ሰለባዎች ወይስ ሰማዕቶች ልዩነቱ ምንድን ነው?
የሰው ልጅ በታሪክ ዘመን ሁሉ በወንዶች፣ በሴቶችና በሕፃናት ላይ እጅግ በጣም ብዙ መከራ እንዲደርስና በሚልዮን የሚቆጠሩ ደግሞ በጭካኔ እንዲገደሉ አድርጓል። በፖለቲካዊም ሆነ በብሔር፣ በዘር ወይም በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት ንጹሕ ደም ሲፈስ ቆይቷል፣ አሁንም እየፈሰሰ ነው። ፍቅርና ማስተዋል በጥላቻ ተሸፍነዋል። ተስማምቶ መኖር በግትርነት ታፍኗል። ግድያው ቀጥሏል።
ባለፉት መቶ ዘመናት ጦርነት ይደረግ የነበረው በወታደሮች መካከል ብቻ ነበር። የሲቪሎች ተሳትፎ በጣም ትንሽ ነበር። በ20ኛው መቶ ዘመናችን የቦንብ ውርጅብኝ፣ ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችና መድፎች፣ በጦርነቱ የተጎዱትን ሲቪሎች ቁጥር ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉን አንድ ጥናት ሲጠቅስ “በአሁኑ ጊዜ ሲቪሎች ይበልጥ የጦርነት ሰለባዎች እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ መቶ ዘመን ከወታደሮች ይልቅ ያልታጠቁ ሲቪሎች በጦርነቶች ሞተዋል” ብሏል። የፖለቲካ መሪዎች የጦር መሣሪያዎቻቸውን ሲጠቀሙባቸው ንጹሐን ሰዎች የጥይት ራት ሆነዋል። በእኛ መቶ ዘመን ብቻ በጦርነቱ የተሠዉት ሰዎች ከአንድ መቶ ሚልዮን በላይ ሲሆኑ በመቶ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ በደረሰባቸው የአካል ጉዳትና የሚያፈቅሯቸው ሰዎች ስለሞቱባቸው ተሠቃይተዋል።
በዘመናችን በተፈጠረው ግጭት ሰለባዎች ከሆኑት በተጨማሪ ሰማዕት የሆኑ ሰዎችም አሉ።a ልዩነቱ ምንድን ነው? በሚልዮን የሚቆጠሩ አይሁዶች፣ ስላቮች፣ ጂፕሲዎች፣ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎችና ሌሎች ሰዎች በናዚ ጀርመን ግዛት ወቅት በማንነታቸው ብቻ ሰለባዎች ሆነው ተገድለዋል። ማምለጫ መንገድ ወይም አማራጭ አልነበራቸውም። በዚያ ክፉ ሥርዓት ሥር ሞት የማይቀርላቸው ሰዎች ሆነው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች መሞት አልነበረባቸውም። ከሞት የሚያመልጡበት መንገድ ነበራቸው። ይሁን እንጂ በሚከተሉት መሠረታዊ ሥርዓት ምክንያት ማምለጫ መንገዱን ሳይመርጡ ቀርተዋል።
ለዚህ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል ጎላ ብለው የሚታዩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አይሁዳዊ ስደተኞችን ሲረዱ የነበሩት ካቶሊካዊ ቄስ ማክሲሚሊያን ኮልቤ ይገኙበታል። በ1941 “በኦሽዊትዝ ወደሚገኘው የናዚ ማጎሪያ ሰፈር በመርከብ ተወሰዱ፤ በዚያም ፍራንሲዝ ጋጆውኒዝ ለተባለ ሞት የተፈረደበት እስረኛ ራሳቸውን ምትክ አድርገው በማቅረብ ለመሞት ያላቸውን ፈቃደኝነት አሳይተዋል። መጀመሪያ በረሃብ ከቀጧቸው፣ ከዚያም ፌኖል ወግተው ከገደሏቸው በኋላ ሬሳቸውን አቃጠሉት።” (ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ) የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ሃይማኖቶች ካላቸው ሕግ ለየት ባለ መንገድ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉ ሰማዕት ሆነዋል።
በጀርመን ውስጥ በናዚ ዘመን (1933–1945) የይሖዋ ምሥክሮች ገለልተኞች በመሆናቸውና በሂትለር የጦርነት ትግል ውስጥ አንገባም የሚል የድፍረት አቋም በመያዛቸው አስከፊ ስደት ደርሶባቸዋል። በሺህ የሚቆጠሩት አስፈሪ ወደሆኑ የማጎሪያ ሰፈሮች ተወስደው ተገድለዋል እንዲሁም በደረሰባቸው መንገላታት ምክንያት ሞተዋል። ይሁን እንጂ መከራ መቀበልና መሞት አልነበረባቸውም። ምርጫ ነበራቸው። ከችግሩ ማምለጥ የሚችሉበት መንገድ ቀርቦላቸው ነበር። እምነታቸውን እንደካዱ በማረጋገጥ ከፈረሙ በነፃ ሊለቀቁ ይችሉ ነበር። ብዙዎቹ አለመፈረሙን ስለመረጡ የናዚ ሽብር ሰለባዎች ብቻ ሳይሆን ሰማዕቶችም ጭምር ሆነዋል። ስለሆነም ሰማዕት የሆኑት ሁሉ ሰለባ ቢሆኑም ሰማዕት የሆኑት፣ ደግሞም ለመሆን የመረጡት በጣም ጥቂቶች ናቸው። ሞት ከፊታቸው ቢደቀንም ድል ነሥተውታል።
የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ብዙ ሰዎች የሰጡት አድልዎ የሌለበት ምሥክርነት ይህንን ሐቅ ያረጋግጣል። “ብሩፓቸር የተባሉ የስዊስ ተወላጅ የሆኑ ፕሮቴስታንት ቄስ በ1939 የታዘቡትን ሲናገሩ ‘ራሳቸውን ክርስቲያኖች ነን ብለው የሚጠሩ ሰዎች በዚያ ወሳኝ ወቅት ባጋጠማቸው ፈተና ሲሸነፉ እነዚህ የማይታወቁ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ሕሊናን ለሚያስገድደውና እንግዳ ለሆነው የጣዖት አምልኮ የማይናወጥ ተቃውሞ በማሳየት ክርስቲያን ሰማዕቶች ሆነው ጸንተዋል። . . . መከራ የተቀበሉትና ደማቸውን ያፈሰሱት፣ የይሖዋ ምሥክሮችና የክርስቶስ መንግሥት እጩዎች በመሆናቸው ሂትለርንና ስዋስቲካውን ለማምለክ አሻፈረን ስላሉ ነው’ ብለዋል።”
ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ሞት ከፊታቸው ተደቅኖ ፍጹም አቋማቸውን የጠበቁት በናዚ ጀርመን ብቻ አይደለም። በኮሚኒዝም፣ በፋሺዝምና በሌሎች የፖለቲካ አምባገነናዊ ሥርዓቶችም ሆነ በሃይማኖታዊ ተቃውሞ ፊት ድፍረት ማሳየት አስፈልጓቸዋል። ዲሞክራሲያዊ ናቸው በሚባሉት በምዕራቡ አገሮችም እንኳ ምሥክሮቹ የደረሰባቸውን ዓመፅ ተጋፍጠዋል። በሚቀጥለው ርዕሳችን ሞት ከፊታቸው ቢደቀንም ድል አድራጊ የሆኑ ምሥክሮችን ታሪክ የያዙ ጥቂት ሁኔታዎችን እንዘረዝራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሰለባ ሆኖ የሞተ ሰውን “በሌላ ሰው የተጐዳ ወይም የተገደለ . . . በአንድ ዓይነት ድርጊት፣ ሁኔታ፣ ወኪል ወይም አጋጣሚ የተጐዳ ወይም መከራ የደረሰበት” ብሎ መግለጽ ይቻላል። በሌላ በኩል ግን ሰማዕት የሆነ ሰው “ሃይማኖታዊ መሠረታዊ ሥርዓትን ከመካድ ይልቅ መሞትን የመረጠ . . . አንድን እምነት፣ ዓላማ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት ለማስፋፋት በማሰብ የራሱን ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚሠዋ ወይም መከራ የሚቀበልን ሰው ያመለክታል።” — ዘ አሜሪካን ሄሪቴጅ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኢንግሊሽ ላንጉዊጅ፣ ሦስተኛ እትም።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የምሥራቅ ጀርመን ፍርድ ቤቶች የይሖዋ ምሥክሮች የአሜሪካ ሰላዮች ናቸው በማለት በሐሰት ክስ መሥርተውባቸው ነበር
[ምንጭ]
Neue Berliner Illustrierte