ነፍስ የሚጠብቃት የተሻለ ተስፋ
የሮም ወታደሮች ፈጽሞ ያልጠበቁት ነገር ነበር። በተራራ ላይ የሚገኘውን ማሳዳ የተባለ የአይሁድ ዓማፂያን የመጨረሻ ምሽግ ሲወርሩ በጠላቶቻቸው ላይ ከባድ ጥቃት ለመሰንዘር ከመዘጋጀታቸውም በተጨማሪ የተዋጊዎች ጩኸት እንዲሁም የሴቶችና የልጆች ዋይታ ይኖራል ብለው ጠብቀው ነበር። የሰሙት ግን የእሳት ነበልባል ድምፅ ብቻ ነበር። ሮማውያኑ እየተቃጠለ ያለውን ምሽግ ሲያስሱ የደረሱበት ነገር በጣም የሚሰቀጥጥ ነበር፦ 960 የሚያክሉ ጠላቶቻቸው አልቀው ጠበቋቸው! የአይሁድ ተዋጊዎች መጀመሪያ ቤተሰቦቻቸውን ከጨፈጨፉ በኋላ እርስ በርሳቸው ተራርደው አልቀው ነበር። ከዚያም መጨረሻ የቀረው ሰው ራሱን ገደለ።a እንደዚህ በአሠቃቂ ሁኔታ እርስ በራሳቸው እንዲገዳደሉና ራሳቸውን እንዲገድሉ የገፋፋቸው ምን ነበር?
በጊዜው የነበረው ጆሴፈስ የተባለው ታሪክ ጸሐፊ እንደተናገረው ለዚህ ክስተት ዋነኛ ምክንያቱ ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት ነበር። ዜሎት ተብለው የሚጠሩ በማሳዳ የነበሩ የተቃዋሚ ቡድን አባላት መሪ የነበረው ኤልዔዘር ቤን ጄዪር በሮማውያን እጅ ከመሞት ወይም የእነርሱ ባሪያ ከመሆን ራስን መግደል የሚያኮራ ተግባር እንደሆነ ተከታዮቹን ለማሳመን ሞክሯል። ይህን እርምጃ ለመውሰድ እንዳመነቱ ሲመለከት ስለ ነፍስ በግለት መናገር ጀመረ። ሥጋ ሸክምና የነፍስ እስር ቤት እንደሆነ ነገራቸው። በመቀጠልም እንዲህ አለ፦ “ነፍሳችን ወደ ምድር ከሚጎትታትና አስሮ ከሚይዛት ሸክም ነፃ ስትሆን ግን ወደ ቦታዋ ትመለሳለች። ከዚያም ከፍተኛ ኃይልና ይህ ነው የማይባል ጥንካሬ ከማግኘቷም በተጨማሪ እንደ ራሱ እንደ አምላክ በዓይን የማትታይ ትሆናለች።”
ምን ምላሽ አገኘ? ኤልዔዘር ስለ ጉዳዩ አንድ በአንድ እየተናገረ ሳለ “ያዳምጡት የነበሩ ሁሉ ንግግሩን ገና ሳይጨርስ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ስሜት የተባሉትን ለማድረግ ተቻኮሉ” በማለት ጆሴፈስ ዘግቧል። ጆሴፈስ በመቀጠልም እንዲህ አለ፦ “አንድ ነገር የገፋፋቸው ያህል ሁሉም ቀድሞ ለመገደል ይሽቀዳደም ነበር። . . . ሚስቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና ራሳቸውን ለመግደል ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ፍላጎት አድሮባቸው ነበር።”
ይህ አሠቃቂ ታሪክ ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ሰዎች ለሞት ባላቸው አመለካከት ላይ ምን ያህል ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ያሳያል። ነፍስ አትሞትም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ሞትን የሚመለከቱት እንደ ሰዎች ቀንደኛ ጠላት ሳይሆን ነፍስ ነፃ ወጥታ ወደ ተሻለ ሕይወት የምትሸጋገርበት በር እንደሆነ አድርገው ነው። ሆኖም ዜሎትስ የሚባሉት አይሁዶች ነፍስ አትሞትም የሚል እምነት ያደረባቸው ለምንድን ነው? አብዛኞቹ ዜሎትስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎቻቸው ሰው ሕያው መንፈስ ማለትም ከሞት በኋላ በሕይወት የሚቀጥል ነፍስ አለው ብለው የሚያስተምሩ ይመስላቸው ነበር። ይህ እውነት ነውን?
ነፍስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ
በአጭሩ ይህ እውነት አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ነፍስ ማለት በውስጥህ የሚገኝ ነገር ሳይሆን አንተው ራስህ እንደሆንክ ተገልጿል። ስለመጀመሪያው ሰው አዳም ሲናገር “ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ” ይላል። (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 ትርጉም) እዚህ ላይ ነፍስ ለሚለው ቃል የገባው ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ700 ጊዜ በላይ ይገኛል። ሆኖም ቃሉ አንድም ጊዜ ቢሆን ነፍስ ራሷን የቻለች የማትጨበጥ መንፈሳዊ የሰው አካል እንደሆነች አይገልጽም። ከዚህ ይልቅ ነፍስ ተጨባጭ አካል ነች።
ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመልከታቸው፤ በሁሉም ጥቅሶች ላይ ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ይገኛል። እነዚህ ጥቅሶች ነፍስ አደጋ ላይ ልትወድቅና አልፎ ተርፎም ታፍና ልትወሰድ (ዘዳግም 24:7 አዓት፤ መሳፍንት 9:17፤ 1 ሳሙኤል 19:11)፤ አንድን ነገር ልትነካ (ኢዮብ 6:7 አዓት)፤ በእግረ ሙቅ ልትያዝ (መዝሙር 105:18 አዓት)፤ የሚበላ ነገር ሊያምራት፣ በጾም ልትጎዳ፣ በረሃብና በጥም ልትደክም፣ በሚያከሳ በሽታ ወይም ሐዘን እንቅልፍ አሳጥቷት ልትሠቃይ እንደምትችል በግልጽ ያሳያሉ። (ዘዳግም 12:20 አዓት፤ መዝሙር 35:13፤ 69:10፤ 106:15፤ 107:9፤ 119:28 አዓት) በሌላ አባባል ነፍስህ ማለት አንተው ራስህ ስለሆንክ በአንተ ላይ የደረሰው ነገር በነፍስህ ላይ ደርሷል ማለት ነው።b
ይህ ሲባል ነፍስ ልትሞት ትችላለች ማለት ነውን? አዎን። የሰው ነፍስ አትሞትም ከሚለው ትምህርት በተለየ መልኩ በዕብራይስጡ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ነፍስ ‘ልትቀጠፍ’ ወይም በጥፋቷ ልትቀጣ፣ እስክትሞት ድረስ ልትመታ፣ ልትገደል፣ ልትጠፋና ልትሰበር እንደምትችል ተነግሯል። (ዘጸአት 31:14 አዓት፤ ዘዳግም 19:6 አዓት፤ 22:26 አዓት፤ መዝሙር 7:2) ሕዝቅኤል 18:4 “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” ይላል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን ሞት የሁሉም ነፍስ የመጨረሻ ዕጣ ነው። (መዝሙር 51:5) ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም የተነገረው የኃጢአት ቅጣት ሞት ነው እንጂ ወደ መንፈሳዊ ዓለም ተዛውሮ እስከ መጨረሻ ሕያው ሆኖ መኖር አልነበረም። (ዘፍጥረት 2:17) ኃጢአት በሠራ ጊዜ የተወሰነበት ቅጣት “አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” የሚል ነበር። (ዘፍጥረት 3:19) አዳምና ሔዋን ሲሞቱ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ እንደሚናገረው ‘የሞቱ ነፍሳት’ ሆኑ።—ዘኁልቁ 5:2፤ 6:6 አዓት
ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ነፍስ ምን ነገር ለማመልከት እንደገባ ሲናገር “ሰው ማለት የነፍስና የሥጋ ጥምረት ሳይሆን ራሱን የቻለ አካል መሆኑን ብሉይ ኪዳን ይናገራል” ማለቱ አያስደንቅም። በመቀጠልም “ነፈሽ . . . ከሥጋ የተለየ እንደሆነ የተገለጸበት ቦታ የለም” ብሏል።
ታዲያ ታማኝ የነበሩት አይሁዶች ሞት ምን እንደሆነ ያምኑ ነበር? በቀላሉ ለመናገር ያህል ሞት የሕይወት ተቃራኒ እንደሆነ ያምኑ ነበር። መዝሙር 146:4 የአንድ ሰው መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል ከአንድ ሰው ሲወጣ ምን እንደሚሆን ሲናገር “ነፍሱ [“መንፈሱ፣” አዓት] ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ [“ሐሳቡ፣” አዓት] ሁሉ ይጠፋል” ይላል።c በተመሳሳይም ንጉሥ ሰሎሞን “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” በማለት ጽፏል።—መክብብ 9:5
ታዲያ በማሳዳ እንደነበሩት ዜሎትስ ያሉ አያሌ የመጀመሪያ መቶ ዘመን አይሁዶች ነፍስ አትሞትም ብለው ያምኑ የነበሩት ለምንድን ነው?
የግሪክ ተጽዕኖ
አይሁዳውያን ይህን ሐሳብ ያገኙት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ከግሪክ ነው። ነፍስ አትሞትም የሚለው አመለካከት ከዘአበ በሰባተኛውና በስምንተኛው መቶ ዘመናት መካከል ምሥጢራዊ ከሆኑት የግሪክ ሃይማኖታዊ እምነቶች ወደ ግሪክ ፍልስፍና የገባ ይመስላል። መጥፎ ነፍሳት ሥቃይ የተሞላበት ቅጣት ስለሚቀበሉበት ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ያለው አመለካከት ተቀባይነት ካገኘ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፤ ይህ አመለካከት ሥር ከመስደዱም በተጨማሪ ስፋት አግኝቷል። ፈላስፎች የነፍስን ትክክለኛ ምንነት በተመለከተ በየጊዜው መቋጫ የሌለው ክርክር ያደርጉ ነበር። ሆሜር አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ነፍሱ የንብ ድምፅ የሚመስል፣ ጭውጭው እንደሚሉ ወፎች ያለ ድምፅ ወይም የሚንኮሻኮሽ ድምፅ እያሰማች እንደምትወጣ ተናግሯል። ኤፊቆሮስ የተባለው ፈላስፋ ነፍስ ክብደት እንዳላትና በዚህም የተነሳ መጠኗ በጣም ይነስ እንጂ አካል እንደሆነች ተናግሯል።d
ሆኖም ነፍስ አትሞትም ለሚለው ትምህርት ከፍተኛ ድጋፍ የሰጠው በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የኖረው የግሪኩ ፈላስፋ ፕላቶ ሳይሆን አይቀርም። አስተማሪው ስለነበረው ስለ ሶቅራጥስ ሞት የሰጠው መግለጫ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት በማሳዳ ይኖሩ ከነበሩት ዜሎትስ ጋር በጣም የሚመሳሰል እምነት እንደነበረው ያሳያል። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ኦስካር ኩልማን እንዲህ ብለዋል፦ “ሶቅራጥስ በፍጹም ሰላምና እርጋታ እንደሞተ ፕላቶ ገልጾልናል። ሶቅራጥስ አሟሟቱ አምሮለታል። በፕላቶ መግለጫ ላይ ሞት አስፈሪ እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም። ሞት ከሥጋችን ነፃ የሚያወጣን ነገር ስለሆነ ሶቅራጥስ ሞትን የሚፈራበት ምክንያት የለውም። . . . ሞት የነፍስ የቅርብ ወዳጅ ነው። ስለዚህ ሶቅራጥስ ሞት አስፈሪ እንዳልሆነ አስተማረ፤ ካስተማረው ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሞተ።”
ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው አይሁዳውያን ይህን ትምህርት ከግሪካውያን መቅዳት የጀመሩት ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ዘመን በመቃባውያን ጊዜ ነበር። ጆሴፈስ ፈሪሳውያንና ኢሴኔስ ተብለው የሚጠሩ ተደማጭነት የነበራቸው የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይህን ትምህርት እንደተቀበሉ ተናግሯል። በዚያን ዘመን የተገጠሙ አንዳንድ ግጥሞች ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት ያንጸባርቁ ነበር።
ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ትምህርት ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? እርሱና ተከታዮቹ ይህን ትምህርት ከግሪክ ሃይማኖት በመውሰድ አስተምረው ነበርን?
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለነፍስ የነበራቸው አመለካከት
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ነፍስን በተመለከተ ከግሪካውያን የተለየ አመለካከት ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል የኢየሱስ ጓደኛ የነበረውን የአልዓዛርን ሞት ተመልከት። አልዓዛር በሞት ጊዜ ከሥጋው ተለይታ ነፃና ደስተኛ ሆና የምትኖር ነፍስ ብትኖረው ኖሮ በዮሐንስ ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ታሪክ ሌላ መልክ አይኖረውም ነበርን? አልዓዛር ወደ ሰማይ ሄዶ በሕይወት መኖር ቢጀምር ኖሮ ኢየሱስ ይህን በተመለከተ ለተከታዮቹ አንዳንድ ነገሮች ይነግራቸው እንደነበር አያጠራጥርም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚናገሩት ጋር በመስማማት አልዓዛር እንደተኛ ወይም በድን እንደሆነ ነገራቸው። (ቁጥር 11) ጓደኛው በሰማይ ግሩም የሆነ አዲስ ሕይወት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ይደሰት ነበር፤ ነገር ግን በአልዓዛር ሞት በግልጽ እንዳለቀሰ ጥቅሱ ይነግረናል። (ቁጥር 35) የአልዓዛር ነፍስ አስደሳች የሆነ ያለመሞት ባሕርይ ለብሳ በሰማይ እየኖረች ቢሆን ኖሮ “እስር ቤት” የሆነውን ፍጽምና የጎደለው ሥጋዊ አካል ለብሶ በበሽታ በሚሠቃዩና ሟች በሆኑ የሰው ልጆች መካከል ተጨማሪ ጥቂት ዓመታት እንዲያሳልፍ አልዓዛርን ወደዚህ ዓለም መመለሱ ለኢየሱስ ጭካኔ ይሆንበት ነበር።
አልዓዛር ከሞት ሲመለስ መንፈሳዊ ፍጥረት ሆኖ በነፃነት ስላሳለፋቸው አራት አስገራሚ ቀናት በአድናቆት ተርኮ ነበርን? አልተረከም። ነፍስ አትሞትም ብለው የሚያምኑ ሰዎች አልዓዛር እንዲህ ያላደረገው ያጋጠመው ነገር በቃላት ሊገለጽ የማይችል ስለሆነ ነው በማለት መልስ ይሰጡ ይሆናል። ይህም ቢሆን አሳማኝ ምክንያት አይደለም። ሌላው ቀርቶ በጣም አስገራሚ ከመሆኑ የተነሳ በቃላት ሊገለጽ የማይቻል ነገር እንዳጋጠመው ለወዳጆቹ መናገር አይችልም ነበርን? ሆኖም አልዓዛር ሞቶ ሳለ ስላጋጠመው ነገር ምንም ነገር አልተናገረም። እስቲ አስበው ሰዎች ከሁሉ ይበልጥ ለማወቅ ስለሚጓጉለት ርዕሰ ጉዳይ ማለትም ሞት ምን እንደሚመስል የተናገረው ነገር የለም! ለዚህ ዝምታ ልንሰጠው የምንችለው ፍቺ አንድ ብቻ ነው። ሞት ምን እንደሚመስል የሚናገረው ነገር አልነበረውም። ሙታን ምንም የማይሰማቸው በድን ናቸው።
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሞት የነፍስ ወዳጅ እንደሆነና ከአንድ ዓይነት ሕይወት ወደ ሌላ የምንሸጋገርበት መተላለፊያ እንደሆነ ይናገራልን? እንደዚህ አይልም! እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ላሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሞት ወዳጅ ሳይሆን “በመጨረሻ የሚደመሰሰው ጠላት” ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:26 የ1980 ትርጉም) ክርስቲያኖች ሞትን የሚመለከቱት በተፈጥሮ ያለ ነገር አድርገው ሳይሆን ሰዎች ኃጢአት በመሥራታቸውና በአምላክ ላይ በማመፃቸው ምክንያት ከጊዜ በኋላ የመጣ አስፈሪ ነገር አድርገው ነው። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) አምላክ ለሰዎች በነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ውስጥ ሞት አልነበረም።
ሆኖም ነፍስ ትሞታለች ሲባል እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት አይደለም። አልዓዛር ከሞት ስለመነሳቱ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሞቱ ነፍሳት ያላቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው እውነተኛ ተስፋ ትንሣኤ እንደሆነ ከሚያሳዩ ብዛት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አንዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለት የተለያዩ ትንሣኤዎች ይናገራል። በመቃብር ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ጻድቃን ቢሆኑም ባይሆኑም ከሞት ተነስተው ገነት በምትሆነው እዚችው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። (ሉቃስ 23:43 አዓት፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) ኢየሱስ “ታናሽ መንጋ” ብሎ የጠራቸው ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሞት የማይቀጭ መንፈሳዊ ሕይወት ይዘው ከሞት ከተነሱ በኋላ በሰማይ ይኖራሉ። ከእነርሱም መካከል የክርስቶስ ሐዋርያት ይገኙበታል፤ እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ሰዎችን በመግዛት ወደ ፍጽምና ያደርሷቸዋል።—ሉቃስ 12:32፤ 1 ቆሮንቶስ 15:53, 54፤ ራእይ 20:6
ታዲያ ሕዝበ ክርስትና ትንሣኤ አለ ከማለት ይልቅ የሰው ነፍስ አትሞትም ብላ የምታስተምረው ለምንድን ነው? የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ቨርነር ዬገር በ1959 ዘ ሃርቫርድ ቲኦሎጂካል ሪቪው በተባለ መጽሐፍ ላይ ለዚህ ጥያቄ የሰጡትን መልስ ተመልከት፦ “በእስክንድርያ ትምህርት ቤት የፕላቶን ፍልስፍናዎች ያስተምር የነበረው የክርስትና ትምህርት አባት ኦሪገን በክርስትና መንፈሳዊ ትምህርት ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ነው። ኦሪገን ነፍስን በተመለከተ ከፕላቶ የወሰዳቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትምህርቶች ወደ ክርስትና አስገብቷል።” በዚህ የተነሳ ቤተ ክርስቲያን ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት አይሁዶች ያደረጉትን ተከትላለች! የግሪክን ፍልስፍና በመደገፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት ችላ ብለዋል።
የትምህርቱ ሥረ መሠረት
ታዲያ በዓለማችን የሚገኙ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሃይማኖቶች በተመሳሳይም ሆነ በተለያየ መልኩ ነፍስ አትሞትም የሚለውን መሠረተ ትምህርት በጋራ የሚያስተምሩት ለምንድን ነው? በማለት አንዳንዶች መከላከያ ያቀርቡ ይሆናል። ቅዱሳን ጽሑፎች ይህ ትምህርት በዚህ ዓለም ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘበትን ትክክለኛ ምክንያት ይነግሩናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ይለናል፤ በተጨማሪም “የዚህ ዓለም ገዥ” ሰይጣን እንደሆነ ለይቶ ይጠቁማል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ ዮሐንስ 12:31) የዓለም ሃይማኖቶች ከሰይጣን ተጽዕኖ ነፃ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በጊዜያችን በዓለም ላይ ላለው ችግርና አምባጓሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ነፍስን በተመለከተም የሰይጣንን አስተሳሰብ ያንጸባርቃሉ። ይህን ያደረጉት እንዴት ነው?
የመጀመሪያውን ውሸት አስታውስ። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ እንደሚሞቱ አምላክ ነግሯቸው ነበር። ሆኖም ሰይጣን “ሞትን አትሞቱም” በማለት ለሔዋን አረጋገጠላት። (ዘፍጥረት 3:4) አዳምና ሔዋን አምላክ እንደተናገረው ሞተው ወደ አፈር ተመልሰዋል። ‘የሐሰት አባት’ የሆነው ሰይጣን የመጀመሪያ ውሸቱን አሁንም አልተወም። (ዮሐንስ 8:44) ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በራቁ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ጭራሹኑ ወደ ጎን ገሸሽ በሚያደርጉ ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ሃይማኖቶች ውስጥ ‘ሞትን አትሞቱም። ሥጋችሁ ይበሰብስ ይሆናል፤ ነፍሳችሁ ግን እንደ አምላክ ለዘላለም ትኖራለች!’ የሚለው ሐሳብ እስካሁን ድረስ እያስተጋባ ነው። የሚያስገርመው ሰይጣን ለሔዋንም ‘እንደ አምላክ’ እንደምትሆን ነግሯት ነበር!—ዘፍጥረት 3:5
በውሸት ወይም በሰዎች ፍልስፍና ላይ ሳይሆን በእውነት ላይ የተመሠረተ ተስፋ መጨበጡ ምንኛ የተሻለ ነው። በሕይወት ያሉት ነፍሳት ይሄኔ የት ይሆኑ እያልን ከመጨነቅ ይልቅ የሞቱ ወዳጅ ዘመዶቻችን በድን ሆነው መቃብር ውስጥ እንዳሉ እርግጠኛ መሆኑ እንዴት የተሻለ ነው! ሙታን ያሉበት ሁኔታ ሊያስፈራን ወይም ሊያስጨንቀን አይገባም። አስተማማኝ በሆነ የእረፍት ቦታ እንዳሉ አድርገን ልንወስድ እንችላለን። አስተማማኝ ቦታ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ የሚወዳቸው ሙታን በአንድ የተለየ መንገድ በሕይወት እየኖሩ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያረጋግጥልን ነው። (ሉቃስ 20:38) ትዝታቸው ከይሖዋ አእምሮ አልጠፋም። የይሖዋ የማስታወስ ችሎታ ወሰን የሌለው ስለሆነ ይህ ሁኔታ በጣም የሚያጽናና ነው። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታንን ከሞት ለማስነሳትና በምድራዊ ገነት ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ አጋጣሚ ለመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት አለው።—ከኢዮብ 14:14, 15 ጋር አወዳድር።
ይሖዋ የተናገረው ሁሉ መፈጸም ስላለበት ሙታን የሚነሱበት አስደናቂ ጊዜ ይመጣል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፣ ሬሳቸውም ይነሣል። መሬት ውስጥ የተኙ ከሞት ተነስተው በደስታ ይዘምራሉ፤ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፣ ምድርም ሙታንን እንደገና ትወልዳለች” የሚለው ትንቢት የሚፈጸምበትን ጊዜ እስኪ አስበው። (ኢሳይያስ 26:19፣ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ስለዚህ በመቃብር ውስጥ ተኝተው ያሉ ሙታን በእናቱ ማኅፀን ውስጥ እንዳለ ሕፃን በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ ‘ይወለዱና’ በገነቲቱ ምድር ላይ እንደገና መኖር ይጀምራሉ!
ከዚህ የተሻለ ምን ተስፋ ሊኖር ይችላል?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሁለት ሴቶችና አምስት ልጆች ተደብቀው እንደተረፉ ተዘግቧል። እነዚህ ሴቶች በምርኮ ለያዟቸው ሮማውያን ጉዳዩን በዝርዝር ነግረዋቸዋል።
b እርግጥ ነው፣ እንደ ብዙዎቹ ሰፊ አጠቃቀም ያላቸው ቃላት ነፈሽ የሚለው ቃልም ሌሎች የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። ለምሳሌ ያህል በተለይ ጥልቅ ከሆኑ ስሜቶች ጋር የተያያዘ ሲሆን ውስጣዊ ማንነትን ሊያመለክት ይችላል። (1 ሳሙኤል 18:1) በተጨማሪም አንድ ሰው ነፍስ እንደመሆኑ መጠን ሕይወቱን ሊያመለክት ይችላል።—1 ነገሥት 17:21-23
c “መንፈስ” ተብሎ የተተረጎመው ሩህ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ትንፋሽ” ወይም “ነፋስ” ማለት ነው። መንፈስ ከሰዎች ጋር በተያያዘ ሁኔታ ሕያው የሆነ መንፈሳዊ አካል አያመለክትም፤ ከዚህ ይልቅ ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ እንዳስቀመጠው “የሰው የሕይወት ኃይል” ነው።
d እንደዚህ ዓይነት እንግዳ የሆነ አመለካከት የነበረው የመጨረሻ ፈላስፋ እርሱ አልነበረም። በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ አንድ ሳይንቲስት ሰዎች ሊሞቱ ሲሉ ከነበራቸው ክብደት ላይ ልክ እንደሞቱ ያላቸውን ክብደት በመቀነስ የብዙ ሰዎችን ነፍስ እንደመዘነ ተናግሯል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በማሳዳ የነበሩት ዜሎትስ የሚባሉት አይሁዶች ሞት ነፍሳችንን ነፃ ያወጣታል ብለው ያምኑ ነበር