በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ በደል የሚያስከትለው ስውር ቁስል
“ራሴን ጠላሁ። ድርጊቱን ለማስቆም አንድ ነገር ማድረግና መናገር ነበረብኝ ብዬ ዘወትር አስባለሁ። ርካሽ እንደሆንኩ ሆኖ ይሰማኛል።”—አን
“ከሰዎች እንደተገለልኩ ሆኖ ይሰማኛል። ብዙውን ጊዜ ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር እታገላለሁ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሞትን እመኛለሁ።”—ጂል
“በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ በደል . . . በሕፃናት አእምሮ፣ ነፍስና ሥጋ ላይ የሚሰነዘር እጅግ ከባድ የሆነ፣ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትልና ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ጥቃት ነው . . . እንዲህ ዓይነቱ በደል የአንድን ሰው ሕልውና በሁሉም አቅጣጫ የሚነካ ነው።” ይህ ሐሳብ በቤቨርሊ ኤንጀል ከተዘጋጀው ዘ ራይት ቱ ኢኖሰንስ ከተባለው ጽሑፍ ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው።
ሁሉም ሕፃናት ለሚደርስባቸው ወሲባዊ በደል አንድ ዓይነት ምላሽ አይሰጡም።a ሕፃናት ያላቸው ባሕርይ፣ አስቸጋሪ ሁኔታን የመቋቋም ችሎታና ስሜታዊ ጥንካሬ የተለያየ ነው። በተጨማሪም የሚሰጡት ምላሽ በአብዛኛው በደሉን ከፈጸመው ሰው ጋር ባላቸው ዝምድና፣ በተፈጸመው ወሲባዊ በደል ክብደት፣ ድርጊቱ በወሰደው የጊዜ መጠን፣ በሕፃናቱ ዕድሜና በሌሎች ጉዳዮችም ላይ የተመካ ነው። ከዚህም ሌላ የተፈጸመው ወሲባዊ በደል ይፋ ከወጣና ልጅቷ ዐዋቂ ከሆነ ሰው ፍቅራዊ ድጋፍ ካገኘች ብዙውን ጊዜ ጉዳቱ ሊቀንስ ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የዚህ ድርጊት ሰለባዎች ጥልቅ የሆነ ስሜታዊ ቁስል ይደርስባቸዋል።
በጣም ጎጂ የሆነበት ምክንያት
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ጉዳት የሚደርስበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። መክብብ 7:7 “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” ይላል። አንድ ዐዋቂ ሰው ግፍ ሲፈጸምበት ይህን ያህል የሚሰማው ከሆነ አንዲት ትንሽ ሕፃን በተለይ እምነት የምትጥልበት ወላጅዋ ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ሲፈጽምባት ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድርባት እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። በዚህ ላይ ደግሞ በሕይወት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ለልጆች ስሜታዊና መንፈሳዊ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ ወቅቶች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) አንዲት ልጅ የሥነ ምግባር ድንበሮች ማበጀትና ለራሷ ጥሩ ግምት መስጠት የምትጀምረው ከለጋ ዕድሜዋ አንስቶ ነው። በተጨማሪም አንዲት ልጅ ከወላጆቿ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመፍጠር የፍቅርንና በሌላው ላይ እምነት የመጣልን ትርጉም ትማራለች።—መዝሙር 22:9
“ወሲባዊ በደል የተፈጸመባቸው ሕፃናት” አሉ ዶክተር ጄ ፓትሪክ ጋነን፣ “ቀደም ሲል ሲያጎለብቱት የቆዩት በሌላ ሰው ላይ እምነት የመጣል መንፈስ ይጠፋል።” ወሲባዊ በደሉን የፈጸመው ሰው ልጅቷ በሌሎች ላይ የነበራትን እምነት ያንኮታኩተዋል። የደህንነት፣ የነፃነትና በራስ የመተማመን መንፈሷን በማሳጣት የራሱን የግል ጾታዊ ስሜት ለማርካት እንደ ዕቃ ይጠቀምባታል።b ትንንሽ ልጆች በኃይል የሚፈጸሙባቸው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ምን ትርጉም እንዳላቸው ባይረዱም እንኳ ሁሉም ማለት ይቻላል፣ የሚፈጸምባቸው ነገር የሚረብሽ፣ የሚያስፈራና የሚያዋርድ ሆኖ ያገኙታል።
በመሆኑም በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ በደል “ከሁሉ የከፋ ክህደት” ተብሏል። ይህ የሚከተለውን የኢየሱስ ጥያቄ ያስታውሰናል:- “ወይስ ከእናንተ፣ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፣ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው?” (ማቴዎስ 7:9) በአንዲት ሕፃን ላይ ወሲባዊ በደል የሚፈጽም ሰው ፍቅርን ሳይሆን “ድንጋይ” እንደ መስጠት የሚቆጠረውን እጅግ አስከፊ የሆነ ወሲባዊ ጥቃት ይፈጽምባታል።
ቁስሉ ቶሎ የማይሽረው ለምንድን ነው?
ምሳሌ 22:6 “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ይላል። ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ዕድሜ ልክ ሊዘልቅ እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ አንዲት ልጅ ራሷን ከወሲባዊ ጥቃት የመከላከል ኃይል እንደሌላት ሆኖ እንዲሰማት ተደርጋ ካደገችስ? “ፍቅር” ለሚያሳያት ሰው ውለታ ለመመለስ ብልሹ የጾታ ድርጊት መፈጸም እንዳለባት አድርጋ እንድታስብ ከተደረገችስ? ራሷን ከንቱና ርካሽ አድርጋ እንድትመለከት ከተደረገችስ? ይህ ዕድሜ ልኳን ብልሹ ምግባር ይዛ እንድትኖር ሊያደርጋት አይችልምን? እርግጥ በልጅነት የተፈጸመ ወሲባዊ በደል በኋላ በጉልምስና ዘመን ለሚንጸባረቅ ብልሹ ምግባር ሰበብ ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም እንዲህ ዓይነት በደል የደረሰባቸው ሰዎች የሆነ ዓይነት ምግባር ወይም ስሜት የማሳየት አዝማሚያ የሚንጸባረቅባቸው ለምን እንደሆነ ግልጽ ሊያደርግልን ይችላል።
በልጅነታቸው ወሲባዊ በደል የተፈጸመባቸው ብዙ ሰዎች የመንፈስ ጭንቀትን ጨምሮ በርከት ያሉ ምልክቶች ይታዩባቸዋል። በተጨማሪም አንዳንዶች ሥር በሰደደና አንዳንዴም በጣም ከባድ በሆነ የጥፋተኝነት፣ የኀፍረትና የቁጣ ስሜት ይዋጣሉ። ሌሎቹ ሰለባዎች ደግሞ ስሜታቸው ከናካቴው ሊጠፋና ስሜታቸውን መግለጽ ሊሳናቸው አልፎ ተርፎም ምንም ዓይነት ስሜት ላይሰማቸው ይችላል። እንዲሁም ብዙዎቹ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሊመለከቱና ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችሉ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። አጎቷ ወሲባዊ በደል የፈጸመባት ሳሊ ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ “ወሲባዊ በደል በፈጸመብኝ ቁጥር ምንም ማድረግ እንደማልችል ሆኖ ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ እፈዝዛለሁ፣ እደነዝዛለሁ፣ ሰውነቴ ሁሉ በድን ይሆናል፣ እንዲሁም ግራ እጋባለሁ። ይህ ይሆን የነበረው ለምንድን ነው?” ሲንቲያ ታወር የተባሉ የሥነ ልቦና ባለሙያ “ብዙውን ጊዜ በልጅነታቸው ወሲባዊ በደል የተፈጸመባቸው ሰዎች ዕድሜልካቸውን የጥቃት ሰለባ ነን የሚል እምነት ይዘው እንደሚኖሩ የተካሄዱት ጥናቶች አመልክተዋል” ሲሉ ገልጸዋል። በደል የሚፈጽም ባል ያገቡ ይሆናል፣ ለአደጋ የተጋለጡ እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ይሆናል ወይም ደግሞ አደጋ ላይ ሲወድቁ ራሳቸውን የመከላከል ኃይል እንደማይኖራቸው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል።
በአብዛኛው ልጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚቀሰቀሱት ስሜቶች ዝግጁ የሚሆኑት ከ12 ዓመት ገደማ በኋላ ነው። ሆኖም በአንዲት ሕፃን ላይ ሥነ ምግባር የጎደለው ወሲባዊ ድርጊት በኃይል በሚፈጸምበት ጊዜ በሚቀሰቀሱት ስሜቶች በእጅጉ ግራ ልትጋባ ትችላለች። በአንድ ጥናት ላይ እንደታየው ይህ ከጊዜ በኋላ የትዳርን ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንዳታጣጥም እንቅፋት ሊሆንባት ይችላል። ሊንዳ የተባለች አንዲት ሰለባ እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “በትዳር ውስጥ የጾታ ግንኙነት መፈጸም በሕይወቴ ከገጠሙኝ አስቸጋሪ ነገሮች ሁሉ ይበልጥ ከባድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የጾታ ግንኙነቱን ከአባቴ ጋር እየፈጸምኩ እንዳለሁ ሆኖ ስለሚሰማኝ እሸበራለሁ።” ሌሎች ሰለባዎች ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ስሜት በማሳየት ከልክ ያለፈ የጾታ ፍላጎት ያዳብሩ ይሆናል። ጂል “ልቅ የሆነ ሕይወት በመምራት ፈጽሞ ከማላውቃቸው ሰዎች ሁሉ ጋር የጾታ ግንኙነት እፈጽም ነበር” ስትል ሐቁን ሳትሸሽግ በግልጽ ተናግራለች።
በተጨማሪም በልጅነታቸው ወሲባዊ በደል የተፈጸመባቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር ጤናማ ግንኙነት ይዞ መቀጠል ሊሳናቸው ይችላል። አንዳንዶች ከወንዶች ወይም በሥልጣን ቦታ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር መግባባት ይቸገሩ ይሆናል። አንዳንዶች በደል በመፈጸም ወይም ተቆጣጣሪ ለመሆን በመሞከር የመሠረቱትን ወዳጅነት ወይም ትዳር ያፈርሳሉ። ሌሎች ደግሞ ከናካቴው የቅርብ ዝምድና ከመመሥረት ይቆጠባሉ።
ጎጂ የሆኑ ስሜቶቻቸውን ወደራሳቸው የሚያነጣጥሩ ሰለባዎችም አሉ። “ሰውነቴ ለወሲባዊ ጥቃቱ ምላሽ በመስጠቱ ተጸየፍኩት” ስትል ሬባ ተናግራለች። የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ወሲባዊ በደል የተፈጸመባቸው ሰዎች ስሜቶቻቸውን ለማዳፈን በሚያደርጉት ጥረት የአመጋገብ ሥርዓታቸው ሲዛባ፣c የሥራ ሱሰኞች ሲሆኑ፣ አልኮል አላግባብ ሲጠጡና አደገኛ ዕፆችን ሲወስዱ ይታያሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለራሳቸው ያላቸውን ጥላቻ ይበልጥ ቀጥተኛ በሆኑ መንገዶች ይገልጹ ይሆናል። “ሰውነቴን ቆርጫለሁ፣ ክንዶቼን በጥፍሬ ተልትያለሁ፣ እንዲሁም ራሴን አቃጥያለሁ” ስትል ሬባ አክላ ተናግራለች። “መሠቃየት እንዳለብኝ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።”
ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማው ወይም እንዲህ የሚያደርግ ሰው ሁሉ ወሲባዊ በደል ተፈጽሞበታል ብለን ለመደምደም መቸኮል የለብንም። ለዚህ ምክንያት የሆኑት ሌሎች አካላዊ ወይም ስሜታዊ ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ልጆቻቸውን የሚደበድቡ፣ የሚያንቋሽሹና የሚያዋርዱ፣ የሚያስፈልጓቸውን ሥጋዊ ነገሮች ችላ የሚሉ ወይም ደግሞ የአደገኛ ዕፅ ወይም የአልኮል ሱሰኛ የሆኑ ወላጆች ያሳደጓቸው ሰዎች ተመሳሳይ ምልክቶች እንደሚታዩባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
መንፈሳዊ ጉዳት
በሕፃናት ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ በደል ከሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች ሁሉ ይበልጥ አደገኛው በመንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ነው። ወሲባዊ ጥቃት ‘ሥጋንና መንፈስን ያረክሳል።’ (2 ቆሮንቶስ 7:1) በአንዲት ሕፃን ላይ ወሲባዊ በደል የሚያደርስ ሰው በልጅቷ ላይ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት በመፈጸም፣ አካላዊና ሥነ ምግባራዊ ወሰኖቿን በመጣስና በሌሎች ላይ ያላትን እምነት እንድታጣ በማድረግ መንፈሷን ወይም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድረውን የአእምሮ ዝንባሌዋን ይበክለዋል። ይህ ከጊዜ በኋላ የልጅቷን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ዕድገት ሊያስተጓጉለው ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ በፒያ ሜሎዲ የተዘጋጀው ፌሲንግ ኮዲፔንደንስ የተባለው መጽሐፍ “በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት ከባድ በደል . . . ሕፃናቱ በአንድ ከፍተኛ ኃይል ላይ የነበራቸውን እምነትም የሚበክል በመሆኑ መንፈሳዊ በደልም ነው” ሲል ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል ኢለን የተባለች አንዲት ክርስቲያን ሴት “የምድራዊ አባቴ ጭካኔና ኃይለኝነት ወለል ብሎ እየታየኝ ይሖዋን እንዴት እንደ አባት አድርጌ ልመለከተው እችላለሁ?” ብላለች። ቴሪ የተባለች አንዲት ሌላ ሰለባ “ይሖዋን እንደ አባት አድርጌ ተመልክቼው አላውቅም። አምላክ፣ ጌታ፣ ሉዓላዊ ገዢና ፈጣሪ እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ! እንደ አባት አድርጌ መመልከት ግን ያስቸግረኛል!” ብላለች።
እነዚህ ግለሰቦች እንዲህ ብለው የተናገሩት በመንፈሳዊ ደካማ ስለሆኑ ወይም እምነት ስለሚጎድላቸው ነው ብለን ወዲያውኑ መደምደም የለብንም። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል ያልተቆጠበ ጥረት የሚያደርጉ መሆኑ መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውን የሚያሳይ ነው! ሆኖም አንዳንዶች እንደ መዝሙር 103:13 ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲያነቡ ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል። ጥቅሱ “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል” ይላል። አንዳንዶች ይህን በእውቀት ደረጃ ይቀበሉት ይሆናል። ሆኖም አባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ጤናማ ጽንሰ ሐሳብ ከሌላቸው ይህ ጥቅስ ስሜታቸውን ላይነካው ይችላል!
በተጨማሪም አንዳንዶች “እንደ ሕፃን” ማለትም ራሱን እንዳልቻለ፣ ትሑትና ሁሉን እንደሚያምን ልጅ ሆነው በአምላክ ፊት መቅረብ ያስቸግራቸው ይሆናል። ወደ አምላክ ሲጸልዩ እውነተኛ ስሜታቸውን ይደብቁት ይሆናል። (ማርቆስ 10:15) በመዝሙር 62:7, 8 ላይ ያሉትን የዳዊት ቃላት በራሳቸው ላይ ለመተርጎም ያመነቱ ይሆናል:- “መድኃኒቴና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፤ የረድኤቴ አምላክ ተስፋዬም እግዚአብሔር ነው። የሕዝብ ማኅበር ሁላችሁ፣ በእርሱ ታመኑ፣ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው።” አልፎ ተርፎም የጥፋተኝነትና የከንቱነት ስሜት እምነታቸውን ሊያዳክመው ይችላል። አንዲት ሰለባ እንዲህ ብላለች:- “በይሖዋ መንግሥት ላይ ጠንካራ እምነት አለኝ። ይሁን እንጂ እዚያ የመግባት ብቃት እንዳለኝ ሆኖ አይሰማኝም።”
ይሁን እንጂ ሁሉም ሰለባዎች እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል ማለት አይደለም። አንዳንዶች ይሖዋን እንደ አንድ አፍቃሪ አባት አድርገው በማየት ወደ እርሱ መቅረብ የቻሉ ከመሆኑም በላይ የልባቸውን አውጥተው ለመናገር አይቸገሩም። በዚያም ሆነ በዚህ በልጅነትሽ ወሲባዊ በደል ተፈጽሞብሽ ከነበረ በደሉ በሕይወትሽ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለይተሽ ማወቅሽ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኚው ትችያለሽ። አንዳንዶች ጉዳዩን እርግፍ አድርጎ መተዉ በቂ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ጉዳቱ በጣም ከባድ ሆኖ ከታየሽ ተስፋ አትቁረጪ። ቁስልሽ ሊሽር ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እዚህ ላይ የሰፈረው ማብራሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ፖርኒያ ወይም ዝሙት ብሎ በሚጠራው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 6:9፤ ከዘሌዋውያን 18:6-22 ጋር አወዳድር።) ይህ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነውን ሁሉንም ዓይነት የጾታ ግንኙነት ያጠቃልላል። ኀፍረተ ሥጋን ማሳየት፣ የሌሎችን ኀፍረተ ሥጋ በማየት ወሲባዊ እርካታ ለማግኘት መሞከር፣ ወሲባዊ ጽሑፎችንና ሥዕሎችን ማሳየትና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ጸያፍ ድርጊቶች ፖርኒያ ባይሆኑም እንኳ የሕፃናትን ስሜት ሊጎዱ ይችላሉ።
b ሕፃናት ዐዋቂ የሆኑ ሰዎችን የማመን ዝንባሌ ስላላቸው አንድ የሚያምኑት የቤተሰባቸው አባል፣ ታላቅ ወንድማቸው፣ የቤተሰባቸው ወዳጅ ወይም ፈጽሞ የማያውቁትም ሰው እንኳ ወሲባዊ በደል ሲፈጽምባቸው በሌሎች ሰዎች ላይ የነበራቸው እምነት ጨርሶ ይንኮታኮታል።
c የታኅሣሥ 22, 1990 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ተመልከት።