“ለመፈወስም ጊዜ አለው”
አን የሁሉ ሰው አጽናኝ ነበረች፤ ለማንኛውም ሰው ችግር ፈጥና ትደርስ ነበር። እንዲሁ ከውጪ ስትታይ የረጋ መንፈስ የነበራትና እንከን የማይወጣላት ነበረች። የሆነው ነገር ሁሉ በአእምሮዋ እስካቃጨለበት ቀን ድረስ ድብቅ የሆነ ስሜታዊ ቁስል እንዳላት የሚጠቁም ምንም ፍንጭ አይታይባትም ነበር። “ሥራ ላይ እንዳለሁ ነበር” ስትል አን መለስ ብላ ታስታውሳለች፤ “ሕመምና ከባድ የሆነ የኀፍረት ስሜት ይሰማኝ ጀመር። መነሳት ሁሉ አቃተኝ! ለበርካታ ቀናት ተሠቃየሁ። ከዚያም የእንጀራ አባቴ ወሲባዊ ጥቃት የፈጸመብኝን ጊዜ አስታወስኩ። አስገድዶ ደፍሮኝ ነበር። ይህን ድርጊት የፈጸመብኝ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ አልነበረም።”
“ለመፈወስም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:3) እንደ አን ሁሉ በልጅነታቸው ወሲባዊ በደል የተፈጸመባቸው ብዙ ሰዎች ለረጅም ጊዜ በውስጣቸው ተዳፍኖ የቆየው ትዝታ መቆስቆሱ ለፈውስ ሂደቱ በጣም ጠቃሚ ነው።
ይሁን እንጂ ወሲባዊ ጥቃትን የመሰለ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ የሚፈጥር ነገር እንዴት ሊረሳ ይችላል? አንዲት ሕፃን በአባቷ ወይም በሌላ ጉልበተኛ ሰው ፊት ምን ያክል አቅመ ቢስ እንደሆነች አስብ። ሮጣ ማምለጥ አትችልም። እንዳትጮህ ትፈራለች። ለማንም ሰው ለመንገርም አትደፍርም! ሆኖም ወሲባዊ በደል የፈጸመባትን ሰው በየዕለቱ እያየችው ምንም እንዳልተፈጸመ አስመስላ ለመኖር ትገደድ ይሆናል። እንዲህ አስመስሎ መኖር ለአንድ ዐዋቂ ሰው እንኳ ከባድ ነው፤ ለአንዲት ሕፃን ደግሞ ፈጽሞ ለመሸከም የሚከብድ ነገር ነው። ስለዚህ የልጆች ልዩ ተሰጥኦ የሆነውን ምናባዊ የሆነ ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ከአእምሮዋ ውስጥ ታስወግደዋለች! ጨርሶ ከአእምሮዋ በማስወጣትም ሆነ ስሜቷን በማደንዘዝ ወሲባዊ በደሉ እንዳልተፈጸመ ለማስመሰል ትሞክራለች።
እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ማየት ወይም መስማት ለማንፈልጋቸው ነገሮች አእምሯችንን የምንዘጋበት ጊዜ አለ። (ከኤርምያስ 5:21 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ወሲባዊ በደል የደረሰባቸው ሰዎች ይህን ችሎታ በሕይወት ለመቀጠል የሚያስችል መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። አንዳንድ ሰለባዎች እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በደሉ የተፈጸመው በሌላ ሰው ላይ እንደሆነና እኔ ተመልካች እንደነበርኩ አድርጌ ለማሰብ እሞክራለሁ።” “በእንቅልፍ ልቤ የተፈጸመ ነገር እንደሆነ አድርጌ አስባለሁ።” “የደረሰብኝን ወሲባዊ በደል ላለማስታወስ ስል በአእምሮዬ የሒሳብ ስሌት እሠራለሁ።”—ስትሮንግ አት ዘ ብሮክን ፕሌስስ፣ በሊንዳ ቲ ሳንፎርድ።
እንግዲያው ሰርቫይቪንግ ቻይልድ ሴክሹዋል አቢዩዝ የተባለው መጽሐፍ “በልጅነታቸው ወሲባዊ በደል ከተፈጸመባቸው ሰዎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ይህ ድርጊት የተፈጸመባቸው መሆኑን እንደማያውቁ ይገመታል” ማለቱ ምንም አያስደንቅም። አንዳንዶቹ የደረሰባቸውን በደል ቢያስታውሱም እንኳ እንደ ሐዘን፣ ቁጣና ኀፍረት ላሉት ከድርጊቱ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ስሜቶች በር አይከፍቱም።
ስሜትን አፍኖ መያዝ—በአእምሮ ውስጥ የሚካሄድ ትግል
እንግዲያው እነዚህ ነገሮች ተዳፍነው ቢቀሩና በደሉ የደረሰባቸው ሰዎች ሁኔታውን ቢረሱት የተሻለ አይሆንም? አንዳንዶች እንደዚህ ማድረጉን ይመርጡ ይሆናል። ሌሎች ግን እንዲህ ማድረግ አይቻላቸውም። ሁኔታው ኢዮብ 9:27, 28 እንደሚለው ነው:- “‘የሐዘኔን ሮሮ ልርሳ፣ ፊቴንም ማጥቆር ትቼ ፈገግታ ላሳይ’ ብል . . . መከራና ሥቃይ ይመጣብኛል።” (የ1980 ትርጉም) አስፈሪ ትዝታዎችን አፍኖ ለመያዝ የሚደረገው ጥረት አእምሮን የሚያደክም ከመሆኑም በላይ ሥር የሰደደ የጤና ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ትግል ነው።
በልጅነቷ ወሲባዊ በደል የደረሰባት ሴት ዕድሜዋ እየገፋ ሲሄድ ብዙውን ጊዜ የኑሮ ተጽዕኖዎች የቀድሞ ትዝታዋን አፍና የመያዝ አቅሟን ያዳክሙታል። የሽቶ ጠረን፣ የሚያውቁትን ሰው የሚያስታውስ መልክ፣ የሚያስደነግጥ ድምፅ፣ አልፎ ተርፎም የአንድ ዶክተር ወይም የጥርስ ሐኪም ምርመራ አስፈሪ የሆኑ ትዝታዎችና ስሜቶች ሊቀሰቅስ ይችላል።a እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ለመርሳት የበለጠ ጥረት ማድረጓ ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልምን? በዚህ ወቅት ብዙዎቹ ሰለባዎች እፎይታ የሚሰጣቸው ለማስታወስ የሚያደርጉት ጥረት ነው! ጂል የተባለች አንዲት ሴት ‘ትዝታዎቹን አንዴ ሙሉ በሙሉ ማስታወስ ከተቻለ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በጣም ይቀንሳል። ለማስታወስ ከሚደረገው ጥረት ይበልጥ ጎጂና አደገኛ የሚሆነው አፍኖ ለማስቀረት የሚደረገው ሙከራ ነው’ ብላለች።
ድርጊቱ መፈጸሙን አምኖ መቀበል ያለው ጥቅም
ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንደኛ ነገር፣ አንዲት ሰለባ ድርጊቱን ማስታወሷ እንድታዝን ያደርጋታል። የስሜት ቀውስ ሲደርስብን ማዘናችን የተለመደ ነገር ነው፤ የሚረብሹ ክስተቶችን በኋላችን እንድንተው ይረዳናል። (መክብብ 3:4፤ 7:1-3) ይሁን እንጂ ወሲባዊ በደል የደረሰባት ሴት ሐዘኗ እንዳይወጣላት ተከልክላለች፣ የደረሰባት አሰቃቂ ነገር እንዳልተፈጸመ አድርጋ እንድታስብና የተረበሸ ስሜቷን አፍና እንድትይዝ ተገድዳለች። ስሜትን እንዲህ አፍኖ መያዝ ሐኪሞች ፖስትትሮማቲክ ስትሬስ ዲስኦርደር (የስሜት ቀውስ በደረሰባቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ሥነ ልቦናዊ ችግር) ብለው የሚጠሩትን ስሜት አልባ ድንዛዜ ሊያስከትል ይችላል።—ከመዝሙር 143:3, 4 ጋር አወዳድር።
ትዝታው ሲቀሰቀስ የድርጊቱ ሰለባ የሆነችው ሴት በደሉ እንደገና እየተፈጸመባት እንዳለ ሆኖ በምናቧ ሊታያት ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ሰለባዎች ለጥቂት ጊዜ ወደ ልጅነት ሁኔታ ይመለሳሉ። “የተፈጸመብኝን በደል ድንገት ማስታወስ ስጀምር” ትላለች ጂል፣ “ብዙውን ጊዜ አካላዊ ምልክቶች ይታዩብኛል። አንዳንድ ጊዜ ትዝታዎቹ በጣም ስለሚረብሹኝ የማብድ ሆኖ ይሰማኛል።” ለረጅም ጊዜ ታፍኖ የቆየው ቁጣ ሊገነፍል ይችላል። “ድርጊቱን ሳስታውስ የመንፈስ ጭንቀትና ብስጭት ይይዘኛል” ትላለች ሼላ። ሆኖም በእነዚህ ለየት ያሉ ሁኔታዎች ወቅት መቆጣቱ አግባብነት ያለው ነው። ታፍኖ የቆየ የጽድቅ ቁጣ በመቆጣት የተሰማሽን ሐዘን መግለጽሽ ነው! የተፈጸመብሽን የጭካኔ ድርጊት የመጥላት መብት አለሽ።—ሮሜ 12:9
ወሲባዊ በደል የደረሰባት አንዲት ሴት እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “በደንብ ማስታወስ ከቻልኩ በኋላ ከፍተኛ እፎይታ አግኝቻለሁ . . . ሌላው ቢቀር አሁን ከምን ጋር ስታገል እንደኖርኩ ተገንዝቤያለሁ። ማስታወሱ በጣም አስቸግሮኝ የነበረ ቢሆንም የማይታወቅና ምስጢራዊ በመሆኑ ምክንያት አስፈሪ ሆኖ የነበረውን የሕይወቴን ክፍል መልሼ ማግኘት እንድችል ረድቶኛል።”—ዘ ራይት ቱ ኢኖሰንስ
በተጨማሪም አንዲት ሰለባ የደረሰባትን በደል ማስታወሷ ለአንዳንድ ችግሮቿ መንስኤ የሆነውን ነገር እንድትገነዘብ ሊረዳት ይችላል። “ለራሴ ሥር የሰደደ ጥላቻና ብስጭት እንዳለብኝ ባውቅም ለምን እንደሆነ ግን አላውቅም ነበር” ስትል አንዲት በቅርብ ዘመዷ ወሲባዊ በደል የተፈጸመባት ሴት ተናግራለች። ብዙዎች የተፈጸመውን ድርጊት ማስታወሳቸው ጥፋቱ የእነሱ እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።
እርግጥ ነው፣ ሁሉም የተፈጸመባቸውን ወሲባዊ በደል እንደ ሌሎች ጉልህ ወይም ግልጽ በሆነ መንገድ ያስታውሳሉ ማለት አይደለም። በተጨማሪም ወሲባዊ በደል ከሚያስከትለው መዘዝ ለማገገም እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ሁሉ የግድ ማስታወስ እንደማያስፈልግ አብዛኞቹ አማካሪዎች ይስማሙበታል። ወሲባዊ በደል መፈጸሙን አምኖ መቀበሉ ብቻ ለማገገም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል።—ገጽ 9 ላይ የሚገኘውን ሳጥን ተመልከት።
እርዳታ ማግኘት
በልጅነትሽ ወሲባዊ በደል ተፈጽሞብሽ ከሆነ የትዝታውን ናዳ ብቻሽን ለመቋቋም አትሞክሪ። ስሜትሽን ለሌላ ሰው ማካፈልሽ ጠቃሚ ነው። (ከኢዮብ 10:1 እና 32:20 ጋር አወዳድር።) ከልክ በላይ የተጨነቁ አንዳንዶች በሙያው የተካነ ሐኪም፣ አማካሪ ወይም የአእምሮ ጤና ባለሙያ እርዳታ ለማግኘት ይወስኑ ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ አሳቢነት በተሞላበት መንፈስና በአክብሮት የሚያዳምጡ እምነት የሚጣልባቸው ወዳጆች፣ የትዳር ጓደኛ፣ የቤተሰብ አባላት ወይም ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ጥሩ አጋሮች ሊሆኑ ይችላሉ።b “ከሁሉ ይበልጥ የረዳችኝ የቅርብ ጓደኛዬ ጁሊ ናት” ትላለች ጃኔት። “ትዝታውን ደግሜ ደጋግሜ እንድነግራት ትፈቅድልኛለች። የልብን አውጥቶ መናገር የሚፈጥረው ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጋኛለች። ታዳምጠኛለች፣ እንዲሁም አሳቢነት የተሞላበት ምላሽ ትሰጠኛለች።”
በሌላው ላይ እምነት መጣል አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችል ከመሆኑም በላይ የሌላን ሰው እርዳታ ማግኘት የሚገባሽ ሰው እንዳልሆንሽ ሆኖ ሊሰማሽ ወይም ደግሞ ስለደረሰብሽ ወሲባዊ በደል ማውራት በጣም ሊያሳፍርሽ ይችላል። ሆኖም እውነተኛ ጓደኛ “ለመከራ ይወለዳል፤” በመሆኑም ዕድሉን ከሰጠሽው ወይም ከሰጠሻት በእጅጉ የምትጠቀሚበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆናል። (ምሳሌ 17:17) ይሁንና የልብሽን የምታካፍይውን ሰው በጥንቃቄ መምረጥ አለብሽ። የሚያሳስቡሽን ነገሮች ቀስ በቀስ መግለጡ የተሻለ ይሆናል። ጓደኛሽ ርኅሩኅና ምስጢር ጠባቂ ሆና ካገኘሻት ተጨማሪ ምስጢር ልታካፍያት ትችይ ይሆናል።
በተጨማሪም ለራስሽ አካላዊ እንክብካቤ ማድረግሽ ጠቃሚ ነው። በቂ ዕረፍት ውሰጂ። ልከኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርጊ። ጤናማ አመጋገብ ይኑርሽ። የሚቻል ከሆነ አኗኗርሽ ቀላል ይሁን። ለማልቀስ ነፃነት ይሰማሽ። ሥቃዩ ማብቂያ የሌለው መስሎ ሊታይሽ ቢችልም እንኳ ቀስ በቀስ እየከሰመ ይሄዳል። ምንም ማድረግ የማትችዪ ሕፃን በነበርሽበት ጊዜ እንኳ የደረሰብሽን ወሲባዊ በደል ተቋቁመሽ እዚህ እንደደረሽ አትዘንጊ! አሁን ዐዋቂ እንደመሆንሽ መጠን በዚያን ጊዜ ያልነበረሽ ብቃትና ጥንካሬ አለሽ። (ከ1 ቆሮንቶስ 13:11 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ የሚረብሹሽን ትዝታዎች ፊት ለፊት በመጋፈጥ ዕረፍት ለማግኘት ጥረት አድርጊ። ብርታት ለማግኘት በአምላክ ላይ ታመኚ። መዝሙራዊው “ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት” ብሏል።—መዝሙር 94:19
የጥፋተኝነትንና የኀፍረትን ስሜት ማስወገድ
ማገገም እንድትችይ የሚረዳሽ ሌላው ትልቁ ነገር ራስሽን ከመውቀስ መታቀብ ነው። “አሁንም እንኳ ቢሆን ተጠያቂ አይደለሁም ብዬ ለማሰብ ይቸግረኛል” ስትል ሬባ የተባለች አንዲት ሰለባ ተናግራለች። “ለምን አላስቆምኩትም እያልኩ አስባለሁ።”
ይሁንና ወሲባዊ በደል የሚፈጽሙ ሰዎች አስገድደው ያሰቡትን ለመፈጸም እጅግ ሰይጣናዊ የሆኑ ዘዴዎች ይጠቀማሉ:- ሥልጣናቸውን ይጠቀማሉ (‘አባትሽ ነኝ!’)፣ ያስፈራራሉ (‘ከተናገርሽ እገድልሻለሁ!’)፣ ጉልበት ይጠቀማሉ አልፎ ተርፎም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማት ያደርጓታል (‘ከተናገርሽ አባትሽ ይታሰራል።’)። በአንጻሩ ደግሞ አንዳንዶች የማባበያ ዘዴ ወይም ስጦታና ውለታን መሣሪያ አድርገው ይጠቀማሉ። አንዳንዶች ወሲባዊ ድርጊቱ ጨዋታ ወይም የወላጅ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገው ይነግሯቸዋል። “የሚዋደዱ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ነው ነበር ያለኝ” ስትል አንዲት ሰለባ ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ ተናግራለች። አንዲት ትንሽ ልጅ እንዲህ ዓይነቱን ሥነ ልቦናዊ ማስፈራሪያና ማጭበርበሪያ እንዴት አድርጋ ልትጋፋ ትችላለች? (ከኤፌሶን 4:14 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ ልጆች ምንም ማድረግ የማይችሉ፣ ለአደጋ የተጋለጡና “ለክፋት ነገር ሕፃናት” በመሆናቸው ወሲባዊ በደሉን የሚፈጽመው ሰው በደንታ ቢስነት መንፈስ ያሰበውን ለመፈጸም ይህን ሁኔታቸውን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል።—1 ቆሮንቶስ 14:20
እንግዲያው ልጅ በነበርሽበት ወቅት ምን ያህል ለአደጋ የተጋለጥሽ እንደነበርሽና ራስሽን ለመከላከል አቅሙ እንዳልነበረሽ ቆም ብለሽ ማሰብ ያስፈልግሽ ይሆናል። ከተወሰኑ ትንንሽ ልጆች ጋር ጊዜ ልታሳልፊ ወይም ደግሞ የራስሽን የልጅነት ፎቶዎች ልትመለከቺ ትችያለሽ። በተጨማሪም እገዛ የሚያደርጉ ጓደኞች ጥፋተኛዋ አንቺ እንዳልሆንሽ አዘውትረው በማሳሰብ ሊረዱሽ ይችላሉ።
ያም ሆኖ ግን አንዲት ሴት “አባቴ ቀስቅሶብኝ የነበረውን ስሜት ሳስታውስ በጣም እበሳጫለሁ” ብላለች። አንዳንድ ሰለባዎች (ጥናት ከተካሄደባቸው መካከል 58 በመቶ የሚሆኑት) ወሲባዊ ጥቃት በተፈጸመባቸው ጊዜ ስሜታቸው ተቀስቅሶ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ከፍተኛ የኀፍረት ስሜት እንደሚያስከትልባቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሰርቫይቪንግ ቻይልድ ሴክሹዋል አቢዩዝ የተባለው መጽሐፍ “አንድ ሰው ሰውነቱ ሲደባበስ ወይም በሆነ መንገድ እንዲነቃቃ ሲደረግ አካላዊ ስሜቱ መቀስቀሱ የማይቀር ነገር” እንደሆነና አንዲት ሕፃን “ይህን የስሜት መነቃቃት ልትቆጣጠረው እንደማትችል” ይገልጽልናል። በመሆኑም ለተፈጸመው ድርጊት ሙሉ በሙሉ በኃላፊነት የሚጠየቀው ወሲባዊ በደሉን ያደረሰው ግለሰብ ብቻ ነው። ጥፋቱ የአንቺ አይደለም!
አምላክ በዚህ ረገድ ‘የዋህና ነውር የሌለብሽ’ አድርጎ እንደሚመለከትሽ ማወቅሽም ሊያጽናናሽ ይገባል። (ፊልጵስዩስ 2:15) ከጊዜ በኋላ ራስን የሚጎዳ ድርጊት እንድትፈጽሚ የሚገፋፋሽ ስሜት ሁሉ እየከሰመ ሊሄድና ሰውነትሽን በእንክብካቤ መያዝን ልትማሪ ትችያለሽ።—ከኤፌሶን 5:29 ጋር አወዳድር።
ከወላጆችሽ ጋር ዕርቅ መፍጠር
ለማገገም ሲባል ከሚወሰዱት እጅግ ከባድ የሆኑ እርምጃዎች መካከል አንዱ ይህ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ቁጣ፣ በቀል ወይም የጥፋተኝነት ስሜት በውስጣቸው ታምቆ ይኖራል። ወሲባዊ በደል የደረሰባት አንዲት ሴት “ይሖዋ ወሲባዊ ጥቃት የፈጸመብኝን ሰው ይቅር እንድል የሚጠብቅብኝ ይመስለኛል፤ ሆኖም ይህን ማድረግ አልችልም። ይህ ደግሞ በጣም ያስጨንቀኛል” ብላለች። በሌላ በኩል ደግሞ ወሲባዊ በደል የፈጸመብሽን ሰው እንደ ጦር ትፈሪው ይሆናል። ወይም እናትሽ የተፈጸመው ወሲባዊ በደል ገሃድ ሲወጣ ጉዳዩን ችላ ብላ ካለፈችው ወይም ለመቀበል አሻፈረኝ ካለች ወይም መልሳ ከተቆጣች በእናትሽ ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ስሜት ሊያድርብሽ ይችላል። “እናቴ [አባቴ] የፈጸመውን ድርጊት ላልፈው እንደሚገባ ነገር አድርጋ ነበር የነገረችኝ” ስትል አንዲት ሴት በምሬት ተናግራለች።
ወሲባዊ በደል የደረሰበት ሰው መቆጣቱ ሊያስገርመን አይገባም። ሆኖም ቤተሰቦችን የሚያስተሳስረው ገመድ በጣም ጠንካራ ሊሆን ይችላል፤ እናም ከወላጆችሽ ጋር ያለሽን ዝምድና ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ አትፈልጊ ይሆናል። እንዲያውም ዕርቅ ለመፍጠር ፈቃደኛ ትሆኚ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ በአብዛኛው በሁኔታዎቹ ላይ የተመካ ነው። አንዳንድ ጊዜ ወሲባዊ በደል የደረሰባቸው ሰዎች የተፈጸመባቸውን በደል አቅልለው መመልከታቸው ባይሆንም እንኳ ብስጭትንና ፍርሃትን ለማስወገድ ሲሉ ወላጆቻቸውን ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላሉ። አንዳንዶች ስሜታዊ ግጭት ላለመፍጠር ሲሉ ‘የልባቸውን በልባቸው ይዘው’ ዝም ማለት ይመርጣሉ።—መዝሙር 4:4
ይሁን እንጂ ጉዳዩ ሊፈታ የሚችለው የተፈጸመውን ወሲባዊ በደል በተመለከተ ወላጆችሽን በአካል፣ በስልክ ወይም በደብዳቤ በማነጋገር ብቻ እንደሆነ ሊሰማሽ ይችላል። (ከማቴዎስ 18:15 ጋር አወዳድር።) እንደዚህ የሚሰማሽ ከሆነ ሊገነፍል የሚችለውን የታመቀ ስሜት መቋቋም ትችይ ዘንድ አስቀድመሽ በበቂ ሁኔታ ማገገም ይኖርብሻል። ወይም ቢያንስ ቢያንስ በቂ ድጋፍ ማግኘት አለብሽ። መጯጯህ የሚያስገኘው ፋይዳ ስለማይኖር ጽኑ አቋም መያዝ ቢኖርብሽም እንኳ ለመረጋጋት ጥረት አድርጊ። (ምሳሌ 29:11) (1) የተፈጸመውን ነገር፣ (2) ድርጊቱ ምን ያህል እንደጎዳሽና (3) አሁን ከእነሱ የምትጠብቂው ነገር ምን እንደሆነ (እንደ ይቅርታ መጠየቅ፣ ለሕክምና ያወጣሽውን ወጪ የሚሸፍን ገንዘብ ወይም የጠባይ ለውጥ ያሉ ነገሮች) በመግለጽ ልታነጋግሪያቸው ትችያለሽ። ሌላው ቢቀር በጉዳዩ ላይ በግልጽ መወያየትሽ ልትቋቋሚያቸው ያልቻልሻቸውን ለረጅም ጊዜ የቆዩ ስሜቶች ለማስወገድ ሊረዳሽ ይችላል። በተጨማሪም ከወላጆችሽ ጋር አዲስ ዝምድና ለመመሥረት መንገዱን ሊጠርግልሽ ይችላል።
ለምሳሌ ያህል አባትሽ ከልብ መጸጸቱን በመግለጽ በደሉን መፈጸሙን አምኖ ይቀበል ይሆናል። በተጨማሪም ምናልባት ከአልኮል ሱስ ለመላቀቅ የሕክምና እርዳታ በመውሰድ ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ለውጥ ለማድረግ ከልቡ ጥረት አድርጎ ሊሆን ይችላል። እናትሽም ተገቢውን ጥበቃ ሳታደርግልሽ በመቅረቷ ይቅርታ እንድታደርጊላት ትለምንሽ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የተሟላ ዕርቅ ሊወርድ ይችላል። ያም ሆኖ ግን ወላጆችሽን በተመለከተ አንዳንድ ጥርጣሬ ቢያድርብሽና ወዲያውኑ የተቀራረበ ዝምድና ከመመሥረት ብትታቀቢ ሊገርምሽ አይገባም። ሆኖም ቢያንስ ቢያንስ ምክንያታዊ የሆኑ ቤተሰባዊ ግንኙነቶችን ዳግመኛ መጀመር ትችይ ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ፍጥጫው ወሲባዊ ጥቃቱን የፈጸመውም ሰው ሆነ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ድርጊቱን ለመቀበል አሻፈረኝ እንዲሉና የስድብና የዘለፋ መዓት እንዲያዥጎደጉዱ ሊያደርጋቸው ይችላል። እንዲያውም ግለሰቡ አሁንም ቢሆን ለአንቺ አስጊ መሆኑን ትገነዘቢ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ይቅርታ ማድረጉ አግባብነት ላይኖረው ይችላል። የቅርብ ዝምድና መመሥረትም አስቸጋሪ ነው።—ከመዝሙር 139:21 ጋር አወዳድር።
በዚያም ሆነ በዚህ የተጎዳው ስሜትሽ እስኪጠገን ድረስ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። የመጨረሻውን የፍትሕ እርምጃ የሚወስደው አምላክ መሆኑን በተደጋጋሚ ራስሽን ማሳሰብ ሊያስፈልግሽ ይችላል። (ሮሜ 12:19) ጥሩ ድጋፍ ለሚሰጥ አድማጭ ሐሳብን ማካፈል አልፎ ተርፎም ስሜትሽን በጽሑፍ ማስፈር ቁጣሽን ለማብረድ ሊረዳሽ ይችላል። በአምላክ እርዳታ ቁጣሽን መቆጣጠር ትችያለሽ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የተጎዳው ስሜትሽ አስተሳሰብሽን የመቆጣጠር ኃይሉ እየተዳከመ ይሄዳል።—ከመዝሙር 119:133 ጋር አወዳድር።
በመንፈሳዊ ማገገም
ከዚህ ሁኔታ ጋር ዝምድና ያላቸውን ስሜታዊ፣ ባሕርያዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች በሙሉ እንተንትን ብንል ቦታም አይበቃንም። በአምላክ ቃል አማካኝነት ‘ልብሽን ማደስሽ’ በቀላሉ ማገገም እንድትችይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን መጥቀሱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 12:2) ሕይወትሽ በመንፈሳዊ ሐሳቦችና እንቅስቃሴ እንዲሞላ በማድረግ ‘በፊትሽ ያለውን ለመያዝ ጥረት አድርጊ።’—ፊልጵስዩስ 3:13፤ 4:8, 9
ለምሳሌ ያህል ወሲባዊ በደል የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች መዝሙረ ዳዊትን በማንበብ ብቻ ብዙ ማጽናኛ ማግኘት ችለዋል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በትጋት ሥራ ላይ በማዋል ከዚህ የላቁ ጥቅሞችም ማግኘት ይቻላል። ውሎ አድሮ በትዳር ውስጥ ያለው ውጥረት ሊረግብ ይችላል። (ኤፌሶን 5:21-33) ጎጂ የሆነው ባሕርይ ሊጠፋ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ጤናማ ያልሆኑ ጾታዊ ስሜቶች ሊፈወሱ ይችላሉ። (ምሳሌ 5:15-20፤ 1 ቆሮንቶስ 7:1-5) በተጨማሪም ከሌሎች ጋር ባለሽ የግል ዝምድና ሚዛናዊ መሆንን መማር የምትችይ ከመሆኑም በላይ ጠንካራ የሆኑ የሥነ ምግባር ገደቦች ማበጀት ትችያለሽ።—ፊልጵስዩስ 2:4፤ 1 ተሰሎንቄ 4:10-12
ማገገም እንድትችይ ቆራጥ አቋም መውሰድና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለብሽ አትዘንጊ! ሆኖም መዝሙር 126:5 “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። ከዚህም በተጨማሪ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ለደህንነትሽ እንደሚያስብ አስታውሺ። “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” (መዝሙር 34:18) ወሲባዊ በደል የደረሰባት አንዲት ሴት “ይሖዋ የሚሰማኝን እያንዳንዱን ስሜት እንደሚያውቅና በእርግጥ እንደሚያስብልኝ ከተገነዘብኩ በኋላ ውስጣዊ ሰላም አግኝቻለሁ” ብላለች።
አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ ከአእምሮ ሰላም የበለጠ ነገርም ይሰጠናል። በልጅነታችን የደረሰብንን የማንኛውንም ሥቃይ ትዝታ የሚያጠፋበት ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:3, 4፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 65:17ን ተመልከት።) ሙሉ በሙሉ ማገገም በምትችይበት ጎዳና ላይ ስትጓዢ ይህ ተስፋ ሊያበረታሽና ሊያጠነክርሽ ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንዶቹ ትዝታዎች የሳይኮሶማቲክ ሕመም (በአእምሮ ወይም በስሜት መረበሽ ሳቢያ የሚከሰቱ አካላዊ ችግሮች) ይዘው ብቅ ይላሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ የቅዠት ዓለም ውስጥ ይከታሉ። አንዳንዶች ይህን ሁኔታ በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ከአጋንንታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዘ ትርጉም ሊሰጡት ይችላሉ። በእንዲህ ዓይነት የቅዠት ዓለም ውስጥ የገቡ ሰዎች አንድ ሰው ቀስ ብሎ በር ከፍቶ ሲገባ የሚሰሙ ድምፆችን ሊሰሙ ይችላሉ፤ በደጃፎችና በመስኮቶች በኩል ውልብ የሚሉ ጥላዎችን ያያሉ፤ የሆነ የማይታይ አካል አልጋቸው ላይ እንዳለ ሆኖ ይሰማቸዋል። በጥቅሉ ሲታይ እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት የተፈጸመባቸውን በደል ሙሉ በሙሉ ካስታወሱት በኋላ ይጠፋል።
b ወሲባዊ በደል የደረሰባቸውን ሰዎች እንዴት መርዳት እንደሚቻል የሚገልጽ ጠቃሚ ሐሳብ ከዚህ መጽሔት ጋር እየታተመ በሚወጣው መጠበቂያ ግንብ በተባለው መጽሔት የጥቅምት 1, 1983 (እንግሊዝኛ) እትም ገጽ 27-31 ላይ ይገኛል። ሁሉም የጉባኤ ሽማግሌዎች መለስ ብለው ይህን እትም እንዲመለከቱና ለሚቀርቡላቸው ጉዳዮች በሙሉ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ እናበረታታቸዋለን።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማገገም የሚቻልባቸው መንገዶች
◻ የተፈጸመውን በደል ማስታወስና አምኖ መቀበል
◻ በተፈጸመው ድርጊት ከልብ ማዘን
◻ ጥሩ እገዛ ለሚያደርግ አድማጭ ስሜትን ማካፈል
◻ የጥፋተኝነትንና የኀፍረትን ስሜት ማሸነፍ
◻ ከወላጆች ጋር ዕርቅ መፍጠር
◻ ጎጂ ባሕርይን ለመለወጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ
◻ ጤናማ ያልሆኑ ወሲባዊ ስሜቶችን መፈወስ
◻ ጤናማ የሆኑ የግልና የሥነ ምግባር ገደቦች ማበጀት
◻ ከአምላክና ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ትዝታን መቀስቀስ
ብዙውን ጊዜ ትዝታዎች ሲቀሰቀሱ ሳምንታት፣ ወራት፣ ወይም ዓመታት ይወስዳሉ። እያንዳንዱ ትዝታ ጊዜያዊ የሆነ ቀውስ ያስከትላል። ዘ ራይት ቱ ኢኖሰንስ አንዳንድ ጊዜ “የኋልዮሽ እየሄድሽ እንዳለሽ ሆኖ ሊሰማሽ ይችላል። ሁኔታው ግን እንደዚያ አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻለሽ ትሄጃለሽ። ይበልጥ ጥልቅ የሆኑና አልፎ ተርፎም ይበልጥ የሚያሰቃዩ ስሜቶችንና ሐሳቦችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ታገኛለሽ” ሲል ይገልጻል። ሆኖም አንድ ሰው ለተወሰነ ጊዜ ማገገም የመቻሉ ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ቢያሳስበው ሊያስገርመን አይገባም።—ምሳሌ 18:14
አንዳንድ ሰለባዎች ሌሎች ሰለባዎች የተናገሩትን ማንበብ ወይም መስማት ጠቃሚ ሆኖ ያገኙታል። የቤተሰብ ፎቶዎችንና በልጅነትሽ የሰበሰብሻቸውን ማስታወሻዎች መመልከት፣ ያደግሽበትን ቦታ መጎብኘት፣ ጥሩ እገዛ ለሚያደርጉ ወዳጆችና የቤተሰብ አባላት ሐሳብን ማካፈልም ትዝታዎችን ሊቀሰቅስ ይችላል። ይበልጥ ውጤታማ የሆነው ደግሞ በጽሑፍ ማስፈር ነው። አንዳንድ ሰለባዎች የደረሰባቸውን የስሜት ቀውስ በተመለከተ የሚያስታውሱትን ነገር ሁሉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን በሚያሰፍሩበት ማስታወሻ ደብተራቸው ላይ ይጽፉታል። ሌሎች ደግሞ ደብዳቤውን የሚልኩት ባይሆንም እንኳ ስሜታቸውን ወሲባዊ በደሉን ለፈጸመባቸው ሰው በሚጽፉት ደብዳቤ ላይ ይገልጻሉ። ይህ ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ትዝታዎች ይቀሰቅሳል። ጸሎትም ለማገገም የሚያስችል ውጤታማ መሣሪያ ነው። ልክ እንደ መዝሙራዊው “ፈትነኝ፤ አሳቤንም ዕወቅ። በእኔ ውስጥ በደል እንዳለ ተመልከት፤ በዘላለማዊውም መንገድ ምራኝ” ብለሽ ልትጸልይ ትችያለሽ።—መዝሙር 139:23, 24 የ1980 ትርጉም
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያለፈውን እውነታ መጋፈጥና ታሪኩን ገጣጥሞ ለማየት መሞከር ፈውስ ለማግኘት የሚያስችል አንድ እርምጃ ሊሆን ይችላል