ከሞት ጋር ተፋጥጦ ድል መንሳት
“ይሁን እንጂ ናዚዎቹ [ምሥክሮቹን] ሊያጠፉአቸው አለመቻላቸው አስገራሚ ነው። በተጨቆኑ ቁጥር እንደ አልማዝ እየጠነከሩ በመሄድ ችግሩን ይቋቋሙት ነበር። ሂትለር የሕልውናቸው መጨረሻ ለማድረግ ቢዋጋቸውም እምነታቸውን ጠብቀዋል። . . . በጣም አሠቃቂ በሆነ ሁኔታ ሥር በሕይወት መትረፍ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ እነርሱ የገጠማቸው ነገር ጥሩ ትምህርት ይዟል። ከእልቂቱ በሕይወት ተርፈዋል።”— ቱጌዘር በተባለው መጽሔት ላይ ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ዶክተር ክርስቲን ኪንግ የጠቀሱት ነጥብ።
የይሖዋ ምሥክሮች በ20ኛው መቶ ዘመን ታሪክ ውስጥ በምድር ላይ ከማንም ይበልጥ የተጠሉና ስደት የደረሰባቸው ሃይማኖታዊ ቡድን ናቸው። በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውና በጦርነት ለመካፈል የሚያስችል ሥልጠናና ትምህርት አንቀበልም በማለታቸው ምክንያት ችግራቸውን ሰዎች ሳይረዱላቸውና ብዙ ጊዜ ሲጉላሉ ኖረዋል። ከሁሉም የፖለቲካ ቁርኝት የተለዩ መሆናቸው በብዙ አገሮች ያሉትን አምባገነናዊ ገዥዎች በቁጣ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል። ይህም ሆኖ ለዘመናችን የታሪክ መዝገብ በጥብቅ ገለልተኝነታቸውና በማይታጠፈው ፍጹም አቋማቸው የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል።a
እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ አርኖልድ ቶይንቢ በ1966 ሲጽፉ “በዘመናችን በጀርመን ውስጥ አዶልፍ ሂትለር በተባለው ሰብአዊ ጣዖት ለተወከለው በኃይል ለተስፋፋው ብሔራዊ ስሜት ከመንበርከክ ይልቅ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ክርስቲያን ሰማዕቶች ነበሩ” ብለዋል። ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ከእነዚህ ሰማዕቶች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች ዋነኞች ነበሩ። በናዚ የአገዛዝ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች በፍጹም አቋም ጠባቂነታቸው ምክንያት ሞትን ጨምሮ ከባድ ስደት እንደ ደረሰባቸው የሚያሳዩ አንዳንድ ተሞክሮዎችን ለማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል። ሞት በፊታቸው ቢደቀንም በብዙዎቹ የዓለም ክፍሎች ያስመዘገቧቸው ድሎች ዘላቂና ተወዳዳሪ የሌላቸው ናቸው።
የዩክሬኑ የአናኒ ግሮጉል ታሪክ
“በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በ1942 የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አባቴ ተያዘና ታሰረ፤ በኋላም በኡራል ተራሮች ወደሚገኘው የሶቪየቶች ሰፈር ተወሰደ። በ1944 የ15 ዓመት ልጅ በነበርኩበት ጊዜ በጦር ኃይሎች ውስጥ የሥልጠና አገልግሎት እንድካፈል በወታደራዊ ባለ ሥልጣኖች ተጠራሁ። በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ስለነበረኝ የጦር ልምምድ ለማድረግ እምቢ አልኩ። በዚህ ምክንያት በዚያ የለጋነት ዕድሜዬ የአምስት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።
“ከዚያም በጣም አስቸጋሪው ዓመት 1950 ደረሰ። ምሥክር ሆኜ በማደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት እንደገና ተያዝኩና የ25 ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። በዚህ ጊዜ 21 ዓመቴ ነበር። ከባድ ሥራ እየሠሩ እስረኞች በሚቀጡበት ቦታ ሰባት ዓመት ከአራት ወር አሳለፍኩ። ብዙ ሰዎች በረሃብና በከባዱ ሥራ ምክንያት ጠውልገው ሲሞቱ ተመልክቻለሁ።
“ስታሊን በ1953 ከሞተ በኋላ ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩና በ1957 ባለ ሥልጣኖቹ ከእስር ቤት እንድወጣ አደረጉ። እንደገና ‘ነፃነት’ አገኘሁ። ሆኖም በዚህ ጊዜ ለአሥር ዓመት ሳይቤሪያ ውስጥ በግዞት እንድኖር ተወሰድኩ።
በእኅቴ ላይ የተፈጸመ ኢሰብአዊ ቅጣት
“በሳይቤሪያ ለሽባነት ከተዳረገችው እኅቴ ጋር እንደገና ተገናኘን። የታሰረችው እኔ በ1950 ከታሰርኩ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነበር። በእሷ ላይ የተደረገው ምርመራ ፈጽሞ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተከናወነ ነበር። ለብቻዋ በታሰረችበት ጠባብ ክፍል ውስጥ አይጦች በላይዋ ላይ እንዲሯሯጡ ለቀቁባት። እነዚህ አይጦች እግሮቿን ይበሉና በሰውነቷ ላይ ይሄዱባት ነበር። በመጨረሻም የሚያሰቃዩአት ሰዎች ሥቃይዋን እየተመለከቱ እስከ ደረቷ ድረስ በሚያሰጥም ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ እንድትቆም አደረጓት። በስብከት ሥራዋ ምክንያት የ25 ዓመት እስራት ተፈርዶባት ነበር። ሁለቱም እግሮቿ ሽባ ሆነዋል። ነገር ግን እጆቿና ክንዶቿ መሥራት ይችሉ ነበር። ለአምስት ዓመት በካምፑ ውስጥ ባለው ሆስፒታል ውስጥ ካቆዩአት በኋላ በመጨረሻ እንደሞተች አድርገው በመቁጠር አባረሯት። ከዚያም በ1951 ወላጆቻችን የዕድሜ ልክ ግዞተኞች ሆነው እንዲቀመጡ ወደተላኩበት ወደ ሳይቤሪያ አዛወሯት።”
ወደ ዩክሬን ተመለስኩና ተጨማሪ ስደት ደረሰብኝ
ልጆች ከወለደችልኝ ከባለቤቴ ከናዲያ ጋር በሳይቤሪያ ተዋወቅን። በሳይቤሪያም ቢሆን የስብከት ሥራችንን ቀጥለን ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማዘጋጀትና የማባዛት ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ነበር። በእያንዳንዱ ሌሊት እኔና ወንድሜ ጃኮብ ምድር ቤት ውስጥ ተቆፍሮ በተዘጋጀ ቦታ ውስጥ መጠበቂያ ግንብ እናባዛ ነበር። ሁለት የታይፕ መኪናዎችና አንድ በቤት ውስጥ የተሠራ የማባዣ መኪና ነበረን። ቤታችን በየጊዜው በፖሊሶች ይፈተሽ ነበር። በመጡ ቁጥር ግን ባዶአቸውን ይመለሱ ነበር።
“የግዞት ዘመኔ አበቃ። ቤተሰቤን በሙሉ ይዤ ወደ ዩክሬን ተዛወርኩ። ሆኖም ስደቱ ተከትሎን መጣ። ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመድቤ ነበር። ቤተሰቤን ለመርዳት ተቀጥሬ መሥራት ነበረብኝ። በአንድ ወር ውስጥ ሁለትና ሦስት ጊዜ የመንግሥት ደኅንነት አባሎች ሥራ ቦታዬ ድረስ እየመጡ እምነቴን ለማስካድና ለማሳመን ይሞክሩ ነበር። አንድ ጊዜ ልዩ በሆነ መንገድ የይሖዋን እርዳታ አግኝቻለሁ። ተይዤ በኪየቭ ወደሚገኘው የመንግሥት ደኅንነት መሥሪያ ቤት ወሰዱኝና ለስድስት ቀናት አሰሩኝ። በዚያ ጊዜ ሁሉ አምላክ የለሽ በሆነ ፕሮፓጋንዳ ግራ ሊያጋቡኝ ሞክረው ነበር። በእነሱ አምላክ የለሽ አነጋገር በመጠበቂያ ግንብ እና በሌሎቹ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ አቃቂር ያወጡ ነበር። ተጽዕኖው በጣም ከበደብኝ። ወደ መታጠቢያ ቤት ገብቼ በጉልበቴ ተንበርክኬ እያለቀስኩ ወደ ይሖዋ ጮህኩ። ከእስር ነፃ እንዲያወጣኝ ሳይሆን ለመጽናት እንድችልና ወንድሞቼን አሳልፌ እንዳልሰጥ እንዲያበረታኝ ጸለይኩ።
“ከዚያም የፖሊስ አዛዡ ሊጠይቀኝ መጣና ከፊት ለፊቴ ተቀምጦ የምከራከርለትን ነገር በእርግጥ አምንበት እንደሆነና እንዳልሆነ ጠየቀኝ። አጠር ያለ ምሥክርነት ሰጠሁትና ለእውነት ስል ለመሞት ዝግጁ መሆኔን አረጋገጥኩለት። እርሱም መልሶ ‘ደስተኛ ሰው ነህ። ይህ እውነት ነው ብዬ የማምን ብሆን ኖሮ እስር ቤት ውስጥ ለ3 ወይም ለ5 ዓመት ብቻ ሳይሆን በአንድ እግሬ ቆሜ 60 ዓመት እታሰር ነበር’ አለኝ። ለጥቂት ጊዜ እያሰበ ዝም ብሎ ከተቀመጠ በኋላ ‘የዘላለም ሕይወት ጉዳይ ነው። የዘላለም ሕይወት ምን እንደሚመስል መገመት ትችላለህ?’ በማለት ንግግሩን ቀጠለ። ጥቂት ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ‘ወደ ቤትህ ሂድ!’ አለኝ። እነዚህ ቃሎች ያልታሰበ ብርታት ሰጡኝ። ከእንግዲህ ወዲያ አልራብም። ቦታውን ለቅቄ መውጣት ብቻ ነበር የፈለግሁት። ያበረታኝ ይሖዋ እንደነበረ አልተጠራጠርኩም።
“በቅርብ ዓመታት በቀድሞዋ የሶቪየት ሕብረት የነበሩት ሁኔታዎች ተለውጠዋል። አሁን የተትረፈረፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ አለ። የክልል ስብሰባዎችና የወረዳ ስብሰባዎች ለመካፈልና ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክን ጨምሮ በሁሉም ዓይነት የስብከት እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ ችለናል። በእውነትም፣ ብዙ መከራዎች ቢደቀኑብንም ይሖዋ ድል አድራጊ እንድንሆን አስችሎናል።
በአፍሪካ የተፈተነው ፍጹም አቋም ጠባቂነት
በ1960ዎቹ ማለቂያ ናይጄሪያ ከፍተኛ እልቂት ባስከተለ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወድቃ ነበር። በጦርነቱ ድል መደረጋቸው እያየለ ሲመጣ በማፈግፈግ ላይ የነበረው የቢያፍራ ጦር ወንዶችን ለጦርነቱ በግድ መመልመል ጀመረ። የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ጉዳይ ገለልተኞች ስለሆኑና በጦርነት ስለማይሳተፉ በቢያፍራ የነበሩ ብዙ ምሥክሮች ብዙ ንዝነዛ፣ ጭካኔ የተሞላበት ግፍና ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ “እንደ አይጦች ሆነን ነበር። ወታደሮች መምጣታቸውን ስንሰማ እንደበቅ ነበር” ብሏል። በአብዛኛው ለመደበቅ በቂ ጊዜ አይገኝም ነበር።
በ1968 ዐርብ ጠዋት፣ 32 ዓመት የሞላው ፊሊፕ የሚባል የሙሉ ጊዜ አገልጋይ፣ የቢያፍራ ወታደሮች ለምልመላ አካባቢውን ሲያስሱ በኡሙይሞ መንደር ውስጥ ለአንድ አረጋዊ ሲሰብክ አገኙት።
“ምን እየሠራህ ነው?” አለና የቡድን መሪው ጠየቀው። ፊሊፕ ስለምትመጣዋ የይሖዋ መንግሥት እየተናገረ መሆኑን ነገረው።
“አሁን የስብከት ጊዜ አይደለም!” በማለት ሌላው ወታደር ጮኸበት። “አሁን የጦርነት ወቅት ነው። ስለዚህ እንደ አንተ ያለ ሰው ያለምንም ሥራ ወዲያና ወዲህ እያለ ማየት አንፈልግም።” ከዚያም ወታደሮቹ የፊሊፕን ልብስ ገፈፉና እጆቹን ጠፍረው ወሰዱት። 43 ዓመት የሆነው እስራኤል የሚባል ክርስቲያን ሽማግሌ ለመደበቅ ጊዜ አልነበረውም። የተያዘው ለልጆቹ ምግብ ሲያዘጋጅ ነበር። ከቀኑ 8 ሰዓት ሲሆን ወታደሮቹ ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ ሰዎች ያዙ። የያዟቸውን ሰዎች 24 ኪሎ ሜትር ያህል እንዲሮጡ በማስገደድ ኡሙዋካ ቤዴአላ የተባለው ቦታ ድረስ ወዳለው የጦር ሰፈራቸው ወሰዷቸው። ከሩጫው ወደ ኋላ የቀረ ይገረፍ ነበር።
እስራኤል ከባድ መትረየስ እንዲሸከም ሲነገረው ፊሊፕ ደግሞ የቀላል መትረየስ ሥልጠና እንደሚሰጠው ተነገረው። ይሖዋ ጦርነትን ስለሚከለክል በጦር ኃይሉ ውስጥ መግባት እንደማይችሉ በሚያስረዱበት ጊዜ የጦር አዛዡ በር እንዲቆለፍባቸው ትእዛዝ አስተላለፈ። በ10 ሰዓት በዘብ ቤት ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ የተመለመሉት ሁሉ እንዲሰለፉ ታዘዙ። ከዚያም ወታደሮቹ እያንዳንዱ ሰው ከሠራዊቱ ጋር ለመቀላቀል መስማማቱን በሚገልጽ ወረቀት ላይ እንዲፈርም መጠየቅ ጀመሩ። ፊሊፕ ተራው ሲደርስ በ2 ጢሞቴዎስ 2:3, 4 ላይ የሚገኙትን ቃሎች ጠቅሶ ጦር አዛዡን “እኔ አስቀድሜ ‘የክርስቶስ በጎ ወታደር’ ሆኜአለሁ። ለክርስቶስ እየተዋጋሁ ለሌላ ሰውም ልዋጋ አልችልም። ይህንን ባደረግ ክርስቶስ እንደ ከሀዲ ይቆጥረኛል” አለው። የጦር አዛዡ አናቱን በዱላ መታውና “የክርስቶስ ወታደር ሆነህ የተሾምክበት ጊዜ አብቅቷል! አሁን አንተ የቢያፍራ ወታደር ነህ” አለው።
ፊሊፕ መለሰና “የእርሱ ወታደር ሆኜ የተሾምኩበት ጊዜ ማለቁን ኢየሱስ ገና አልነገረኝም። ሹመቴ ደግሞ እንደዚህ ያለው ማስታወቂያ እስኪነገረኝ ድረስ ይቀጥላል” አለው። ከዚህ በኋላ ወታደሮቹ ፊሊፕንና እስራኤልን ሰማይ አድርሰው አፈረጧቸው። ደንዝዘውና በዓይናቸው፣ በአፍንጫቸውና በአፋቸው ደም እየፈሰሰ ሁለቱንም እየጎተቱ ወሰዷቸው።
በሚረሽኑ ወታደሮች ፊት
በዚያው ዕለት ትንሽ ቆየት ብሎ እስራኤልና ፊሊፕ በሚረሽኗቸው ወታደሮች ፊት መቆማቸውን ተመለከቱ። ወታደሮቹ ግን አልረሸኗቸውም። ከዚህ ይልቅ በጡጫና በሰደፍ ደበደቧቸው። ከዚያም የካምፑ አዛዥ እስኪሞቱ ድረስ እንዲገረፉ ወሰነ። ይህንንም ለማስፈጸም 24 ወታደሮች መደበ። ስድስቱ ፊሊፕን ሲገርፉ ሌሎች ስድስት ደግሞ እስራኤልን ይገርፋሉ። የቀሩት 12 ወታደሮች ደግሞ ዱላዎቹ ሲሰበሩ ሌላ ዱላ የሚያቀብሉና ገራፊዎቹ ሲደክማቸው የሚለውጧቸው ነበሩ።
ፊሊፕና እስራኤል እጅና እግራቸው ታስሮ ነበር። እስራኤል የሆነውን ነገር ሲናገር “በዚያ ሌሊት ስንት ግርፋት እንዳረፈብን ለመናገር አልችልም። አንዱ ወታደር ሲደክመው ሌላው ይተካል። ሕሊናችንን ከሳትን በኋላ እንኳ ለረጅም ሰዓት ገርፈውናል” ይላል። ፊሊፕ ደግሞ “እየተገረፍኩ ሳለ በማቴዎስ 24:13 ላይ እስከ መጨረሻ ስለ መጽናት የሚናገሩት ቃሎች ትዝ አሉኝና አበረቱኝ። የግርፋቱ ሥቃይ የተሰማኝ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሰኮንዶች ብቻ ነበር። በዳንኤል ጊዜ እንዳደረገው ይሖዋ መልአኩን ልኮ የረዳን ይመስል ነበር። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ከዚያ አሠቃቂ ሌሊት በሕይወት ልንተርፍ አንችልም ነበር” በማለት ተናገረ።
ወታደሮቹ ግርፊያቸውን ሲጨርሱ እስራኤልና ፊሊፕን እንደሞቱ ስለቆጠሯቸው ትተዋቸው ሄዱ። ይዘንብ ነበር። እስከሚቀጥለው ቀን ጠዋት ድረስ ሁለቱ ክርስቲያኖች ሕሊናቸውን ስተው ነበር። ወታደሮቹ አሁንም በሕይወት መኖራቸውን ሲያውቁ እየጐተቱ ወደ ዘብ ቤት ወሰዷቸው።
“እንደ ሬሳ ሸታችኋል”
ግርፋቱ ሥጋቸውን ተልትሎና አቁስሎ ደም በደም አድርጓቸው ነበር። እስራኤል “ቁስላችንን እንድንታጠብ አልተፈቀደልንም ነበር። ከጥቂት ቀን በኋላ ዝንቦች ያለማቋረጥ ወረሩን። ከሥቃዩ የተነሳ መብላት እንኳ አንችልም ነበር። ከውኃ ሌላ ሌሎች ነገሮች ከጉሮሮአችን መውረድ የጀመሩት ከሳምንት በኋላ ነበር” በማለት የሚያስታውሰውን ይናገራል።
በእያንዳንዱ ቀን ጠዋት ወታደሮቹ እያንዳንዳቸውን 24 ጊዜ ይገርፏቸው ነበር። ወታደሮቹ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ግርፋቱን “ቁርስ” ወይም “ትኩስ የጥዋት ሻይ” በማለት ይጠሩት ነበር። በየዕለቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን ወታደሮቹ ወደ ውጭ ያወጧቸውና እስከ 7 ሰዓት ድረስ በቀትሩ ፀሐይ ይጠብሷቸው ነበር። እንዲህ እያደረጉ ካሠቃዩአቸው ከጥቂት ቀን በኋላ አዛዡ ጠራቸውና አቋማቸውን ለውጠው እንደሆነ ጠየቃቸው። አለወጥንም አሉት።
አዛዡም “እስር ቤት እንዳላችሁ ትሞቷታላችሁ። እንዲያውም እንደ ሬሳ ሸትታችኋል” አላቸው።
ፊሊፕ “ብንሞትም እንኳ የምንዋጋለት ክርስቶስ ከሞት ሊያስነሣን እንደሚችል እናውቃለን” በማለት መለሰለት።
በዚህ አሠቃቂ ወቅት እንዴት ሊጸኑ ቻሉ? እስራኤል “በመከራችን ጊዜ ሁሉ እኔና ፊሊፕ እርስ በርሳችን እንበረታታ ነበር። ገና ከመጀመሪያው ‘አትፍራ። ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ይረዳናል። በበኩሌ ምንም ነገር በውትድርና ውስጥ እንድገባ አያደርገኝም። እሞታታለሁ እንጂ በእነዚህ እጆቼ ጠመንጃ አልጨብጥባቸውም’ በማለት እነግረው ነበር” ብሏል። ፊሊፕም እንዲሁ ተመሳሳይ የሆነ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ እንደነበረ ተናግሯል። አብረው ልዩ ልዩ ጥቅሶችን እያስታወሱ ይወያዩባቸው ነበር።
አዲሱ አዛዥ ወደ መቶ የሚጠጉ የተመለመሉ ሰዎች አይቤማ ወደ ተባለው በአሁኑ ጊዜ የኢሞ ግዛት ተብሎ በሚጠራው በምባኖ አካባቢ ወደሚገኘው የማሠልጠኛ ሰፈር እንዲዛወሩ ወሰነ። ከዚያ በኋላ የሆነውን እስራኤል ሲናገር “ትልቁ መኪና ዝግጁ ነበር። ምልምሎቹም ተሳፍረው ነበር። ባለቤቴ ጁን ወደ ወታደሮቹ ሮጣ በመሄድ ደፈር ብላ እንዳንወሰድ ለመነቻቸው። ልመናዋን ንቀው እምቢ ባሏት ጊዜ መኪናው አጠገብ ተንበርክካ ጸለየችና ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አሜን በማለት ጸሎቷን ደመደመች። ከዚያ በኋላ መኪናው ተጓዘ” ይላል።
አዛኝ ከሆነ ቅጥረኛ ተዋጊ ጋር መገናኘት
መኪናው በአይቤማ ወደሚገኘው የጦር ሰፈር በሚቀጥለው ቀን ከሰዓት በኋላ ደረሰ። በዚያ ኃላፊ ይመስል የነበረው ሰው እስራኤላዊ ቅጥረኛ ተዋጊ ነበር። ፊሊፕና እስራኤል ምን ያህል እንደ ተጐሳቆሉና እንደ ደከሙ ሲመለከት ቀረብ ብሎ እንደዚህ በመሰለ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ለምን እንደ ወደቁ ጠየቃቸው። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውንና ወታደራዊ ሥልጠና ለመቀበል ባለመፈለጋቸው ሥቃይ የደረሰባቸው መሆኑን አስረዱት። በነገሩ ተናድዶ አጠገቡ ወደነበሩት የጦር መኰንኖች ሄደ። “ቢያፍራ በዚህ ጦርነት እንደምትሸነፍ አትጠራጠሩ” አላቸው። “የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያጐሳቁል ማንኛውም በጦርነት ላይ የሚገኝ አገር ይሸነፋል። የይሖዋ ምሥክሮችን መመልመል የለባችሁም። አንድ ምሥክር ግን በፈቃዱ እዋጋለሁ ካለ መልካም ነው። ነገር ግን አልዋጋም ካለ ተዉት።”
የጦር ሰፈሩ ሐኪም ሁለቱን ምስክሮች ተከትበውና ብቁ ናቸው የሚል የሕክምና ማስረጃ ይዘው እንደሆነ ጠየቃቸው። ምንም ማስረጃ ስላልነበራቸው ቅጥረኛ ተዋጊው የተመለመሉትን ሁሉ አልቀበልም በማለት ወደመጡበት ወደ ኡሙዋካ እንዲመልሷቸው አዘዘ።
“ሂዱ፤ አምላካችሁን አገልግሉ”
ቆይቶም የእስራኤል ሚስትና የፊሊፕ እናት ኡሙዋካ ወደሚገኘው ጦር ሰፈር ሁኔታውን ለማጣራት ሄዱ። እዚያ በደረሱ ጊዜ በሰፈሩ ውስጥ የሁካታ ድምፅ ሰሙ። በመግቢያው በር ላይ ዘበኛው “የይሖዋ ምሥክሮች! ጸሎታችሁ ተመልሶላችኋል። ከሦስት ቀን በፊት የተላከው ቡድን ተመልሶ መጥቷል” አላቸው።
በዚያው ቀን ፊሊፕና እስራኤል ከጦር ሰፈሩ ነፃ ተለቀቁ። አዛዡ ጁንን “ጥረታችንን ሁሉ ፍሬ ቢስ ያደረገብን ያንቺ ጸሎት እንደሆነ ታውቂያለሽ?” አላት። ከዚያም እስራኤልንና ፊሊፕን “ሂዱ፤ አምላካችሁን አገልግሉ። ለይሖዋችሁ ታማኝነታችሁን መጠበቃችሁን ቀጥሉ” አላቸው።
እስራኤልና ፊሊፕ ግን ከደረሰባቸው ሁኔታ አገግመው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸውን ቀጠሉ። ከጦርነቱ በኋላ እስራኤል ለሁለት ዓመት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ከተሠማራ በኋላ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል። ፊሊፕ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመሆን ለአሥር ዓመት ካገለገለ በኋላ አሁንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ይገኛል። እሱም ቢሆን የጉባኤ ሽማግሌ ነው።
ለጦር መሣሪያ መግዢያ መዋጮ አለማድረግ
ዜቡላን ዙማሎ እና ፖላይት ሞጋኔ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው። ዜቡላን እንዲህ በማለት ይተርካል:- “አንድ እሁድ ጠዋት ሰዎች ወደ ቤታችን መጡና ለጦር መሣሪያ መግዣ 35 ብር ስጡን ብለው ጠየቁን። አክብሮት በተሞላው መንገድ የእሁድ ፕሮግራማችን በጣም የተጣበበ ስለሆነ ስለ ጉዳዩ ለመወያየት ወደ ማታ ተመልሰው እንዲመጡ ጠየቅናቸው። ጥያቄአችንን መቀበላቸው አስገረመን። በዚያው ዕለት ምሽት 15 ሰዎች መጡ። ከፊታቸው እንደሚነበበው በቂ ገንዘብ ለማግኘት ታጥቀው እንደተነሡ ግልጽ ነበር። ራሳችንን በትሕትና ካስተዋወቅናቸው በኋላ ምን እንደፈለጉ ጠየቅናቸው። ከተቃዋሚው የፖለቲካ ወገን ጋር ሲዋጉ የሚጠቀሙበትን ትልቅና የተሻለ የጦር መሣሪያ ለመግዛት ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸው አስረዱን።
“‘እሳትን በቤንዚን ማጥፋት ይቻላል?’ ብዬ ጠየቅኋቸው።
“‘አይቻልም’ ብለው መለሱ።
“በተመሳሳይም ረብሻ ረብሻንና በቀልን ያባብሳል ብለን አስረዳናቸው።
“ይህ አነጋገር በዚያ ከተገኙት ውስጥ ብዙዎቹን ቅር አሰኛቸው። ከዚህ በኋላ ጥያቄያቸው ፈታኝ የሆነ ማስፈራሪያን አስከተለ። ‘እንዲህ ያለው የአመለካከት ልውውጥ ጊዜ ማጥፋት ነው’ ብለው ጮኹ። ‘መዋጮው የማያጠያይቅ ግዴታ ነው። ትከፍላላችሁ ክፈሉ አይሆንም ካላችሁ ዋጋችሁን ታገኛላችሁ!’ አሉ።
“እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሱ ዜቦላን ስለ ሁኔታው እንዲህ ይላል:- “ሲደርሱና ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ መሆን ሲጀምሩ መሪያቸው ጣልቃ ገባ። ችግሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈለገ። አቋማችንን ስናስረዳው በጥንቃቄ አዳመጠን። ለሚያምኑበት የፖለቲካ አቋም ያላቸውን ቅንዓት እንደ ምሳሌ ተጠቀምንበት። የእነርሱ ድርጅት አባል ሆኖ የሠለጠነ አንድ ወታደር ቢያዝና አቋሙን እንዲለውጥ ቢገደድ ምን ያደርጋል ብለው እንደሚጠብቁ ጠየቅናቸው። ይህ ሰው ላመነበት ነገር ለመሞት ዝግጁ መሆን አለበት አሉ። ለሰጡት መልስ ስናመሰግናቸው ፈገግ አሉ። የራሳችንን ጉዳይ በምሳሌ ለማስረዳት የሚያስችል አመቺ መንገድ እንደከፈቱልን አልገባቸውም ነበር። ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የተለየን መሆናችንን አስረዳናቸው። የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎች እንደመሆናችን መጠን ‘ሕገ መንግሥታችን’ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ማንኛውንም ዓይነት ግድያ የሚያወግዝ መሆኑን ገለጽንላቸው። በዚህ ምክንያት የጦር መሣሪያ ለመግዛት አንዲት ሳንቲም እንኳ ቢሆን ለማዋጣት አልተዘጋጀንም።
“በዚህ ጊዜ ውይይቱ መጨረሻ ደረጃው ላይ ሲደርስ ብዙ ሰዎች ቤታችን ውስጥ ገብተው ስለነበረ ለብዙ ሰዎች እየተናገርን ነበር። ውይይቱ ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ምን ያህል ተግተን እንጸልይ እንደነበረ አላወቁም።
“አቋማችንን ግልጽ ካደረግን በኋላ ረዘም ያለ ጸጥታ ሰፈነ። በመጨረሻም መሪያቸው ለቡድኑ እንዲህ ሲል ተናገረ:- ‘የእነዚህ ሰዎች አቋም ገብቶኛል። ለአረጋውያን ቤት ልንሠራላቸው ብንፈልግ ወይም ከጐረቤታችን አንዱ ታምሞ ለሆስፒታል ወጪዎች ገንዘብ ብንፈልግ እነዚህ ሰዎች ጠቀም ያለ ገንዘብ ይሰጡን ነበር። ግደሉ ብለው ለእኛ ገንዘብ ለመስጠት ግን ዝግጁዎች አይደሉም። በበኩሌ የእነዚህን ሰዎች እምነት አልቃወምም።’
“ከዚህ በኋላ ሁሉም ተነሡ። ተጨባበጥንና ስለ ትዕግሥታቸው አመስግነናቸው ተለያየን። ሕይወታችንን ሊያሳጣን በሚችል መንገድ ተጀምሮ የነበረው አስከፊ ሁኔታ በታላቅ ድል ተጠናቀቀ።”
ቄሶች ያቀነባበሩት የሕዝብ ረብሻ
ጀርዚ ኩሌዛ የተባለ ፖላንዳዊ ምሥክር እንደተናገረው:-
“አባቴ አሌክሳንደር ኩሌዛ ቅንዓት በማሳየትና የመንግሥቱን ፍላጎቶች በማስቀደም ረገድ ሊከተሉት የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ነበር። የመስክ አገልግሎት፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እና የግልና የቤተሰብ ጥናት ለእሱ በጣም ቅዱስ ነገሮች ነበሩ። በረዶ ቢዘንብ ወይም ውርጭ ወይም ኃይለኛ ነፋስ ወይም ሙቀት ቢኖር አይቀርም ነበር። በክረምት ወራት የበረዶ መንሸራተቻውን ያደርግና በላስቲክ ከረጢት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቹን ይዞ ለሁለት ቀናት ያህል በፖላንድ ወዳልተሠራባቸው የአገልግሎት ክልሎች ይሄድ ነበር። የተለያዩ አደገኛ ሁኔታዎች፣ ኃይለኛ የደፈጣ ተዋጊዎች ጭምር አጋጥመውት ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ቄሶች በምሥክሮቹ ላይ የሕዝብ ረብሻ በማስነሣት ይቃወሙ ነበር። ያፌዙባቸው፣ ድንጋይ ይወረውሩባቸው ወይም ይመቷቸው ነበር። ነገር ግን ስለ ክርስቶስ በመሰደባቸው ደስ እያላቸው ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር።
“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት በእነዚያ የመጀመሪያ ዓመታት ባለ ሥልጣኖቹ በአገሪቱ ውስጥ ሕግና ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ አልቻሉም ነበር። ረብሻዎችና ዝብርቆች ነበሩ። የፖሊስና የደኅንነት ኃይሎች አካባቢውን ቀን ቀን ሲቆጣጠሩ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የሽምቅ ተዋጊዎችና የተለያዩ የዓመፅ ቡድኖች አካባቢውን ይቆጣጠሩ ነበር። ሌብነትና ዝርፊያ ከመብዛታቸውም በላይ ብዙ ጊዜ ሰዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ይገደሉ ነበር። ምንም መከላከያ የሌላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በተለይ በቄሶች የሚመሩ ቡድኖች በምሥክሮቹ ላይ በሚነሱበት ጊዜ በቀላሉ ይጠቁ ነበር። ቤታችንን ወርረው ጥቃት በሚሰነዝሩበት ጊዜ ለአባቶቻቸው እምነት ማለትም ለካቶሊክ ሃይማኖት እየተዋጋን ነው የሚል ሰበብ ያቀርቡ ነበር። እንደዚህ ባሉት ወቅቶች መስኮቶችን ሰባብረዋል፣ ከብቶችን ዘርፈዋል እንዲሁም ልብሶች፣ ምግቦችና ጽሑፎችን አውድመዋል። መጽሐፍ ቅዱሶችን ውኃ ጉድጓድ ውስጥ ጥለዋል።”
ያልታሰበ ሰማዕትነት
“በሰኔ 1946 አንድ ቀን ጠዋት ራቅ ወዳሉ የአገልግሎት ክልሎች በብስክሌት ከመሄዳችን በፊት ካዝሚየርዝ ካዜላ የተባለ ወጣት ወንድም መጣና ከአባቴ ጋር በሹክሹክታ ተነጋገሩ። አባቴ እኛ እንድንሄድ ከሸኘን በኋላ ያለወትሮው ከእኛ ጋር ባለመሄዱ ተገረምን። ምክንያቱን ያወቅነው በኋላ ነበር። ወደ ቤት ስንመለስ ቀደም ባለው ሌሊት የካዜላ ቤተሰቦች በሚያሠቅቅ ሁኔታ ተደብድበው ስለነበር አባቴ ክፉኛ ቆስለው የነበሩትን ወንድሞችና እኅቶች ለመርዳት ሄዶ ነበር።
“ቆይቼ ተኝተው ወደነበረበት ክፍል ስገባ፣ ያየሁት ነገር አስለቀሰኝ። ግድግዳዎቹና ኮርኒሱ ደም ተረጭቶባቸው ነበር። ሰዎች በፋሻ ተጠቅልለው በየአልጋቸው ላይ ተኝተው ጠቁረውና ዘጉነው፣ አብጠውና የጎድናቸው አጥንቶችና እጅና እግሮቻቸው ተሰባብረው ነበር። ማንነታቸውን ለመለየት ያስቸግር ነበር። የቤተሰቡ እናት የነበረችው እኅት ካዜላ ክፉኛ ተደብድባለች። አባቴ እየረዳቸው ነበር። ከመሄዱም በፊት ‘አቤቱ፣ አምላኬ ሆይ፣ እኔ ጤናማና ሙሉ አቋም ያለኝ ሰው ነኝ [በዚያን ጊዜ ዕድሜው 45 ዓመት ሲሆን ከዚያ በፊት ታሞ አያውቅም] ለአንተ ስል ምንም መከራ ተቀብዬ አላውቅም። ይህች ያረጀች እኅት ይህ ሁሉ ለምን ደረሰባት?’ በማለት የማይረሳ ነገር ተናግሮ ነበር። ምን ይጠብቀው እንደነበረ አላወቀም።
“ፀሐይዋ ስትጠልቅ ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቀው ቤታችን ተመለስን። የጦር መሣሪያ የታጠቁ 50 ሰዎች ቤታችንን ከብበው ነበር። የዊንሰንሱክ ቤተሰቦችም እንዲመጡ ስለተደረጉ በጠቅላላው ዘጠኝ ሰዎች ሆንን። እያንዳንዳችን ‘የይሖዋ ምሥክር ነህ?’ እየተባልን ተጠየቅን። አዎን፣ ብለን ስንመልስ እንመታ ነበር። ከዚያም ከእነዚህ ጨካኝ ነፍሰ ገዳዮች መካከል ሁለቱ በየተራ አባቴን እየደበደቡ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብህንና መስበክህን ትተዋለህ አትተውም እያሉ ይጠይቁት ነበር። ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ኃጢአቱን ይናዘዝ እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ነበር። ‘ዛሬ ጳጳስ አድርገን እንሾምሃለን’ እያሉ ያፌዙበት ነበር። አባቴ አንዲትም ቃል አልመለሰላቸውም። አንድም ጊዜ አላቃሰተም። ያደረሱበትን ሥቃይ እንደ በግ ዝም ብሎ በጽናት ተቀበለ። ሲነጋ እንዳይሞት እንዳይሽር አድርገው የደበደቡት ጨካኞቹ ሃይማኖታውያን ከሄዱ ከ15 ደቂቃ በኋላ ሕይወቱ አለፈ። ነገር ግን ከመሄዳቸው በፊት ቀጥሎ የመረጡት ተረኛ እኔ ነበርኩ። ያን ጊዜ የ17 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ሲደበድቡኝ ሁለት ጊዜ ሕሊናዬን ስቼ ነበር። ከድብደባው የተነሣ ሰውነቴ ከወገቤ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ዘጉኖ ነበር። ለስድስት ሰዓት አንገላቱን። ይህ ሁሉ የደረሰብን የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆንን ብቻ ነበር!”
ታማኝ ሚስት የምትሰጠው ድጋፍ
“ከዘጠኝ ካሬ ሜትር በሚያንስ ጨለማ በሆነ ትንሽ እስር ቤት ውስጥ ለሁለት ወር ከታሰሩት 22 እስረኞች መካከል አንዱ ነበርኩ። የእስራቱ ጊዜ የሚያበቃበት ጊዜ ሲዳረስ የሚሰጠን ምግብ ተቀነሰ። በየቀኑ ትንሽ ቁራሽ ዳቦና መራራ ቡና በትንሽ ኩባያ ይሰጠን ነበር። በቀዝቃዛው የሲሚንቶ ወለል ላይ መተኛት ይቻል የነበረው ሌሊት አንድ እስረኛ ለጥያቄ ሲወሰድ ብቻ ነበር።
“በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዬ ምክንያት አምስት ጊዜ ተይዤ በድምሩ ስምንት ዓመት ታስሬአለሁ። እንደ ልዩ እስረኛ እቆጠር ነበር። ከዚህም የተነሣ ‘እንደገና ሥራውን እንዳይቀጥል ፍላጐቱን ለማጥፋት ኩሌዛን በጣም አበሳጩት’ የሚል ማስታወሻ በግል ማኅደሬ ውስጥ ተጽፎ ነበር። ይሁን እንጂ በተፈታሁ ቁጥር ክርስቲያናዊ አገልግሎቴን አከናውን ነበር። ባለ ሥልጣኖቹ ባለቤቴን ኡርዙላንና ሁለቱን ሴት ልጆቻችንን ያስቸግሯቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል የመንደሩ ባለ ሥልጣን ለአሥር ዓመት ሚስቴ የለፋችበትን ደሞዟን ከልክሏት ነበር። አንተ በድብቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስለምትጽፍ ይህን ያደረግነው ቀረጥ ለማስከፈል ነው ይሉ ነበር። ለኑሮ የግድ ያስፈልጋሉ ከተባሉት ነገሮች በስተቀር ሁሉም ነገር ተወስዶብናል። ይሖዋ ደፋር ሚስት ስለሰጠኝና እነዚህን ሥቃዮች ሁሉ ችላ ለእኔ እውነተኛ ደጋፊ ሆና በመቆሟ አመስጋኝ ነኝ።
“በፖላንድ መንፈሳዊ ድል ሲገኝ ተመልክተናል። በአሁኑ ጊዜ ሕጋዊ የሆነ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ዋርሶ አቅራቢያ በሚገኘው በናዳርዚን ተከፍቷል። በአሥርተ ዓመታት ከሚቆጠሩ የስደት ዘመናት በኋላ በአሁኑ ጊዜ ከ108,000 በላይ ምሥክሮች በ1,348 ጉባኤዎች ይሰበሰባሉ።”
ብዙዎች ሰማዕት የሆኑት ለምንድን ነው?
በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ያስመዘገቡት የፍጹም አቋም ጠባቂነት መዝገብ ብዙ መጻሕፍት ይወጣዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰማዕቶች ሆነው ሞተዋል ወይም በእስር ቤት መከራ ተቀብለዋል፤ እንዲሁም በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር ሥቃይ፣ በጾታ መነወር፣ እንደ ማላዊና ሞዛምቢክ ባሉ አገሮች የደረሰባቸው የንብረት መዘረፍ፣ በስፔይን በፋሺስታዊ አገዛዝ ሥር፣ በአውሮፓ በናዚ አገዛዝ ሥር፣ በምሥራቅ አውሮፓ በኮሙኒዝም ሥርና በአሜሪካ ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መከራ ደርሶባቸዋል። እዚህ ላይ ለምን የሚለው ጥያቄ ይነሣል። ምክንያቱም በአቋማቸው ድርቅ ያሉ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች ቅን ክርስቲያኖች መግደልን የመማር ፍላጐት እንዳይኖራቸውና ከሁሉም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሳቸውን እንዲያገልሉ ያደረጋቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን ለማክበር ፈቃደኞች ስላልሆኑ ነው። ነገሩ ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 15:17–19 ላይ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ። ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” በማለት እንደተናገረው ተፈጸመ።
ይህ ሁሉ ዓለም አቀፍ ስደት እየደረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በ1943 በ54 አገሮች ውስጥ ከነበረው ከ126,000 በ1993 በ229 አገሮች ውስጥ ወደ 4,500,000 ከፍ ብሏል። ሞት በፊታቸው ቢደቀንም እንኳ ድል አድራጊነትን ቀምሰዋል። ይሖዋ የስብከቱ ሥራ ማብቃቱን እስከሚያስታውቅበት ጊዜ ድረስ የመንግሥቱን ምሥራች ስብከት የሚያጠቃልለውን ልዩ የሆነውን የማስተማር ሥራቸውን ለመቀጠል ቆርጠው ተነሥተዋል።— ኢሳይያስ 6:11, 12፤ ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፍጹም አቋም ጠባቂነት “አንድን ዓይነት የሥነ ምግባር ሕግ ወይም መመሪያ በጥብቅ መደገፍ” ማለት ነው።— ዘ አሜሪካን ሄሪቴጅ ዲክሽነሪ፤ ሦስተኛው እትም።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]
በጀርመን ውስጥ ሰማዕት የሆነ
ኦገስት ዲክማን የኤስ ኤስ መሪ የነበረው ሄንሪክ ሂምለር በሳክሰንሃውሰን ማጎሪያ ሰፈር ሌሎች ምስክሮች እየተመለከቱት እንዲረሸን ባዘዘ ጊዜ 23 ዓመቱ ነበር። የዓይን ምስክር የነበረው ጉስታቭ ኦሽነር “እምነታችንን እንድንክድ በሚያዘው ጽሑፍ ላይ የማንፈርም ከሆነ እንደምንገደል ነገሩንና ወንድም ዲክማንን ረሸኑት። 30 ወይም 40 የምናክለው ወደ አሸዋው ጉድጓድ ተወስደን በአንድ ጊዜ ሁላችንን እንደሚረሽኑን ነገሩን። በሚቀጥለው ቀን የኤስ ኤስ ወታደሮች ለእያንዳንዳችን ፈርሙ አለበለዚያ ትረሸናላችሁ የሚል ጽሑፍ ይዘውልን መጡ። አንድም ሰው ሳይፈርምላቸው በመመለሳቸው እንዴት እንደተበሳጩ መገመት ትችላላችሁ። በአደባባይ ትገደላላችሁ በሚለው ዛቻ ይፈራሉ ብለው አስበው ነበር። ከእነርሱ ጥይት ይልቅ የፈራነው ይሖዋን ማሳዘንን ነበር። ከእኛ መካከል ማንኛችንንም በአደባባይ አልረሸኑም።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]
ከሁሉ የሚበልጠው ክፍያ
አንዳንድ ጊዜ ሞት በፊትህ ሲደቀን ድል ማድረግ ከሁሉ የሚበልጠውን ክፍያ መክፈልን ይጨምራል። በደቡብ አፍሪካ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው በናታል ክፍለ ሀገር ካለው ከሴሌኒ ጉባኤ የደረሰን ደብዳቤ አንድ አስደንጋጭ ታሪክ ይዞ ነበር። “ይህንን ደብዳቤ የምንጽፍላችሁ ተወዳጁ ወንድማችን ሞሰስ ያሙሱዋ መሞቱን እንድታውቁ ስለፈለግን ነው። ሥራው መኪናዎችን መበየድና መጠገን ነበር። አንድ ጊዜ አንድ የፖለቲካ ቡድን እቤት የተሠራ ጠመንጃ እንዲጠግንለት ጠይቆት እምቢ ብሎት ነበር። ከዚያም የካቲት 16, 1992 ከተቃዋሚው ቡድን ጋር የሚዋጉበት የፖለቲካ ስብሰባ ነበራቸው። በዚያው ዕለት ምሽቱ ላይ ከጦርነቱ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ወንድም ወደ ሥራ ቦታው ሲሄድ መንገድ ላይ አገኙት። እዚያው በያዙት ጦር ወግተው ገደሉት። የገደሉት ለምን ነበር? ‘ጠመንጃዎቻችንን ለመበየድ እምቢ ስላልክ ጓዶቻችን በውጊያው ተገድለዋል’ በሚል ምክንያት ነው።
“ይህ ወንድሞችን አስደነገጣቸው። ነገር ግን አገልግሎታችንን እንደቀጠልን ነን” በማለት የጉባኤው ጸሐፊ ወንድም ዱማኩድ ተናገረ።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]
በፖላንድ ውስጥ ሰማዕት ሆነ
በ1944 የጀርመን ወታደሮች አካባቢውን በአስቸኳይ እየለቀቁ ባፈገፈጉበት ጊዜና የተፋፋመው ውጊያ ወደ ምሥራቃዊው የፖላንድ ከተማ እየተቃረበ ሲመጣ አካባቢውን ተቆጣጥረው የነበሩት ባለ ሥልጣኖች ጸረ ታንክ የሆኑ የቦይ ጉድጓዶች እንዲቆፍሩ ሲቪሎችን ያስገድዱ ነበር። የይሖዋ ምስክሮች በዚህ ሥራ አንሳተፍም ብለው ነበር። ስቲፋን ኪርሎ የተባለ ከተጠመቀ ሁለት ወር የሆነው ወጣት ምስክር በዚህ ሥራ እንዲሳተፍ ቢያስገድዱትም ያንኑ የገለልተኝነት አቋም ያዘ። ፍጹም አቋም ጠባቂነቱን ለማስተው ብዙ የተለያዩ እርምጃዎች ወሰዱበት።
በትንኞችና በሌሎች ነፍሳት እንዲነደፍ ብለው በረግረጋማ ቦታ ካለ ዛፍ ጋር ራቁቱን አሰሩት። ይህንንና ሌሎች ሥቃዮችን ከተቋቋመ በኋላ ተዉት። ይሁን እንጂ አንድ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ሥራውን ለመቆጣጠር በመጣበት ጊዜ አንድ ሰው የእሱን ትእዛዝ በምንም ዓይነት መንገድ የማይታዘዝ ሰው እንዳለ ነገረው። ስቲፋን ጉድጓዱን እንዲቆፍር ሦስት ጊዜ ታዘዘ። አካፋ በእጁ ለማንሣት እንኳ አልፈለገም። በጥይት ተገደለ። ሁኔታውን ይመለከቱ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በደንብ ያውቁት ነበር። የእርሱ ሰማዕትነት ይሖዋ ለሚሰጠው ትልቅ ብርታት ማስረጃ ሆኗል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አናኒ ግሮጉል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጀርዚ ኩሌዛ