስት እምነት ክፍል ተደርገው ታይተው ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
ሁለቱ ሃይማኖቶች የጋራ የሆኑ ብዙ ነገሮች የነበሯቸው ይመስላል። ታሪክ ጸሐፊው ዱራንት እንዳሉት “ከጥንት ለተወረሱ ነገሮች አክብሮት መስጠት፣ ጠበል፣ ሻማዎች፣ ዕጣን፣ መቁጠሪያ፣ የካህናቱ አለባበስ፣ ከቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ የጠፉ ቋንቋዎች፣ መነኩሴዎች፣ ለምንኩስና ጸጉርን መላጨትና ብሕትውና፣ መናዘዝ፣ የጾም ቀኖች፣ ለሞቱ ቅዱሳን ክብር መስጠት፣ መንጽሔና ለሞቱ ሰዎች ፍታት ማድረግ” የመሳሰሉ ነገሮች ይገኙበታል። እነዚህ ነገሮች “በመጀመሪያ በቡድሂስት እምነት ውስጥ የተከሰቱ ይመስላል” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። እንዲያውም ቡድሂዝም “ለሁለቱም ሃይማኖቶች የጋራ የሆኑትን ሥነ ሥርዓቶችና ሃይማኖታዊ ይዘቶች ሁሉ በማቋቋምና በመጠቀም ረገድ ከሮማ ቤተ ክርስቲያን አምስት መቶ ዘመናት ይቀድማል” ተብሎ ይነገርለት ነበር።
እነዚህ የተመሳሰሉባቸው ነገሮች እንዴት እያደጉ እንደመጡ ሲገልጹ፣ ደራሲው ሌይማን አንድ የጋራ የሆነ መነሻን ይጠቁማሉ። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በክርስትና ዘመን . . . የአረማውያን እምነት በቡድሂስት የአምልኮ ይዘቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ይመስላል። . . . የአረማውያን እምነት ያሳደረው ተጽዕኖ በክርስትና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጎለበቱት አንዳንድ የአምልኮ ልማዶች [ጭምር] ተጠያቂ ሳይሆን አይቀርም።”
ቡድሂዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ድል ቢቀዳጅም በአገር ውስጥ ከፍተኛ ሽንፈት አጋጥሞታል። በዛሬው ጊዜ ከህንድ ሕዝብ ውስጥ የቡድሂስት እምነት ተከታዮች ከ1 በመቶ በታች ሲሆኑ 83 በመቶ የሚሆኑት የሂንዱ እምነት ተከታዮች ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ምናልባት ቡድሂዝም ማንኛውንም እምነትና አመለካከት የሚቀበል በመሆኑ በብዙዎቹ የሂንዱ ባሕላዊ እምነቶች ውስጥ እንደገና ተካቶ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ የቡድሂስት መነኩሴዎች ምእመናኑን በመጠበቅ ረገድ ቸልተኞች ሆነው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ዋነኛው ምክንያት እስልምና ወደ ህንድ ሰርጎ መግባቱ ነው። ይህም ብዙ ሰዎች ወደ እስልምና በተለወጡበት በተለይ በሰሜናዊው የህንድ ግዛት የእስልምና አገዛዝ እንዲከሰት አድርጓል። እንዲያውም በ13ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል ወደ ሩብ የሚጠጉት እስላሞች ነበሩ። በዚያ ወቅት ብዙ ቡድሂስቶች ወደ ሂንዱይዝም ተለወጡ። ይህም የእስልምናን ጥቃት በተሻለ መንገድ ለመቋቋም በመፈለግ የተደረገ ይመስላል። ሁሉን ችሎ መኖር የሚል ትርጉም ካለው ስሙ ጋር በመስማማት ሂንዱይዝም እንደገና ሁለት እጁን ዘርግቶ ተቀበላቸው። ቡድሃ ቪሽኑ ከሞተ በኋላ እንደገና ሕያው ሆኖ የመጣ አምላክ ነው ብሎ በማወጅ ወደ ሂንዱይዝም መመለስ የሚችሉበትን መንገድ አመቻቸላቸው!
ቡድሃ ያሉት ብዙ መልኮች
“የመጀመሪያዎቹ የቡድሃ ምስሎች የተሠሩት በግሪኮች ነው” በማለት ኢ ኤም ሌይማን ጽፈዋል። ቡድሂስቶች፣ እነዚህን ሐውልቶች አናመልካቸውም፤ ለአምላክ ያደሩ ለመሆን የሚረዱንና ለታላቁ አስተማሪ አክብሮት ለማሳየት ታልመው የተሠሩ ናቸው ይላሉ። አንዳንድ ጊዜ ቡድሃ ቆሞ ይታያል፤ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ እግሮቹን አቆላልፎ ተቀምጦ ይታያል። ውስጥ እግሮቹ ወደ ላይ የዞሩ ናቸው። እጆቹን አንዱን በአንዱ ላይ ሲያደራርብ እያሰላሰለ ነው። ቀኝ እጁን በአገጩ አቅጣጫ ሲያነሳ እየባረከ ነው። የቀኝ እጁ አውራ ጣት አመልካች ጣቱን በሚነካበት ጊዜ ወይም ሁለቱንም እጆቹን በደረቱ ፊት ለፊት በሚያገናኝበት ጊዜ እያስተማረ ነው። ጋደም ብሎ የሚታይበት ምስል ደግሞ ወደ ኒርቫና በመሸጋገር ላይ ያለበትን ወቅት የሚያሳይ ነው።
የተለያዩ አቋቋሞች እንዳሉት ሁሉ የተለያዩ መሠረተ ትምህርቶችም አሉት። እሱ በሞተ በ200 ዓመታት ውስጥ 18 የተለያዩ የቡድሂዝም ትርጉሞች ይገኙ ነበር ተብሏል። በዛሬው ጊዜ ጎታማ “የእውቀት ጮራ” ከፈነጠቀለት 25 መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ የኒርቫናን ግብ እንዴት ዳር ማድረስ እንደሚቻል የሚገልጹት የቡድሂስት ማብራሪያዎች ብዙ ናቸው።
በኔዘርላንድ ውስጥ የሚገኘው የሌደን ዩኒቨርሲቲው ኤርክ ዙርቸር “በቡድሂዝም ውስጥ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የመሠረተ ትምህርት ሐሳቦች፣ የአምልኮ ልማዶች፣ ቅዱሳን ጽሑፎችና በሥዕላዊ መግለጫዎች የተወረሱ ባሕሎች ያሏቸው ሦስት ዋና ዋና አቅጣጫዎች” አሉ በማለት ገልጸዋል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች በቡድሂስት እምነት አጠራር የመጓጓዣ መንገዶች ተብለው ይጠራሉ። ምክንያቱም ልክ እንደ መመላለሻ ጀልባዎች አንድ ሰው በመጨረሻ ወደ ነጻነት ዳርቻ እስኪደርስ ድረስ የሕይወትን ወንዝ ያሻግሩታል። ከዚያም መጓጓዣውን ያለምንም ችግር መተው ይቻላል። የቡድሂስት እምነት የመሄጃው መንገድ፣ የመጓጓዣው ዓይነት ለውጥ አያመጣም ይላል። ዋናው ቁም ነገር እዚያ መድረሱ ነው።
እነዚህ መጓጓዣዎች ቡድሃ ከሰበከው ትምህርት ጋር ተቀራራቢ የሆኑ ትምህርቶችን ይዞ የዘለቀውን ቴራቫዳ ቡድሂዝምን ያጠቃልላሉ። ይህም በተለይ በበርማ፣ በስሪላንካ፣ በላኦስ፣ በታይላንድና በካምፑቺያ (በቀድሞዋ ካምፖድያ) ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ይታመንበታል። በይበልጥ በቻይና፣ በኮሪያ፣ በጃፓን፣ በቲቤትና በሞንጎሊያ በስፋት የሚታመንበት ማሃያና ቡድሂዝም የተለያዩ አመለካከቶችን በመቀበል ረገድ ላቅ ብሎ ይታያል፤ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ትምህርቶቹን ከሁኔታዎች ጋር እንዲስማሙ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት ከአነስተኛው መጓጓዣ ከቴራቫዳ ጋር ሲነጻጸር ትልቁ መጓጓዣ ተብሎ ተጠርቷል። በአብዛኛው ታንትሪዝም ወይም ኤሶተሪክ ቡድሂዝም ተብሎ የሚጠራው አልማዙ መጓጓዣ ቫጅራያና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችንና የዮጋን ልምምድ አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው። አንድ ሰው ወደ ኒርቫና የሚያደርገውን ጉዞ ያፋጥንለታል ተብሎ ይነገራል።
እነዚህ ሦስት እንቅስቃሴዎች ወደ ብዙ ጽንሰ ሃሳቦች ይከፋፈላሉ። እያንዳንዳቸው ለአንድ መሠረታዊ ትምህርት የሚሰጡት ፍቺ ይለያያል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ የሚሆነው በተወሰኑ የቡድሂስት ጽሑፎች ክፍሎች ላይ ልዩ ትኩረት ስለሚሰጡ ነው። ዙርቸር እንዳሉትም የትም ይሂድ የት “መጠኑ ይለያይ እንጂ ቡድሂዝም በአካባቢ እምነቶችና ልማዶች ይመራል።” በዚህም ምክንያት እነዚህ ጽንሰ ሐሳቦች በጥቂት ጊዜ ውስጥ የትኞቹንም በአካባቢው የሚገኙ የእምነት ክፍሎችን ቁጥር በልጠው ይሄዳሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ግራ የሚያጋቡ የእምነት ክፍሎችና ንዑሳን ክፍሎችን ከያዘችው ከሕዝበ ክርስትና ባልተለየ መልኩ በምሳሌያዊ አነጋገር ቡድሃ ብዙ ገጽታዎችን ተላብሷል።
ቡድሂዝምና ፖለቲካ
ልክ እንደ ይሁዲነትና እንደ ስመ ክርስትና ሁሉ ቡድሂዝምም በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ አልተወሰነም፤ ፖለቲካዊ አስተሳሰብንና ባሕርይንም በመቅረጽ ረገድ አስተዋጽኦ አበርክቷል። “ቡድሂዝምና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋሃዱት በ[ንጉሥ] አሶካ የግዛት ዘመን ነበር” በማለት ደራሲው ጄሮልድ ስቼክተር ይናገራሉ። ይህ የቡድሂዝም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እኛ እስካለንበት ዘመን ድረስ ቀጥሏል። በ1987 መገባደጃ ላይ የቲቤት ተወላጆች የሆኑ 27 የቡድሂስት መነኩሴዎች በፀረ ቻይና ትዕይንተ ሕዝብ ላይ በመካፈላቸው በላሃሳ ውስጥ ተይዘው ታስረዋል። በ1960 በተካሄደው የቬትናም ጦርነት ውስጥ ቡድሂዝም ያደረገው ተሳትፎ ስቼክተር እንዲህ ብለው እንዲደመድሙ አድርጓቸዋል:- “‘የሚድል ዌይ’ ሰላማዊ መንገድ ወደ አዲስ የጎዳና ላይ የዓመፅ ትዕይንተ ሕዝብ ተለውጧል። . . . በእስያ ውስጥ ቡድሂዝም በተጋጋለ ዓመፅ ውስጥ የተዘፈቀ እምነት ነው።”
በጣም መጥፎ በሆነው የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የሥነ ምግባር ሁኔታዎች ያልተደሰቱ አንዳንድ ሰዎች ማብራሪያዎችን ለማግኘት ቡድሂዝምን ጨምሮ ወደ ምሥራቅ ሃይማኖቶች አቅንተዋል። ይሁን እንጂ “በዓመፅ ውስጥ የተዘፈቀ እምነት” ጥያቄዎቻቸውን ሊመልስ ይችላልን? “አንድ ሃይማኖት የሚፈተነው . . . ሊያብራራቸው በሚችላቸው ነገሮች ብዛት ነው” የሚለውን የኢመርሰንን መመዘኛ ብትጠቀም የጎታማን የእውቀት ጮራ እንዴት ታየዋለህ? “ትክክለኛውን መንገድ ለማግኘት በሚደረገው ፍለጋ” ከሌሎቹ የእስያ ሃይማኖቶች መካከል አንዳንዶቹ የተሻሉ ይሆኑን? ለመልሱ በሚቀጥለው መጽሔት ላይ የሚወጣውን ትምህርት አንብብ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከሕዝቦቹ፣ ከቦታዎቹና ካሉት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ
የአዳም ጫፍ፤ በስሪላንካ ውስጥ የሚገኝ እንደ ቅዱስ ተደርጎ የሚታይ ተራራ፤ በተራራው ላይ በሚገኝ አንድ ድንጋይ ላይ ያለውን ምልክት የቡድሂስት እምነት ተከታዮች የቡድሃ ዱካ ነው ይላሉ፤ እስላሞች የአዳም ነው ይላሉ፤ ሂንዱዎች ደግሞ የሲቫ ነው ይላሉ።
ቦድሂ ዛፍ፣ ጎታማ ከበታችዋ ተቀምጦ ቡድሃ የሆነባት የበለስ ዛፍ፣ “ቦድሂ” ማለት “የእውቀት ጮራ” ማለት ነው፤ የመጀመሪያው ዛፍ ጉቶ እስካሁን አለ ይባላል፤ ይህ ጉቶ በስሪላንካ አኑራዳፑራ ውስጥ ይመለካል።
የቡድሂስት መነኩሴዎች፣ ልዩ በሆኑት ልብሶቻቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ዋነኛ የቡድሂዝም ትምህርት መሥርተዋል፤ እውነተኛ ለመሆን፣ ለሰውና ለእንስሳ አሳቢዎች ለመሆን፣ በልመና ለመተዳደር፣ ከደስታ ለመራቅና በድንግልና ለመኖር ቃል ይገባሉ።
ዳላይ ላማ፣ የቲቤት ተወላጅ የሆነ ዓለማዊና ሃይማኖታዊ መሪ፣ ቡድሂስቶች ቡድሃ ከሞተ በኋላ እንደገና በሌላ መልክ እሱን ሆኖ እንደተወለደ አድርገው ይመለከቱታል፣ በ1959 ወደ ግዞት ተወስዶ ነበር፤ “ዳላይ” “ውቅያኖስ” የሚል ትርጉም ካለው የሞንጎላውያን ቃል የተወሰደ ሲሆን ሰፊ እውቀትን ያመለክታል፤ “ላማ” መንፈሳዊ አስተማሪን ያመለክታል (በሳንስክሪት ቋንቋ ደብተራ እንደሚለው ማለት ነው)። የዜና ሪፖርቶች እንደሚሉት በ1987 በቲቤት ውስጥ በተካሄዱት ትዕይንተ ሕዝቦች ዳላይ ላማ “የሕዝብ አሻፈረኝ ባይነትን ባርኳል፤ ዓመጽን ግን ተቃውሟል፤” በዚህም ምክንያት ፖለቲካን በሚመለከት መናገር በእንግድነት በሚኖርባት አገር በህንድ የመቆየቱን አጋጣሚ ሊያጨናግፉበት እንደሚችል እንዲገነዘብ አድርገውታል።
ጥርሱ የሚገኝበት ቤተ መቅደስ፣ በስሪላንካ ካንዲ ውስጥ የሚገኝ የቡድሂስት ቤተ መቅደስ፣ በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገኛል ተብሎ የሚነገረው አንድ የቡድሃ ጥርስ እንደ ቅዱስ ቅርስ ተደርጎ ይታያል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሻይና የቡድሂስት “ጸሎት”
የቡድሂስት “ጸሎት” ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር የሚመሳሰልባቸው መንገዶች ቢኖሩም “ማሰላሰል” ተብሎ ቢጠራ ይበልጥ ትክክል ይሆናል። ራስን መገሰጽንና በጥልቀት ማሰላሰልን ለየት ባለ መንገድ የሚያጎላው ዜን ቡድሂዝም አንዱ መልክ ነው። ወደ ጃፓን የገባው በ12ኛው መቶ ዘመን እዘአ ሲሆን ቦድሂዳራማ የተባለ አንድ የሕንድ መነኩሴ ባመነጨው ቻን ተብሎ በሚጠራው የቻይናውያን ቡድሂዝም ዓይነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ሰው ወደ ቻይና የሄደው በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ሲሆን ቻንን ሲመሠርት ከታኦይዝም ብዙ ነገሮች ተውሷል። በአንድ ወቅት እያሰላሰለ ሳለ እንቅልፍ ስለወሰደው በንዴት የዓይኑን ቅንድቦች ነጭቶ እንደጣላቸው ይነገራል። ወደ ምድር ወደቁ፤ ከዚያም ሥር ሰደዱና የመጀመሪያውን የሻይ ተክል አበቀሉ። ይህ አፈ ታሪክ ለዜን መነኩሴዎች አንድ ሰው በሚያሰላሰልበት ጊዜ ንቁ ሆኖ እንዲቆይ ሻይ መጠጣት ጥሩ ነው ለሚለው ልማዳቸው መሠረት ሆኗቸዋል።
[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በታይላንድ ባንኮክ ውስጥ እንደሚገኘው ማርብል ቴምፕል ያሉ የቡድሂስት ቤተ መቅደሶች ከፍተኛ መስህብነት አላቸው
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቤተ መቅደስ የሚጠብቅ አንድ የቡድሂስት ጋኔን ሐውልትም ሥዕሉ ላይ ይታያል። ከታች ደግሞ የቡድሃ ሐውልት አለ። እነዚህ ነገሮች የቡድሂስት እምነት ተከታይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የተለመዱ እይታዎች ናቸው