ከሞት በኋላ ሕይወት—ሰዎች ምን ብለው ያምናሉ?
“በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?”—ኢዮብ 14:14
1, 2. ብዙ ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት በሚያጡበት ጊዜ መጽናኛ ለማግኘት የሚሞክሩት እንዴት ነው?
በኒው ዮርክ ከተማ በአንድ የሬሳ ማቆያ ክፍል ውስጥ የሟቹ ቤተሰብና ጓደኞች በካንሰር በሽታ ሕይወቱ የተቀጨውን የ17 ዓመቱን ልጅ አስከሬን በያዘው ክፍት የሬሳ ሳጥን አጠገብ ጸጥ ብለው በሰልፍ ያልፋሉ። በሐዘን የተዋጠችው እናቱ እንባዋን እያፈሰሰች “ይህን ጊዜ ቶሚ ደስ ብሎታል። አምላክ ቶሚ በሰማይ ከእሱ ጋር እንዲሆን ስለፈለገ ወስዶታል” እያለች በተደጋጋሚ ትናገራለች። እሷ የተማረችውም ሆነ የምታምነው ይህንን ነው።
2 ወደ 11,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው ጃምናጋር በምትባል አንዲት የሕንድ ከተማ ከሦስት ወንዶች ልጆች የመጀመሪያው ልጅ የሞተውን አባታቸውን አስከሬን ለማቃጠል የተዘጋጀውን የተረበረበ እንጨት በእሳት ያያይዛል። እሳቱ ሲቀጣጠል ከሚያሰማው ድምፅ በላይ ብራህማው “ለዘላለም የማትሞተው ነፍስ የሁሉ የበላይ ከሆነው ኃይል ጋር አንድ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንድትገፋበት እንመኛለን” የሚሉትን የሳንስክሪት ማንትራዎች ቃላት እየደጋገመ ይናገራል።
3. ባለፉት ዘመናት ሰዎች የትኞቹን ጥያቄዎች ሲጠይቁ ኖረዋል?
3 የሞት ጥላ በዙሪያችን አጥልቶ ይገኛል። (ሮሜ 5:12) ሁሉም ነገር የሚደመደመው በሞት ይሆን ብለን ማሰባችን የማይቀር ነው። ኢዮብ የሚባል አንድ ጥንታዊ ታማኝ የይሖዋ አምላክ አገልጋይ ስለ ተክሎች ተፈጥሯዊ ዑደት እንዲህ ብሏል:- “ዛፍ ቢቆረጥ ደግሞ ያቆጠቁጥ ዘንድ፣ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው።” ታዲያ ስለ ሰዎች ምን ለማለት ይቻላል? ኢዮብ “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?” ሲል ጠይቋል። (ኢዮብ 14:7, 14) ባለፉት ዘመናት በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ኖረዋል:- “ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? ካለስ ምን ዓይነት ሕይወት? ሰዎች ምን ብለው ያምናሉ? ለምንስ?
ጭብጡ አንድ፣ መልሱ ግን ብዙ
4. በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ምን ብለው ያምናሉ?
4 ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች ሰው ከሞተ በኋላ ወደ ሰማይ አለዚያም ደግሞ ወደ ሲኦል ይሄዳል ብለው ያምናሉ። ሂንዱዎች ደግሞ በሪኢንካርኔሽን ያምናሉ። በእስልምና እምነት መሠረት ከሞት በኋላ በሚኖረው የፍርድ ቀን አላህ የእያንዳንዱን ሰው አኗኗር በመመርመር ወደ ገነት አለዚያም ወደ እሳታማ ሲኦል እንዲገባ ይወስናል። በአንዳንድ አገሮች ሙታንን በተመለከተ ያሉት እምነቶች የአካባቢው ባሕልና የስመ ክርስትና ትምህርቶች ድብልቅ ውጤቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል በስሪ ላንካ ቡድሂስቶችም ሆኑ ካቶሊኮች የቤተሰባቸው አባል ሲሞት የቤቱን በሮችና መስኮቶች ወለል አድርገው ይከፍታሉ። የሬሳ ሳጥኑን የሟቹ እግር ፊት ለፊት ባለው በር ትይዩ እንዲሆን አድርገው ያስቀምጡታል። እንዲህ ማድረጋቸው የሟቹ መንፈስ ወይም ነፍስ ከቤቱ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል ብለው ያምናሉ። በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ብዙ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች አንድ ሰው ሲሞት ማንም ሰው የሟቹን መንፈስ እንዳያይ ለማድረግ ሲባል መስተዋቶችን ሁሉ የመሸፈን ልማድ አላቸው። ከዚያም ሰውየው ከሞተ ከ40 ቀን በኋላ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ የሰውየው ነፍስ ወደ ሰማይ ማረጓን በማስመልከት ድግስ ይደግሳሉ።
5. አብዛኞቹ ሃይማኖቶች በየትኛው መሠረታዊ እምነት ይስማማሉ?
5 እንዲህ ዓይነት የሐሳብ ልዩነት ቢኖርም አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ቢያንስ ቢያንስ በአንድ መሠረታዊ ነጥብ ላይ የሚስማሙ ይመስላሉ። ብቻ ነፍስም ትባል መንፈስ ወይም ጣረሞት ፈጽሞ የማትሞትና ሥጋ ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነገር በሰው ውስጥ አለች ብለው ያምናሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶችና ኑፋቄዎች በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት ይደግፋሉ። ይህ እምነት በአይሁድ ሃይማኖትም ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሠረተ ትምህርት ነው። የሂንዱኢዝም ሃይማኖት የሚያስተምረው የሪኢንካርኔሽን ትምህርት በዚህ እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ሙስሊሞች ሥጋ ከሞተ በኋላ ነፍስ ሕያው ሆና ትቀጥላለች ብለው ያምናሉ። የአውስትራሊያ አቦርጂኖች፣ የአፍሪካ አኒሚስቶች፣ የሺንቶይዝምና አልፎ ተርፎም የቡዲዝም ተከታዮች በዚሁ ጭብጥ ላይ ተመሥርተው የተለያዩ ትምህርቶች ያስተምራሉ።
6. አንዳንድ ምሁራን ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት እንዴት ይመለከቱታል?
6 በሌላ በኩል ደግሞ ሕይወት በሞት ያከትማል ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። ስሜታዊውና አእምሯዊው ሕይወት ከሥጋ በተለየችና ሰብዓዊ ባልሆነች የማትታይና የማትጨበጥ ነፍስ ውስጥ መኖሩን ይቀጥላል የሚለው አስተሳሰብ ለእነዚህ ሰዎች አይዋጥላቸውም። የ20ኛው መቶ ዘመን ምሁር የሆኑት ስፔናዊው ሚገል ደ ኡናሙኖ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ነፍስ አትሞትም ብሎ ማመን ነፍስ ዘላለማዊ ሆና እንድትኖር መመኘት ማለት ነው፤ ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ምኞት አንድ ሰው ምክንያታዊነትን ወደ ጎን ገሸሽ እንዲያደርግ ተጽዕኖ ያሳድርበታል።” እንዲህ ያለ እምነት ከነበራቸው የተለያዩ ሰዎች መካከል የታወቁት የጥንት ፈላስፎች አርስቶትልና ኤፊቆሮስ፣ ሐኪሙ ሂፖክራተስ፣ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ ዴቪድ ሁም፣ አረቡ ምሁር አቬሮዊዝና ሕንድ ነፃነቷን ባወጀች ጊዜ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት ጃዋሃርላል ኔህሩ ይገኙበታል።
7. ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት በሚመለከት የትኞቹን ዋና ዋና ጥያቄዎች መመርመር ያስፈልጋል?
7 እነዚህን የመሳሰሉ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አመለካከቶችና እምነቶች መጋረጣቸው የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንድንጠይቅ ያደርጉናል:- በእርግጥ የማትሞት ነፍስ አለችን? ነፍስ በእርግጥ ሟች ከሆነች ታዲያ ነፍስ አትሞትም የሚለው የሐሰት ትምህርት በዛሬው ጊዜ ያሉት የአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ዋነኛ ክፍል ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ሐሳቡ የመነጨው ከየት ነው? የወደፊት ሕይወታችን በዚህ ላይ የተመካ በመሆኑ ለእነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛና አጥጋቢ መልሶች ማግኘታችን እጅግ አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:19) በመጀመሪያ ግን፣ ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት እንዴት እንደተጸነሰ እንመርምር።
የመሠረተ ትምህርቱ መወለድ
8. ሶቅራጥስና ፕላቶ ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት በማስፋፋት ረገድ ምን ሚና ተጫውተዋል?
8 በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖሩ የነበሩት የግሪክ ፈላስፎች ሶቅራጥስና ፕላቶ ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው የሚለውን ትምህርት ካስፋፉት ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ሆኖም ሐሳቡን ያመነጩት እነሱ አልነበሩም። ይሁንና ጽንሰ ሐሳቡን በማዳበርና ወደ ፍልስፍና ትምህርትነት በመለወጥ በእነሱ ዘመን ለነበረውና ከእነሱ ዘመን በኋላ ለመጡት የተማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይበልጥ ማራኪ አድርገው ሊያቀርቡት ችለዋል። ጽንሰ ሐሳቡን እነሱ ያዳብሩት እንጂ በጥንቷ የፋርስ ግዛት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዞራስትሪያውያን እና ከእነሱ በፊትም ግብጻውያን ነፍስ አትሞትም ብለው ያምኑ ነበር። አሁን የሚነሳው ጥያቄ የዚህ ትምህርት ምንጭ ምንድን ነው? የሚል ነው።
9. በግብጽ፣ በፋርስና በግሪክ ጥንታዊ ልማዶች ላይ ተጽእኖ አሳድሮ የነበረው ነገር ምንድን ነው?
9 “በጥንቱ ዓለም” ይላል ዘ ሪሊጂን ኦቭ ባቢሎኒያ ኤንድ አሲሪያ የተባለው መጽሐፍ፣ “የባቢሎን ሃይማኖት በግብጽ፣ በፋርስና በግሪክ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።” መጽሐፉ በመቀጠል የግብጻውያንን ሃይማኖታዊ እምነቶች አስመልክቶ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በኤል አማርና ፅላቶች ላይ እንደተገለጸው በቀድሞ ዘመን በግብጽና በባቢሎኒያ መካከል ከነበረው ግንኙነት አንጻር ሲታይ የባቢሎናውያን አስተሳሰቦችና ልማዶች ወደ ግብጻውያን የጣዖት አምልኮ የሚሰርጹባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ምንም አያጠራጥርም።”a የጥንቶቹን የፋርስና የግሪክ ልማዶችንም በተመለከተ ተመሳሳይ ነገር ለማለት ይቻላል።
10. ባቢሎናውያን ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ምን አመለካከት ነበራቸው?
10 ይሁን እንጂ የጥንቶቹ ባቢሎናውያን በነፍስ አለመሞት ያምኑ ነበር? በዚህ ነጥብ ላይ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በሚገኘው የፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ጁንየር ፕሮፌሰር ሞሪስ ያስትሮው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሕዝቡም ሆነ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ የነበራቸው መሪዎች [የባቢሎኒያ ማለት ነው] ሕይወት ከናካቴው ከሕልውና ውጪ ይሆናል ብለው አስበው አያውቁም። [በእነሱ አመለካከት] ሞት አንድ ሰው ወደ ሌላ ዓይነት ሕይወት የሚሸጋገርበት ድልድይ ነው፤ አንድ ሰው ዘላለማዊ ሊሆን አይችልም [በአሁኑ ሕይወት ማለት ነው] የሚለው እምነታቸው ማንም ሰው በሞት አማካኝነት ወደ ሌላ ሕይወት ከመሸጋገር ሊያመልጥ አይችልም የሚለውን አመለካከታቸውን ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው።” አዎን፣ ባቢሎናውያንም ሕይወት ከሞት በኋላም በሌላ መልክ መኖሩን ይቀጥላል ብለው ያምናሉ። እንዲህ ዓይነት እምነት ያላቸው በመሆኑም አንድ ሰው ሲሞት ሰውየው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀምባቸውን ዕቃዎች አንድ ላይ ይቀብራሉ።
11, 12. ከጥፋት ውኃ በኋላ ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት የተወለደው የት ነበር?
11 ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በጥንቷ ባቢሎንም የነበረ ትምህርት እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይህ ትኩረትን የሚስብ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት የባቢሎን ወይም የባቤል ከተማ የተመሠረተችው ከኖህ የልጅ ልጅ በተወለደው በናምሩድ አማካኝነት በመሆኑ ትኩረትን የሚስብ ነው። በኖህ ዘመን ከደረሰው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት ብቻ ነበር። ናምሩድ ‘ይሖዋን የሚቃወም’ ሰው ከመሆኑም በተጨማሪ እሱም ሆነ ተከታዮቹ ‘ስማቸውን ለማስጠራት’ ይፈልጉ ነበር። በመሆኑም ከተማዋን በመቆርቆርና አንድ ትልቅ ግንብ በመገንባት ናምሩድ አንድ የተለየ ሃይማኖት አቋቋመ።—ዘፍጥረት 10:1, 6, 8-10፤ 11:1-4
12 ናምሩድ የሞተው በሰው እጅ ተገድሎ ነው የሚል ከጥንት ጀምሮ የሚነገር አፈ ታሪክ አለ። ናምሩድ ከሞተ በኋላ ባቢሎናውያን ከተማቸውን የመሠረተና የገነባ የመጀመሪያ ንጉሥ አድርገው በመመልከት ከፍተኛ ክብር እንደሚሰጡት የታወቀ ነው። ማርዱክ (ሜሮዳክ) የተባለው አምላክ የባቢሎን መሥራች ነው ተብሎ ስለሚታመንና በርካታ የባቢሎን ነገሥታት በስሙ ይጠሩ ስለነበር አንዳንድ ምሁራን፣ ማርዱክ ባቢሎናውያን ያመልኩት የነበረውን ናምሩድን ይወክላል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። (2 ነገሥት 25:27፤ ኢሳይያስ 39:1፤ ኤርምያስ 50:2) ይህ አባባል ትክክል ከሆነ ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው የሚለው አስተሳሰብ ሌላው ቢቀር ናምሩድ በሞተበት ዘመን ይታመንበት ነበር ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ የታሪክ ገጾች እንደሚያሳዩት ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት የተወለደው ከጥፋት ውኃ በኋላ በባቤል ወይም በባቢሎን ውስጥ ነው።
13. ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በምድር ላይ የተስፋፋው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
13 መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ እንደሚያሳየው አምላክ በባቤል የነበሩትን ግንበኞች ቋንቋ በመዘበራረቅ ጥረታቸውን አጨናገፈ። እርስ በርስ ሊግባቡ ባለመቻላቸው የግንባታ ሥራቸውን ትተው “በምድር ሁሉ ላይ” ተበታተኑ። (ዘፍጥረት 11:5-9) የእነዚህ ግንበኞች ቋንቋ ቢለወጥም አስተሳሰባቸውና ጽንሰ ሐሳባቸው ግን አለመለወጡን ልናስታውስ ይገባል። በመሆኑም በሄዱበት ሁሉ ሃይማኖታዊ አስተሳሰባቸውን ይዘው ተበታተኑ። በዚህ መንገድ ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት ጨምሮ ባቢሎናዊ የሃይማኖት ትምህርቶች በመላው ምድር ላይ በመሰራጨት የታላላቆቹ የዓለም ሃይማኖቶች መሠረት ሆኑ። ይህም በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ “ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት” በማለት በትክክል የሚገልጻት የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ተቋቋመች።—ራእይ 17:5
የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ወደ ምሥራቅ ተስፋፋ
14. የባቢሎናውያን ሃይማኖታዊ እምነቶች ወደ ንዑስ አህጉሪቷ ሕንድ የተሰራጩት እንዴት ነበር?
14 ከ3,500 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነጣ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው የአርያን ሰዎች ከሰሜን ምዕራብ ተነስተው በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው በፓኪስታንና በሕንድ ውስጥ ወደሚገኘው የኢንደስ ሸለቆ በብዛት እንደፈለሱ አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች ይናገራሉ። ከዚያም በመነሣት በጋንጅስ ወንዝ ዙሪያ በሚገኙ ሜዳማ ሥፍራዎችና በመላው ሕንድ ተሰራጩ። አንዳንድ ኤክስፐርቶች እንደሚሉት የእነዚህ ፈላሾች ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች በጥንቶቹ የኢራንና የባቢሎን ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። እነዚህ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች የሂንዱኢዝም ሥረ መሠረት ሆኑ።
15. የማትሞት ነፍስ አለች የሚለው ትምህርት በዘመናዊው ሂንዱኢዝም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የቻለው እንዴት ነበር?
15 ሕንድ ውስጥ ነፍስ አትሞትም የሚለው አስተሳሰብ የሪኢንካርኔሽንን መሠረተ ትምህርት ይዞ ብቅ አለ። ዓለም አቀፋዊ ችግር ከሆነውና በሰው ልጆች መካከል ከሚገኘው ክፋትና መከራ ጋር ይታገሉ የነበሩት የሂንዱ ጠበብት የካርማ ሕግ እየተባለ የሚጠራውን የምክንያትና የውጤት ሕግ አገኙ። ይህን ሕግ ነፍስ አትሞትም ከሚለው እምነት ጋር በማጣመር አንድ ሰው በቀድሞ ሕይወቱ ለፈጸመው በጎ ምግባር ሽልማት አለዚያም ደግሞ ለመጥፎ ምግባሩ ቅጣት ይቀበላል የሚለውን የሪኢንካርኔሽንን ትምህርት ፈለሰፉ። የታማኝ ሰዎች ግብ ሞክሻ ወይም ከዳግም መወለድ ዑደት መላቀቅና የሁሉ የበላይ የሆነ ኃይል ብለው ከሚጠሩት አካል ወይም ኒርቫና ጋር አንድ መሆን ነው ይላሉ። ሂንዱኢዝም ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት እየተስፋፋ ሲሄድ የሪኢንካርኔሽን ትምህርትም አብሮት ተስፋፍቷል። እንዲሁም ይህ መሠረተ ትምህርት የዘመናዊው ሂንዱኢዝም ምሰሶ ሆኗል።
16. በምሥራቅ እስያ በሚኖረው ሰፊ ሕዝብ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብና ልማዶች ላይ ተጽእኖ ያሳደረው የትኛው ስለ ወዲያኛው ዓለም የሚናገረው እምነት ነው?
16 ከሂንዱኢዝም ሃይማኖት የመነጩ እንደ ቡዲዝም፣ ጃይኒዝምና ሲኪዝም የመሳሰሉ ሌሎች እምነቶች አሉ። እነዚህም ሃይማኖቶች በሪኢንካርኔሽን ያምናሉ። ከዚህም በተጨማሪ ቡዲዝም ወደ አብዛኛው የምሥራቅ እስያ ክፍሎች ማለትም ወደ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓንና ሌሎችም ቦታዎች ሰርጎ ሲገባ በክልሉ በሚገኘው ባህልና ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህም የቡዲዝምን ትምህርት፣ መናፍስታዊ ሥራዎችንና የቀድሞ አባቶችን አምልኮ ቀላቅለው የያዙ እምነቶችን የሚያንጸባርቁ ሃይማኖቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ከእነዚህ ሃይማኖቶች መካከል ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደሩት እንደ ታኦይዝም፣ ኮንፊሺያኒዝምና የሺንቶ እምነት ይገኙበታል። በዚህ መንገድ ሥጋ ከሞተም በኋላ ነፍስ በሕይወት ትቀጥላለች የሚለው እምነት በዚያ የዓለም ክፍል በሚገኘው በአብዛኛው የሰው ዘር ሃይማኖታዊ አስተሳሰብና ልማዶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ችሏል።
ስለ አይሁድ እምነት፣ ስለ ሕዝበ ክርስትናና ስለ እስልምናስ ምን ለማለት ይቻላል?
17. የጥንቶቹ አይሁዶች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ምን ብለው ያምኑ ነበር?
17 የአይሁድ እምነትን፣ የሕዝበ ክርስትናንና የእስልምና ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ምን ብለው ያምናሉ? ከእነዚህ ሃይማኖቶች ውስጥ ረዥም እድሜ ያለው የአይሁድ ሃይማኖት ነው። ሃይማኖቱ የተመሠረተው ከ4,000 ዓመታት ገደማ በፊት በአብርሃም ዘመን ነው። ይህም ሶቅራጥስና ፕላቶ ነፍስ አትሞትም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ከማዳበራቸው ከብዙ ዓመታት በፊት መሆኑ ነው። የጥንቶቹ አይሁዶች የሰው ነፍስ አትሞትም በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ሳይሆን በትንሣኤ ያምኑ ነበር። (ማቴዎስ 22:31, 32፤ ዕብራውያን 11:19) ታዲያ ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት ከአይሁድ ሃይማኖት ጋር የተቀላቀለው እንዴት ነው? ታሪክ መልሱን ይሰጠናል።
18, 19. ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት ከአይሁድ ሃይማኖት ጋር የተቀላቀለው እንዴት ነው?
18 በ332 ከዘአበ ታላቁ እስክንድር ኢየሩሳሌምን ጨምሮ መካከለኛውን ምሥራቅ ድል አድርጎ ያዘ። የእስክንድር ተተኪዎች የእስክንድርን የሄለናይዜሽን ፕሮግራም ማራመዳቸውን በመቀጠላቸው የግሪክና የአይሁድ ባሕሎች ውሕደት ፈጠሩ። ውሎ አድሮ አይሁዶች የግሪክን አስተሳሰብ መቅሰም ጀመሩ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ፈላስፎች ሆኑ።
19 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው የእስክንድሪያው ፊሎ ከእነዚህ የአይሁድ ፈላስፎች አንዱ ነበር። ፊሎ ፕላቶን ከፍ አድርጎ ይመለከተው የነበረ ከመሆኑም በላይ የአይሁድ እምነትን በተመለከተ በግሪክ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ትንተና ለመስጠት ሞክሯል፤ ይህም ከጊዜ በኋላ ለተነሱት የአይሁድ ፈላስፎች መንገዱን ጠርጎላቸዋል። ረቢዎች በቃሉ ሕግ ላይ የሰጡትን ትንተና በጽሑፍ የያዘው ታልሙድም የግሪክ አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። “ታልሙድን ያዘጋጁት ረቢዎች” ይላል ኢንሳይክለፒዲያ ጁዳይካ፣ “ነፍስ ከሞት በኋላም በሕይወት ትቀጥላለች ብለው ያምኑ ነበር።” ከጊዜ በኋላ እንደ ካባላ ያሉት የአይሁድ ምሥጢራዊ ሥነ ጽሑፎች ይባስ ብለው ሪኢንካርኔሽንን እስከ ማስተማር ደረሱ። ስለዚህም ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በግሪክ ፍልስፍና አማካኝነት በተዘዋዋሪ መንገድ ከአይሁድ ሃይማኖት ጋር ተቀላቀለ። ትምህርቱ ከሕዝበ ክርስትና እምነት ጋር ስለተቀላቀለበት ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል?
20, 21. (ሀ) የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች የፕላቶን ወይም የግሪክን ፍልስፍና በተመለከተ ምን አቋም ነበራቸው? (ለ) የፕላቶ አመለካከቶች ከክርስትና ትምህርቶች ጋር እንዲቀላቀሉ ምክንያት የሆነው ምን ነበር?
20 እውነተኛ ክርስትና የተቋቋመው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሚገል ደ ኡናሙኖ ኢየሱስን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እንደ [ግሪኩ] የፕላቶ ፍልስፍና ነፍስ አትሞትም የሚል እምነት አልነበረውም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ አይሁዳውያኑ እምነት በሥጋ ትንሣኤ ያምን ነበር።” እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት . . . የአረማውያን ፍልስፍናዊ እምነት ነው።” ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሐዋርያው ጳውሎስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል” እንዳይማረኩ አጥብቆ ያስጠነቀቀው ለምን እንደሆነ ልናስተውል እንችላለን።—ቆላስይስ 2:8
21 ይህ “የአረማውያን ፍልስፍናዊ እምነት” ወደ ሕዝበ ክርስትና ሰርጎ የገባው መቼና እንዴት ነው? ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ከ2ኛው መቶ ዘመን እዘአ አጋማሽ ጀምሮ የግሪክን ፍልስፍና በተወሰነ ደረጃ የተማሩ ክርስቲያኖች የራሳቸውን አእምሮ ለማርካትና የተማሩ አረማውያንን ወደ ክርስትና ለመለወጥ ሲሉ እምነታቸውን ከግሪክ ፍልስፍና አኳያ መግለጽ እንዳለባቸው ሆኖ ተሰማቸው። ይበልጥ የተስማማቸው የፕላቶ ፍልስፍና ነበር።” በሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩት ሁለቱ የጥንት ፈላስፎች የእስክንድሪያው ኦሪጀንና የሂፖው ኦውግስቲን ነበሩ። ሁለቱም የፕላቶ አስተሳሰብ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሲሆን የፕላቶን አስተሳሰብ ከክርስትና ትምህርቶች ጋር በመቀላቀል ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
22. ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በእስልምና ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ቦታ እንደያዘ ሊቀጥል የቻለው እንዴት ነው?
22 ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ከአይሁድ ሃይማኖትና ከሕዝበ ክርስትና እምነት ጋር የተቀላቀለው የፕላቶ ፍልስፍና ባሳደረው ተጽዕኖ ሲሆን በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ግን ጽንሰ ሐሳቡ ሃይማኖቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ነው። የሙስሊሞች ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ቁራን ሰው ከሞተም በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለችው ሲል ያስተምራል። ነፍስ በመጨረሻ በሰማያዊ ገነት የአትክልት ሥፍራ ውስጥ ስለምታገኘው ሕይወት አለዚያም ደግሞ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ስለሚደርስባት ቅጣት ይናገራል። ይህ ማለት ግን የአረብ ምሁራን የእስልምናን ትምህርቶች ከግሪክ ፍልስፍና ጋር ለመቀላቀል ምንም ዓይነት ሙከራ አላደረጉም ማለት አይደለም። እንዲያውም የአርስቶትል ፍልስፍና በአረቡ ዓለም ላይ በተወሰነ ደረጃ ተጽእኖ አሳድሯል። ሆኖም ነፍስ አትሞትም የሚለው የሙስሊሞች እምነት አልተለወጠም።
23. ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት በተመለከተ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራሩት የትኞቹ ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች ናቸው?
23 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሃይማኖቶች ነፍስ አትሞትም በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ በመመርኮዝ ስለ ወዲያኛው ሕይወት ግራ የሚያጋቡ የተለያዩ እምነቶች አዳብረዋል። እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉ እምነቶች በቢልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽእኖ በማሳደር ባሪያ አድርገዋቸዋል። ይህን ሁሉ ስንመለከት ‘ስንሞት ምን እንደምንሆን በትክክል ማወቅ ይቻላልን? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?’ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። እነዚህን ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኤል-አማርና በ14ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደተገነባች የሚነገርላት የግብጿ ከተማ የአክታተን ፍርስራሽ የሚገኝበት ቦታ ነው።
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ በአብዛኞቹ ሃይማኖታዊ እምነቶች ውስጥ ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት በሚመለከት ምን የጋራ ጭብጥ አለ?
◻ ታሪክና መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት ምንጭ የጥንቷ ባቢሎን መሆኗን የሚጠቁሙት እንዴት ነው?
◻ የምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ስለ ነፍስ አለመሞት የሚናገረው ባቢሎናዊ እምነት ተጽእኖ ያሳደረባቸው እንዴት ነው?
◻ ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ከአይሁድ ሃይማኖት፣ ከሕዝበ ክርስትናና ከእስልምና ጋር የተቀላቀለው እንዴት ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሚገኙ ሥዕሎች]
ታላቁ እስክንድር የተቀዳጀው ድል የግሪክና የአይሁድ ባሕሎች እንዲደባለቁ አድርጓል
እስክንድር:- ሙሴ ካፒቶሊኒ፣ ሮማ፤ ኦውግስቲን:- ግሬት ሜን ኤንድ ፌመስ ዉሜን ከተባለው መጽሐፍ
[ምንጭ]
ኦውግስቲን የፕላቶን ፍልስፍና ከክርስትና ጋር ለመቀላቀል ሞክሯል