የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 7/8 ገጽ 3-4
  • ኤድስ በአፍሪካ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኤድስ በአፍሪካ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሞቱትና በሞት አፋፍ ላይ ያሉት
  • ተዳፍኖ የሚቆይ በሽታ
  • “እዚህ ምን እንደደረሰብን ንገሯቸው”
  • አፍሪካ ክፉኛ የተጠቃችው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1995
  • ኤድስ የያዛቸውን ሰዎች መርዳት
    ንቁ!—1995
  • ለኤድስ ተጋልጫለሁን?
    ንቁ!—1994
  • ስለ ኤድስ የቀረበ አስደንጋጭ አኃዛዊ መረጃ!
    ንቁ!—2001
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1995
g95 7/8 ገጽ 3-4

ኤድስ በአፍሪካ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

የተነገሩትን ትንበያዎች ሳይሰሙ አይቀሩም። ትንበያዎቹ በፍርሃት የሚያርዱ ነበሩ። በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኤድስ ይለከፋሉ ተብሎ ተተንብዮአል። የሰውነት የተፈጥሮ መከላከያዎች አስከፊ ለሆኑ በሽታዎች ጥቃት እንዲጋለጡ በማድረግ የሰው ልጅ በሽታን የመቋቋም ኃይሉ ይኮላሻል። በ14ኛው መቶ ዘመን በአውሮፓ ብዙ ሰዎችን እንደፈጀው እባጭ ይህ በሽታም ታይቶ በማያውቅ መጠን ከፍተኛ ሞትና ጥፋት ያስከትላል ተብሏል።

ከዚያም በመሐሉ ይህ ወሬ ጋብ ብሎ ነበር። የዜና ማሰራጫዎች በኤድስ ዘገባ ስለተጥለቀለቁ ሕዝቡ የሚያስፈራራ የመቅሰፍት ዜና መስማቱ እየሰለቸው ሄደ። እውነት ሁኔታው ይህን ያህል እየከፋ ሄዷልን? የኤድስ ወረርሽኝ በአፍሪካ ውስጥ በትክክል ምን ያህል ተስፋፍቷል?

“ወደፊት የኤድስ ሕሙማን ቁጥር ምን ደረጃ ላይ እንደሚደርስ የሚያውቅ የለም” በማለት የኤድስ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አንድሬ ስፒየር ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ብሩህ ተስፋ አይታያቸውም። “ቁጥሩ በጣም በመጨመር በመላው ኅብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ጥፋት ይደርሳል” ብለዋል። በተመሳሳይም በ1988 በስቶክሆልም፣ ስዊድን ውስጥ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኤድስ ኮንፈረንስ ላይ ዶክተር ላርስ ኮሊንግስ “በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ . . . በጣም አስደንጋጭ የሆነ የሟቾች ቁጥር [ይኖራል]” ሲሉ ተንብየዋል።

ይህ ከተተነበየ ከ“ሁለት ዓመታት” በላይ አልፈዋል። በአሁኑ ጊዜ ከእነዚህ ትንበያዎች ብዙዎቹ በጣም አስፈሪ በሆነ ሁኔታ እየተፈጸሙ ነው። አኃዛዊ መረጃዎች የሟቾቹን ቁጥር መግለጥ ጀምረዋል። ከዚህ እጅግ የከፋ ሁኔታ ደግሞ ገና ይመጣል።

የሞቱትና በሞት አፋፍ ላይ ያሉት

ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሞት ሕዝብን እንደ ሣር እያጨደ ነው። ኔቸር በተባለው ሳይንሳዊ መጽሔት ላይ በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት “በአንዳንድ ከተሞች በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በአሁኑ ጊዜ በግንባር ቀደምትነት ለሞት እየዳረገ ያለውና ለሕፃናት በሞት መቀጨት ዋና መንስኤ ከሆኑት መካከል የሚጠቀሰው ኤድስ ነው” ይላል። በአንድ የአፍሪካ ከተማ ቄሶች በኤድስ ሳቢያ የተከሰቱ ብዛት ያላቸው የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ማካሄዱ ውጥረት ውስጥ ከቷቸዋል።

ጥቅምት 1991 በሐራሬ ዚምባብዌ የተሰበሰቡት የጋራ ብልጽግና አገሮች መሪዎች ኤድስ በአፍሪካ ውስጥ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ስጋትን የሚገልጽ አስፈሪ ሪፖርት ቀርቦላቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በሆስፒታሎች ውስጥ ካሉት አልጋዎች ከ50 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት በኤድስ ሕሙማን የተያዙ መሆናቸው ተገልጿል። በኤድስ ክፉኛ የተመታችውን ኡጋንዳን በተመለከተ የኤድስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ስታን ሂዩስተን ኤድስ በኡጋንዳ ውስጥ የፈጃቸው ሰዎች ቁጥር ባለፉት 15 ዓመታት በዚያች አገር ውስጥ በእርስ በርስ ጦርነት ካለቁት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተሮችና ሳይንቲስቶች በአቢጃን ኮትዲቭዋር ውስጥ የደረሱባቸው ግኝቶችም ከዚህ ባላነሰ ሁኔታ የሚያስደነግጡ ናቸው። ባለፉት ጥቂት ወራት በከተማው ሁለት ዋና ዋና የአስከሬን ማቆያ ተቋሞች ውስጥ በነበሩ አስከሬኖች ሁሉ ላይ ምርምር ተካሄዶ ነበር። የተገኘው ውጤት ምን ነበር? ሪፖርቱን ያወጣው ሳይንስ መጽሔት በአቢጃን ውስጥ የሚገኙ በጉልምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ወንዶችን “በግንባር ቀደምትነት ለሞት እየዳረገ ያለው” ኤድስ ሆኖ ተገኝቷል ሲል ገልጿል። መጽሔቱ አክሎም የተጠቀሰው የሟቾች ቁጥር “በኤች አይ ቪ [ሂዩማን ኢሚዩኖዴፊሸንሲ ቫይረስ] በመለከፍ የሞቱትን ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር በትክክል የሚገልጽ ላይሆን ይችላል” ብሏል።

የበሽታውን ዓለም አቀፍ ስርጭት የሚከታተለው የዓለም የጤና ድርጅት እንኳን ይህ ቁንጽል መግለጫ ብቻ እንደሆነ ያምናል። ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት በገለጸው መሠረት የዓለም የጤና ድርጅት “በምሥራቅና በመካከለኛው አፍሪካ የሚገኙ ብዙ አገሮች ሪፖርት ያደረጉት የኤድስ ሕሙማን ቁጥር አንድ አሥረኛውን ብቻ እንደሆነ በሚገባ ያውቃል . . . የተደረገው ጥናት ላይ ላዩን ብቻ በመሆኑ ሪፖርቶቹ ትክክለኛና የተሟሉ አይደሉም።”

ተዳፍኖ የሚቆይ በሽታ

ኤድስን በተመለከተ አንዱ በጣም አስፈሪ የሆነው ነገር የኤድስ በሽታ በተጠናከረ ሁኔታ ሰውነትን ማጥቃት ሲጀምር የሚከሰቱት አካላዊ ምልክቶች ሙሉ በሙሉ ከመታየታቸው በፊት በሽታው ለረጅም ጊዜ በሰውነት ውስጥ የሚቆይ መሆኑ ነው። እስከ አሥር ዓመታት ድረስ አንድ በበሽታው የተለከፈ ሰው ገዳይ የሆነውን ኤች አይ ቪ በሰውነቱ ውስጥ ተሸክሞ ሊቆይ ይችላል። ጤነኛ መስሎ ሊታይና ሙሉ ጤንነት ሊሰማው ይችላል። የበሽታው ሰለባ የሆነው ሰው በሽታው እንዳለበትና እንደሌለበት ለማወቅ ምርምራ ካላደረገ በስተቀር የበሽታው ምልክቶች ድንገት እስከሚታዩ ድረስ ፈውስ በማይገኝለት በሽታ እንደተለከፈ ፈጽሞ ሊያውቅ አይችልም! ምንም እንኳ ጤናማ መስሎ ቢታይም ምንም ሳይታወቀው ኤድስን የሚያሰራጨው ይኸኛው በበሽታው የተለከፈ የኅብረተሰቡ ክፍል ነው።

በኤች አይ ቪ የተለከፉ ሰዎችን መጠን ለማወቅ የተደረጉት ምርመራዎች ገዳይ የሆነው ይህ ወረርሽኝ አፍሪካን ምን ያህል እያጥለቀለቀ እንዳለ ይጠቁማሉ። ለምሳሌ አፍሪካን አፌርስ የተባለው መጽሔት “በቪክቶሪያ ሐይቅ ዙሪያ በሚገኘው በሕዝብ ብዛት በተጨናነቀው ክልል . . . [ኤች አይ ቪ] በእጅጉ ተዛምቷል . . .፤ በየትኛውም ቦታ በጉልምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል በኤድስ የመለከፋቸው አደጋ ዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ነው የተባሉት ከ10 እስከ 18 በመቶ ይሆናሉ፤ ብዙ ቅምጦች ካሏቸው መካከል ደግሞ 67 በመቶ የሚሆኑት ለዚህ አደጋ ተጋልጠዋል” ሲል ገልጿል። በተመሳሳይም ኔቸር የተባለው መጽሔት “በጥቅሉ በጉልምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙ ሰዎች መካከል በሽታው ከ1984 ጀምሮ ያለሟቋረጥ በመዛመት ይህ በሽታ ክፉኛ ባጠቃቸው ከተሞች በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከ20–30 በመቶ ደርሷል” በማለት ባገኘው መረጃ ላይ የተመረኮዘ ሐሳብ ሰንዝሯል። እስቲ ያስቡት፣ በጉልምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአሥር ዓመት ውስጥ የሞትን ጽዋ ይጎነጫሉ!

አንድ ወቅት ላይ የኤድስን ስርጭት መጠን ለመግለጽ እምብዛም ፈቃደኛ ያልነበሩ መንግሥታትና መሪዎች በአሁኑ ጊዜ የወረርሽኙ እሳት ከፊት ለፊታቸው እየተንቦገቦገ ነው። የአንዲት አፍሪካ አገር የቀድሞ ፕሬዘዳንት ኤድስን ለመዋጋት ለሚደረገው ዘመቻ ሙሉ ድጋፋቸውን የሰጡት የራሳቸው ልጅ በበሽታው ከሞተ በኋላ ነው። በቅርቡ አንድ ሌላ የመንግሥት መሪ በአገራቸው ውስጥ 500,000 ሰዎች በኤች አይ ቪ እንደተለከፉ በመግለጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ለሞት በሚያደርስ በሽታ መያዛቸውንና በሴሰኝነት ምግባራቸው ይህን መቅሠፍት እያሰራጩ መሆኑን አያውቁም።

“እዚህ ምን እንደደረሰብን ንገሯቸው”

በኤች አይ ቪ የተለከፉ ሰዎች ቁጥር ያለማቋረጥ እየጨመረ ሲሄድ ውሎ አድሮ በጠና እየታመሙ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ይጨምራል። እነዚህ ሰዎች ሲሞቱ ይህ ነው የማይባል ሐዘንና ሥቃይ ትተው ያልፋሉ። ኤድስ ከፍተኛ ጥፋት ባስከተለበት ኡጋንዳንና ታንዛኒያን በሚያዋስነው ድንበር ላይ ይህ ሁኔታ በ59 ዓመት ዕድሜ ላይ በሚገኙት በካምሉዋ ላይ ደርሷል። ከ1987 ጀምሮ 11 ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ቀብረዋል፤ ሁሉም የኤድስ ሰለባዎች ናቸው። “ብሶቴን ለዓለም ሕዝብ አሰሙልኝ” በማለት በደረሰባቸው ሐዘን ቅስማቸው ተሰብሮ ያለቅሳሉ። “እዚህ ምን እንደደረሰብን ንገሯቸው” ብለዋል።

ኤድስ በሚዛመትባቸው መንገዶች የተነሳ በአፍሪካ በካምሉዋ ላይ የደረሰው ሁኔታ በሌሎች ብዙ የዓለም ክፍሎች ላይም ይደርሳል የሚል ሥጋት አለ። ‘ይሁን እንጂ አፍሪካ ይህ ነው የማይባል የሰው ዘር ሥቃይና መከራ ገፈት ቀማሽ የሆነችው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ