የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 4/8 ገጽ 10-14
  • በቤተሰብ ውስጥ ጠብ የማይኖርበት ጊዜ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቤተሰብ ውስጥ ጠብ የማይኖርበት ጊዜ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “አዲሱ ሰው”
  • በሌሎች ላይ እምነት መጣልን መማር
  • ርህሩህ የበላይ ተመልካቾች
  • አምላክ ለጋብቻ ያለው አመለካከት
  • የአምላክ ሕግ ምን ይፈቅዳል?
  • በቤተሰብ መሃል ጠብ የማይኖርበት ጊዜ
  • ቤተሰብን የሚያናጉ ችግሮችን መቋቋም ትችላላችሁ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • በቤተሰብ ውስጥ ለጠብ መንስኤ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው?
    ንቁ!—1998
  • ጠብ ቤተሰብን ሲያናጋ
    ንቁ!—1998
  • የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 4/8 ገጽ 10-14

በቤተሰብ ውስጥ ጠብ የማይኖርበት ጊዜ

“በቤት ውስጥ ጨርሶ ጠብ እንዳይኖር ለማድረግም ሆነ በቤተሰብ ውስጥ የሚነሳውን ጠብ እንዲቀንስ ለማድረግ በኅብረተሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ከፍተኛ መዋቅራዊ ለውጦች ማድረግን ይጠይቃል።”—ቢሃይንድ ክሎዝድ ዶርስ

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነፍስ ግድያ የተፈጸመው በሁለት ወንድማማቾች መካከል በተነሣ ጠብ ምክንያት ነው። (ዘፍጥረት 4:8) ከዚያ ወዲህ ባሳለፍናቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጅ በቤተሰብ መሃል በሚፈጸም የኃይል ድርጊት ሲታመስ ኖሯል። ለዚህ ችግር መፍትሔ ያስገኛሉ ተብለው የተሰነዘሩ በርካታ ሐሳቦች ቢኖሩም እነዚህ ሐሳቦች የየራሳቸው ድክመት ያለባቸው ናቸው።

ለምሳሌ ያህል ተደባዳቢ ለሆኑ ሰዎች ከሚሰጠው የጠባይ ማረሚያ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚሆኑት ችግር እንዳለባቸው አምነው የተቀበሉት ብቻ ናቸው። ችግሩን በማሸነፍ ላይ የሚገኝ ተደባዳቢ የነበረ አንድ ባል “[ማረሚያ በመቀበል ላይ የምንገኘው] ባሎች አንድ እጅ ስንሆን ‘አሮጊትዋን ልክ ማስገባት ያስፈልጋል’ ብለው የሚደነፉ ምንም አይነት እርዳታ የማይደረግላቸው ከእኛ በሦስት እጅ የሚበልጡ ባሎች አሉ” ብሏል። ስለዚህ ዱለኛ የሆነው ባል የባሕርይ ችግር ያለበት መሆኑን አምኖ መቀበል ይኖርበታል። ዱለኛ የሆነበትን ምክንያት መርምሮ ማወቅ አለበት። ጉድለቶቹን እንዲያርም የሚያስችለው እርዳታ ካገኘ ባሕርዩን ለማረቅ የሚያስችለውን መንገድ መከተል ይችል ይሆናል።

ይሁን እንጂ የማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን የሚከታተሉ ፕሮግራሞች የሠራተኛ እጥረት አለባቸው። በዚህም ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ 90 በመቶ የሚሆኑ በልጆች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች የቤተሰብ ሁኔታ በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ግድያው ከመፈጸሙ በፊት ተጠቁሞ እንደነበር ይገመታል። ስለዚህ የማኅበራዊ ኑሮ ፕሮግራሞችና የፖሊስ ድርጅቶች ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር በጣም ውስን ነው። በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ነገር አለ።

“አዲሱ ሰው”

አንድ የተመራማሪዎች ቡድን “በቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ዝምድና ከመለወጥ የተሻለ ምንም ነገር የለም” ብሏል። በቤተሰብ ውስጥ ለጠበኝነት ዋነኛ ምክንያት የሚሆነው የአስተሳሰብ ችግር ስላለ እንጂ ጉልበተኛ መሆንን ለማሳየት የሚደረግ ብቻ አይደለም። ችግሩ የሚመነጨው የቤተሰብ አባሎች ማለትም ባሎች፣ ሚስቶች፣ ልጆች፣ ወላጆች፣ ወንድማማቾችና እህትማማቾች አንዳቸው ለሌላው ካላቸው አመለካከት የተነሳ ነው። በእነዚህ ግንኙነቶች ረገድ መሠረታዊ ለውጥ እንዲኖር ከተፈለገ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አዲስ ሰው’ ብሎ የሚጠራውን አዲስ ስብዕና መልበስ ያስፈልጋል።—ኤፌሶን 4:22-24፤ ቆላስይስ 3:8-10

በቤተሰብ አባሎች መካከል የተሻለ ዝምድና እንዲኖር የሚያስችለውን ክርስቶስ መሰል አዲስ ሰው ለመልበስ የሚረዱንን አንዳንድ ከቤተሰብ ሕይወት ጋር ዝምድና ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመርምር።—ማቴዎስ 11:28-30⁠ን ተመልከት።

ለልጆች ሊኖር የሚገባ አመለካከት:- ወላጅ የመሆን ኃላፊነት በመውለድ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ ሸክም ስለሚቆጥሩ የወላጅነት ግዴታቸውን በፍቅር መወጣት ይቸግራቸዋል። በልጆቻቸው ላይ በደል የሚፈጽሙት እንደነዚህ ያሉት ወላጆች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ‘የይሖዋ ስጦታ’ እንደሆኑና ከእርሱ የተገኙ ‘ሽልማቶች’ መሆናቸውን ይናገራል። (መዝሙር 127:3) ወላጆች ለተሰጣቸው ስጦታ ተገቢውን እንክብካቤ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ልጆቻቸውን እንደ ሸክም የሚቆጥሩ ወላጆች በዚህ አመለካከታቸው ረገድ አዲሱን ሰው ማዳበር ይኖርባቸዋል።a

ከልጆች ምክንያታዊ የሆኑ ነገሮችን መጠበቅ:- አንድ ጥናት እንዳመለከተው በልጆቻቸው ላይ በደል የሚፈጽሙ ብዙ እናቶች ሕፃኑ አንድ ዓመት ሲሞላው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንደሚገባው ይጠብቃሉ። ጥናት ከተደረገባቸው እናቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ በስድስት ወር ዕድሜው ትክክልና ስህተት የሆነውን ሊለይ እንደሚችል ይጠብቃሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው ፍጽምና ያለው ሆኖ እንደማይወለድ ያመለክታል። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሕፃን ገና ከተወለደ ጀምሮ ማስተዋል ይኖረዋል አይልም። ከዚህ ይልቅ የአንድ ሰው ‘የማስተዋል ችሎታ’ የሚዳብረው “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት” የሚያስችለውን ስልጠና ካገኘ በኋላ እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 5:14 NW] ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ልጅነት ጠባይ፣” ስለ ልጅነት “ስንፍና” እንዲሁም ጉርምስና “ከንቱ” ስለመሆኑ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:11፤ ምሳሌ 22:15፤ መክብብ 11:10) ወላጆች የልጆቻቸውን አቅምና ችሎታ በመረዳት ከዕድሜያቸውና ከችሎታቸው ጋር የማይመጣጠን ነገር ከመጠበቅ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።

ለልጆች ዲሲፕሊን መስጠት:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዲሲፕሊን” [NW] ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ትርጉም “ማስተማር” ማለት ነው። ስለዚህ ዲሲፕሊን የሚሰጥበት ዋነኛ ዓላማ ለማሰልጠን እንጂ ለማሳመም አይደለም። መማታት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ቢችልም አለ ዱላ ብዙ ዲሲፕሊን መስጠት ይቻላል። (ምሳሌ 13:24) መጽሐፍ ቅዱስ “ተግሳጽን ስማ፣ ጠቢብም ሁን” ይላል። (ምሳሌ 8:33 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከዚህም በላይ ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን የሚያናድድ ሁኔታ ሲያጋጥመው ራሱን ‘መግታት’ እንደሚያስፈልገውና ተግሳጽ በሚሰጥበት ጊዜ ‘ትዕግሥት’ ማሳየት እንደሚኖርበት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24፤ 4:2) ይህም ልጆች በሚቀጡበት ጊዜ እንኳን ከመጠን በላይ መጮህ ወይም ከልክ ያለፈ ኃይል መጠቀም አግባብ አለመሆኑን ያመለክታል።

በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘የምሰጠው ዲሲፕሊን ያስተምራል ወይስ በማሳመም የሚቆጣጠር ብቻ ነው? የምሰጠው ዲሲፕሊን ትክክለኛ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያሰርጽ ነው ወይስ ፍርሃትን?’

ትልልቅ ሰዎች ሊኖራቸው የሚገባ የባሕርይ ገደብ:- አንድ ተደባዳቢ ባል ሚስቱን የደበደበው “ራሱን መቆጣጠር” ተስኖት እንደሆነ ተናገረ። አንድ አማካሪ ይህን ሰው ሚስትህን በጩቤ ወግተህ ታውቃለህ? ብሎ ጠየቀው። “ይህንንስ በፍጹም አላደርገውም!” ሲል መለሰለት። ሰውዬው ለራሱ ያወጣውና የሚጠብቀው ገደብ እንዳለውና መሠረታዊ ችግሩ ግን እነዚህ ገደቦች ትክክለኛ አለመሆናቸው እንደሆነ እንዲያስተውል ተደረገ።

የአንተስ ገደብ እስከምን ድረስ ነው? አለመግባባቱ ተባብሶ ወደ መደባደብ ከመድረሱ በፊት ታቆማለህ ወይስ በቁጣ ገንፍለህ እስከ መጮህ፣ የስድብ ውርጅብኝ እስከ ማውረድ፣ እስከ መገፍተር፣ የቤት ውስጥ ዕቃዎችን እስከ መወርወር ወይም እስከ መማታት ትደርሳለህ?

አዲሱ ሰው የአእምሮ ወይም የአካል ዱላ እስከ መሰንዘር የማያደርስ ጥብቅ የሆነ ገደብ አለው። ኤፌሶን 4:29 “ክፉ [“የበሰበሰ፣” NW] ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” ይላል። ቁጥር 31 ደግሞ በመቀጠል “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” ይላል። “ቁጣ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ግልፍተኛ የመሆንን ባሕርይ” ያመለክታል። ቶክሲክ ፓረንትስ የተባለው መጽሐፍ ሕፃናትን የሚደበድቡ ወላጆች የጋራ ባሕርይ “በከፍተኛ ደረጃ ግልፍተኛ መሆን ነው” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። አዲሱ ሰው በስሜት ግንፍልነት ላይ ጥብቅ የሆነ የአካልም ሆነ የቃል ገደብ ይጥላል።

እርግጥ አዲሱን ሰው መልበስ የሚኖርበት ባል ብቻ አይደለም። ሚስትም ይህንን ባሕርይ መልበስ ያስፈልጋታል። ባልዋ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ለሚያደርገው ጥረት አድናቆት ማሳየትና ከእርሱ ጋር መተባበር ይኖርባታል እንጂ ቁጣውን የምታነሳሳ መሆን የለባትም። በተጨማሪም ሁለቱም ቢሆኑ አንዳቸው ከሌላው ፍጽምና መጠበቅ አይኖርባቸውም። ከዚህ ይልቅ 1 ጴጥሮስ 4:8⁠ን ሥራ ላይ ለማዋል መጣር ይኖርባቸዋል:- “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።”

ለአረጋውያን አክብሮት ማሳየት:- ዘሌዋውያን 19:32 “ሽማግሌውን አክብር” ይላል። አንድ በዕድሜ የገፋ ወላጅ ሕመምተኛ በሚሆንበት ወይም አስቸጋሪ ጠባይ በሚያሳይበት ጊዜ ይህን ትእዛዝ መፈጸም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አንደኛ ጢሞቴዎስ 5:3, 4 ወላጆችን ስለ ማክበርና ውለታቸውን ስለ መክፈል ይናገራል። ይህም ገንዘብም ሆነ አክብሮት መስጠትን ሊያካትት ይችላል። ወላጆቻችን ራሳችንን ልንረዳ በማንችልበት የጨቅላነት ዕድሜ ብዙ ነገር ስላደረጉልን አሁን እነርሱ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል።

በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል የሚነሳውን ግጭት ማሸነፍ:- ቃየል ያደረበት ጥላቻ ሥር ሰድዶ ወንድሙን አቤልን ከመግደሉ በፊት “ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” የሚል ምክር ተሰጥቶት ነበር። (ዘፍጥረት 4:7) ስሜትን መቆጣጠር ይቻላል። መቻቻልን ተማሩና “እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ።”—ኤፌሶን 4:2

በሌሎች ላይ እምነት መጣልን መማር

በቤታቸው ውስጥ የኃይል ድርጊት ከሚፈጸምባቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ገበናቸውን አይገልጡም። ዶክተር ጆን ራይት “በየጊዜው የሚደበደቡ ሴቶች ስሜታዊና አካላዊ ጥበቃ ለማግኘት ብቃት ያለው ሦስተኛ ሰው መፈለግ ይኖርባቸዋል” በማለት አጥብቀው ይመክራሉ። ይህ ምክር በደል ለሚፈጸምበት ለማንኛውም የቤተሰብ አባል ይሠራል።

አንድ የኃይል ድርጊት የሚፈጸምበት የቤተሰብ አባል እምነቱን በሌላ ሰው ላይ ለመጣል የሚቸገርበት ጊዜ ይኖራል። ምክንያቱም ይህ ሰው በጣም ቅርቡ የሆነው የገዛ ራሱ ቤተሰብ አባል እንኳን ከሥቃይ በስተቀር ያስገኘለት ነገር የለም። ይሁን እንጂ ምሳሌ 18:24 “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” ይላል። እንዲህ ያለውን ወዳጅ ማግኘትና እርሱንም ምሥጢረኛ ለማድረግ መቻል አስፈላጊውን እርዳታ ለማግኘት የሚያስችል ጠቃሚ እርምጃ ነው። እርግጥ ዱለኛውም ግለሰብ ቢሆን እርዳታ ያስፈልገዋል።

በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር ይሆናሉ። እነዚህ ሰዎች አዲሱን ሰው መልበስ የሚጠይቀውን ጥረት በሙሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል በቤተሰባቸው ውስጥ የኃይል ድርጊት ሲፈጽሙ የቆዩ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የቀድሞ ዝንባሌያቸው እንዳያገረሽባቸው መጽሐፍ ቅዱስ “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” እንዲጠቅማቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ለእነዚህ አዳዲስ ምሥክሮች አዲሱን ሰው መልበስ ቀጣይነት ያለው ሂደት እንጂ አንድ ሰሞን ብቻ የሚደረግ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ቆላስይስ 3:10 “የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል” ይላል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ስለዚህ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። የይሖዋ ምሥክሮች እጅግ ብዙ የሆኑ የመንፈሳዊ ‘ወንድሞችንና እህቶችን፣ እናቶችንና ልጆችን’ እርዳታ ስለሚያገኙ በዚህ ረገድ በጣም አመስጋኞች ናቸው።—ማርቆስ 10:29, 30፤ በተጨማሪም ዕብራውያን 10:24, 25 ተመልከት።

ከዚህም በላይ ከ85,000 በላይ በሆኑት በመላው ዓለም በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ፣ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” የሆኑ አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾች አሉ። ‘ዓይኖቻቸውና ጆሮዎቻቸው የሕዝቡን ችግሮች ለማየትና ለማዳመጥ የተከፈቱ’ ናቸው። (ኢሳይያስ 32:2, 3) ስለዚህ አዲሶችም ሆኑ ቆየት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አዲሱን ሰው ለመልበስ በሚያደርጉት ጥረት ከክርስቲያን ጉባኤ ብዙ እርዳታ የማግኘት ግሩም አጋጣሚ አላቸው።

ርህሩህ የበላይ ተመልካቾች

እነዚህ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሰዎች ምክር ለማግኘት ወደ እነርሱ ሲመጡ አላንዳች አድልዎ በጥሞና እንዲያዳምጡ የሚያስችላቸውን ስልጠና አግኝተዋል። ሁሉን ሰው፣ በተለይም ከፍተኛ የጭካኔ ድርጊት የተፈጸመባቸውን በታላቅ ርህራሄና ማስተዋል እንዲያዳምጡ ይመከራሉ።—ቆላስይስ 3:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14

ለምሳሌ ያህል ባልዋ የደበደባት አንዲት ሚስት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊደርስባት ይችላል። በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች በቤተሰብ አባሎች ላይ የሚደርሰው ዱላ ከቤተሰቡ ውጪ ባሉ ሰዎች ላይ ቢፈጸም ኖሮ ተደባዳቢው ሰው ወህኒ መግባቱ አይቀርም ነበር። እንደ ጾታዊ በደል ያሉት ሌሎች ዓይነት በደሎች የተፈጸመባቸው በሚያዙበት መንገድ በደግነት መያዝ አስፈላጊ ነው።

ከዚህም በላይ የአምላክን ሕግ የሚጥሱ ሁሉ ስለ ድርጊታቸው ተጠያቂዎች ናቸው። በዚህ መንገድ የጉባኤው ንጽሕና ይጠበቃል፣ ለንጹሐን ሰዎችም አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ይቻላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአምላክ መንፈስ ሳይታገድ በነጻ እንዲፈስ ያስችላል።—1 ቆሮንቶስ 5:1-7፤ ገላትያ 5:9

አምላክ ለጋብቻ ያለው አመለካከት

አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር በሚሆንበት ጊዜ በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቦ ከሚገኘው የክርስቲያናዊ አኗኗር ሥርዓት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ይስማማል። ወንድ የቤተሰብ ራስ በመሆን በእውነተኛ አምልኮ ረገድ ቤተሰቡን እንደሚመራ ይማራል። (ኤፌሶን 5:22) ይሁን እንጂ ራስ መሆኑ ሚስቱን እንዲደበድብ ወይም ዝቅ አድርጎ እንዲመለከታት ወይም ፍላጎቶችዋን ችላ እንዲል ሥልጣን አይሰጠውም።

እንዲያውም በተቃራኒው የአምላክ ቃል የሚከተለውን ግልጽ ምክር ይሰጣል:- “ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለ ሆንን፣ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፣ ይመግበዋል ይከባከበውማል።” (ኤፌሶን 5:25, 28, 29) የአምላክ ቃል ሚስቶች መከበር እንዳለባቸው በግልጽ ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 3:7፤ በተጨማሪም ሮሜ 12:3, 10⁠ንና ፊልጵስዩስ 2:3, 4⁠ን ተመልከት።

ማንኛውም ክርስቲያን ባል ሚስቱን በአንደበቱም ሆነ በአካል እያቆሰለ እወዳታለሁ ወይም አከብራታለሁ ሊል አይችልም። የአምላክ ቃል “ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው” ስለሚል እንዲህ ብሎ ቢናገር ትልቅ ግብዝነት ይሆንበታል። (ቆላስይስ 3:19) በአርማጌዶን የአምላክ ፍርድ በቅርቡ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ሲወርድ ግብዞች ሁሉ የአምላክን አገዛዝ የሚቃወሙ ሰዎች የሚደርስባቸው ዓይነት ዕጣ ይቀበላሉ።—ማቴዎስ 24:51

ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ ባል ሚስቱን እንደ ገዛ አካሉ መውደድ ይኖርበታል። የራሱን አካል ይደበድባል፣ ወይስ ፊቱን በቡጢ ይመታል፣ ወይስ የገዛ ራሱን ፀጉር ይነጫል? ራሱን በሌሎች ፊት ያመናጭቃል ወይስ ያሽሟጥጣል? እንዲህ የሚያደርግ ሰው ሌላው ቢቀር አእምሮው ልክ አይደለም መባሉ አይቀርም።

አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን ቢደበድብ ክርስቲያናዊ ሥራዎቹ በሙሉ በአምላክ ፊት ከንቱ ይሆኑበታል። “የሚማታ” ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ሊሰጠው እንደማይበቃ አስታውሱ። (1 ጢሞቴዎስ 3:3 NW፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1-3) በባልዋ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት የምትፈጽም ሚስትም የአምላክን ሕግ ትጥሳለች።

ገላትያ 5:19-21 “ጥል፣ ክርክር . . . ቁጣ” አምላክ የሚያወግዛቸው ባሕርያት መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ “እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ይላል። ስለዚህ የትዳር ጓደኛን ወይም ልጅን መደብደብ ትክክል ሊሆን የሚችልበት አንድም ምክንያት የለም። የአብዛኞቹን አገሮች ሕግም ሆነ የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ድርጊት ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳትሙት መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት ክርስቲያን ነን እያሉ የዱለኛነት ጠባይ ስላላቸው ሰዎች ሲናገር “ክርስቲያን ነኝ የሚል ማንኛውም ሰው በተደጋጋሚ በቁጣ እየገነፈለ የኃይል ድርጊት የሚፈጽም ከሆነና ከዚህም ድርጊቱ ንስሐ የማይገባ ከሆነ ሊወገድ ይችላል” በማለት በዚህ ጉዳይ ላይ ቅዱሳን ጽሑፎች ያላቸውን አመለካከት ግልጽ አድርጓል።—ግንቦት 1, 1975 ገጽ 287 (የእንግሊዝኛ) ከ2 ዮሐንስ 9, 10 ጋር አወዳድር።

የአምላክ ሕግ ምን ይፈቅዳል?

የአምላክን ሕግ በሚጥሱ ሁሉ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጠው አምላክ ራሱ ነው። ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ግን ተደባዳቢው የትዳር ጓደኛ የማይለወጥና ከድርጊቱ የማይመለስ በሚሆንበት ጊዜ የአምላክ ቃል ለተበደለው ክርስቲያን ምን የሚፈቅደው ነገር ይኖራል? ንጹሕ የሆነው ወገን የሚደርስበትን አእምሮአዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ጉዳት ችሎ፣ ሕይወቱን ሳይቀር ለአደጋ አጋልጦ እንዲኖር ይገደዳልን?

መጠበቂያ ግንብ በቤት ውስጥ ስለሚፈጸም የኃይል ድርጊት ካተተ በኋላ የአምላክ ቃል ምን እንደሚፈቅድ ገልጿል። “ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፣ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፣ ባልም ሚስቱን አይተዋት’ ሲል መክሯል።” ጽሑፉ በመቀጠል “የሚፈጸመው በደል ለመሸከም የማይቻል ከሆነ ወይም ለሕይወት የሚያሰጋ ከሆነ የሚያምነው ወገን ‘ለመለየት’ ሊመርጥ ይችላል። ቢሆንም በተቻለ መጠን እንደገና ‘ታርቆ’ አብሮ ለመኖር ጥረት መደረግ እንደሚኖርበት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:10-16) ይሁን እንጂ ‘መለየት’ ብቻውን ለመፋታትና ሌላ ለማግባት የሚያስችል ምክንያት አይሆንም። ቢሆንም በሕግ መፋታት ወይም በሕግ ተለያይቶ መኖር በሌላ ጊዜ ሊደርስ ከሚችል ዱላ ሊከላከል ይችላል።”—የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መጋቢት 15, 1983፤ ገጽ 28-9፤ በተጨማሪም 21-109 ገጽ 16-17 ተመልከት።

እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች በደል የተፈጸመበት ግለሰብ የሚመርጠው እርምጃ በግሉ የሚወሰን ይሆናል። “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።” (ገላትያ 6:5) ማንም ቢሆን ይህን ሊወስንላት አይችልም። በተጨማሪም ማንም ለጤናዋ፣ ለሕይወትዋና ለመንፈሳዊነትዋ አደገኛ ወደሆነባት ዱለኛ ባልዋ እንድትመለስ ሊያስገድዳት ወይም ሊጫናት አይገባም። ይህ በራስዋ ምርጫና ፍላጎት እንጂ ሌሎች በሚጭኑባት ፈቃድ ወይም ተጽእኖ የሚወሰን አይደለም።—ፊልሞና 14⁠ን ተመልከት።

በቤተሰብ መሃል ጠብ የማይኖርበት ጊዜ

የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ሰዎች “ተሳዳቢዎች” “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” እንዲሁም “አስፈሪዎች” እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በተነበየው በዚህ የመጨረሻ ቀን በቤተሰብ መሃል ጠብ እንደሚስፋፋ ተምረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) አምላክ ከመጨረሻው ቀን በኋላ ሰዎች “ምንም የሚያስደነግጣቸው ሳይኖር በሰላም” የሚኖሩበት ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል።—ሕዝቅኤል 34:28 የ1980 ትርጉም

በዚህ አስደናቂ የሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ በቤተሰብ መሃል የሚነሳ ጠብ የተረሳ ነገር ይሆናል። “ገሮች ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11

መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ስለሚሰጠው ተስፋ ያገኛችሁትን እውቀት የበለጠ እንድትማሩ አጥብቀን እንመክራችኋለን። በአሁኑ ጊዜ እንኳን በቤተሰባችሁ ክልል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋል ብዙ ጥቅም ልታገኙ ትችላላችሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው በተባለው መጽሐፍ ከምዕራፍ 7 እስከ 9 ላይ “ልጅ መውለድ ኃላፊነትም ስጦታም ነው፣” “በወላጅነታችሁ የምታከናውኗቸው የሥራ ድርሻዎች” እና “ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሰልጠን” የተሰኙት ምዕራፎች የተዋጣ ወላጅ ለመሆን የሚያስችሉ ግሩም የሆኑ በርካታ ምክሮችን ይዘዋል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በቤተሰብ ውስጥ ለሚፈጠሩ ግጭቶች መፍትሔ እንድታገኙ ይረዱዋችኋል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በደል የተፈጸመባቸው ሰዎች ችግራቸውን ብቃት ላለው ወዳጅ መግለጽ ይኖርባቸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ