በትንሣኤ ላይ ያለህ እምነት ምን ያህል ጠንካራ ነው?
“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል።”—ዮሐንስ 11:25
1, 2. አንድ የይሖዋ አምላኪ በትንሣኤ ተስፋ ማመን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
በትንሣኤ ላይ ያለህ ተስፋ ምን ያህል ጠንካራ ነው? የሞትን ፍርሃት ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ የሚያስገኝልህና የምትወዳቸውን ሰዎች በሞት በምታጣበት ጊዜ የሚያጽናናህ ነውን? (ማቴዎስ 10:28፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13) በትንሣኤ ላይ የነበራቸው እምነት በሰጣቸው ጥንካሬ ሥቃይን፣ ፌዝን፣ ግርፋትንና እስርን በጽናት እንደተቋቋሙት እንደ ብዙዎቹ የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ነህን?—ዕብራውያን 11:35-38
2 አዎን፣ አንድ ቅን የይሖዋ አምላኪ ትንሣኤ እንደሚኖር ቅንጣት ታህል ሊጠራጠር አይገባውም፤ ሕይወቱን የሚመራበት መንገድም በትንሣኤ እንደሚያምን የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። አምላክ በወሰነው ጊዜ ባሕር፣ ሞትና ሔድስ በውስጣቸው ያሉትን ሙታን እንደሚሰጡና እነዚህ በትንሣኤ የተነሡት ደግሞ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንደሚኖራቸው ማሰቡ በጣም የሚያስደስት ነው።—ራእይ 20:13፤ 21:4, 5
የወደፊቱን ሕይወት በተመለከተ ያለው ጥርጣሬ
3, 4. አሁንም ቢሆን ብዙ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ያላቸው እምነት ምንድን ነው?
3 ሕዝበ ክርስትና ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ለረጅም ጊዜ ስታስተምር ኖራለች። ዩ ኤስ ካተሊክ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ይላል:- “ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ክርስቲያኖች ሰላምና እርካታ እንዲሁም ስኬትና ደስታ የሞላበት አንድ ሌላ ሕይወት ይመጣል ብለው በጉጉት በመጠባበቅ ይህን ብስጭትና ሥቃይ የሞላበት ሕይወት ችለው ለመኖር ሲጥሩ ቆይተዋል።” በብዙ የሕዝበ ክርስትና አገሮች የሚገኙ ሰዎች ሃይማኖትን በጥርጣሬ ዓይን በመመልከት ወደ ጎን ገሸሽ ያድርጉት እንጂ አሁንም ቢሆን ብዙዎች ከሞት በኋላ አንድ ዓይነት ሕይወት መኖር አለበት ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ እርግጠኛ ያልሆኑባቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
4 ታይም በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ብሏል:- “ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ያላቸው እውቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ ሄዷል፤ ቄሶቻቸውም ስለ ጉዳዩ የሚነግሯቸው አልፎ አልፎ ነው። ያም ሆኖ [ከሞት በኋላ ሕይወት አለ] ብለው ያምናሉ።” ሃይማኖታዊ አገልጋዮች በፊት ያደርጉት የነበረውን ያህል ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት አዘውትረው የማይናገሩት ለምንድን ነው? የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ጄፍሪ በርተን ራስል እንዲህ ብለዋል:- “[ቀሳውስት] ስለ ጉዳዩ መናገር የማይፈልጉት ትምህርቱን የሚጠራጠሩ ብዙ ሰዎች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች ለመሸሽ ሲሉ ይመስለኛል።”
5. ዛሬ ብዙ ሰዎች የእሳታማ ሲኦልን መሠረተ ትምህርት እንዴት ይመለከቱታል?
5 በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ትምህርት መሠረት ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት ሰማይንና እሳታማ ሲኦልን ያካተተ ነው። ቀሳውስት ስለ ሰማይ ለመናገር የሚያመነቱ ከሆነ ስለ ሲኦል ለመናገርማ ከዚያ የበለጠ እንደሚያመነቱ የታወቀ ነው። በአንድ ጋዜጣ ላይ የወጣ ርዕስ “በአሁኑ ጊዜ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ዘላለማዊ ቅጣት አለ ብለው የሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ሳይቀሩ . . . ይህን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ለዝቧል” ብሏል። እንዲያውም በዘመናችን የሚገኙ አብዛኞቹ የሃይማኖት ምሁራን ሲኦል ቃል በቃል የመሠቃያ ቦታ ነው በሚለው የመካከለኛው ዘመን ትምህርት አያምኑም። ከዚህ ይልቅ ለሲኦል ይበልጥ “ሰብዓዊነት የተላበሰ” ትርጉም መስጠት ይመርጣሉ። ዘመናዊ አስተሳሰብ ያላቸው ብዙ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ በሲኦል የሚገኙ ኃጢአተኞች እየተሠቃዩ ያሉት ቃል በቃል ሳይሆን “በመንፈሳዊ ከአምላክ በመለያየታቸው” ነው።
6. አንዳንዶች አሳዛኝ ነገሮች ሲገጥሟቸው እምነታቸው የሚጎድለው ነገር እንዳለ የሚገነዘቡት እንዴት ነው?
6 አንዳንዶች ዘመናዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ስሜት ላለመጉዳት ሲሉ የቤተ ክርስቲያንን መሠረተ ትምህርት ማለዘባቸው ተቀባይነትን ሊያስገኝላቸው ቢችልም ቅን ልብ ያላቸውን በሚልዮን የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ግን ግራ ያጋባል። በመሆኑም ከሞት ጋር ፊት ለፊት በሚጋፈጡበት ጊዜ እምነታቸው አንድ የሚጎድለው ነገር እንዳለ ይገነዘባሉ። አመለካከታቸው የቤተሰቧን በርካታ አባላት አሳዛኝ በሆነ አደጋ በሞት ካጣች አንዲት ሴት አመለካከት ጋር ይመሳሰላል። በሃይማኖታዊ እምነቷ ተጽናንታ እንደሆነ በተጠየቀች ጊዜ “ይመስለኛል” ስትል እያቅማማች መልሳለች። ይህች ሴት እምነቴ አጽናንቶኛል በማለት አፏን ሞልታ ተናግራ ቢሆን ኖሮም እንኳ የምታምንበት ነገር ጥሩ መሠረት ከሌለው ምን ዘላቂ ጥቅም ይኖረዋል? እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ስለ ወደፊቱ ሕይወት የሚያስተምሩት ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ፍጹም የተለየ በመሆኑ ይህን ጉዳይ በጥሞና መመልከቱ አስፈላጊ ነው።
ሕዝበ ክርስትና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ያላት አመለካከት
7. (ሀ) አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ምን የጋራ እምነት አላቸው? (ለ) አንድ የሃይማኖት ምሁር ነፍስ አትሞትም የሚለውን መሠረተ ትምህርት እንዴት አድርገው ገልጸውታል?
7 በመካከላቸው ልዩነቶች ይኑራቸው እንጂ ሁሉም የሕዝበ ክርስትና ክፍሎች ለማለት ይቻላል የሰው ልጆች በሚሞቱበት ጊዜ ከሥጋቸው ተነጥላ የምትሄድ የማትሞት ነፍስ አለቻቸው በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። ብዙ ሰዎች አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ነፍሱ ወደ ሰማይ ትሄዳለች ብለው ያምናሉ። አንዳንድ ሰዎች ነፍሳቸው ወደ እሳታማ ሲኦል ወይም ወደ መንጽሔ ትሄድ ይሆናል የሚል ፍራቻ አላቸው። በዚያም ሆነ በዚህ፣ ስለ ወደፊቱ ሕይወት ያላቸው አመለካከት የማትሞት ነፍስ አለች በሚለው አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ኦስካር ኩልማን ኢሞርታሊቲ ኤንድ ሬዘሬክሽን በተባለው መጽሐፍ ላይ ስለዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ዛሬ አንድን ተራ ክርስቲያን . . . ሰው ከሞተ በኋላ ስለሚኖረው ዕጣ አዲስ ኪዳን ምን ብሎ እንደሚያስተምር ብንጠይቀው በአብዛኛው የምናገኘው መልስ ስለ ‘ነፍስ አለመሞት’ ያስተምራል የሚል ነው።” ይሁን እንጂ ኩልማን “ይህ በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ አስተሳሰብ በክርስትና እምነት ውስጥ የተሳሳተ ትርጓሜ ከተሰጣቸው ትምህርቶች ውስጥ አንዱ ነው” በማለት አክለው ተናግረዋል። ኩልማን በመጀመሪያ ላይ እንዲህ ብለው ሲናገሩ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም ትክክል ነበሩ።
8. ይሖዋ በመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ፊት ያስቀመጠው ተስፋ ምን ነበር?
8 ይሖዋ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ከሞቱ በኋላ ወደ ሰማይ እንዲሄዱ አልነበረም። ቀድሞውኑም ቢሆን ሰዎች እንዲሞቱ ዓላማ አልነበረውም። አዳምና ሔዋን ፍጹም ተደርገው ከመፈጠራቸውም በላይ ምድርን ጻድቅ በሆኑ ልጆች የመሙላት አጋጣሚ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ ዘዳግም 32:4) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሚሞቱት የአምላክን ትእዛዝ ከጣሱ ብቻ እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) የሰማዩ አባታቸውን ቢታዘዙ ኖሮ በምድር ላይ ለዘላለም ይኖሩ ነበር።
9. (ሀ) ስለ ሰው ነፍስ እውነት የሆነው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ነፍስ በምትሞትበት ጊዜ ምን ትሆናለች?
9 የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን አምላክን አልታዘዙም። (ዘፍጥረት 3:6, 7) ከዚያ በኋላ የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ 5:12) አዳምና ሔዋን በምድር ላይ ለዘላለም ከመኖር ይልቅ ሞቱ። በዚያን ጊዜ ምን ሆነ? ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ወደ እሳታማ ሲኦል የሚላኩ የማይሞቱ ነፍሳት ነበሯቸውን? ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ አዳም መጀመሪያውኑ ሲፈጠር “ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ” ይላል። (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 ትርጉም) ሰው ነፍስ አልተሰጠውም፤ በሕይወት የሚኖር ሰው ማለትም ነፍስ ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) “ሕይወት ያለበት ነፍስ” የሆነው አዳም ብቻ አልነበረም፤ ዘፍጥረት የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ እንደሚያመለክተው ትንንሽ እንስሳትም “ሕያዋን ፍጥረታት [“ነፍሳት፣” NW]” ነበሩ! (ዘፍጥረት 1:24) አዳምና ሔዋን በሞቱ ጊዜ በድን ነፍሳት ሆኑ። ውሎ አድሮ የደረሰባቸው ይሖዋ እንደሚከተለው ሲል ለአዳም የተናገረው ነገር ነበር:- “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።”—ዘፍጥረት 3:19
10, 11. ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚያስተምረውን ትምህርት በተመለከተ የትኛውን ሐቅ አምኖ ተቀብሏል? ይህስ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር ጋር እንዴት ይነጻጸራል?
10 ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ከዚህ አባባል ጋር ይስማማል። “ነፍስ (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ)” በሚለው ርዕሱ ላይ “በብሉይ ኪዳን [በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች] ውስጥ ሥጋና ነፍስ እንደሚከፋፈሉ [ለሁለት እንደሚለያዩ] የሚገልጽ ነገር የለም” በማለት ይናገራል። አክሎም “ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ከሥጋ ወይም ከግለሰቡ የተለየ ነገር ተደርጎ በፍጹም አልተገለጸም” ብሏል። እንዲያውም ነፍስ አብዛኛውን ጊዜ “ራሱን እንስሳውን ወይም ሰውየውን የሚያመለክት ነው።” እንዲህ ብሎ በግልጽ መናገሩ የሚያስደስት ነው፤ ይሁን እንጂ አንድ ሰው የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ስለ እነዚህ እውነቶች ለምን እንዲያውቁ አልተደረጉም ብሎ ሊጠይቅ ይችላል።
11 የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” እንጂ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ አትሰቃይም የሚለውን ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቢያውቁ ኖሮ ከጭንቀትና ከፍርሃት በዳኑ ነበር። (ሕዝቅኤል 18:4) ይህ ሕዝበ ክርስትና ከምታስተምረው ትምህርት ፍጹም የተለየ ቢሆንም ጠቢቡ ሰሎሞን በመንፈስ ተነሣሥቶ ከተናገረው ነገር ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነው:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ [በአሁኑ ሕይወት] ዋጋ የላቸውም። አንተ በምትሄድበት በሲኦል [የሰው ልጅ የጋራ መቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።”—መክብብ 9:5, 10
12. ሕዝበ ክርስትና ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት ያገኘችው ከየት ነው?
12 ሕዝበ ክርስትና መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው የተለየ ነገር የምታስተምረው ለምንድን ነው? ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ “ነፍስ፣ ሰው፣ ያለመሞት ባሕርይ፣” በሚለው ርዕሱ ሥር የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የማትሞት ነፍስ አለች ለሚለው እምነት ድጋፍ ያገኙት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን “ከባለ ቅኔዎች፣ ከፈላስፎችና ከግሪክ አስተሳሰብ አጠቃላይ ወግ ነበር። . . . ከጊዜ በኋላ እነዚህ ምሁራን የፕላቶን ወይም የአርስቶትልን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመጠቀም መርጠዋል” ሲል ይገልጻል። በመጨረሻ ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት ጨምሮ “የፕላቶ ፍልስፍናና ከጊዜ በኋላ የፕላቶን ትምህርት በማሻሻል የቀረበው የኒኦፕላቶኒዝም ንድፈ ሐሳብ” “የክርስትና መንፈሳዊ ትምህርት ዋነኛ ክፍሎች” ሊሆኑ እንደቻሉም ይገልጻል።
13, 14. ከአረማዊ የግሪክ ፈላስፎች የእውቀት ብርሃን ለማግኘት ተስፋ ማድረግ ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
13 ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው የሕይወት ተስፋና ይህን ስለመሳሰሉ መሠረታዊ ነገሮች ለመማር ወደ አረማዊ የግሪክ ፈላስፎች ዘወር ማለት ነበረባቸውን? በፍጹም። ጳውሎስ በግሪኳ የቆሮንቶስ ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና። እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው የሚይዝ፤ ደግሞም:- ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል ተብሎ ተጽፎአልና” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 3:19, 20) የጥንቶቹ ግሪካውያን ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ። ታዲያ እንዴት የእውነት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ? ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል:- በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፣ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”—2 ቆሮንቶስ 6:16
14 ቀደም ሲል ቅዱስ የሆኑ እውነቶች ራእይ ይገለጥ የነበረው በእስራኤል ብሔር አማካኝነት ነበር። (ሮሜ 3:1, 2) ከ33 እዘአ በኋላ ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ አማካኝነት ይገለጥ ነበር። ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩ ክርስቲያኖች ሲናገር “ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል [ለሚወዱት ያዘጋጀውን ነገር] ገለጠው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 2:10፤ በተጨማሪም ራእይ 1:1, 2ን ተመልከት።) ነፍስ አትሞትም የሚለው የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርት የመነጨው ከግሪክ ፍልስፍና ነው። በእስራኤላውያን ወይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በኩል የተገለጠ የአምላክ ራእይ አይደለም።
ሙታን ያላቸው እውነተኛ ተስፋ
15. ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ሙታን ያላቸው እውነተኛ ተስፋ ምንድን ነው?
15 ነፍስ ሟች ከሆነች ሙታን ያላቸው እውነተኛ ተስፋ ምንድን ነው? ትንሣኤ ነው። ትንሣኤ ዋነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርትና እጅግ አስደሳች የሆነ መለኮታዊ ተስፋ ነው። ኢየሱስ ለወዳጁ ለማርታ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” ብሎ ሲናገር የትንሣኤ ተስፋ በእርግጥ የሚፈጸም መሆኑን መግለጹ ነበር። (ዮሐንስ 11:25) በኢየሱስ ማመን ማለት በትንሣኤ ማመን ማለት እንጂ በማትሞት ነፍስ ማመን ማለት አይደለም።
16. በትንሣኤ ማመን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ቀደም ሲል ኢየሱስ ለአንዳንድ አይሁዳውያን “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ስለ ትንሣኤ ጠቅሷል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ኢየሱስ እዚህ ላይ የገለጸው ነገር በሞት ጊዜ ከሥጋ ተነጥላ በመውጣት በቀጥታ ወደ ሰማይ የምትሄድን የማትሞት ነፍስ አያመለክትም። በመቶ ወይም በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በመቃብር ውስጥ የነበሩ ብዙ ሰዎች ወደፊት ‘ይወጣሉ።’ ሞተው የነበሩ ነፍሳት ሕይወት ያገኛሉ። ይህ የማይቻል ነገር ይሆን? “ለሙታን ሕይወት [ለ]ሚሰጥና የሌለውንም እንዳለ አድርጎ [ለ]ሚጠራ” አምላክ ይህን ማድረግ ቀላል ነው። (ሮሜ 4:17) ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች ሙታን ይነሣሉ በሚለው ሐሳብ ያሾፉ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” እንዲሁም ‘ለሚፈልጉት ዋጋ ይሰጣል’ ከሚሉት እውነታዎች ጋር በትክክል ይስማማል።—1 ዮሐንስ 4:16፤ ዕብራውያን 11:6
17. አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት ምን ያከናውናል?
17 አምላክ ‘እስከ ሞት ድረስ የታመኑ’ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሰዎችን ወደ ሕይወት መልሶ ካላመጣቸው እንዴት አድርጎ ሊክሳቸው ይችላል? (ራእይ 2:10) በተጨማሪም አምላክ “ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት ሐዋርያው ዮሐንስ የጻፈውን ማስፈጸም የሚችለው በትንሣኤ አማካኝነት ነው። (1 ዮሐንስ 3:8) ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ወደ ኃጢአትና ሞት በመምራቱ ለመላው የሰው ዘር ሞት ተጠያቂ ነው። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ዮሐንስ 8:44) ኢየሱስ ፍጹም ሕይወቱን ተመጣጣኝ የቤዛ ዋጋ አድርጎ በመስጠት የሰው ልጆች አዳም በገዛ ፈቃዱ የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ካወረሳቸው የኃጢአት ባርነት ነፃ እንዲወጡ መንገዱን በመክፈት የሰይጣንን ሥራዎች ማፍረስ ጀምሯል። (ሮሜ 5:18) በዚህ አዳማዊ ኃጢአት ምክንያት የሞቱ ሰዎች በትንሣኤ መነሣታቸው ደግሞ የሰይጣንን ሥራዎች ይበልጥ የሚያፈርስ ይሆናል።
ሥጋና ነፍስ
18. ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ በተናገረ ጊዜ አንዳንድ ግሪካውያን ፈላስፎች ምን ተሰማቸው? ለምንስ?
18 ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና በነበረበት ጊዜ አንዳንድ የግሪክ ፈላስፎችን ጨምሮ አንድ ላይ ተሰብስበው ለነበሩ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን ሰብኳል። ስለ እውነተኛው አንድ አምላክ የሰጠውን ማብራሪያና ንስሐ እንዲገቡ ያቀረበውን ጥሪ አዳመጡ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ምን ሆነ? ጳውሎስ ንግግሩን ሲያጠቃልል እንዲህ ብሏል:- “[አምላክ] ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።” እነዚህ ቃላት የመወያያ ርዕስ ሆነው ነበር። “የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት።” (ሥራ 17:22-32) ሃይማኖታዊው ሊቅ ኦስካር ኩልማን እንዲህ ብለዋል:- “ክርስቲያኖች ስለ ትንሣኤ የሚሰብኩትን ለመቀበል ይበልጥ የሚከብዳቸው በነፍስ አለመሞት የሚያምኑት ግሪካውያን ሳይሆኑ አይቀርም። . . . የታላላቆቹ ፈላስፎች የሶቅራጥስና የፕላቶ ትምህርት ከአዲስ ኪዳን ትምህርት ጋር በፍጹም ሊጣጣም አይችልም።”
19. የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ምሁራን የትንሣኤን ትምህርት ነፍስ አትሞትም ከሚለው መሠረተ ትምህርት ጋር ለማጣጣም የጣሩት እንዴት ነበር?
19 ሆኖም ከሐዋርያት ሞት በኋላ ታላቁን ክህደት ተከትሎ፣ የሃይማኖት ምሁራን ክርስቲያናዊውን የትንሣኤ ትምህርት ነፍስ አትሞትም ከሚለው የፕላቶ እምነት ጋር ለማዋሃድ ልዩ ጥረት አድርገው ነበር። በመጨረሻም አንዳንዶች በሞት ጊዜ ነፍስ ከሥጋ ትለያለች (አንዳንዶች እንደሚሉት “ነፃ ትወጣለች”) በሚለው በዓይነቱ አዲስ የሆነ የመፍትሔ ሐሳብ ተስማሙ። በአር ጄ ኩክ የተዘጋጀው አውትላይንስ ኦቭ ዘ ዶክትሪን ኦቭ ዘ ሬዘሬክሽን የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ በፍርድ ቀን “እያንዳንዱ አካል ከራሱ ነፍስ ጋር ይዋሃዳል እንዲሁም እያንዳንዱ ነፍስ ከራሱ አካል ጋር ይዋሃዳል።” አካል ከማትሞተው ነፍስ ጋር እንደገና የሚያደርገው ውህደት ትንሣኤ ተብሏል።
20, 21. ምን ጊዜም ስለ ትንሣኤ እውነት የሆነውን ነገር ሲሰብኩ የቆዩት እነማን ናቸው? ይህስ የጠቀማቸው እንዴት ነው?
20 ይህ ፅንሰ ሐሳብ አሁንም የዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ይፋዊ መሠረተ ትምህርት ነው። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ለአንድ የሃይማኖት ምሁር ምክንያታዊ መስሎ ሊታየው ቢችልም ለአብዛኞቹ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ግን እንግዳ የሆነ ነገር ነው። እነዚህ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ በቀጥታ ወደ ሰማይ እንሄዳለን ብለው ያምናሉ። በዚህ ምክንያት በግንቦት 5, 1995 የኮመንዊል እትም ላይ ጸሐፊው ጆን ጋርቪ “[ከሞት በኋላ ሕይወት አለ በሚለው ጉዳይ ላይ] አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ያላቸው እምነት ክርስቲያናዊ ከመሆን ይልቅ ወደ ኒኦፕላቶኒዝም ያደላና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ነው” በማለት ወቀሳ ሰንዝረዋል። በእርግጥም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱስን በፕላቶ ፍልስፍና በመለወጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የትንሣኤ ተስፋ ከተከታዮቻቸው ሰውረዋል።
21 በሌላ በኩል ግን የይሖዋ ምሥክሮች አረማዊ ፍልስፍናዎችን ይቃወማሉ፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚያስተምረውን ትምህርት በጥብቅ ይከተላሉ። እንዲህ ያለው ትምህርት የሚያንጽ፣ የሚያስደስትና የሚያጽናና ሆኖ አግኝተውታል። ምድራዊ ተስፋ ላላቸውም ሆነ ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት የማግኘት ተስፋ ላላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚያስተምረው ትምህርት ትክክለኛ መሠረት ያለውና ምክንያታዊ መሆኑን በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ እንመለከታለን። እነዚህን ርዕሶች ከማጥናታችሁ በፊት ለዝግጅት እንዲረዳችሁ ለቆሮንቶስ ሰዎች የተላከውን የመጀመሪያ ደብዳቤ ምዕራፍ 15ን በጥሞና እንድታነቡት እናበረታታችኋለን።
[ልታስታውስ ትችላለህ?]
◻ በትንሣኤ ላይ ጠንካራ እምነት ማዳበር የሚገባን ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ በአዳምና በሔዋን ፊት ያስቀመጠው ተስፋ ምን ነበር?
◻ በግሪክ ፍልስፍና ውስጥ እውነትን ለማግኘት መፈለጉ ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
◻ ትንሣኤ ተገቢ ተስፋ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአት በሠሩበት ጊዜ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጡ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ምሁራን ነፍስ አትሞትም የሚለው የፕላቶ እምነት ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል
[ምንጭ]
ሙሴ ካፒቶሊኒ፣ ሮማ