የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 1/8 ገጽ 4-5
  • ቤተሰብ ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቤተሰብ ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—1996
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በቤተሰብ ውስጥ የአልኮል ሱሰኛ ሲኖር
    ንቁ!—1996
  • ከአልኮል ሱስ መላቀቅ ይቻላል
    ንቁ!—1996
  • ቤተሰብን የሚያናጉ ችግሮችን መቋቋም ትችላላችሁ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • የአልኰል መጠጦችን መውሰድ ይገባሃልን?
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1996
g96 1/8 ገጽ 4-5

ቤተሰብ ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

“መጀመሪያ ሰውየው መጠጥ ያዝዛል፤ ከዚያም መጠጡ ሌላ መጠጥ ያዝዛል፤ በመጨረሻም መጠጡ ሰውየውን ያዝዘዋል።”​—የሩቅ ምሥራቅ ሰዎች ብሂል

በአንድ ረግረጋማ በሆነ ሥፍራ ጠርዝ ጠርዙን እየተጓዝክ ነው እንበል። ድንገት መሬቱ ከዳህና ማጡ ውስጥ ገባህ። ከማጡ ለመውጣት በታገልክ መጠን ይባስ እየሰመጥክ ትሄዳለህ።

የአልኮል ሱስም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ መላውን ቤተሰብ በችግር ማጥ ውስጥ ያስገባል። የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ባልዋን ችግር የምትጋራ ሴት ሱሱን እንዲተው ለማድረግ ከፍተኛ ትግል ታደርጋለች። ባልዋን ስለምትወድ ደጋግማ ብታስፈራራውም መጠጣቱን አያቆምም። መጠጡን ስትደብቅበት ሌላ ይገዛል። ገንዘቡን ስትደብቅበት ከጓደኛው ይበደራል። ለቤተሰቡ፣ ለሕይወቱና አልፎ ተርፎም ለአምላክ ሲል መጠጡን እንዲተው ስትማጸነው አይሰማትም። የምታደርገውን ትግል ይበልጥ ባጠናከረች መጠን መላው ቤተሰብ የአልኮል ሱሰኛው በፈጠረው የችግር ማጥ ውስጥ ይበልጥ እየተዘፈቀ ይሄዳል። የቤተሰቡ አባላት የአልኮል ሱሰኛውን መርዳት እንዲችሉ መጀመሪያ የአልኮል ሱስን ጠባይ መረዳት ይኖርባቸዋል። አንዳንድ “የመፍትሔ እርምጃዎች” የማይሰምሩበትን ምክንያትና የተሳካ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት ዘዴዎች የትኞቹ እንደሆኑ ማወቅ አለባቸው።

የአልኮል ሱሰኛ መሆን ከሰካራምነት የከፋ ነገር ነው። የአልኮል ሱሰኝነት የአልኮል ተገዥ በመሆንና ያለ ገደብ በመጠጣት ተለይቶ የሚታወቅ ሥር የሰደደ በሽታ ነው። ይህ በሽታ የተጠናወተው ሰው የአልኮል ተገዥ ከመሆኑም በላይ ያለ ገደብ የመጠጣት ልማድ ይታይበታል። አብዛኞቹ ኤክስፐርቶች ከዚህ ሱስ መላቀቅ አይቻልም ብለው ቢናገሩም ዕድሜ ልክ ከአልኮል በመራቅ የአልኮል ሱስን እርግፍ አድርጎ መተው ይቻላል።​—ከማቴዎስ 5:29 ጋር አወዳድር።

ሁኔታው በአንዳንድ መንገዶች የስኳር በሽታ ከያዘው ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ በሽታ የያዘው ሰው በሽታውን ፈጽሞ ማስወገድ ባይችልም ስኳር ያለባቸውን ምግቦች ባለመመገብ ከሰውነቱ ጋር ተስማምቶ መኖር ይችላል። በተመሳሳይም የአልኮል ሱስ ያለበት ሰው መጠጥ በሰውነቱ ላይ ያስከተለውን ውጤት መለወጥ ባይችልም አልኮልን እርግፍ አድርጎ በመተው ሰውነቱ ካለበት ችግር ጋር ተስማምቶ መኖር ይችላል።

ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ እንዲህ እንደምናወራው ቀላል አይሆንም። የአልኮል ሱስ ያለበት ሰው እውነታውን አይቀበልም። ‘ይኼን ያህል ሥር የሰደደ ችግር የለብኝም።’ ‘እኔ የምጠጣው ቤተሰቦቼ ስለሚያበሳጩኝ ነው።’ ‘እንደ እኔ ዓይነት አለቃ አጋጥሞት የማይጠጣ ሰው ሊኖር አይችልም።’ የሚያቀርባቸው ምክንያቶች ብዙውን ጊዜ በጣም አሳማኝ ስለሚሆኑ መላው ቤተሰብ የእሱን ምክንያቶች በማመን እውነታውን ላይቀበል ይችላል። ‘አባታችሁ ሲሠራ ውሎ ስለሚደክመው ምሽት ላይ ራሱን ማዝናናት ያስፈልገዋል።’ ‘አባዬ የሚጠጣው እማዬ በጣም ስለምትጨቀጭቀው ነው።’ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ አባትዬው የአልኮል ሱሰኛ መሆኑን ላለመቀበል የሚደረግ ጥረት ነው። “አብረው መኖር የሚችሉበት መንገድ ይህ ብቻ ነው” ሲሉ ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ ገልጸዋል። “እንደነዚህ ባሉት ቤቶች ውስጥ ውሸት፣ ሰበብ መፍጠርና ምሥጢር በጣም የተለመዱ ናቸው።”

የቤተሰቡ አባላት ራሳቸው በቅድሚያ ከማጡ ውስጥ ካልወጡ የአልኮል ሱሰኛውን ማውጣት አይችሉም። አንዳንዶች ‘እርዳታ የሚያስፈልገው የአልኮል ሱሰኛው እንጂ እኔ አይደለሁም!’ ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ እስቲ አስበው:- ስሜቶችህና የምታደርጋቸው ነገሮች የአልኮል ሱሰኛው ከሚያሳየው ጠባይ ጋር የተሳሰሩ አይደሉምን? የሚያደርጋቸው ነገሮች ብዙ ጊዜ እንድትቆጣ፣ እንድትጨነቅ፣ እንድትበሳጭና ስጋት እንዲያድርብህ አያደርጉምን? ብዙ ጊዜ ሌሎች ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወን ሲገባህ እቤት ሆነህ የአልኮል ሱሰኛውን ለመርዳት ትገደድ የለምን? የአልኮል ሱስ የሌለባቸው የቤተሰቡ አባላት አኗኗራቸውን ለማሻሻል አንዳንድ እርምጃዎች ሲወስዱ የአልኮል ሱሰኛውም እነርሱን ተከትሎ አንዳንድ እርምጃዎች ሊወስድ ይችላል።

ሱሰኛው እናንተን ሰበብ አድርጎ ሲያቀርብ አትቀበሉት። ‘ባታበሳጩኝ አልጠጣም ነበር’ የሚል ሰበብ ሊያቀርብ ይችላል። ቶቢ ራይስ ድሩውስ የተባሉት አማካሪ “የአልኮል ሱሰኛው የሚጠጣበትን ምክንያት በእናንተ ላይ ለመደፍደፍ እንዲችል ሁልጊዜ ይህን ሰበቡን አምናችሁ እንድትቀበሉት ይፈልጋል” በማለት ተናግረዋል። እንዲህ ዓይነቱን ሰበብ አትቀበሉ። የአልኮል ሱሰኛው ጥገኝነቱ በአልኮል ላይ ብቻ ሳይሆን የሚያቀርበውን ሰበብ በሚቀበሉት ሰዎችም ላይ ጭምር ነው። በመሆኑም የቤተሰቡ አባላት ሳያውቁት በመጠጥ ሱሱ እንዲገፋበት ሊያደርጉት ይችላሉ።

ስለ ቁጡ ሰው የተነገረ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ሰውም ላይ ሊሠራ ይችላል:- “አንድ ጊዜ ከችግሩ ብታወጣው ሌላ ጊዜም እንዲሁ ማድረግህ ስለማይቀር የሥራውን ውጤት እንዲያገኝ ተወው።” (ምሳሌ 19:19፣ ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) አዎን፣ የአልኮል ሱሰኛው ራሱ ለአለቃው ደውሎ ይናገር፤ ራሱ አልጋው ላይ ወጥቶ ይተኛ፤ ያቆሸሸውን ሁሉ ራሱ ያጽዳ። እነዚህን ነገሮች የቤተሰቡ አባላት የሚሠሩለት ከሆነ ሕይወቱን በመጠጥ እንዲያጠፋ እያደረጉት ነው ማለት ይቻላል።

እርዳታ ጠይቁ። አንድ የቤተሰብ አባል በራሱ ትግል ከማጡ ውስጥ ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት አስቸጋሪ እንዲያውም የማይቻል ነገር ሊሆንበት ይችላል። እርዳታ ያስፈልጋችኋል። የአልኮል ሱሰኛው የሚያቀርበውን ሰበብ የማይቀበሉና ባላችሁበት ሁኔታ እንድትቀጥሉ የማይፈልጉ ወዳጆች እንዲረዷችሁ አድርጉ።

የአልኮል ሱሰኛ የሆነው ሰው የሚሰጠውን እርዳታ ለመቀበል ከተስማማ በጣም ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ ከችግሩ ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት የመጀመሪያው ብቻ ነው። በሰውነቱ ውስጥ ያለው አልኮል በሕክምና ዘዴዎች እንዲወጣ ከተደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሱሱ ሊለቀው ይችላል። ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆነው ሥነ ልቦናዊ ችግሩን ማሸነፍ ነው።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአልኮል ሱሰኞች ተለይተው የሚታወቁባቸው ባሕርያት

ዘወትር ስለ አልኮል ማሰብ:- የአልኮል ሱስ ያለበት ሰው መጠጥ የሚጠጣባቸውን ጊዜያት በጉጉት ይጠባበቃል። አልኮል በማይጠጣባቸው ጊዜያት ስለ አልኮል ያስባል።

ራስን መግዛት አለመቻል:- ምንም ያህል ቁርጥ ውሳኔ ቢያደርግ ብዙውን ጊዜ ካሰበው በላይ ይጠጣል።

ግትር መሆን:- የአልኮል ሱሰኛው “የምጠጣው ብቻዬን አይደለም፣” “በሥራ ሰዓት አልጠጣም” እንደሚሉት የመሰሉትን የግል ደንቦች የሚያወጣው “ምንም ነገር መጠጥ ከመጠጣት እንዲያግደኝ አልፈቅድም” በማለት የወሰደውን ግትር ውሳኔ ለመሸፋፈን ሲል ነው።

አለመስከር:- በመጠጥ ኃይል ሳይሸነፉ ብዙ ለመጠጣት መቻል የአልኮል ሱሰኛ መሆንን የሚጠቁም የመጀመሪያ ምልክት እንጂ ልዩ ተሰጥኦ አይደለም።

ጎጂ ውጤቶች:- ተራ የሆኑ ሌሎች ልማዶች በቤተሰብ፣ በሥራና በአካላዊ ጤንነት ላይ ከባድ ጉዳት አያስከትሉም። የአልኮል ሱስ ግን ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።​—ምሳሌ 23:29-35

እውነታውን አለመቀበል:- የአልኮል ሱሰኛ ለጠጪነቱ የተለያዩ ሰበቦች ያቀርባል፤ በተጨማሪም ድርጊቱ ከባድ ሆኖ አይታየውም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ