የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 19:- ከ17ኛው እስከ 19ኛው መቶ ዘመን—ሕዝበ ክርስትና በዓለም ላይ ከተከሰቱት ለውጦች ጋር ያደረገችው ትንቅንቅ
“ፍልስፍናና ሃይማኖት ፈጽሞ ሊታረቁ አይችሉም።”—የ19ኛው መቶ ዘመን ጀርመናዊ ባለቅኔ ጌዎርግ ኼርቪግ
“ፍልስፍና” ብለን የምንተረጉመው “ፊሎዞፊ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “የጥበብ ፍቅር” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው ግሪክኛ ቃል የመጣ ሲሆን ፍቺውን በትክክል ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው። ዘ ኒው ኢንሳክሎፔድያ ብሪታኒካ “አጠቃላይና ሙሉ በሙሉ ሊገልጸው የሚችል ፍቺ” መስጠት ስለ መቻሉ ቢጠራጠርም “በተለያዩ ሰብዓዊ ገጠመኞች ላይ መመራመር” ወይም “የሰውን ልጅ በይበልጥ የሚያሳስቡትን ጉዳዮች እያጤኑ፣ ሥርዓት በተከተለ ዘዴና በብልሃት መመርመር” የሚል ማብራሪያ በመስጠት የዚህን ቃል ፍቺ ለማስቀመጥ የመጀመሪያ ሙከራ አድርጓል።
ይህ ፍቺ እውነተኛ ሃይማኖትና ፍልስፍና ሊታረቁ የማይችሉበትን ምክንያት በግልጽ ያስቀምጣል። እውነተኛ ሃይማኖት አምላክ ለሰው በገለጻቸው መመሪያዎች ላይ እንጂ “በተለያዩ ሰብዓዊ ገጠመኞች” ላይ የተመሠረተ አይደለም። ደግሞም በአንደኛ ደረጃ የሚያተኩረው በፈጣሪ ዓላማ ላይ እንጂ “የሰውን ልጅ በይበልጥ በሚያሳስቡት ጉዳዮች” ላይ አይደለም። በሌላ በኩል ግን የሐሰት ሃይማኖት የተመሠረተው ልክ እንደ ፍልስፍና በሰብዓዊ ገጠመኞች ላይ ሲሆን ሰብዓዊ ጥቅሞችን ከሁሉ በላይ ያስቀምጣል። ሕዝበ ክርስትና ዓለም ከሚያደርገው ለውጥ ጋር ትንቅንቅ ከገጠመችበት ከ17ኛው መቶ ዘመን ወዲህ በተለይ ይህ ሐቅ ገሃድ ሆኗል።
ከሦስት አቅጣጫ የተፈጠረ ስጋት
በ17ኛው መቶ ዘመን ገና ዘመናዊ ሳይንስ ብቅ ሲል በሃይማኖትና በዘመናዊ ሳይንስ መካከል ግጭት መፈጠሩ የማይቀር መስሎ ይታይ ነበር። በጣም ድንቅ የሆኑ ሳይንሳዊ ግኝቶች ሳይንስ የማይሳሳትና የመጨረሻው ወሳኝ ነገር እንደሆነ የሚያስመስል አክሊለ ብርሃን እንዲያጠልቅና ሳይንሳዊነት የሚባል የጣዖት አምልኮ ማለትም አንድ ራሱን የቻለ ሃይማኖት እንዲፈጠር አድርገዋል። ሃይማኖት እርግጠኛ ሆኖ ይናገራቸው የነበሩ ነገሮች ሁሉ ሳይንሳዊ “ሐቅ” ከፈነጠቀው ብርሃን አንጻር ሲታዩ በማስረጃ ሊረጋገጡ የማይችሉ ከንቱ ሐሳቦች መስለው ቁጭ አሉ። ሳይንስ አዲስና ስሜትን የሚመስጥ ነገር መስሎ ሲታይ ሃይማኖት ግን ጊዜ ያለፈበትና የተሰለቸ ተደርጎ ይታይ ጀመር።
በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ዘመን አውሮፓን አጥለቅልቆ የነበረው “ኢንላይትንመንት” (Enlightenment) የተባለ የተመራማሪነት እንቅስቃሴ ሃይማኖትን በተመለከተ እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል። የተመራማሪነት እንቅስቃሴ ለምሁራዊነትና ለቁሳዊ እድገት ትልቅ ቦታ በመስጠት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥልጣን እንዲሁም ልማድ እንዲዳከሙና የትችት ሐሳቦች እንዲበረታቱ አደረገ። ይህ አካሄድ እውቀትና ደስታ ያመጣል ተብሎ ታስቦ ነበር። ዘ ኒው ኢንሳክሎፔድያ ብሪታኒካ “የተመራማሪነት እንቅስቃሴ ሥረ መሠረት የግሪክ ፍልስፍና” እንደሆነ ይገልጻል።
የተመራማሪነት እንቅስቃሴ በተለይ በፈረንሳይ ጐልቶ የሚታይ ክስተት ነበር። ከታላላቆቹ የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች መካከል ቮልቴርና ደኒስ ዲድሮ ይገኙበታል። በታላቋ ብሪታንያ ውስጥም እንደ ጆን ሎክ እና ዴቪድ ኸም የመሳሰሉ አፈቀላጤዎች ተነሱለት። ከዩናይትድ ስቴስትስ መሥራች አባቶች መካከል እነ ቶማስ ፔይን፣ ቤንጃሚን ፍራንክሊንና ቶማስ ጀፈርሰን የዚህ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ነበሩ። እንዲያውም ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እንዲለያዩ የሚጠይቀው የዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግሥት የተመራማሪነት ፅንሰ ሐሳብ ነፀብራቅ ነው። በጀርመን ውስጥ ከታወቁት የዚህ እንቅስቃሴ ተከታዮች መካከል ክርስቲያን ቮልፍ፣ ኢማኑኤል ካንት እና የሙዚቃ ደራሲው የፌሊክ ሜንደልሰን ወንድ አያት ሞሰስ ሜንደልሰን ይገኙበታል።
ሃይማኖትን በጥርጣሬ ይመለከት የነበረው ካንት “ተመራማሪነት ሰዎች ራሳቸው በራሳቸው ላይ ካመጡት የጥገኝነት ቀንበር የተላቀቁበት ነው” የሚል ፍቺ እንደሰጠ ይነገራል። የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አለን ደብልዩ ዉድ የካንትን አባባል ሲያብራሩ “ሰዎች ስለ ሥነ ምግባር፣ ፖለቲካና ሃይማኖት እናውቅላችኋለን የሚሉ ፖለቲከኞች፣ የቤተ ክርስቲያን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የሚነግሯቸውን አሜን ብለው ከሚቀበሉ ይልቅ ስለ እነዚህ ጉዳዮች የሚሻለውን ራሳቸው አስበው የመወሰን ድፍረት የሚያዳብሩበት ሂደት” ነው ማለቱ እንደነበረ ገልጸዋል።
በ18ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በመጀመሪያ በታላቋ ብሪታንያ ተጀመረ። በዚህ ወቅት ትኩረቱ ሁሉ ከግብርና ይልቅ በማሽኖችና በልዩ ልዩ ኬሚካሎች አማካኝነት ሸቀጣ ሸቀጦችን ወደ ማምረቱ ተግባር ዞሮ ነበር። ይህም በግብርና የሚተዳደረውን የገጠሩን ኅብረተሰብ ከኑሮው በማናጋት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ ፍለጋ ከተሞችን እንዲያጨናንቁ አደረገ። ይህ ደግሞ ሥራ አጥነትን፣ የመኖሪያ ቤት እጥረትን፣ ድህነትንና ከሥራ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮችን አስከተለ።
ሕዝበ ክርስትና ከሳይንስ፣ ከተመራማሪነት እንቅስቃሴና ከኢንዱስትሪ ከሦስት አቅጣጫ የተደቀነባትን አስጊ ሁኔታ መወጣት ትችል ይሆን?
ቀስ በቀስ አምላክን ወደ ጎን ገሸሽ ማድረግ
ለብዙዎቹ የኅብረተሰብ ችግሮች መንሥኤው ሃይማኖት ነው የሚለው የተመራማሪነት እንቅስቃሴ አመለካከት ሰዎችን አሳመናቸው። “አንድ ኅብረተሰብ መገንባት ያለበት መለኮታዊና ተፈጥሮአዊ ሕግ ባስቀመጠው ንድፍ መሠረት ነው” የሚለው አስተሳሰብ “አንድ ኅብረተሰብ የሚገነባው ወይም ሊገነባ የሚችለው በራሱ በሰው ‘ብልሃት’ ወይም ‘ዘዴ’ ነው በሚለው አስተሳሰብ ተተካ። በዚህ መንገድ ዓለማዊና ማኅበራዊ ሰብዓዊነት ብቅ ያለ ሲሆን እሱ ደግሞ በተራው በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ፍልስፍናዎችና የማኅበረሰብ ሳይንስ ፅንሰ ሐሳቦች እንዲፈልቁ አድርጓል” በማለት ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ይናገራል።
እነዚህ ፅንሰ ሐሳቦች ትልቅ ተደማጭነት የነበረው ዣን ዣክ ሩሶ የተባለው ፈረንሳዊ የተመራማሪነት ደጋፊ የሆነ ፈላስፋ ያራምድ የነበረውን “ሕዝባዊ ሃይማኖት” የሚጨምሩ ነበሩ። ይህ ጽንሰ ሐሳብ የሚያተኩረው በአንድ መለኮታዊ አካልና ለዚህ መለኮታዊ አካል በሚቀርበው አምልኮ ላይ ሳይሆን ኅብረተሰቡንና እያንዳንዱን ግለሰብ በሚያሳስቡ ጉዳዮች ላይ ነበር። ፈረንሳዊው የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ ክሎድ ኦንሪ ደ ሩቭሯ “አዲስ የክርስትና እምነት” ያራምድ የነበረ ሲሆን የእሱ ተከታይ የነበረው ኦጉስት ኮንት “የሰብዓዊነት ሃይማኖት” የሚል ጽንሰ ሐሳብ ያራምድ ነበር።
በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ማኅበራዊ ወንጌል በመባል የሚታወቀው የአሜሪካውያን ንቅናቄ በፕሮቴስታንቶች መካከል ማቆጥቆጥ ጀመረ። አውሮፓውያን ያራምዱት ከነበረው ፅንሰ ሐሳብ ጋር በጣም የሚመሳሰል ነበር። ይህ በሃይማኖታዊ ትምህርት ላይ የተመሠረተ ፅንሰ ሐሳብ የአንድ ክርስቲያን ዋና ተግባር በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ እንደሆነ ይገልጽ ነበር። ይህ ሐሳብ እስከ አሁን ድረስ በፕሮቴስታንቶች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳገኘ ነው። ይህ ዓይነቱ አቋም በካቶሊኮችም ዘንድ በተለያየ መልኩ አለ። ለምሳሌ በፈረንሳይ አገር ሠራተኛም ቄስም መሆንን፣ በላቲን አሜሪካም ከጭቆና ነፃ የመውጣትን መንፈሳዊ ትምህርት ለማስፋፋት የሚታገሉ አሉ።
በ1982 የታተመው የታይም መጽሔት ሪፖርት እንደሚያመለክተው የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ጭምር ይህንኑ ዝንባሌ አንጸባርቀዋል። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “በፕሮቴስታንቶች ዘንድ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ወደሆኑት የሕዝቡ መሠረታዊ ችግሮች የማዘንበል አዝማሚያ ይታያል። . . . ቁጥራቸው እያደገ ያለ የካቶሊክ ሚስዮናውያን ድሆችን ለመርዳት መሰለፍ ማለት ሥር ነቀል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለሚያመጡ ንቅናቄዎች ድጋፍ መስጠት ማለት ነው። እነዚህን ለውጦች ለማምጣት የሚታገለው ንቅናቄ በማርክሲስት አብዮት የሚመራም እንኳ ቢሆን ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ አይሉም። እንዲያውም ሰዎችን ወደ ራሳቸው ሃይማኖት ማስለወጥ ከትክክለኛው ተግባራቸው አንፃር ሲታይ ምንም ፋይዳ እንደሌለው የሚሰማቸው ሚስዮናውያን አሉ።” እነዚህ ሚስዮናውያን በአንድ ወቅት ‘ሃይማኖታዊ አምልኮ የሚያነጣጥረው በኅብረተሰቡ ላይ እንጂ በአምላክ ላይ አይደለም’ የሚል አስተያየት ከሰጠው ከፈረንሳዊው የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁር ከኤሚል ደርክሃይም ጋር ይስማማሉ።
ሕዝበ ክርስትና ቀስ በቀስ ይሁን እንጂ አምላክን ከሃይማኖት ገሸሽ እያደረገች እንደሄደች ግልጽ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች ኃይሎችም ወጥረው ያዟት።
አምላክን የሃይማኖት መልክ ባላቸው ርዕዮተ ዓለማት መተካት
አብያተ ክርስቲያናት ኢንዱስትሪ ባመጣው ሥር ነቀል ለውጥ ለተፈጠሩት ችግሮች ምንም መፍትሄ አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ የሰብዓዊ ፍልስፍና ውጤት የሆኑ የሃይማኖት መልክ ያላቸው ርዕዮተ ዓለማት መፍትሔውን እናሳያችሁ በማለት ክፍት ቦታውን ለመያዝ መሯሯጥ ጀመሩ።
ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች ሀብትና ንብረት ማካበት የሕይወት ዋና ዓላማ ሆኖ ታያቸው። ይህም የኢንዱስትሪው ሥር ነቀል ንቅናቄ ያራገበው ስለ ራስ ብቻ የመጨነቅ ዝንባሌ ነው። ፍቅረ ነዋይ አንድ ራሱን የቻለ ሃይማኖት ሆነ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ‘ሁሉን ቻይ በሆነው ገንዘብ’ ተተካ። ጆርጅ በርናርድ ሾው በጻፈው ተውኔት ላይ አንድ ተዋናይ “እኔ ሚልየነር ነኝ። የእኔ ሃይማኖት እሱ ነው” በማለት ይህን አባባል በተዘዋዋሪ ገሃድ አውጥቶታል።
ሌሎች ሰዎች ደግሞ ወደ ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች ዞር አሉ። የካርል ማርክስ ተባባሪ የነበረው የሶሻሊዝም ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኤንግልስ ውሎ አድሮ ሶሻሊዝም ሃይማኖትን እንደሚተካና ሃይማኖታዊ ባሕርይ እያዳበረ እንደሚሄድ ተንብዮ ነበር። ጡረተኛ ፕሮፌሰር ሮበርት ኒዝቤት እንደተናገሩት ሶሻሊዝም አውሮፓ ላይ እግሩን ሲተክል “ሶሻሊስቶች የአይሁድን ወይም የክርስትናን እምነት በመካድ እነርሱን ወደተካቸው ፍልስፍና መፍለሳቸው በወቅቱ ጐልቶ የሚታይ ክስተት ነበር።”
ሕዝበ ክርስትና በዓለም ላይ የተከሰቱ ለውጦችን መቋቋም አለመቻሏ “ሃይማኖት የለሽነት፣ ሳይንሳዊ ቁስ አካል፣ አምላክ የለሽ ኮሚኒዝም፣ ብሔራዊ ስሜት፣ ናሲዝም፣ ፋሺዝም፣ ማኦይዝም፣ ሰብዓዊ ነፃነትና እንደ ሃይማኖት የሚታዩ ሌሎች በርካታ ርዕዮተ ዓለማት” በማለት ወርልድ ክርስቺያን ኢንሳክሎፔድያ የሚጠቅሳቸው ኃይሎች እንዲፈለፈሉ በር ከፍቷል።
እነዚህ እንደ ሃይማኖት የሚታዩ ርዕዮተ ዓለማት ካፈሩት ፍሬ አንፃር ሲታዩ እንግሊዛዊው ባለ ቅኔ ጆን ሚልተን “ሁሉም ከንቱ ጥበብ፤ ሁሉም የውሸት ፍልስፍና ናቸው” ሲል የተናገረው ትክክል ይመስላል።
አማካይ አቋም መፈላለግ
በአንድ በኩል፣ ደካማ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች በሌላ በኩል ደግሞ የሃይማኖት መልክ ያላቸው አታላይ ፍልስፍናዎች ከፊታቸው ሲደቀኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሌላ የተሻለ ነገር መፈለግ ጀመሩ። አንዳንዶች “የተፈጥሮ ሃይማኖት” በመባል ጭምር በሚታወቀው ዲኢዝም በሚባለው ፍልስፍና ሲናፍቁት የነበረውን ነገር እንዳገኙ ተሰምቷቸው ነበር። በ17ኛው መቶ ዘመን በተለይ በእንግሊዝ አገር ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የዲኢዝም ፍልስፍና አምላክን ሳይተዉ ሳይንስን መቀበል የሚያስችል አማካይ አቋም እንደሆነ ተገልጿል። ስለዚህ የዲኢዝም ፍልስፍና ተከታዮች ነፃ አመለካከት ያላቸው መሐል ሰፋሪዎች ሆኑ።
ዉድ የተባሉት ደራሲ እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ:- “የዲኢዝም ፍልስፍና መሠረታዊ ትርጉሙ በአንድ አምላክ ማመንና ከአምላክ የመጣን መመሪያ እየተከተሉ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ የማመዛዘን ችሎታ ተጠቅሞ ሃይማኖታዊ ተግባር ማከናወን ማለት ነው።” ይሁን እንጂ አንዳንድ የዲኢዝም ፍልስፍና ተከታዮች “ከአምላክ በመጣ መመሪያ” አናምንም ማለታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ አንቀበልም እስከ ማለት አድርሷቸዋል። ምንም እንኳን ይህ ፍልስፍና ዛሬ እምብዛም ባይኖርም የግል አመለካከታቸውን ወይም ሌሎች አማራጭ ፍልስፍናዎችን በማስቀደም የቤተ ክርስቲያንን ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥልጣንን ገሸሽ የሚያደርጉ ክርስቲያን ነን ባዮች የዚህን ፍልስፍና መሠረታዊ ሐሳቦች ይከተላሉ።
የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳቦች
በሃይማኖትና በሳይንስ መካከል ኃይለኛው ግጭት የተደረገው ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳቡን ያቀረበበት የሕያዋን ነገሮች አመጣጥ (Origin of Species) የተባለው መጽሐፍ 1859 በታተመ ጊዜ ነው። በተለይ በዩናይትድ ስቴትስና በእንግሊዝ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች በመጀመሪያ ላይ ይህን ፅንሰ ሐሳብ በጥብቅ አውግዘውት ነበር። ሆኖም ተቃውሞው ብዙ ሳይቆይ ረገበ። ዳርዊን ሲሞት “በጣም አስተዋይ የሆኑና የተማሩ ቀሳውስት ዝግመተ ለውጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ በመመርመር ከሚገኘው እውቀት ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል” በማለት ዘ ኢንሳክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ይናገራል።
ቫቲካን በጥብቅ የተከለከሉ መጻሕፍት ዝርዝር በምትለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ውስጥ የዳርዊንን መጻሕፍት ያላስገባችበት ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በ1893 በቺካጎ ተደርጎ በነበረው የዓለም ሃይማኖቶች ጉባኤ ላይ የተገኙ ተሰብሳቢዎች ያሳዩትን ስሜት ለምን እንዳሳዩ ሊገልጽ ይችላል። ቡድሂስቶችና ሒንዱዎች እየሰሙ አንድ “ክርስቲያን” ተናጋሪ እንደሚከተለው አለ:- “የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ በሃይማኖታችን መግቢያ ላይ የነበረውን ክፍተት ይደፍናል፤ ሳይንስ ፍጥረት ስለተገኘበት መንገድ የሚናገረውን የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ በአጠቃላይ ሲታይ አጥጋቢ ሆኖ ካገኘው የአምላክን መንገድ የሚያውቁና የሚወዱ ሰዎች ይህን ፅንሰ ሐሳብ በደስታ መቀበል እንዳለባቸው ግልጽ ነው።” ይህ አነጋገር በከፍተኛ ጭብጨባ ተቀባይነት አግኝቷል።
በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ አንፃራዊ ሃይማኖት የሚል ስያሜ የተሰጠው እንቅስቃሴ ካገኘው ተወዳጅነት አንፃር ሲታይ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ምንም አያስደንቀንም። አንፃራዊ ሃይማኖት በዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተደረገ ሳይንሳዊ ጥናት ሲሆን ዓላማው ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ያላቸውን ተዛምዶና አመሠራረታቸውን ለማወቅ የተካሄደ ጥናት ነበር። ለምሳሌ እንግሊዛዊው የሥነ ሰብ ሊቅ ጆን ሉበክ ‘ሰዎች በመጀመሪያ በአምላክ አያምኑም ነበር፣ ከዚያም የአስማት ኃይል አላቸው በሚባሉ ነገሮች ላይ እምነት ተጀመረ፣ ቀጥሎ ተፈጥሮን ማምለክ ተጀመረ፣ ከዚያ በማስከተል በረቂቁ ዓለም ውስጥ ብዙ አማልክት አሉ ማለት ተጀመረ፣ በመጨረሻም አንድ አምላክ ወደማምለክ ተደረሰ’ የሚል ጽንሰ ሐሳብ አቅርበዋል።
ሆኖም ዘ ኢንሳክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን እንደሚገልጸው ከሆነ “በዚህ አመለካከት መሠረት ሃይማኖት በመለኮታዊ ኃይል የተገለጸ ፍጹም እውነት ሳይሆን ሰው ስለ አምላክና ስለ ሥነ ምግባር ያለው አመለካከት እያደገ በመሄዱ የተገኘ ነገር ነው።” ስለዚህ ይህን ፅንሰ ሐሳብ የተቀበሉ ሰዎች በሃይማኖታዊ ዝግመተ ለውጥ መሰላል ላይ ሽቅብ የወጣውን ዲኢዝምን ማለትም “ሕዝባዊ ሃይማኖትን” ወይም “የሰብዓዊነት ሃይማኖትን” መቀበል ምንም አላዳገታቸውም።
እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በመጨረሻ ወዴት ይመራ ይሆን? ገና በ19ኛው መቶ ዘመን ላይ እንግሊዛዊው ፈላስፋ ኸርበርት ስፔንሰር ኅብረተሰቡ ፈጽሞ ከሃይማኖት ጋር ወደማይጣጣምበት የእድገት ደረጃ እየገሰገሰ እንዳለ ተናግሮ ነበር። ወደ 20ኛው መቶ ዘመን ስንመጣም ፕሮፌሰር ኒዝቤት የማኅበረሰብ ጠበብት ስለ ሃይማኖት ያላቸውን አጠቃላይ እምነት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- ሃይማኖት “የሰው ልጆችን ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ፍላጎቶች ያሟላል። እነዚህ ፍላጎቶች ሰው በዝግመተ ለውጥ ሂደት እየቀጠለ ሲሄድ ካልከሰሙ በስተቀር በዚህም ሆነ በዚያ ሃይማኖት ምን ጊዜም የማይጠፋ የሰው ልጆች ባሕል እንደሆነ ይቀጥላል።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በዚህ መሠረት የማኅበረሰብ ጠበብት “የዝግመተ ለውጥ እድገት” ውሎ አድሮ ሃይማኖት እንዲከስም ያደርጋል ብለው ያስባሉ ማለት ነው።
እውነተኛውን አምልኮ ለማግኘት የተደረገ የተጧጧፈ ፍለጋ
ሕዝበ ክርስትና 200 ለሚያክሉ ዓመታት በዓለም ከሚከሰቱት ለውጦች ጋር ባደረገችው ውጊያ እየተሸነፈች እንደመጣች በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ግልጽ ሆኖ ነበር። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት ከዓለማዊ ፍልስፍና እምብዛም ወደማይሻልበት ደረጃ አዝቅጦ ነበር። ሁኔታው በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ሰዎችን የሚያሳስብ ነበር። እውነተኛውን አምልኮ ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ ተጧጧፈ። በእርግጥም ሕዝበ ክርስትናን ማደስ ፈጽሞ የማይሞከር ነገር ነው ሊባል ወደሚቻልበት ደረጃ ተደርሶ ነበር። ከዚህ ይልቅ የሚያስፈልገው እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ማቋቋም ነበር። ስለዚህ ጉዳይ በሚቀጥለው እትማችን ላይ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ትችላለህ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የዓለም ለውጥ ባሳደረባት ተፅእኖ ሕዝበ ክርስትና አቋሟን አላላች
የዘመናዊ ሳይንስ ብቅ ማለት በማይታይ ነገር ላይ የነበረውን እምነት ከማዳከሙም በላይ በሳይንስ “ሊረጋገጡ” ባልቻሉ ነገሮች ላይ ጥርጣሬ ፈጥሯል። ሕዝበ ክርስትና የአምላክ መንግሥት ለዓለም ችግሮች መፍትሄ ታመጣለች ብላ ከመጠበቅ ይልቅ ምንም ማረጋገጫ የሌላቸውን እንደ ዝግመተ ለውጥ ያሉትን ሳይንሳዊ የሚባሉ ፅንሰ ሐሳቦች በመቀበልና በሳይንሳዊ እውቀት ላይ በመተማመን በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ የነበራትን አቋም አላልታለች።
የተለያዩ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማት መፈጠራቸው (ካፒታሊዝም፣ ዲሞክራሲ፣ ሶሻሊዝም፣ ኮሚኒዝምና የመሳሰሉት) ብሔራዊ ግጭቶችና ርዕዮተ ዓለማዊ ሽኩቻዎች እንዲከሰቱ አድርጓል። ይህም ትክክለኛው የምድር ገዥ ሰው ሳይሆን አምላክ መሆኑን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲደበዝዝ አድርጓል። ሕዝበ ክርስትና ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን በመጣስና የአንድ ሃይማኖት ተከታዮችን እርስ በርስ ባጨራረሱ ጦርነቶች ውስጥ በመግባት ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የላላ አቋም አሳይታለች። ሕዝበ ክርስትና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሃይማኖት መልክ ያላቸውን ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማት ደግፋለች።
ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ የኢንዱስትሪና የሳይንስ ሥር ነቀል ለውጥን ተከትሎ መጣና በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ስግብግብነትን ከማስፋፋቱም በላይ ፍትሕና እኩልነት የሌሉ መሆናቸውን ፈጦ እንዲታይ አድርጓል። ሕዝበ ክርስትና በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በሥነ ከባቢ ወይም በፖለቲካ ላይ በሚያተኩሩ ሰብዓዊ ጉዳዮች ውስጥ በመጠላለፍ መለኮታዊ ጉዳዮችን ቸል በማለት አቋሟን አላልታለች።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሽቅብ ወይስ ቁልቁል?
ሰዎች ፍጹም ሆነው እንደተፈጠሩና ፈጣሪያቸውን እንዴት አድርገው በትክክል እንደሚያመልኩ ያውቁ እንደነበረ፤ ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ በማመፃቸው ለ6,000 ዓመታት ያህል በአካላዊም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ደረጃቸው ወደታች እያሽቆለቆሉ በመሄድ ላይ እንዳሉ፤ አልፎ ተርፎም በመጀመሪያ ይከተሉት ከነበረው እውነተኛ አምልኮ ከምን ጊዜውም ይበልጥ እየራቁ በመሄድ ላይ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
የሥነ ሕይወትና የሃይማኖት ዝግመተ ለውጥ ደግሞ ሰዎች ኋላ ቀር ከሆነ ደረጃ ተነስተው ቀስ በቀስ እንደተሻሻሉ እንዲሁም ቀደም ሲል ምንም ሃይማኖት የሌላቸው አምላክ የለሾች እንደነበሩ፣ በኋላ ግን በአካላዊም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ደረጃቸው እንደተሻሻሉ፣ ወደ አዲስ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ምግባራዊ የእድገት ደረጃ እንደደረሱ ይናገራል።
ስለ ሰብዓዊ ባሕርይ፣ የሰው ዘር አሁን ስላለበት ሁኔታና ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ለሃይማኖት ስለሚሰጠው ቦታ ካለህ ከራስህ እውቀት በመነሳት የትኛው አመለካከት ይበልጥ ከሐቁ ጋር የሚስማማ ይመስልሃል?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳርዊን “የሕያዋን ነገሮች አመጣጥ” በተባለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፉ ላይ ያሰፈራቸው ግምታዊ ሐሳቦች ሰበብ ሆኑላቸውና ብዙ ሰዎች ከአምላክ በመጣ መመሪያ ላይ የነበራቸውን እምነት እርግፍ አድርገው ተዉት
[ምንጭ]
Harper’s