የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የልጅነት ሕይወታቸው ለተበላሸባቸው ሰዎች የሚሆን እርዳታ
“ያደግኸው የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ፣ አስተዳደግህ የቀረጸብህን የተዛባ አመለካከትና የስሜት ቀውስ ማስተካከል መቻል ይኖርብሃል። ሌላ አማራጭ የለም።”— ዶክተር ጆርጅ ደብልዩ ቭሩም
አንድ ክፉኛ የቆሰለ ወታደር በውጊያው አውድማ ወድቆ ደሙ እየፈሰሰ ነው። ቁስለኛው ወዲያውኑ እርዳታ አገኘና ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። ወታደሩ ከሞት ቢተርፍም የደረሰበት ችግር ሙሉ በሙሉ ተወገደለት ማለት አይደለም። ቁስሉ ጥሩ ሕክምና ማግኘት አለበት፤ የደረሰበት ሥቃይ ያስከተለበት የሥነ ልቦና ቀውስም ለብዙ ዓመታት ሊቆይ ይችላል።
የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ያላቸው ልጆችም ቤታቸው ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች የጥቃት ዒላማ የሆኑበት የውጊያ አውድማ ሊሆንባቸው ይችላል። አንዳንድ ልጆች በጾታ ተነውረዋል፤ ሌሎች አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ ብዙዎቹ ደግሞ ስሜታቸው በእጅጉ ተጎድቷል። አንድ ወጣት የልጅነት ሕይወቱን አስታውሶ ሲናገር “አንድ ልጅ በቤቱ አካባቢ ቦምብ ሲፈነዳ ወይም አውቶማቲክ ጠመንጃ ሲተኮስ የሚሰማው ዓይነት ከባድ የፍርሃት ስሜት ይሰማኝ ነበር” ብሏል። የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ያላቸው ብዙ ልጆች ጦርነት ዘምተው የተመለሱ ሰዎች የሚታይባቸው ዓይነት የሥነ ልቦና ቀውስና የጭንቀት ምልክቶች የሚታዩባቸው መሆኑ አያስደንቅም!
እርግጥ፣ ብዙ ልጆች የደረሰባቸውን የስሜት ቁስል በሙሉ ተቋቁመው በማደግ ራሳቸውን ችለው መኖር ጀምረዋል። ሆኖም ሙሉ ሰው ወደ መሆን ዕድሜ የደረሱት የሚታይ አይሁን እንጂ ልክ እንደ ቁስለኛው ወታደር ለረጅም ጊዜ አብሯቸው የሚኖር ቁስል ይዘው ነው። “አሁን 60 ዓመት ሆኖኛል” ስትል ግሎሪያ ትናገራለች፤ “ይሁን እንጂ የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ በመወለዴ ምክንያት የደረሰብኝ የሥነ ልቦና ቁስል አሁንም ድረስ ኑሮዬን እያቃወሰው ነው።”
እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሐዘናቸው ተካፋይ ሁኑ’ ሲል ይመክራል። (ሮሜ 12:15 ፊሊፕስ) አንድ ሰው ይህን ለማድረግ እንዲችል የአልኮል ሱሰኛ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ መኖር የሚያስከትለውን የሕሊና ቁስል መረዳት ይኖርበታል።
“የልጅነትን ሕይወት ጣዕም አላውቅም”
ማንኛውም ልጅ እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግለት እንዲሁም ዘወትር የሚወደድ መሆኑ ሊገለጽለት ይገባል። የአልኮል ሱሰኛ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ልጆች ይህን የመሰለ ትኩረት አይሰጣቸውም። እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች የሥራ ድርሻቸው የተገላቢጦሽ ይሆንና ልጅ ወላጁን ለመንከባከብ ይገደዳል። ለምሳሌ ያህል አልበርት ገና በ14 ዓመቱ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት ወድቆበት ነበር! ጃን የምትባል አንዲት ትንሽ ልጅ የአልኮል ሱሰኛ ወላጅዋን ተክታ በቤት ውስጥ የሚሠሩትን ከባድ ሥራዎች ታከናውን ነበር። በተጨማሪም ወንድሞቿንና እህቶቿን በዋነኛነት የምትንከባከበው እሷ ነበረች፤ ይህን ሁሉ ታደርግ የነበረው ገና የስድስት ዓመት ልጅ ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ ነው!
ልጆች አዋቂዎች አይደሉም፤ በመሆኑም የአዋቂዎችን ሥራ ሊሠሩ አይችሉም። ሁኔታው የተገላቢጦሽ ሆኖ ልጅ የወላጁን የሥራ ድርሻ ለማከናወን ከተገደደ አድጎ ትልቅ ሰው ሲሆን ከሕይወት እርካታ ለማግኘት የማይችል ሰው ይሆናል። (ከኤፌሶን 6:4 ጋር አወዳድር።) የቤተሰብ አማካሪ የሆኑት ጆን ብራድሾው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አድገው የትልቅ ሰው አካል ይኖራቸዋል። ትልልቅ ሰዎች መስለው ይታያሉ። እንደ ትልቅ ሰውም ይናገራሉ። ሆኖም በውስጣቸው፣ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ያልተሟሉላቸው ገና ብዙ ነገር የሚፈልጉ ትንንሽ ልጆች ናቸው።” እንደነዚህ ያሉት ሰዎች አንድ ክርስቲያን የተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማቸው ይሆናል:- “ልጅ ሳለሁ ሊሟሉልኝ ይገቡ ከነበሩት መሠረታዊ የሆኑ ስሜታዊ ፍላጎቶች አብዛኞቹን ባለማግኘቴ አሁንም ድረስ ያልሻረ ቁስል በውስጤ አለ።”
“ጥፋቱ የእኔ ነው”
ሮበርት አባቱ በድንገተኛ አደጋ የሞተው ገና የ13 ዓመት ልጅ እያለ ነው። “ጥሩ ልጅ ለመሆን ጥረት አድርጌያለሁ” በማለት አቀርቅሮ መሬት መሬት እያየ ያለፈውን ሁኔታ በማስታወስ ይናገራል። “አባቴ የማይወዳቸውን ነገሮች አደርግ እንደነበረ አውቃለሁ፤ ሆኖም መጥፎ ልጅ አልነበርኩም።” ሮበርት አባቱ የአልኮል ሱሰኛ የሆነው በእሱ ምክንያት እንደሆነ አድርጎ በማሰብ ከባድ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማዋል፤ ይህ ስሜቱ ለረጅም ዓመታት አብሮት ኖሯል። ሮበርት ከላይ ያለውን ሲናገር 74 ዓመት ሆኖት ነበር!
ብዙ ጊዜ ልጆች ወላጃቸው የአልኮል ሱሰኛ የሆነው በእነርሱ ምክንያት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። አንድ ልጅ ጥፋተኛው እርሱ እንደሆነ አድርጎ ማሰቡ ሁኔታው ሊስተካከል ይችል ነበር የሚል የተሳሳተ ግምት እንዲያድርበት ያደርገዋል። ሁኔታው ልክ ጃኒስ እንደገለጸችው ነው:- “የተሻልኩ ልጅ ብሆን ኖሮ አባቴ መጠጥ ያቆም ነበር የሚል ስሜት ይሰማኛል” ብላለች።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ማንኛውም ልጅ ሆነ ትልቅ ሰው አንድ ሰው ጠጪ እንዲሆን ወይም ደግሞ የመጠጥ ልማዱን እንዲቀንስ ወይም እንዲተው ምክንያት ሊሆን አይችልም። ወላጅህ የአልኮል ሱሰኛ ከሆነ ሌሎች ምንም ይናገሩ ምን ተወቃሹ አንተ ልትሆን አትችልም! በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ሰው ከሆንክ ሌሎች ሰዎች ለሚያደርጓቸው ነገሮችና ለሚያሳዩት ጠባይ ራስህን አላግባብ በደለኛ አድርገህ ትቆጥር እንደሆነና እንዳልሆነ መመርመር ያስፈልግህ ይሆናል።— ከሮሜ 14:12 እና ከፊልጵስዩስ 2:12 ጋር አወዳድር።
“ማንንም ማመን አልችልም”
መተማመን የሚኖረው ግልጽነትና ሐቀኝነት ሲኖር ነው። የአልኮል ሱሰኛ ባለበት ቤተሰብ ግን ምሥጢር የመያዝና ሐቁን የመካድ መንፈስ ይሰፍናል።
ሣራ ወጣት እያለች አባቷ የአልኮል ሱሰኛ መሆኑን ታውቅ ነበር። ሆኖም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላ በማስታወስ “በቤተሰቤ ውስጥ ይህን ቃል የሚጠራ ሰው ስላልነበረ ቃሉን ማሰቡ እንኳ ጥፋት ሆኖ ይታየኝ ነበር” ብላለች። ሱዛንም የገጠማትን ተመሳሳይ ሁኔታ ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “ምን ሁኔታ እየተፈጸመ እንዳለ፣ በሁኔታው ምን ያህል እንደተከፋ ወይም [የአልኮል ሱሰኛ በሆነው እንጀራ አባቴ] ምን ያህል እንደምንበሳጭ ትንፍሽ የሚል ሰው አልነበረም። ከቤተሰቦቼ የተለየ አመለካከት ያለኝ ሰው እንደሆንኩ አድርጌ አስብ ነበር።” ብዙውን ጊዜ አንድ ወላጅ የአልኮል ሱሰኛ መሆኑ በዚህ መንገድ ይሸፋፈናል። “ብዙ መጥፎ ነገር ስላየሁ የማያቸውን ነገሮች እንዳላየሁ ሆኜ ማለፍ ተማርኩ” ስትል ሱዛን ተናግራለች።
በተጨማሪም የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ሰው ተለዋዋጭ ባሕርይ ስለሚኖረው እንዲህ ዓይነቱን ሰው ማመን አስቸጋሪ ይሆናል። ዛሬ ፍልቅልቅ ሆኖ ይውልና ነገ ቁጣ ቁጣ ይለዋል። የአልኮል ሱሰኛ የሆነች እናት የነበራትና በዚህም ምክንያት የልጅነት ሕይወትዋ የተበላሸባት ማርቲን “ቁጣዋ የሚገነፍለው መቼ እንደሆነ ፈጽሞ አላውቅም ነበር” ብላለች። የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ሰው የገባውን ቃል ያፈርሳል። እንዲህ የሚያደርገው ቸልተኛ ሆኖ ሳይሆን ባለበት የአልኮል ሱስ ምክንያት ነው። ዶክተር ክላውዲያ ብላክ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ለአልኮል ሱሰኛ ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበው ነገር መጠጥ ነው። ሌላው ሁሉ የሚታየው ከዚያ በኋላ ነው።”
“ስሜቴን እደብቃለሁ”
ልጆች ስሜታቸውን በነፃነት መግለጽ በማይችሉበት ጊዜ ስሜታቸውን አፍነው መያዝ ይጀምራሉ። ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ “ፊታቸው ፈገግታ ቢነበብበትም ውስጣቸው ግን በጭንቀት ስሜት ይብሰለሰላል” በማለት አደልት ችልድረን— ዘ ሴክሬትስ ኦቭ ዲስፈንክሽናል ፋሚሊስ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። የቤተሰባቸውን ምሥጢር እንዳያወጡ ስለሚፈሩ ሐሳባቸውን ለሌሎች ለማካፈል አይደፍሩም። ከውጪ ሲታዩ ደህና ይመስላሉ፤ በውስጣቸው ግን ሊያወጡት የማይፈልጉት የታመቀ ስሜት አለ።
እነዚህ ልጆች ትልልቅ ሰዎች በሚሆኑበት ጊዜ ችግራቸውን አምቀው ይዘው ምንም እንዳልሆኑ መስለው ለመታየት የሚያደርጉት ጥረት ችግር ያስከትልባቸዋል። ስሜቶችን በቃላት መግለጽ ካልተቻለ እነዚህ ስሜቶች አልሰር፣ ሥር የሰደደ ራስ ምታትና ሌሎችም አካላዊ በሽታዎች ሊያስከትሉ ይችላሉ። “ውስጣዊ ስሜቶቼ በቁሜ እየጨረሱኝ ነበር” ስትል ሺርሊ ተናግራለች። “አለ የሚባል በሽታ በሙሉ ይዞኛል።” ዶክተር ቲመን ሰርማክ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “የመጠጥ ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የልጅነት ሕይወታቸው የተበላሸባቸው ልጆች ምንም ጭንቀት የሌለባቸው መስለው በመታየት የጭንቀት ስሜታቸውን ለመቆጣጠር ይሞክራሉ። ሆኖም ተፈጥሮን ማታለል አይችሉም። . . . ለዓመታት በከፍተኛ ጭንቀት ተወጥሮ የኖረ ሰውነት በበሽታ መደቆስ ይጀምራል።”
ችግሩን ለመቋቋም መቻል ብቻውን አይበቃም
የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የልጅነት ሕይወታቸው የተበላሸባቸው ሰዎች ጠንካሮች ናቸው። በልጅነታቸው የደረሰባቸውን የሥነ ልቦና ቀውስ መቋቋም መቻላቸው ይህን ሐቅ ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ ችግሩን መቋቋም መቻላቸው ብቻ በቂ አይደለም። በቤተሰብ ግንኙነት ረገድ ሊማሯቸው የሚገቡ አዳዲስ ጽንሰ ሐሳቦች አሉ። የጥፋተኝነት ስሜት፣ ቁጣና ራስን ዝቅ አድርጎ የመመልከት መንፈስ መፍትሔ የሚያሻቸው ጉዳዮች ናቸው። የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የልጅነት ሕይወታቸው የተበላሸባቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ‘አዲሱ ሰውነት’ ብሎ የሚጠራውን ባሕርይ ለመላበስ ባለ ኃይላቸው ሁሉ ጥረት ማድረግ አለባቸው።— ኤፌሶን 4:23, 24፤ ቆላስይስ 3:9, 10
ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የልጅነት ሕይወቱ ተበላሽቶበት የነበረው ለሮይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በራሱ ቤተሰብ ውስጥ ሥራ ላይ ለማዋል 20 ዓመት ለሚያክል ጊዜ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። “ማኅበሩ ቤተሰብ በተባለው መጽሐፍና በሌሎችም ጽሑፎች አማካኝነት የሰጠውን ፍቅራዊ ምክር ሳነብ የምክሩን ጽንሰ ሐሳብ መጨበጥ አልችልም ነበር።a በዚህም ምክንያት ትምህርቱን በሚገባ ሥራ ላይ ማዋል ተስኖኝ ነበር። . . . ልክ ፈሪሳውያን ያደርጉት እንደነበረው ስሜት ሳይኖረኝ እንደ ግዴታ በመቁጠር መመሪያዎችን ለማግኘትና በሥራ ላይ ለማዋል እጥር ነበር።”— ማቴዎስ 23:23, 24ን ተመልከት።
ለሮይን ለመሰለ ሰው “ይበልጥ አፍቃሪ እንዲሆን” ወይም “ውስጣዊ ስሜቱን እንዲገልጽ” ወይም ደግሞ “ልጆቹን እንዲገሥጽ” ማሳሰብ ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል። ለምን? የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የልጅነት ሕይወቱ የተበላሸበት ሰው እንዲህ ዓይነት ባሕርያትን ወይም ችሎታዎችን ጨርሶ ላያውቃቸው ስለሚችል ይህን ማድረጉ አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። ለሮይ አባቱ የአልኮል ሱሰኛ መሆኑ በእሱ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመረዳት ምክር ጠየቀ። ይህም መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚችልበትን መንገድ አመቻቸለት። “በሕይወቴ ውስጥ እንደዚህ ጊዜ በጣም የተጨነቅሁበት ወቅት ባይኖርም ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት ያደረግሁበት ጊዜ ነበር” ሲል ተናግሯል። “በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአምላክ ፍቅር ምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ እንደጀመርኩ ተሰማኝ።”— 1 ዮሐንስ 5:3
ሸሪል የተባለች አንዲት ክርስቲያን ሴት የአልኮል ሱሰኛ ያለባቸውን ቤተሰቦች በመርዳት ጥሩ ልምድ ያካበተ አንድ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ያደረገላት እርዳታ በጣም ጠቅሟታል። በተጨማሪም ችግሯን የሌሎችን ችግር ለሚረዳ አንድ ሽማግሌ ተናገረች። “ከይሖዋም ሆነ ከራሴ ጋር ሰላም ሊኖረኝ የቻለው አፍኜው የነበረውን ስሜቴን ግልጽልጽ አድርጌ ከተናገርኩ በኋላ ነው” ስትል ተናግራለች። “አሁን ይሖዋን እንደ አባቴ አድርጌ እመለከተዋለሁ (ከዚህ በፊት ጨርሶ እንደዚህ ዓይነት ስሜት አልነበረኝም)፤ ከእንግዲህ ወዲያ ሰብዓዊ አባቴ የሚያስፈልገኝን ፍቅርና መመሪያ አልሰጠኝም ብዬ አልበሳጭም።”
የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ያሳደጋት አሚ “የመንፈስ ፍሬ” ለመኮትኮት ጥረት ማድረጓ በእጅጉ ረድቷታል። (ገላትያ 5:22, 23) በተጨማሪም የሚሰማትን ስሜት የሌሎችን ችግር ለሚረዳ አንድ ሽማግሌ ማካፈል ጀመረች። “ይበልጥ መጣር የሚገባኝ የይሖዋ አምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ሞገስ ለማግኘት መሆን እንዳለበት አሳሰበኝ። የእነርሱን ፍቅርና ሞገስ ለማግኘት መጣር በራስ ላይ የሚያመጣው አንዳችም ጉዳት የለም” ስትል አሚ ተናግራለች።
የተሟላ ፈውስ
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ የሚመጡ በጭንቀት የዛሉ ሰዎች እፎይታ እንደሚያገኙ የገባው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። (ማቴዎስ 11:28-30) በተጨማሪም ይሖዋ ‘በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ ተብሎ ተጠርቷል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ሞሬና “ይሖዋ በአካል፣ በአእምሮም ሆነ በስሜት የማይጥለኝ አምላክ እንደሆነ አውቄያለሁ” ብላለች።
በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን ብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ነው፤ ይህ ወቅት ብዙዎች በቤተሰባቸው ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች እንኳ ‘ተሳዳቢዎች፣ የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸውና ጨካኞች’ የሚሆኑበት ዘመን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3፤ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ይሁን እንጂ አምላክ በቅርቡ ሰላም የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣና እንባንና ሐዘንን ሁሉ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:4, 5) የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ያሳደገው አንድ ክርስቲያን እንዲህ ብሏል:- “ሁላችንም ይሖዋ ብቻ ሊሰጠን የሚችለውን የተሟላ ፈውስ ወደምናገኝበት አዲስ ዓለም እንደምንገባ ተስፋ እናደርጋለን።”
ችግሩ የደረሰባት ሴት ታሪክ
“የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የአስተዳደግ በደል የደረሰብኝ ሰው ነኝ። የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴ የአልኮል ሱሰኛ ሆነ። ሲሰክር ጠበኛ ይሆናል። መላው ቤተሰባችን ምን ያህል ይሸበር እንደነበረ አስታውሳለሁ። አስደሳች የልጅነት ጊዜ ላሳልፍበት በሚገባኝ ዕድሜ ላይ ስሜቴን፣ ምኞቴን፣ ፍላጎቴንና ተስፋዬን ለማፈን ተገደድኩ። አባቴና እናቴ የአባቴ ጠጪነት ባስከተለው ችግር ተጠምደው ስለነበረ እኔን ዞር ብለው አያዩኝም ነበር። ስለ እኔ የሚያስቡበት ጊዜ አልነበረም። ምንም ዋጋ የሌለኝ ሰው ነኝ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። በስምንት ዓመቴ የወደቀብኝ ኃላፊነት የልጅነት ሕይወቴ እንዲያበቃና ያለዕድሜዬ የቤተሰብ ኃላፊነቶችን እንድሸከም አስገደደኝ። ውጥረት ውስጥ ገባሁ።
“አባቴ የነበረው በጣም አሳፋሪ ጠባይ እኔንም ያሳፍረኝ ጀመር። የአባቴን ጠባይ ለማካካስ ስል ፍጹም ለመሆን ጥረት አደረግሁ። ሰው እንዲወደኝ ብዬ ብዙ ነገር አደርግ ነበር። ሰዎች በእኔነቴ ብቻ ሊወዱኝ እንደማይችሉ ይሰማኝ ነበር። ሕይወቴ ምንም ዓይነት ስሜት የሌለው የማስመሰል ኑሮ ሆነብኝ። ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ባለቤቴና ልጆቼ በደመ ነፍስ የምትሠሪ ሮቦት ነሽ አሉኝ። ለ30 ዓመታት እንደ ባሪያ አገልግያቸዋለሁ። ስሜታዊ ፍላጎቶቼን በሙሉ ለእነርሱ ሰውቻለሁ። ለወላጆቼ አደርግ እንደነበረው ለእነርሱም ብዙ ብዙ ነገር አድርጌላቸዋለሁ። ታዲያ ውለታዬ ይኼ ነው? የመጨረሻው ከባድ የሕሊና ቁስል ደርሶብኛል!
“በብስጭት፣ ግራ በመጋባትና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ተነሳስቼ ችግሬ ምን እንደሆነ ለማወቅ ቆረጥኩ። የአልኮል ሱሰኛ ባለባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ሰዎችን ቀርቤ ሳነጋግራቸው በውስጤ ታምቆ የነበረው ስሜት መውጣት ጀመረ። ቀደም ሲል አስታውሻቸው የማላውቃቸውና በተደጋጋሚ ለሚመላለስብኝ የመንፈስ ጭንቀት መንስኤ የሆኑ ነገሮች ግልጽ መሆን ጀመሩ። ከባድ ሸክም ከላዬ ላይ እንደወረደ ሆኖ ተሰማኝ፤ በውስጤ ታምቆ የነበረውን ስሜት ግልጽልጽ አድርጌ በመናገሬ ተንፈስ አልኩ። እንዲህ ዓይነት ችግር የደረሰብኝ እኔ ብቻ አለመሆኔንና የአልኮል ሱሰኛ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ በማደጌ የደረሰብኝን የሥነ ልቦና ቀውስ የሚረዱልኝ ሰዎች እንዳሉ ማወቁ እንዴት የሚያስደስት ነው!
“የአልኮል ሱሰኛ በሆኑ ወላጆች ምክንያት የልጅነት ሕይወታቸው የተበላሸባቸውን ሰዎች ለመርዳት ከተቋቋመ አንድ ማኅበር እርዳታ ከጠየቅሁ በኋላ በሚሰጧቸው አንዳንድ የሕክምና ዘዴዎች መጠቀም ጀመርኩ። ስለዚህ ጉዳይ የተጻፉ መጻሕፍት የነበሩኝን የተዛቡ አመለካከቶች እንዳስተካክል ረድተውኛል። ለብዙ ዓመት በውስጤ ተቀብረው የቆዩ ሌሎች ስሜቶችን ለማውጣት እንዲረዳኝ የአንድ መጽሔት ደንበኛ ሆንኩ። የራስን ችግር በራስ ለመፍታት የሚረዱ ካሴቶችን ማዳመጥ ጀመርኩ። የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ወላጅ ምክንያት የአስተዳደግ በደል ደርሶበት የነበረ አንድ ሰው ይሰጥ የነበረውን የቴሌቪዥን ሴሚናር ተከታተልኩ። በፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ማዕከል የተዘጋጀው ፊሊንግ ጉድ የተባለው መጽሐፍ በራሴ የመተማመን መንፈስ እንዲኖረኝና የነበረኝን የተዛባ አስተሳሰብ እንዳስተካክል ረድቶኛል።
“ከእነዚህ አዳዲስ አመለካከቶች መካከል አንዳንዶቹ አስተሳሰቤን ለማስተካከል ጥሩ መሣሪያዎች ሆነውልኛል። ኑሮን በተቃና ሁኔታ ለመምራትና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው። ከተማርኳቸውና በሥራ ላይ ካዋልኳቸው መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:- ችግር የሚፈጥርብን በእኛ ላይ የደረሰው ነገር ሳይሆን ለደረሰብን ሁኔታ ያለን አመለካከት ነው። ስሜቶቻችን በውስጣችን ተዳፍነው መቅረት የለባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ሊመረመሩና ገንቢ በሆነ መንገድ ሊገለጹ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ ተረስተው ሊቀሩ ይገባል። ሌላው መሣሪያ ‘ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖርህ ራስህን አስገድድ’ የሚለው ሐረግ ነው። በተደጋጋሚ የሚደረግ ጥረት አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖር ያስችላል።
“ከሁሉ የላቀው መሣሪያ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ከይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች፣ በተለይም ከጉባኤ ሽማግሌዎችና ከሌሎች የጎለመሱ ምሥክሮች ያገኘሁት እርዳታ ከሁሉ የተሻለ መንፈሳዊ ፈውስ እንዳገኝ አስችሎኛል። በተጨማሪም ለራሴ ያለኝ ግምት ከፍ ሊል ችሏል። ከዚህም በላይ ከማንኛውም ሰው የተለየሁ እንደሆንኩና በጽንፈ ዓለም ውስጥ እኔን የሚመስል ሌላ ማንም እንደሌለ ተገንዝቤያለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ይሖዋ እንደሚወደኝና ኢየሱስ ለእኔም ሆነ ለሌሎች ሲል እንደሞተ አውቄያለሁ።
“አሁን አንድ ዓመት ተኩል ከሚያክል ጊዜ በኋላ 70 በመቶ ተሽሎኛል ማለት እችላለሁ። የተሟላ ፈውስ የሚገኘው ይህ ያለንበት ክፉ ዓለምና የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ጠፍተው በቦታቸው ይሖዋ የሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ሲተካ ብቻ ነው።”
ማጠቃለያ
መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው [“አስተዋይ” አዓት] ሰው ግን ይቀዳዋል” ይላል። (ምሳሌ 20:5) አንድን በጭንቀት የተዋጠ ግለሰብ የሚረዳ ሰው ግለሰቡ የሚሠቃይባቸውን በልቡ ውስጥ ያሉ ጥልቅ ነገሮች በተሳካ ሁኔታ ማውጣት እንዲችል አስተዋይ መሆን ያስፈልገዋል። ማስተዋል ያላቸው “ብዙ አማካሪዎች” መኖራቸው ከፍተኛ ጥቅም አለው። (ምሳሌ 11:14) የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌም ከሌሎች ምክር መጠየቅ ጠቃሚ እንደሆነ ያሳያል:- “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።” (ምሳሌ 27:17) ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ሐሳብ ለሐሳብ ሲለዋወጡ ‘እርስ በርስ መበረታታት ይችላሉ።’ (ሮሜ 1:12) በተጨማሪም አንድ ማጽናኛ የሚሰጥ ሰው “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መፈጸም እንዲችል መጽናኛ የሚያስፈልገውን ሰው እንዲጨነቅ ያደረጉትንና ከጭንቀቱ ጋር የተያያዙትን ነገሮች መረዳት ይኖርበታል።— 1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው፤ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ያላቸው ብዙ ልጆች ጦርነት ዘምተው የተመለሱ ሰዎች የሚታይባቸው ዓይነት የሥነ ልቦና ቀውስና የጭንቀት ምልክቶች ይታዩባቸዋል!
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ውስጣዊ ስሜቶቼ በቁሜ እየጨረሱኝ ነበር”
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአልኮል ሱሰኛ ባለበት ቤተሰብ ምሥጢር የመያዝና ሐቁን የመካድ መንፈስ ይሰፍናል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ “ፊታቸው ፈገግታ ቢነበብበትም ውስጣቸው ግን በጭንቀት ስሜት ይብሰለሰላል”
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“አሁን ይሖዋን እንደ አባቴ አድርጌ እመለከተዋለሁ (ከዚህ በፊት ጨርሶ እንዲህ ዓይነት ስሜት አልነበረኝም)”
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሁሉ የላቀው መሣሪያ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው