አፍሪካ ክፉኛ የተጠቃችው ለምንድን ነው?
የ42 ዓመቱ ጃኮብ ሕመምተኛ ሰው ነው። ኤድስ ይዞታል። ሚስቱም በኤድስ እንድትለከፍ አድርጓል። ጃኮብ “ሚስቴ በሽታው ከእኔ እንደያዛት ታውቃለች” በማለት እውነቱን ሳይሸሽግ ይናገራል።
ይሁን እንጂ ጃኮብ ይህ ገዳይ ቫይረስ ሊይዘው የቻለው እንዴት ነው? እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ሐራሬ ውስጥ ብቻዬን እኖር ነበር፤ ከዛምቢያ ተነስቼ በዚምባብዌ በኩል እስከ ቦትስዋናና ስዋዚላንድ ድረስ ባለው መንገድ በሹፌርነት እሠራለሁ። ሚስቴ ከልጆቻችን ጋር በማኒካላንድ [ዚምባብዌ ውስጥ] ትኖር ነበር። እኛ ሹፌሮች ደግሞ ልንሸሻቸው የሚገቡንን አንዳንድ ነገሮች አድርገናል።”
እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋው ልቅ የጾታ ብልግና
በዛሬው ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ ለኤድስ መዛመት ዋነኛው ምክንያት ሴሰኝነት ነው። በአጭር አነጋገር “የጾታ ሥነ ምግባር ደንቦች ተጥሰዋል” በማለት የኤድስ ተመራማሪ የሆኑት ዶውን ሞክሆቦ ገልጸዋል። አፍሪካን አፌርስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ልጅ መውለድ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው ነገር ነው፤ ትዳርን ግን እጅግ አቅልለው ይመለከቱታል። ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸም የጾታ ብልግና . . . እርግዝና ቢያስከትልም እንኳን ብዙም አይወገዝም።” ኔቸር የተባለው መጽሔት እንደሚለው ከሆነ በሽታው የሚተላለፍበት አንዱ ዓይነተኛ መንገድ ሴተኛ አዳሪነት ነው። “ሴተኛ አዳሪዎች ወረርሽኙን አንድ ባል ብቻ ወዳላቸው ባለትዳር ሴቶች በሴሰኛ ባሎቻቸው አማካኝነት ያስተላልፉባቸዋል” ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል።
ምግባራቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ የሆኑት ጥቂቶች ናቸው። ፓኖስ ዶክመንት ኤድስ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በዛየር ውስጥ አንድ የሕክምና ተመራማሪ ያጋጠማቸውን የሚከተለውን ነገር ይተርክልናል:- “አንድ ቀን ማታ አብረውኝ ከሚሠሩት የዛየር ዜጎች የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በአንድ የገጠር ቦታ የደም ምርመራዎች ካካሄድን በኋላ አብረውኝ ሲሠሩ የዋሉት እነዚህ የሕክምና ባለሙያዎች በአካባቢው ከሚኖሩት ልጃገረዶች ጋር ተያይዘው ሄዱ። ከልጃገረዶቹ ጋር አደሩ፤ ከመካከላቸው በኮንዶም የተጠቀመው አንዱ ብቻ ነበር።” አደጋውን አትፈሩም ወይ ብሎ ሲጠይቃቸው “ገና ለገና በሽታ ሊይዘኝ ይችላል ብለህ ሕይወትን ልትተው አትችልም በማለት ተሳለቁበት።” አዎን፣ ብዙዎች በየቦታው መልከስከስን እንደ “ሕይወት” ማለትም ከፍተኛ ደስታ የሚሰጥ መዝናኛ አድርገው ይመለከቱታል።
በብዙ ሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደሚታየው ሁሉ በአፍሪካም በተለይ ወጣቶች ለሴሰኝነት የተጋለጡ ናቸው። በደቡብ አፍሪካ በቅርቡ በ377 ወጣቶች ላይ በተካሄደ አንድ ጥናት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጾታ ግንኙነት እንደፈጸሙ ተገልጿል። በተመሳሳይም በደቡባዊ መካከለኛ አፍሪካ የሚገኝ አንድ ሚስዮናዊ “በ15 ዓመት ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ልጃገረዶች መካከል ያላረገዙ ሴቶች በጣም ጥቂት መሆናቸውን” ማስተዋል ችሏል። “አንዲት ያላገባች ወጣት ልጃገረድ ስትመለከቱ በልባችሁ ‘ይቺ ልጅ የዛሬ ዓመት ታረግዛለች’ ብላችሁ ታስባላችሁ” ሲል አክሎ ተናግሯል።
ይሁን እንጂ በአፍሪካ ውስጥ ኤድስ በፍጥነት እንዲዛመት ያደረጉ ሌሎች ነገሮችም አሉ።
የተበታተኑ ቤተሰቦች
“ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በሃያዎቹ ወይም በሠላሳዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች ከሚስቶቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው በመሄድ በከተሞች ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎች፣ በማዕድን ማውጫዎች፣ በእርሻ ልማት ጣቢያዎችም ሆነ በከባድ መኪና አሽከርካሪነት ለመሥራት እስከተገደዱ ድረስ ኤድስ ምንም ነገር ሳይገታው መዛመቱን ይቀጥላል” በማለት አፍሪካ ሳውዝ የተባለው መጽሔት ገልጿል። ሥራ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንከራተቱ አፍሪካውያን ፍዳ የተሞላበት ኑሮ ይገፋሉ። ብዙዎች ከሚስቶቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በከተሞች ውስጥ መኖሪያና ሥራ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። አፍሪካን አፌርስ መጽሔት በሚለው መሠረት ሥራ ፍለጋ የሚንከራተተው ሰው ራሱንና ትቶት በመጣው ቀዬው የሚገኘውን ቤተሰቡን ለመርዳት የሚያደርገው ጥረት የሚፈጥርበት ጭንቀት “እንዲበሳጭና ምንም ነገር ለማድረግ የሚያስችል ብቃት እንደሌለው ሆኖ እንዲሰማው” ያደርገዋል። መጽሔቱ አክሎ ሲናገር ብዙውን ጊዜ ይህ ሁኔታ ሥራ ፍለጋ መኖሪያውን ጥሎ የሚንከራተተው ሰው “ያሉበትን ኃላፊነቶች ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጎ እንዲተው” ይገፋፋዋል ብሏል።
በተለይ ከባድ መኪናዎች የሚመላለሱባቸው ጎዳናዎች ቀሳፊው ኤድስ የሚዛመትባቸው መተላለፊያ መንገዶች ተደርገው ይታያሉ። ሁኔታው አንድ የከባድ መኪና ሹፌር እንደገለጸው ነው:- “በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የሚያስፈልጉኝን አንዳንድ ነገሮች የምታደርግልኝ ወዳጅ እንድትኖረኝ እፈልጋለሁ” ብሏል። ኤድስ በስፋት ከሚባዛባቸው ቦታዎች አንዱ በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኝ ችምችም ያሉ ደሳሳ ቤቶች የሚገኙበትና 600 ሴተኛ አዳሪዎች ሥራቸውን የሚያካሄዱበት አንድ ሰፈር ነው። ብዙዎቹ ደንበኞቻቸው ሻይ እንጠጣ ብለው ወደዚህ ሰፈር ጎራ የሚሉ የከባድ መኪና ሹፌሮች ናቸው። ከእነዚህ ሴተኛ አዳሪዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በኤች አይ ቪ ተለክፈዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኤች አይ ቪ የተለከፉት የከባድ መኪና ሹፌሮች ይህን ገዳይ በሽታ እያሰራጩ ወደሚቀጥለው “የሻይ መጠጫ” ጣቢያ ያመራሉ፤ በመጨረሻም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።
በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መሰደድ ምክንያት የሚሆኑት የፖለቲካና የእርስ በርስ ጦርነቶችም አሉ። የኤድስ ኤክስፐርት የሆኑት አላን ዋይትሳይድ “የፖለቲካና የእርስ በርስ ጦርነት ሲኖር ቀደም ሲል ትክክለኛ ነው ተብሎ ይታመንበት የነበረው ማኅበራዊ ጠባይ ሁሉ ይለወጣል። . . . ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ስደተኞች በሽታው እንዲስፋፋ የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥሩለታል። በጾታ ግንኙነታቸውም በአንድ ሰው ተወስነው አይቀሩም” ብለዋል።
ከሕክምና ጋር የተያያዙ አደጋዎች
ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ያለባት አፍሪካ የሕክምና ችግሮቿን መወጣት አትችልም። “በብዙ የአፍሪካ አገሮች በዓመት ለእያንዳንዱ ሰው የጤና እንክብካቤ የሚመደበው በጀት ለኤድስ ቫይረስ የደም ምርመራ ሲደረግ ከሚከፈለው ዋጋ ያነሰ ነው” በማለት አንደርስታንዲንግ ኤንድ ፕሪቬንቲንግ ኤድስ የተባለው ብሮሹር ገልጿል። በተመሳሳይም ኤድስ— ካውንት ዳውን ቱ ዱምስዴይ (መዓቱን የሚያወርድበትን ቀን እያስቆጠረ ያለው ኤድስ) የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ኪት ኤድልሰን “ብዙውን ጊዜ ሌላው ቀርቶ የሕክምና መሣሪያን ከጀርሞች ለማጽዳት የሚያገለግል ሳሙና ወይም ወለል ላይ የፈሰሰን ደም ለማጽዳት የሚያገለግል ተራ በረኪና እንኳ አይገኝም” ሲሉ ገልጸዋል።
በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሚታየው ብዙ ሕሙማንን በአንድ መርፌ የመውጋት ልማድ ኤድልሰን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ አነሳስቷቸዋል:- “በአፍሪካ ውስጥ . . . መርፌ መወጋት ካስፈለጋችሁ ተጠንቀቁ . . . ዓይናችሁ እያየ ከጀርም ነጻ የሆነና የታሸገ አዲስ መርፌ አውጥተው እንዲጠቀሙ ጠይቋቸው።”
በድንገተኛ አጋጣሚ በበሽታው የመለከፉ አደጋ የሕክምና ባለሙያዎችን ሥራውን እየለቀቁ እንዲሄዱ እያስገደደ ነው። በአንድ የደቡብ አፍሪካ ሆስፒታል ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሁለት ዶክተሮች የኤድስ ሕሙማንን በሚያክሙበት ጊዜ እየተጠቀሙበት የነበረው መርፌ ወጋቸው። በበሽታው ተለከፉና ሞቱ። በዚህም ሳቢያ ስድስት የውጪ አገር ዶክተሮች ሆስፒታሉን ለቀው ወጡ።
ነገሩን ከነዚህ ሁኔታዎች አኳያ በማየት ብዙ ሰዎች ኤድስ በኃይል እንዲዛመት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የሆነውን ማለትም ለሕመምተኛ ደም የመስጠትን ልማድ እንደገና እያሰቡበት መሆናቸው አያስደንቅም! “በበሽታው የተበከለ ደም መስጠት በሽታው የሚተላለፍበት አንዱ ዓቢይ መንገድ ነው” በማለት ሳውዝ አፍሪካን ሜዲካል ጆርናል ገልጿል። አክሎም “በመካከለኛው አፍሪካ እስካሁንም ድረስ የሚሰጠው ደም ከበሽታው የጠራ እንደሆነና እንዳልሆነ ምርመራ አይደረግም ለማለት ያስደፍራል፤ ለበሽተኞች ከሚለገሰው ደም ቢያንስ ቢያንስ 60 በመቶው በበሽታው የተበከለ ነው” ብሏል።
ስለዚህ ቀድሞውንም በብዙ አሳዛኝ ክስተቶች የታመሰችው አፍሪካ አሁንም እንደገና እየተጠቃች ነው። በአፍሪካ ውስጥ የኤድስ ወረርሽኝ ካስከተላቸው እጅግ አሳዛኝ ውጤቶች አንዱ በሴቶችና በልጆች ላይ የደረሰው ሰቆቃ ነው።
ባልሠሩት ጥፋት ፍዳቸውን የሚያዩ ሰዎች
ሉሲ ባልሠራችው ጥፋት ለኤድስ ሰለባነት የተዳረገች ሴት ናት። በሽታው የያዛት ሴሰኛ ከሆነው ባልዋ ነው። አለ ባል የቀረችው የ23 ዓመቷ ሉሲ በአሁኑ ጊዜ ከራሷ ስሜቶች ጋር ትሟገታለች። “የባሌን ትዝታ ልውደደው ወይስ በበሽታው እንድለከፍ ስላደረገኝ ባሌን ልጥላው እያልኩ ከራሴ ሐሳብ ጋር እሟገታለሁ” ስትል ተናግራለች። ሉሲ የተሰማት ስሜት ሌላው ባመጣው መዘዝ ለኤድስ ሰለባነት በተዳረጉ ሰዎች ላይ ኤድስ ለሚያስከትለው ከባድ ሥቃይና መከራ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው።
“ምንም እንኳ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በኤድስ የሚያዙት ወንዶችና ሴቶች ቁጥር ተመጣጣኝ ቢሆንም” ይላል ዘ ወርልድ ቱደይ መጽሔት፤ “በሴቶች ላይ መዘዙ . . . ይበልጥ የከበደ ነው።” ይህ በተለይ መሃይምነትና ድህነት ክፉኛ ያጠቃቸው እንዲሁም ሥራ ፍለጋ እነርሱን ጥለው በከተሞች የሚንከራተቱ ባሎች ያሏቸው ስሜታቸውን አምቀው የሚሠቃዩ ሴቶች በሚኖሩባት በአፍሪካ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው።
ይሁን እንጂ ኤድስ ከሁሉ ይበልጥ እጅግ አሳዛኝ ጠባሳ የሚጥለው በልጆች ላይ ነው። ዩኒሴፍ (የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት) በያዝነው አሥርተ ዓመት በአፍሪካ 2.9 ሚልዮን ሴቶች በኤድስ እንደሚሞቱና 5.5 ሚልዮን የሚሆኑ ልጆች ወላጅ አልባ እንደሚሆኑ ገምቷል። ወላጆቻቸው በኤድስ ሳቢያ የሞቱባቸው ቢያንስ ቢያንስ 40,000 ልጆች የሚገኙባት የአንዲት አገር ባለሥልጣን የሆኑ ሰው በአሁኑ ጊዜም እንኳ “ልጆች ብቻ . . . የሚኖሩባቸው መንደሮች አሉ” ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል።
በበሽታው የተለከፉ እናቶችንና ሕፃናትን ማየቱ የሚያዝና የሚጨበጥ ነገር ለሚያሳጡት ሁኔታዎች ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ሳውዝ አፍሪካን ሜዲካል ጆርናል “በበሽታው የተለከፈ ሕፃን ያላት እናት የምታነሳው የተለመደ ጥያቄ ‘ከሁለታችን ቀድሞ የሚሞተው ማን ይሆን?’ የሚል ነው” ሲል ገልጿል።
ብዙ ሴቶች ለኤድስ የተጋለጡ እንደሆኑ ቢሰማቸው ምንም አያስደንቅም። ዛምቢያዊው ዶክተር ኤም ፊሪ እንዲህ ብለዋል:- “ይህ በሽታ እንዳይዛቸው ለመከላከል ምን ማድረግ እንደሚችሉ የሚጠይቁ ሴቶች ያጋጥሙናል . . . ይህ ፍርሃት የመጣው እነርሱ ራሳቸውን ቢጠብቁም የትዳር ጓደኞቻቸው የሆኑት ባሎቻቸው ታማኝ ላይሆኑ ስለሚችሉ ነው። ይህ በጣም ያስጨንቃቸዋል።”
ታዲያ ያገባ(ች) ግለሰብ የትዳር ጓደኛው(ዋ) ሴሰኛ ሆና(ኖ) ብት(ቢ)ገኝ ምን ሊደረግ ይችላል? በዳዩ ወገን ይቅር ከተባለና በትዳሩ መሐል እርቅ ከተፈጠረ ጥፋተኛው የትዳር ጓደኛ ምናልባት በኤች አይ ቪ ተለክፎ ሊሆን ስለሚችል የሕክምና ምርመራ ለማድረግ መስማማት ይኖርበታል። (ከማቴዎስ 19:9 እና ከ1 ቆሮንቶስ 7:1–5 ጋር አወዳድር።) የምርመራው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸው ባለ ትዳሮች የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም ሊታቀቡ ወይም ቢያንስ ቢያንስ በበሽታው እንዳይለከፉ ለመከላከል በሚያስችል ዘዴ ለመጠቀም ሊወስኑ ይችላሉ።
ኤድስ ለረጅም ጊዜ በሰውነት ውስጥ ተደብቆ የሚቆይ በመሆኑ ለማግባት የሚያስቡ ወጣቶችም ምንም እንኳ የሚያገቡት ሰው በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያናዊ የአቋም ደረጃዎችን ጠብቆ የሚመላለስ ቢሆንም ቀደም ሲል በሥነ ምግባር አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ከሆነ ለማግባት ከመወሰናቸው በፊት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህን አደጋ አስመልክቶ ዶክተር ኤስ ኤም ቲባንጋዩካ የተባሉ አንድ ታንዛኒያዊ የኤድስ ኤክስፐርት ወጣቶች “ከማግባታቸው በፊት የኤች አይ ቪ ምርመራ በማድረግ” ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ ይችላሉ በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል።
ያም ሆነ ይህ ኤድስ በአፍሪካም ሆነ በተቀረው የዓለም ክፍል እስካለ ድረስ የትዳር ጓደኞችንና ልጆችን ጨምሮ ሌላው ሰው ባመጣው መዘዝ በበሽታው የሚለከፉ ሰዎች መኖራቸውና ለሥቃይ መዳረጋቸው አይቀርም።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤድስ በአፍሪካ ላይ የሞት ጥላ እንዲያጠላ ያደረጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ
[ምንጭ]
WHO/E. Hooper