የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 21:- ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ—ደም የተረጨ መጎናጸፊያ
“በደም ላይ አስተማማኝ መሠረት መጣል አይቻልም።”—ሼክስፒር፣ እንግሊዛዊው ባለ ቅኔና ጸሐፌ ተውኔት (1564-1616)
ከአሥራ ዘጠኝ ዓመት በፊት በጉያና ጆንስታውን የተፈጸመውን አሳዛኝ ክስተት ታስታውሳለህ? ከ900 የሚበልጡ ፒፕልስ ቴምፕል በመባል የሚታወቅ አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት በጅምላ የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሲሆን ብዙዎቹ የሞቱት በፈቃደኛነት ሳይናይድ የተቀላቀለበት የፍራፍሬ ጭማቂ በመጠጣት ነበር።
ይህ ድርጊት ያስደነገጣቸው ሰዎች ‘የገዛ አባላቱን ሕይወት የሚሠዋ ምን ዓይነት ሃይማኖት ቢሆን ነው?’ ሲሉ ጠይቀዋል። ይሁንና ላለፉት 6,000 የሚያክሉ ዓመታት በሃይማኖት ስም የንጹሐን ደም ሲፈስስ ኖሯል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ግን በየትኛውም የታሪክ ወቅት ታይቶ በማያውቅ መጠን በተደጋጋሚና በብዙ መንገዶች ደም መፋሰስ ተከስቷል። ይህንን ሐቅ ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች እጅግ ጥቂቱን ብቻ ተመልከት።
ለሐሰት አምላክ የቀረቡ የሰው መሥዋዕቶች
ከ1914 ወዲህ የተካሄዱት ሁለቱ የዓለም ጦርነቶችና ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑት ትናንሽ ግጭቶች ደም እንደ ጎርፍ እንዲፈስ አድርገዋል። ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ፈረንሳዊው ጸሐፊ ጉይ ደ ሞፓሶ የአገር ፍቅር ስሜት “ጦርነት የሚፈለፈልበት እንቁላል” ነው ከማለቱም ሌላ “ራሱ እንደ ሃይማኖት ሆኗል” ብሏል። እንዲያውም ዚ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን እንዳለው ከሆነ ከአገር ፍቅር ስሜት ጋር ተዛማጅነት ያለው ብሔረተኝነት “በባሕላዊ ሃይማኖቶች ውስጥ የነበሩት የሥነ ምግባር ደንቦች እየተፈረካከሱ በመውደቃቸው ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት” በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ገናና ሃይማኖት ሆኗል። (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) የሐሰት ሃይማኖት እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ የተሳነው መሆኑ በፈጠረው ክፍተት ውስጥ ብሔረተኝነት ተተክቷል።
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ ከነዋሪዎቿ መካከል 94.4 በመቶ የሚያክሉት ክርስቲያን ነን ባዮች ከነበሩባት ከናዚ ጀርመን የበለጠ ይህን ጉዳይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ አናገኝም። የፕሮቴስታንት እምነት መገኛ የሆነችውና በ1914 ሊቀ ጳጳስ ፓየስ አሥረኛ “የዓለማችን ምርጥ ካቶሊኮች መኖሪያ” በማለት ያወደሷት ጀርመን ከሌሎቹ አገሮች ሁሉ የሕዝበ ክርስትናን ትክክለኛ ገጽታ በተሻለ መንገድ ታንጸባርቃለች ብሎ መጠበቁ የተገባ ነው።
የሚያስገርመው ካቶሊኩ አዶልፍ ሂትለር ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘው ከካቶሊኮች ይልቅ በፕሮቴስታንቶች ዘንድ ነበር። በ1930 በተደረገው ምርጫ ወቅት ፕሮቴስታንት ነዋሪዎች በሚበዙባቸው ክፍለ ግዛቶች 20 በመቶ ድምፅ ሲያገኝ የካቶሊኮች መኖሪያ በሆኑት ክፍለ ግዛቶች ያገኘው ድምፅ 14 በመቶ ብቻ ነበር። በተደረጉት የመንግሥት ምርጫዎች የናዚ ፓርቲ ከፍተኛውን አብላጫ ድምፅ ያገኘው በ1932 በኦልደንበርግ ሲሆን ከዚህ ክልል ነዋሪዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ፕሮቴስታንቶች ነበሩ።
ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው “በባሕላዊ ሃይማኖቶች ውስጥ የነበሩት የሥነ ምግባር ደንቦች እየተፈረካከሱ በመውደቃቸው ምክንያት የተፈጠረው ክፍተት” ጉልህ ሆኖ የሚታየው ከካቶሊክ ይልቅ በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ ነበር። ደግሞም ይህ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ትንሽ ለቀቅ ያለ ሃይማኖታዊ ትምህርት እንዲጀመር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትችት እንዲያቆጠቁጥ በር የከፈቱት ጀርመንኛ ተናጋሪ የሆኑ የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ምሁራን ናቸው።
ከዚሁ ጋር ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው ነገር ደግሞ ካቶሊኮች ለሂትለር የሚሰጡትን ድጋፍ የኋላ ኋላ እንዲያጠናክሩ ያደረጋቸው ምክንያት ነው። የጀርመኑ ታሪክ ጸሐፊ ክላውስ ሾልደር እንዳሉት “የጀርመን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተለይ ከሮማ ጋር በጣም የቀረበ ግንኙነት አላት።” ቫቲካን፣ ናዚ ኮሙኒዝምን የሚመክት ጋሻ ነው ብላ ስላመነች የነበራትን ተሰሚነት በመጠቀም የሂትለርን ክንድ ለማበርታት ቆርጣ ተነሣች። ሾልደር እንዲህ ብለዋል:- “መሠረታዊ የሆኑት ውሳኔዎች እያደር በካቶሊኩ አስተዳደር እጅ ገቡ፤ እንዲያውም በመጨረሻ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሦስተኛው ራይክ ዘመን የሚኖራት አቋምና የወደፊት ዕጣ ፋንታዋ የተወሰነው ሙሉ በሙሉ በሮም ነበር።”
ሕዝበ ክርስትና በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ወቅት የተጫወተችው ሚና በእጅጉ ስሟን አጉድፎባታል። ኮንሳይስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ዎርልድ ሚሽን እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ክርስቲያን ያልሆኑት ሰዎች . . . አንድ ሺህ ለሚያክሉ ዓመታት የክርስትና ትምህርት ሲማሩ የኖሩ ብሔራት ስሜታቸውን መግታት ተስኗቸው ከንቱ የሥልጣን ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ሲሉ መላውን ዓለም በእሳት ሲያጋዩት በዓይናቸው ተመልክተዋል።”
እርግጥ ነው፣ በሃይማኖት ምክንያት የተቆሰቆሱ ጦርነቶች መኖራቸው አዲስ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ የተለያየ እምነት ያላቸው ብሔራት እርስ በርሳቸው ይዋጉ ከነበረበት ከቀድሞው ዘመን ጋር ሲወዳደር 20ኛው መቶ ዘመን ተመሳሳይ ሃይማኖት ባላቸው ብሔራት መካከል የሚደረጉ አስከፊ ግጭቶች የተፋፋሙበት ዘመን ሆኗል። የብሔረተኛነት አምላክ የሃይማኖት አማልክትን እንደፈለገ እንደተጠቀመባቸው ግልጽ ነው። በታላቋ ብሪታንያና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊኮች በኢጣልያና በጀርመን የሚገኙ ካቶሊኮችን በገደሉበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓን የሚገኙ ቡድሂስቶችም በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚገኙት ቡድሂስት ወንድሞቻቸው ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመዋል።
የሆነ ሆኖ የራሷ የሕዝበ ክርስትና ልብስ በደም የተበከለ በመሆኑ በሌሎች ላይ ጣቷን መቀሰር አትችልም። ክርስቲያን ነን የሚሉትም ሆኑ ክርስቲያን ያልሆኑት ወገኖች ፍጽምና ከሌላቸው ሰብዓዊ መንግሥታት ጎን ቆመው መሟገታቸው፣ መደገፋቸውና አንዳንድ ጊዜም እነርሱን መምረጣቸው እነዚህ መንግሥታት ባፈሰሱት ደም ጭምር ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥታትን ከአምላክ የሚያስበልጥና የራሱን አባላት በጦርነት አምላክ መሠዊያ ላይ ፖለቲካዊ መባ አድርጎ የሚያሳልፍ ምን ዓይነት ሃይማኖት ነው?
‘ንጹሕ ደም ማፍሰሳቸውን ቀጠሉ’
ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ከሃዲዋን እስራኤልን በሚመለከት የተነገሩት እነዚህ ቃላት በሐሰት ሃይማኖቶች በተለይም ደግሞ በሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ላይ የሚሠሩ ናቸው። (መዝሙር 106:38) በዚህ እልቂት የረገፉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስታውስ፤ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትም ጭምር በዚህ አሳዛኝ ድርጊት ከመጠየቅ አያመልጡም።—ሚያዝያ 8, 1989 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ተመልከት።
የጀርመን ቀሳውስትም እንዲሁ እምብዛም በሰፊው የማይታወቅ ግን ከዚህ ያላነሰ አሳዛኝ ድርጊት ሲፈጸም እያዩ እንዳላዩ ሆነዋል። ሂትለር በ1927 ሜይን ካምፍ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ ዘርን በሚመለከት ያለውን ሐሳብ ካሰፈረ ከሁለት ዓመታት በኋላ ካቶሊካዊው ጸሐፊና የሃይማኖት ምሁር ጆሴፍ ማየር ያሳተሙት የኤፒስቆጶሳቱ ፈቃድ ያለበት መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “የአእምሮ ሕሙማን፣ የሥነ ምግባር ዕብደት የተጠናወታቸውና ሌሎች ዝቅተኛ ሰዎች እንዲዋለዱ መፍቀድ ከተማዋን በእሳት እንዲለኩሱ መፍቀድ ነው።” የሉተራኑ ፓስተር ፍሬድሪክ ቮን ቦደልሽዊንግ አካለ ስንኩል የሆኑ ሰዎችን ማምከን ከኢየሱስ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።
ሃይማኖታዊ ድጋፍ ያገኘው ይህ አመለካከት ከ100,000 በላይ የሚሆኑ የአእምሮ ሕሙማን የሆኑ ነዋሪዎች እንዲገደሉና ቁጥራቸው 400,000 እንደሚደርስ የሚገመቱ ሰዎች ተገድደው እንዲመክኑ ምክንያት ለሆነው በ1939 ለወጣው የሂትለር “የዩተኔዢያ ድንጋጌ” መንገድ ጠርጓል።a
በራይላንድ የሚገኙት የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት ጥፋታቸውን በግልጽ ያመኑት ጦርነቱ ካበቃ ከ40 ዓመታት በኋላ በ1985 ነበር፤ እንዲህ ብለዋል:- “ቤተ ክርስቲያናችን በሰዎች ላይ በኃይል የማምከን ድርጊት ሲፈጸም፣ ሕሙማንና አካለ ስንኩላን ሲገደሉ እንዲሁም ሰዎችን ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ የሕክምና ዘዴ መሞከሪያ ሲያደርጉ ተቃውሞ ሳታሰማ ቀርታለች። ዛሬ በሕይወት የቀሩት የዚህ ጥፋት ሰለባዎችና ዘመዶቻቸው ይቅር እንዲሉን እንማጸናለን።”
መንግሥት የሚያካሂደው የዩተኔዢያ ዘመቻ ጋብ ያለው የማንስተሩ የካቶሊክ ጳጳስ ነሐሴ 3, 1941 ቀን ይህ የነፍስ ማጥፋት ፖሊሲ ነው በማለት በኃይለ ቃል ጠንካራ ተቃውሟቸውን ካሰሙ በኋላ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ የ60,000 ሰዎች ሕይወት እስኪቀጠፍ ድረስ ድርጊቱ ለ19 ወራት በይፋ ሳይወገዝ የቆየው ለምንድን ነው?
የሃይማኖት የደም ዕዳ
አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ለሕይወት አክብሮት እንዳላቸውና ሰዎችን ከጉዳት ለመከላከል የቆሙ መሆናቸውን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ቀሳውስቱ ማጨስ እንዲሁም አልኮልን ጨምሮ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን አላግባብ መጠቀም፣ ደምን ወደ ሰውነት ማስገባት እና ሴሰኛነት በአካል ላይ የሚያስከትሉትን አደጋ ሳይቦዝኑ ለመንጋቸው ያሳስባሉን? ከዚህ ይበልጥ ደግሞ እነዚህ ድርጊቶች የአምላክን ሞገስ ሊያሳጡን የሚችሉ የሥጋ ሥራዎች መሆናቸውን በመናገር ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያወግዟቸዋልን?—ሥራ 15:28, 29፤ ገላትያ 5:19-21
እርግጥ ነው አንዳንዶቹ ይህን ያደርጋሉ። እንዲሁም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ብዙ ፋንዳሜንታሊስት አብያተ ክርስቲያናት ውርጃ ንጹህ ደም ማፍሰስ ነው እያሉ በማውገዝ ለሕይወት አክብሮት እንዳላቸው ለማሳየት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ በአውሮፓ ውስጥ በውርጃ ረገድ እጅግ ልል የሆነ ሕግ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ ካቶሊካዊቷ አገር ኢጣልያ ነች።
የቡድሂዝም እምነትም እንዲሁ ውርጃን ያወግዛል። ይሁን እንጂ 70 በመቶ የሚያክለው ነዋሪ የቡድሂዝም ተከታይ በሆነባት በጃፓን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 618,000 ውርጃ እንደተካሄደ ሪፖርት ተደርጓል። ይህም የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሣል:- እንግዲያው አንድን ሃይማኖት የምንገመግመው በምንድን ነው? የበላይ አካላቱ ወይም ጥቂት ቀሳውስቱ በሚናገሩት ነገር ወይስ ጥሩ አቋም አላቸው የሚባሉት አብዛኛዎቹ አባላት በሚሠሩት ሥራ?
ሌላው ክፉዎችን ከማስጠንቀቅ ወደኋላ እንዳሉ የሚያሳየው ዘርፍ የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ቀመርና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜዎች ናቸው። እነዚህ ሁለት ነገሮች በ1914 የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እንደተቋቋመች ይጠቁማሉ።b ሕዝበ ክርስትና ክርስቶስ የተወለደበት ነው የምትለውን ዕለት በየዓመቱ ታኅሣሥ ውስጥ የምታከብር ቢሆንም ከ1,900 ዓመታት በፊት የአይሁዳውያን መሪዎች ኢየሱስ የተቀባ ንጉሥ መሆኑን እንዳልተቀበሉ ሁሉ የእርሷም ቀሳውስት በመግዛት ላይ ያለ ንጉሥ መሆኑን አያውጁም።
ከየትኛውም ሃይማኖታዊ ወገን ጎን የተሰለፉ ቢሆኑ የአምላክን የሥነ ምግባር ሕግ ሳይታዘዙ መቅረትና በመግዛት ላይ ላለው የአምላክ መንግሥት ለመገዛት እምቢተኛ መሆን ስለሚያስከትለው አስከፊ ውጤት የማያስጠነቅቁ ቀሳውስት በሕዝቅኤል 33:8 መሠረት በራሳቸው ላይ የደም ዕዳ እየቆለሉ ነው። ማስጠንቀቂያ ሳያሰሙ መቅረታቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ የመንጋቸው አባላት የደም ባለ ዕዳ ሲሆኑ እጃቸውን አጣምረው ከማየት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
በዚህ መንገድ የሐሰት ሃይማኖት መጎናጸፊያዋን በንጹሐን ደም በመርጨት ሕይወት ሰጭ የሆነውን የክርስቶስ ኢየሱስን ደም አጣጥላለች። (ማቴዎስ 20:28 እና ኤፌሶን 1:7ን ተመልከት።) ከዚህ የተነሣ በቅርቡ፣ አዎን እጅግ በቅርቡ፣ የሐሰት ሃይማኖት የእጅዋን ታገኛለች!—ራእይ 18:8
‘ያለፈ ታሪኳን እየደገመች ያለችው የሐሰት ሃይማኖት’ ከጥፋት አታመልጥም! ይህን ጉዳይ በሚቀጥለው እትማችን ላይ እናብራራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ ከ15ኛው መቶ ዘመን አንስቶ በሊቀ ጳጳሳቱ ፈቃድ ከ300,000 እስከ 3,000,000 በሚገመቱ “ጠንቋዮች” ላይ የተፈጸመውን ግድያ የሚያስታውስ ነው።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1982 የታተመውን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 16-18 ተመልከት።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ዛሬ በአብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች ሃይማኖት የአብዮት ሎሌ . . . ሆኗል። በሰሜን አየርላንድ እንዲሁም በሕንድ ክፍለ አሕጉርና በፊሊፒንስ እርስ በርስ መገዳደልን ማበረታታቱን ቀጥሏል።”—The Encyclopedia of Religion
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሐሰት ሃይማኖቶች በ20ኛው መቶ ዘመን ያስመዘገቡት ታሪክ ከአሁን ቀደም በራሳቸው ላይ ሲከምሩ ከኖሩት የደም ዕዳ ሁሉ የከፋ ነው። በ15ኛው መቶ ዘመን መናፍቃን ናቸው በሚል ስም በእሳት እንዲቃጠሉ የተደረጉት ሰዎች ሁኔታ የሐሰት ሃይማኖቶች በራሳቸው ላይ የደም ዕዳ ሲከምሩ እንደነበር ያሳያል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ደወሎች ቀልጠው ለጦርነት ዓላማ ውለዋል
[ምንጭ]
Bundesarchiv Koblenz