በቤተሰብ ውስጥ የአልኮል ሱሰኛ ሲኖር
“የመጠጥ ሱስ የሚጎዳው ሱሰኛውን ብቻ አይደለም . . . በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ የአልኮል ሱሰኛ ካለ የመጠጡ ሱስ የሚያስከትለው መዘዝ የሚጎዳው መላውን ቤተሰብ ነው።”— ዶክተር ቨርነን ኢ ጆንሰን
የአምስት ዓመቷ አሊስ ታማ ተኝታለች፤ እግሯ በጣም እየጠዘጠዛት ነው። ከሁለት ቀናት በፊት ተሰብራ ስለነበር እግሯ በጄሶ ታስሯል። ሆኖም ጄሶው በጣም ስለጠበቀ እግሯ እያበጠ ነበር። አሊስ ወደ ሐኪም እንዲወስዷት ወላጆቿን ብትማጸናቸውም አባቷ ያደረበት ስካር ሙሉ በሙሉ አልለቀቀውም፤ እናቷ ደግሞ ማናቸውን መርዳት እንዳለባት ግራ ገብቷት ልቧ ተከፍሏል።
በርከት ያሉ ቀናት ካለፉ በኋላ የአሊስ እግር በድን ሆነ። በመጨረሻ ከእግሯ ጣት ላይ አንድ ጥቁር ነገር መንጠባጠብ ሲጀምር የአሊስ ወላጆች በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ይዘዋት ሄዱ። ጄሶው ተፈትቶ እግሯ ሲታይ በጣም ያሰቅቅ ስለነበረ አንዲት ነርስ ራሷን ስታ ወደቀች። አሊስ ጋንግሪን ይዟት ስለነበር እግሯ የግድ መቆረጥ ነበረበት።
የአልኮል ሱስና የሱሰኞቹን ችግር የሚጋሩ ሰዎች
አሊስ ያጣችው እግሯን ብቻ አይደለም። አባቷ የአልኮል ሱሰኛ ነው። በመሆኑም ልጁ የእሱን እርዳታ በምትሻበት ጊዜ በስሜትም ሆነ በአካል ከጎኗ ሆኖ አልረዳትም። ቶቢ ራይስ ድሩውስ የተባሉ አማካሪ “የመጠጥ ሱስ ሱሰኛው ቤተሰቡን ቸል እንዲል ያደርገዋል። ከሁሉ በፊት የሚያሳስበው የአልኮል ሱሱን ማርካት መቻሉ ነው” ብለዋል።
ስለ አሊስ እናትስ ምን ለማለት ይቻላል? የአልኮል ሱሰኛ ባትሆንም እንኳ የአልኮል ሱሰኛ የሆነው ባልዋ የሚደርስበትን ችግር ትጋራለች። በመሠረቱ ከአልኮል ሱስ ነፃ የሆነች የትዳር ጓደኛ ጊዜዋ በሙሉ የአልኮል ሱስ ያለበት ባልዋ መጠጥ እንዲያቆም በምታደርገው ጥረት ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ተለዋዋጭ ባሕርይውን ችላ ለመኖር በምታደርገው ጥረት የተያዘ ነው።a የአልኮል ሱሰኛው የሚፈጥረው ችግር አላፈናፍን ስለሚላት የአልኮል ሱስ ሳይኖርባት ሱሱ ያለበት ሰው የሚያሳየውን ዓይነት ባሕርይ ታሳያለች። በዚህም ምክንያት ብዙውን ጊዜ እንደ አሊስ እናት ያሉ ሰዎች የሱሰኞቹን ችግር አብረው ይጋራሉ።
የአልኮል ሱሰኛውም ሆነ የሱሰኛውን ችግር የሚጋራው ሰው ሳያውቁት ሕይወታቸው ከራሳቸው ውጭ በሆነ ነገር ወይም ሰው ቁጥጥር ሥር ይወድቃል። ሁለቱም እውነታውን አይቀበሉም። ሁለቱም ለልጆቻቸው ስሜታዊ እርዳታ መስጠት አይችሉም። የአልኮል ሱሰኛው የመጠጥ ሱሱን መቆጣጠር እንደማይችል ሁሉ የአልኮል ሱሰኛውን ችግር የሚጋራውም ሰው ሱሰኛ የሆነውን ሰው መቆጣጠር አይችልም። በተጨማሪም አንዳቸውም ቢሆኑ የአልኮል ሱስ በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ መቆጣጠር አይችሉም። በዚህም ምክንያት ኑሯቸው በብስጭት የተሞላ ይሆናል።
ይሁን እንጂ የአልኮል ሱሰኛውንም ሆነ ቤተሰቡን መርዳት ይቻላል። እንዴት መርዳት እንደሚቻል በሚቀጥሉት ርዕሶች ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአልኮል ሱስ ያለበትን ሰው በተባዕታይ ጾታ የገለጽነው ቢሆንም እዚህ ላይ የተጠቀሱት መሠረታዊ ሥርዓቶች የአልኮል ሱሰኛ በሆኑ ሴቶችም ላይ ይሠራሉ።