ትምህርቱ ከምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ጋር ተቀላቀለ
“ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት ሁሉም ሰው የሚቀበለው ዓለም አቀፋዊ እውነት እንደሆነ አድርጌ አስብ ነበር። በመሆኑም በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ያሉ አንዳንድ ምሁራን ይህን እምነት በጽኑ በመቃወም እንደሚከራከሩ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት እንዴት የሂንዱ እምነት ክፍል ሊሆን እንደቻለ አሁን ሳስበው በጣም ይገርመኛል።”—በሂንዱ እምነት ያደገ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ
1. ሰው ዘላለማዊ ነው የሚለው መሠረተ ትምህርት በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የዳበረበትና የተሰራጨበት ሁኔታ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?
ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው የሚለው ትምህርት ከሂንዱኢዝምና ከሌሎች የምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ጋር የተቀላቀለው እንዴት ነው? ይህ እምነት እያንዳንዱ ሰው ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለውን አመለካከት የሚነካ በመሆኑ ይህ ጥያቄ እነዚህን ሃይማኖቶች የማያውቁትን በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩትንም ሰዎች ትኩረት የሚስብ ነው። የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በዛሬው ጊዜ ባሉት በአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኝ የጋራ ጭብጥ በመሆኑ ጽንሰ ሐሳቡ እንዴት ሊዳብር እንደቻለ ማወቁ የተሻለ ግንዛቤና እውቀት ሊያስጨብጥ ይችላል።
2. ሕንድ በእስያ ውስጥ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ ልታሳድር የቻለችው ለምንድን ነው?
2 በብሪታንያ በሚገኘው የላንካስተር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሃይማኖታዊ ጥናቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ኒኒያን ስማርት እንዲህ ብለዋል:- “ሕንድ በእስያ ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ አሳድራለች። ይህ የሆነው ሕንድ እንደ ሂንዱኢዝም፣ ቡዲዝም፣ ጃይኒዝምና ሲኪዝም የመሳሰሉ በርካታ እምነቶች መፍለቂያ በመሆኗ ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ እምነቶች አንዱ ማለትም ቡዲዝም በመላው ምሥራቅ እስያ ባሕል ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደሩ ነው።” ይህ እምነት ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ብዙ ኅብረተሰቦች “አሁንም ድረስ ሕንድን እንደ መንፈሳዊ ትውልድ አገራቸው አድርገው” እንደሚመለከቷት ኒክሂላናንዳ የተባሉ የሂንዱ ምሁር ተናግረዋል። እንግዲያው ነፍስ አትሞትም የሚለው ይህ ትምህርት ወደ ሕንድና ወደ ሌሎቹ የእስያ አገሮች ሰርጎ ሊገባ የቻለው እንዴት ነው?
የሂንዱኢዝም የሪኢንካርኔሽን ትምህርት
3. አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዳሉት ከሆነ ነፍስ ከአንድ አካል ወደ ሌላ አካል ትሸጋገራለች የሚለው ትምህርት ወደ ሕንድ የገባው በማን አማካኝነት ሊሆን ይችላል?
3 በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በግሪክ ውስጥ ፓይታጎረስና ተከታዮቹ፣ ነፍሳት ሌላ አካል ይዘው መኖር ይቀጥላሉ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ እያራመዱ በነበረበት ወቅት በኢንደስና በጋንጅስ ወንዞች ዳርቻዎች ይኖሩ የነበሩት የሂንዱ ጠበብት ይህንኑ ጽንሰ ሐሳብ እያዳበሩ ነበር። ይህ እምነት “በግሪኩ ዓለምና በሕንድ ውስጥ” በተመሳሳይ ወቅት ላይ ብቅ ማለቱ “እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰተ ነገር ነው ለማለት አዳጋች ነው” ሲሉ ታሪክ ጸሐፊው አርኖልድ ቶይንቤ ተናግረዋል። ቶይንቤ “ከክርስቶስ ልደት በፊት በ8ኛውና በ7ኛው መቶ ዘመናት ወደ ሕንድ፣ ወደ ደቡባዊ ምዕራብ እስያ፣ በጥቁር ባሕር ሰሜናዊ ዳርቻ ወደሚገኘው ደረቅ ምድርና ወደ ባልካንና አናቶሊያን ባሕረ ገብ መሬቶች የፈለሱት ዩራዥያን የሚባሉት ዘላን ሕዝቦች የጋራ [ተጽዕኖ] አሳድረውባቸው ሊሆን ይችላል” የሚል እምነት አላቸው። ወደእነዚህ ቦታዎች የፈለሱት የዩራዥያን ጎሳዎች ሰው ከሞተ በኋላ ወደ ሌላ ፍጡርነት ተለውጦ መኖር ይቀጥላል የሚለውንም ትምህርት ይዘው ወደ ሕንድ እንደተጓዙ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።
4. ነፍስ ከአንድ አካል ወደ ሌላ አካል ትሸጋገራለች የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሂንዱ ጠበብትን የማረከው ለምንድን ነው?
4 የሂንዱኢዝም እምነት የተቋቋመው ይህ ከመሆኑ ከብዙ ዓመታት በፊት ማለትም አርያኖች ወደ ሕንድ በፈለሱበት በ1500 ከዘአበ ገደማ ነው። ሂንዱኢዝም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ነፍስ ከሥጋ የተለየች ከመሆኗም በላይ ከሞት በኋላ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች የሚል እምነት አለው። በመሆኑም ሂንዱዎች የቀድሞ አባቶችን ያመልኩ የነበረ ሲሆን ለሞቱት ወገኖቻቸው ምግብ ያዘጋጁ ነበር። ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ፣ ሰው ሲሞት ነፍሱ ሌላ ፍጡር ሆና ዳግም ትወለዳለች የሚለው ትምህርት ወደ ሕንድ ሲገባ ዓለም አቀፋዊ ችግር ከሆነውና በሰው ልጆች መካከል ከሚገኘው ክፋትና መከራ ጋር የሚታገሉትን የሂንዱ ጠበብት ሳይማርካቸው አልቀረም። የሂንዱ ጠበብት ይህን ትምህርት ከካርማ ሕግ ማለትም ከምክንያትና ከውጤት ሕግ ጋር አንድ ላይ በማጣመር አንድ ሰው በሪኢንካርኔሽን ተለውጦ ዳግም መኖር በሚጀምርበት ጊዜ በቀድሞ ሕይወቱ ለፈጸመው በጎ ምግባር ሽልማት አለዚያም ደግሞ ለመጥፎ ምግባሩ ቅጣት ይቀበላል የሚለውን የሪኢንካርኔሽን ጽንሰ ሐሳብ አዳበሩ።
5. በሂንዱኢዝም እምነት መሠረት የነፍስ የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው?
5 ሆኖም ሂንዱኢዝም ስለ ነፍስ በሚያስተምረው ትምህርት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ሌላም ጽንሰ ሐሳብ ነበር። ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ሌላ አካል ትሸጋገራለች የሚለው ጽንሰ ሐሳብና የካርማ ሕግ በተነደፈበት ጊዜ፣ እንዲያውም ከዚያ አስቀድሞ የብራህማን-አታማን [ታላቁና ዘላለማዊው ብራህማን፣ የሁሉ የበላይ የሆነው ኃይል] ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሐሳብ . . . በሰሜናዊ ሕንድ ጥቂት ምሁራንን ባቀፈ ቡድን ውስጥ ቀስ በቀስ እየዳበረ ሄዶ ነበር።” ይህን አስተሳሰብ ከሪኢንካርኔሽን ጽንሰ ሐሳብ ጋር በማጣመር የአንድ ሂንዱ የመጨረሻ ግብ ከአንድ አካል ወደ ሌላ አካል ከመሸጋገር ዑደት ተላቅቆ የሁሉ የበላይ ከሆነው ኃይል ጋር አንድ መሆን ነው የሚል ፍቺ ሰጡ። ሂንዱዎች ይህን ግብ ዳር ማድረስ የሚቻለው ማኅበራዊ ተቀባይነት ያለው ባሕርይ ለማሳየትና ልዩ የሂንዱ እውቀት ለማካበት በመጣጣር እንደሆነ ያምናሉ።
6, 7. በአሁኑ ጊዜ ያለው የሂንዱኢዝም ሃይማኖት ስለ ወዲያኛው ሕይወት ያለው እምነት ምንድን ነው?
6 በዚህ መንገድ የሂንዱ ጠበብት ነፍሳት ከአንዱ አካል ወደ ሌላው አካል ይሸጋገራሉ የሚለውን ትምህርት ከካርማ ሕግና ከብራህማን ጽንሰ ሐሳብ ጋር በማጣመር ከሪኢንካርኔሽን መሠረተ ትምህርት ጋር እንዲጣጣም አድርገውታል። በሕንድ የሜክሲኮ የቀድሞ አምባሳደር የነበሩትና የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ባለቅኔው ኦክታቢዮ ፓዝ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሂንዱኢዝም እየተስፋፋ ሲሄድ . . . በብራህማኒዝም፣ በቡዲዝምና በሌሎች የእስያ ሃይማኖቶች ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው እምነት ማለትም ነፍሳት ከአንዱ አካል ወደ ሌላው አካል እየተሸጋገሩ ይኖራሉ የሚለው ሜቴምሳይኮሲስ የተባለውም ጽንሰ ሐሳብ አብሮ ተስፋፍቷል።”
7 የሪኢንካርኔሽን መሠረተ ትምህርት የዘመናዊው ሂንዱኢዝም ምሰሶ ነው። ኒክሂላናንዳ የተባሉት የሂንዱ ፈላስፋ “ዘላለማዊነት የተመረጡ ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚያገኙት መብት ሳይሆን ሁሉም ሰው በዘር የሚወርሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንደሆነ እያንዳንዱ ቀናኢ ሂንዱ በሚገባ ያምናል” ብለዋል።
የዳግም መወለድ ዑደት በቡዲዝም እምነት
8-10. (ሀ) ቡዲዝም ለሕልውና የሚሰጠው ፍቺ ምንድን ነው? (ለ) አንድ የቡዲስት ምሁር ዳግም መወለድን ያብራሩት እንዴት ነው?
8 ቡዲዝም የተመሠረተው በ500 ከዘአበ ገደማ በሕንድ ውስጥ ነው። የቡዲስት አፈ ታሪክ እንደሚለው ከሆነ ቡዲዝምን ያቋቋመው መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን ከፈነጠቀለት በኋላ ቡድሃ ተብሎ መጠራት የጀመረው የሕንዱ ልዑል ሲድሃራታ ጉታማ ነው። ቡዲዝም ከሂንዱኢዝም የመነጨ በመሆኑ ትምህርቶቹ በአንዳንድ መንገዶች ከሂንዱኢዝም ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። በቡዲዝም እምነት መሠረት ሕልውና የማያቋርጥ የዳግም መወለድና የሞት ዑደት ነው፤ ከሂንዱኢዝም እምነት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታም እያንዳንዱ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥመው ሁኔታ በቀድሞ ሕይወቱ ባደረጋቸው ነገሮች ላይ የተመካ ነው የሚል አመለካከት አለ።
9 ሆኖም ቡዲዝም ሕልውናን የሚገልጸው ነፍስ ከሞት በኋላ ሕያው ሆና ትቀጥላለች በሚል መልክ አይደለም። “[ቡድሃ] በሰው ነፍስ ውስጥ በምኞት ብቻ እርስ በርሳቸው የተጣመሩ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ተከታታይ የሆኑ የተለያዩ የሥነ ልቦና ደረጃዎች እንዳሉ ተገንዝቧል” ሲሉ አርኖልድ ቶይንቤ ተናግረዋል። ሆኖም ቡድሃ የሆነ ነገር ማለትም የሆነ የሥነ ልቦና ደረጃ ወይም ኃይል ከአንድ ሕይወት ወደ ሌላ ሕይወት ይሸጋገራል የሚል እምነት አለው። የቡዲስት ምሁር የሆኑት ዶክተር ዋልፖላ ራሁል እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:-
10 “ሰው የሥጋዊና የአእምሯዊ ኃይሎች ጥምረት ውጤት ነው። ሞት ብለን የምንጠራው ነገር ሥጋዊው አካል ሥራውን ሙሉ በሙሉ ማቆሙን ያመለክታል። እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ሥራውን ካቆመው አካል ጋር አብረው ያከትማሉ? ቡዲዝም ‘አያከትሙም’ ባይ ነው። ለመኖር፣ በሕይወት ለመቀጠል፣ ዳግም ለመወለድ መፈለግ፣ መመኘትና መጓጓት ሕይወት የተባለን ነገር በጠቅላላ፣ ሕልውናን በጠቅላላ፣ አልፎ ተርፎም መላውን ዓለም የሚያንቀሳቅስ ታላቅ ኃይል ነው። በዓለም ላይ ያለው ከሁሉ የላቀ ኃይል ይህ ነው። በቡዲዝም እምነት መሠረት ይህ ኃይል ሥራውን ከሚያቆመው ማለትም ከሚሞተው አካል ጋር አብሮ አይሞትም፤ ከዚህ ይልቅ በሌላ መልክ ዳግመኛ ወደ ሕልውና ይመጣል፣ ይህም ዳግም መወለድ ይባላል።”
11. ቡዲስቶች ስለ ወዲያኛው ሕይወት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?
11 ቡዲስቶች ስለ ወዲያኛው ሕይወት ያላቸው አመለካከት የሚከተለው ነው:- ግለሰቡ ከዳግም መወለድ ዑደት በመላቀቅ የመጨረሻውን ግብ ማለትም ኒርቫናን ካልጨበጠ በቀር ሕልውናው ዘላለማዊ ነው። ኒርቫና ዘላለማዊ ተድላና ደስታ ማግኘትም ሆነ የሁሉ የበላይ ከሆነው ኃይል ጋር አንድ መሆን ማለት አይደለም። ከሕልውና ውጪ መሆን ማለት ነው፤ ከሰብዓዊ ሕልውና ባሻገር ያለ “ሞት የሌለበት ቦታ” ነው። ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂየት ዲክሽነሪ “ኒርቫና” የሚለውን ቃል “ከጭንቀት፣ ከሥቃይ ወይም ደግሞ ከውጫዊ እውነታ ነፃ የሚሆኑበት ቦታ ወይም ሁኔታ” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ቡዲስቶች ዘላለማዊነትን ከመሻት ይልቅ ኒርቫናን በማግኘት ዘላለማዊነትን አልፈው እንዲሄዱ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል።
12-14. የተለያዩ የቡዲዝም እምነቶች ዘላለማዊነትን የሚያስተምሩት እንዴት ነው?
12 ቡዲዝም በእስያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሥፍራዎች እየተስፋፋ ሲሄድ የየአካባቢውን እምነቶች ለማቀፍ ሲል በትምህርቶቹ ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎች አድርጓል። ለምሳሌ ያህል በቻይናና በጃፓን ጎልቶ የሚታየው ማሃያና ቡዲዝም የሚባለው አንዱ ዓይነት የቡዲዝም እምነት በሰማያዊ ቦዲሳትቫዎች ወይም ወደፊት በሚመጡ ቡድሃዎች ያምናል። ቦዲሳትቫዎች ሌሎች ሰዎችን ለማገልገልና ኒርቫናን እንዲያገኙ ለመርዳት ሲሉ ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ጊዜያት ዳግም ለመወለድ እንዲችሉ ኒርቫናቸውን ለሌላ ጊዜ ያስተላልፉታል። ስለዚህ አንድ ሰው ኒርቫናን ካገኘም በኋላ እንኳ በዳግም መወለድ ዑደት ለመቀጠል ሊመርጥ ይችላል ማለት ነው።
13 በተለይ በቻይናና በጃፓን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ሌላው ማስተካከያ በቡድሃ አሚታብ ወይም አሚዳ የተፈለሰፈው በምዕራብ የምትገኘው የጸዳች ምድር መሠረተ ትምህርት ነው። የቡድሃን ስም በእምነት የሚጠሩ ሰዎች የመጨረሻውን መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን ለማግኘት የሚያስችሉ የተሻሉ ሁኔታዎች ባሉባት የጸዳች ምድር ወይም ገነት ውስጥ ዳግም ይወለዳሉ። ይህ ትምህርት ምን ዓይነት አስተሳሰብ አስከትሏል? ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፕሮፌሰር ስማርት እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ብዙ ሰዎች በአንዳንዶቹ የማሃያና ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በግልጽ የተጠቀሱትን ውብ የገነት ገጽታዎች ከኒርቫና አስበልጠው በማየት የመጨረሻ ታላቅ ግብ አድርገው መመልከታቸው ምንም አያስደንቅም።”
14 የቲቤት ቡዲዝም ሌሎች የአካባቢውን እምነቶች ቀላቅሎ ይዟል። ለምሳሌ ያህል ስለ ሙታን የሚናገረው የቲቤቶች መጽሐፍ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ዳግም ከመወለዱ በፊት ስለሚደርስበት ሁኔታ ይገልጻል። የሁሉ የበላይ የሆነው ኃይል ደማቅ ብርሃኑን በሙታን ላይ እንደሚያበራና ብርሃኑን መቋቋም ያልቻሉ ነፃ ከመውጣት ይልቅ ዳግም መወለዳቸውን እንደሚቀጥሉ ይናገራል። የተለያየ መልክ ይዞ የሚገኘው የቡዲዝም እምነት የዘላለማዊነትን ጽንሰ ሐሳብ እንደሚያስተምር በግልጽ መረዳት ይቻላል።
በጃፓን የሺንቶ ሃይማኖት የቀድሞ አባቶች አምልኮ
15-17. (ሀ) የቀድሞ አባቶች መናፍስት አምልኮ በሺንቶ ውስጥ የዳበረው እንዴት ነው? (ለ) ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት በሺንቶ ሃይማኖት ውስጥ መሠረታዊ እምነት የሆነው እንዴት ነው?
15 በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ቡዲዝም ወደ ጃፓን ከመግባቱ በፊት በጃፓን ውስጥ ሃይማኖት ነበር። ይህ ሃይማኖት የራሱ የሆነ ስም ያልነበረው ከመሆኑም በላይ ከሕዝቡ ግብረ ገብና ባሕል ጋር የተቆራኙ እምነቶችን ያቀፈ ነበር። ይሁን እንጂ ቡዲዝም በጃፓን ውስጥ መስፋፋት ሲጀምር ይኼኛውን የጃፓን ሃይማኖት ከመጤው እምነት ለይቶ ማስቀመጡ የግድ ሆነ። በመሆኑም “የአማልክቱ መንገድ” የሚል ትርጉም ያለው “ሺንቶ” የሚል ስያሜ ተሰጠው።
16 ጥንታዊው ሺንቶ ስለ ወዲያኛው ሕይወት ያለው እምነት ምንድን ነው? እርጥበት አዘል በሆነ መሬት ላይ የሩዝ ልማት ማካሄድ ሲጀመር “እርጥበት አዘል በሆነው መሬት ላይ የግብርና ሥራውን ለማካሄድ በሚገባ የተደራጁና ቋሚ የሆኑ ማኅበረሰቦች አስፈልገው ነበር” ሲል ኮዳንሻ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ጃፓን ይገልጻል፤ “በመሆኑም ከእርሻ ሥራ ጋር የተያያዙ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየዳበሩ ሄዱ፤ እነዚህ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ከጊዜ በኋላ በሺንቶ ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።” እነዚህ የጥንት ሰዎች የሞቱ ሰዎችን ነፍሳት በመፍራት የእነዚህን ነፍሳት ፍላጎት ማርካት የሚችሉባቸውን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች አቋቋሙ። ይህም ከጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ አባቶች መናፍስት አምልኮነት ተለወጠ።
17 በሺንቶ እምነት መሠረት የአንድ “ሟች” ነፍስ ስብዕናዋን የማትለውጥ ቢሆንም እንኳ በሞት አማካኝነት ትረክሳለች። የሟቹ ዘመድ እንደ ተስካር ያለ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሲፈጽም ነፍሷ ከተንኮል ሁሉ ጠርታ ሰላማዊና ደግ ትሆናለች። የዚህ የቀድሞ አባት መንፈስ ከጊዜ በኋላ አምላክ ወይም ጠባቂ ይሆናል። ሺንቶ ከቡዲዝም ጋር ጎን ለጎን የኖረ ሃይማኖት በመሆኑ የገነትን መሠረተ ትምህርት ጨምሮ አንዳንድ የቡዲስት ትምህርቶችን ወርሷል። በመሆኑም የዘላለማዊነት እምነት በሺንቶ ሃይማኖት ውስጥ መሠረታዊ እምነት ሆኖ እናገኘዋለን።
ዘላለማዊነት በታኦይዝም ሃይማኖት፣ የቀድሞ አባቶች አምልኮ በኮንፊሺያኒዝም እምነት
18. ታኦይስቶች ዘላለማዊነትን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው?
18 ታኦይዝም የተመሠረተው በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በቻይና ይኖር እንደነበረ በሚነገርለት ላኦድ-ዘ በተባለ ሰው አማካኝነት ነው። በታኦይዝም እምነት መሠረት የሕይወት ግብ ሰብዓዊ እንቅስቃሴን ከታኦ ማለትም ከተፈጥሮ መንገድ ጋር አስማምቶ መኖር ነው። ታኦዎች ስለ ዘላለማዊነት ያላቸውን አመለካከት በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል:- ታኦ አጽናፈ ዓለምን የሚገዛ መሠረታዊ ሥርዓት ነው። ታኦ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም። አንድ ሰው ከታኦ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር በዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ውስጥ ተሳትፎ ማድረግና ዘላለማዊ መሆን ይችላል።
19-21. የታኦይስቶች መላ ምት ምን ዓይነት ሙከራዎች ለማድረግ አነሳስቷቸዋል?
19 ታኦይስቶች ከተፈጥሮ ጋር አንድ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ ከጊዜ በኋላ የተፈጥሮ ዘላለማዊነትና ተፈጥሮ ራሱን ከአዳዲስ ሁኔታዎችና ለውጦች ጋር በቀላሉ ማስማማት መቻሉ ትኩረታቸውን ሳበው። አንድ ሰው ከታኦ ወይም ከተፈጥሮ መንገድ ጋር ተስማምቶ በመኖር የተፈጥሮን ምሥጢር በተወሰነ ደረጃ ማወቅና አካላዊ ጉዳትን፣ በሽታንና አልፎ ተርፎም ሞትን መቋቋም ይችል ይሆናል የሚል መላ ምት ሰነዘሩ።
20 ታኦይስቶች አካላዊ እርጅናንና ሞትን ሊያዘገይ ይችላል በሚል ማሰላሰል፣ የአተነፋፈስ ልምምድ ማድረግና ጥሩ የአመጋገብ ልማድ መከተል ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ በደመናዎች ላይ መብረር ስለሚችሉና እንደፈለጋቸው መታየትና መሠወር ስለሚችሉ እንዲሁም በጤዛ ወይም በምትሃታዊ ፍሬዎች አማካኝነት በቅዱስ ተራራዎች ወይም በጣም ርቀው በሚገኙ ደሴቶች ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ዓመታት ስለኖሩ ዘላለማዊ አካላት የሚናገሩ አፈ ታሪኮች ተነዙ። በ219 ከዘአበ ንጉሠ ነገሥት ቺን ሺር ሁዋንግ ዲ የዘላለማውያን መኖሪያ ናት ተብላ በአፈ ታሪክ የምትጠቀሰውን የፔንግላይ ደሴት አግኝተው ዘላለማዊነትን የሚያስገኝ ተክል ይዘውላቸው እንዲመጡ 3,000 ወንዶችና ሴቶች ልጆችን የጫኑ በርካታ መርከቦችን ልከው እንደነበረ የቻይና ታሪክ ይገልጻል። ሕይወትን ያራዝማል የተባለውን ንጥረ ነገር ይዘውላቸው እንዳልተመለሱ ምንም ጥርጥር የለውም።
21 ታኦይስቶች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ባደረጉት ጥረት በመካከለኛው ዘመን በነበረው ኬሚስትሪ ተጠቅመው ዘላለማዊነትን የሚያስገኙ እንክብሎችን ለማዘጋጀት ሙከራ አድርገዋል። በታኦይስቶች አመለካከት መሠረት ሕይወት ዪን እና ያንግ (እንስትና ተባዕት) የተባሉት ተቃራኒ ኃይሎች ጥምረት ውጤት ነው። ስለዚህ የዘመኑ ኬሚስትሪ ጠበብት እርሳስን (ጠቆር ያለ ቀለም ያለው ወይም ዪን) ከሜርኩሪ (ደማቅ ቀለም ያለው ወይም ያንግ) ጋር በመቀላቀል የተፈጥሮን ሂደት ለመከተል ሞክረዋል፤ እንዲህ በማድረግም ዘላለማዊነትን የሚያስገኝ እንክብል መሥራት እንችላለን ብለው አስበው ነበር።
22. ቡዲዝም በቻይና ሃይማኖታዊ ሕይወት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን ውጤት አስከትሏል?
22 በሰባተኛው መቶ ዘመን እዘአ ቡዲዝም ወደ ቻይና ሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ሰርጎ ገባ። በዚህም ሳቢያ የቡዲዝምን ትምህርቶች፣ መናፍስታዊ ድርጊቶችንና የቀድሞ አባቶችን አምልኮ ያቀፈ እምነት ተፈጠረ። ፕሮፌሰር ስማርት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ቡዲዝምም ሆነ ታኦይዝም በጥንቱ የቻይና የቀድሞ አባቶች አምልኮ በመጠኑ ይታመንበት የነበረውን የወዲያኛውን ሕይወት እምነት በሚገባ አዳብረዋል።”
23. ኮንፊሽየስ የቀድሞ አባቶችን አምልኮ በተመለከተ ምን አቋም ነበረው?
23 በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረውና ፍልስፍናው ለኮንፊሺያኒዝም ሃይማኖት መሠረት የጣለው ሌላው የታወቀ የቻይና ሃይማኖታዊ ጠቢብ ኮንፊሽየስ ስለ ወዲያኛው ሕይወት ብዙ ትንተና አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ ሥነ ምግባርና ማኅበራዊ ተቀባይነት ያለው ጠባይ የማሳየትን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። ሆኖም የቀድሞ አባቶችን አምልኮ የሚደግፍ ሲሆን ለቀድሞ አባቶች መናፍስት የሚካሄደውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በጥብቅ መከተል እንደሚገባ ጠንከር አድርጎ ገልጿል።
ሌሎች የምሥራቅ ሃይማኖቶች
24. ጃይኒዝም ስለ ነፍስ ምን ብሎ ያስተምራል?
24 ጃይኒዝም በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በሕንድ ውስጥ የተቋቋመ ሃይማኖት ነው። የሃይማኖቱ መሥራች የሆነው ማሃቪራ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ዘላለማዊ ነፍሳት እንዳላቸውና ነፍስ ከካርማ ቀንበር መላቀቅ የምትችለው ከልክ በላይ ራስን በመጣልና ራስን በራስ በመገሰጽ እንዲሁም በሁሉም ፍጥረታት ላይ አንዳችም ዓይነት ጥቃት ላለመሰንዘር ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ብቻ እንደሆነ ገልጿል። ጃይኒዎች እስከ አሁንም ድረስ በዚህ ያምናሉ።
25, 26. በሲኪይዝም ሃይማኖትም ውስጥ የትኞቹ የሂንዱ እምነቶች ይገኛሉ?
25 አሥራ ዘጠኝ ሚልዮን ተከታዮች ያሉት ሲኪዝምም የተመሠረተው ሕንድ ውስጥ ነው። ይህ ሃይማኖት የተቋቋመው ናናክ የተባለ የሂንዱ ሃይማኖታዊ መምህር ትክክለኛ ናቸው ያላቸውን የሂንዱኢዝምና የእስልምና ትምህርቶች አንድ ላይ በመቀላቀል አንድ ሃይማኖት በፈለሰፈበት በ16ኛው መቶ ዘመን ነው። ሲኪዝም የሂንዱ እምነቶች በሆኑት በነፍስ ዘላለማዊነት፣ በሪኢንካርኔሽንና በካርማ ያምናል።
26 ሥጋ ከሞተም በኋላ ሕይወት ይቀጥላል የሚለው እምነት በአብዛኞቹ የምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እምነት ነው። ይሁን እንጂ ሕዝበ ክርስትና፣ የአይሁድ ሃይማኖትና እስልምና በዚህ ረገድ ያላቸው እምነት ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ማዕከላዊ እስያ
ካሽሚር
ቲቤት
ቻይና
ኮሪያ
ጃፓን
ባናራስ
ሕንድ
ቡድ ጋያ
ማያንማር
ታይላንድ
ስሪ ላንካ
ካምቦዲያ
ጃቫ
3ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ
1ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ
1ኛው መቶ ዘመን እዘአ
4ኛው መቶ ዘመን እዘአ
6ኛው መቶ ዘመን እዘአ
7ኛው መቶ ዘመን እዘአ
ቡዲዝም በመላው ምሥራቅ እስያ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሪኢንካርኔሽን የሂንዱኢዝም ምሰሶ ነው
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታኦይስቶች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው በመኖር ዘላለማዊ ለመሆን ይጥራሉ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮንፊሽየስ የቀድሞ አባቶችን አምልኮ ይደግፍ ነበር